በ“ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” መስራች ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

መስራች ጊዜያዊ ኮሚቴ  
ታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም

በሀገራችን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተረጋግጧል ከተባለበት ከ1985ዓ.ም. ጀምሮ የመገናኛ ብዙሃን ሙያ ከመጎልበት ይልቅ እያደር በመጫጨት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ  የሙያው ባለቤቶች የሆኑት ጋዜጠኞች ለተለያዩ ጥቃቶች ሲጋለጡ ቆይተዋል፡፡ ለምሳሌ ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት አለአግባብ ይታሰራሉ፤ ማስፈራሪያና ዛቻ ይደርስባቸዋል፣ ይደበደባሉ፣ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅሞች እና መብቶቻቸውን ይነፈጋሉ፣ ሲልም ከዚህ የከፉ በደሎች ይደርሱባቸዋል፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ከመንግሥት ከሚደርስባቸው መሰል የመብት ጥሰትና እንግልት በተጨማሪ፣ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መገናኛ ብዙሃንን መመዝበር የሚፈልጉ የተለያዩ አካላትም ጥቃት ሰለባ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለያየ መንገድ ጥቅሞቻቸው አይከበሩም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጋዜጠኞች ለሌሎች መብት መከበር የሚጮሁትን ያህል በራሳቸውና በሙያው ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታትም ሆነ እንዳይፈጠሩ ለመስራት አልታደሉም፡፡ ይህንን ሊያከናውን የሚችል ተቋምም ሆነ ማህበር የላቸውም ለማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በኢትዮ-ምኅዳር ከፍተኛ አዘጋጅ ኤፍሬም በየነ ላይ የደረሰውን ሁሉ መመልከት ይቻላል፡፡ ጋዜጠኛው የሥራ ባልደረቦቹ የቀረበባቸውን ክስ ለመከላከል እና እግር መንገዱን የሙያ ግዴታውን ለመወጣት በሄደበት ወቅት የደረሰበትን አወዛጋቢ የትራፊክ አደጋ ተከትሎ በተግባር ለጋዜጠኝነትና ለጋዜጠኞች የሚቆረቆሩ ተቋማት አለመኖራቸው በተጨባጭ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህና መሰል ችግሮች በእርግጥም ነፃና ገለልተኛ የሆነና ለጋዜጠኝነት ሙያ እንዲሁም ለጋዜጠኞች መብት የቆመ ማኅበር ማቋቋም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ አድርጎታል፡፡

ከዚህ እውነት በመነሳት ከጥቅምት ወር 2006 ዓም ጀምሮ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” በሚል ስያሜ በጋዜጠኝት መርህ ላይ የተመሰረተ እና ለጋዜጠኞች መብት የቆመ የሙያ ማኅበር ለመመስረት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የሙያው ባለቤቶችም በጋራ ተባብረው ማኅበሩን በቅርቡ እውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህንንም ጋዜጣዊ መግለጫ ማዘጋጀት ያስፈለገው ይህንን የተግባር እንቅስቃሴ ይፋ ለማድረግ ነው፡፡

“የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የሚመሰረተው በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 30 በተፈቀደው የመደራጀት መብት መሠረት ሲሆን፣ በአጠቃላይ ጋዜጠኞችን በመደገፍ፣ የሙያ ብቃታቸውን በማሻሻል እንዲሁም በማበረታታት በሀገሪቱ ያለውን የጋዜጠኝነት ሙያ ለማበልፀግ የሚሰራ ነፃ የሙያ ማኅበር ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን ማኅበሩ በርካታ ዝርዝር ዓላማዎችን ያነገበ ቢሆንም፣ በዋናነት ተጠቃሾቹ የሚከተሉት ናቸዉ፡-

1. በኢፌድሪ ሕገ- መንግሥት አንቀፅ 29 መሠረት የተፈቀደውን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ለማስከበር

2. የጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ

3. በተከታታይ ትምህርትና ሥልጠና የጋዜጠኞችን ሙያዊ ብቃት ለማጎልበት

4. በጋዜጠኞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር

5. አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የሕግ አገልግሎት ድጋፍ ለማደረግ

6. በዘርፉ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ጋዜጠኞች እውቅና ለመስጠት የሚሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ በዋናነት በአባልነት የሚያቅፋቸው አባላት በጋዜጠኝነት ሙያ በማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን መስክ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትን ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ በሙያው ለመሰማራት በሂደት ላይ የሚገኙትንና ከሙያው ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸውን ግለሰቦች ተባባሪ በሚል የአባልነት ዘርፍ ያቅፋል፡፡

ስለሆነም በሙያው አገልግሎት በመስጠት ላይ የምትገኙ ጋዜጠኞች ሁሉ፣ በዚህ በምስረታ ላይ ባለው የእናንተው ማኅበር ላይ፣ የበኩላችሁን ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የማኅበሩን ህላዌ እውን ታደርጉ ዘንድ ተጋብዛችኋል፡፡ በቅርቡም በሚጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ፣ የማኅበሩን የአመራር አባላት በመምረጥ ሂደት እንድትሳተፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s