የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሠራተኞች በአስተዳደራዊ ችግር ተማረናል አሉ

“የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰራተኞች አሉባልታ ነው” – ዩኒቨርስቲው

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ አስተዳደራዊ ችግር መማረራቸውን የተናገሩት የዩኒቨርስቲው ሠራተኞች፤በየጊዜው  መምህራን ሥራቸውን እየለቀቁ እንደሚወጡ ገለፁ፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ በበኩላቸው፤ የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰራተኞች አሉባልታ እንጂ በዩኒቨርስቲው ውስጥ አስተዳደራዊ ችግር እንደሌለ  ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በዓመት ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የሚመደብለት፣ ከ45 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚያስተምርና ከአምስት ሺህ በላይ ሰራተኞች የሚያስተዳድረው ዩኒቨርስቲው፤ ከአመራርና አስተዳደር ሙያ ጋር የተገናኘ የትምህርት ዝግጅት በሌላቸው አመራሮች እየተመራ፣ ለከፍተኛ አስተዳደራዊ ችግር መጋለጡን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡
አንድ የዩኒቨርስቲው ሠራተኛ በሰጠው አስተያየት፤ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ በፊዚክስ፣ምክትሉ ዶ/ር ፍሬው አሞኜ በእንስሳት ህክምና፣ሌላው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር እያዩ  በባዮሎጂ የተመረቁ መሆናቸውን በመጠቆም፣ አንዳቸውም በአስተዳደር ወይም በአመራር ሙያ አለመመረቃቸውን አስረድቷል፡፡ “አመራሩ ለምን በተፈጥሮ ሳይንስ ምሁራን በሞኖፖል እንደተያዘ አልገባኝም” ብሏል፡፡ የፕሬዚዳንትና የምክትል ፕሬዚዳንቶቹ እርስ በእርስ አለመግባባትና በየስብሰባው መዘላለፍ ሌላው የአስተዳደሩን ችግር ያባባሰ ጉዳይ መሆኑን የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ የአመራሮቹ ውዝግብ በተቀረው ሰራተኛ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አልሸሸጉም፡፡
ዩኒቨርስቲው ከ159 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥቶ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ለመምህራን ኮንዶሚኒየም ቤቶች ቢገዛም እስካሁን  ለመምህራኑ አላስረከበም ሲሉ የሚወቅሱት ሠራተኞቹ ፤ህንፃዎቹ ያለ አገልግሎት ቆመው እየተሰነጣጠቁና ለመፀዳጃነት እየዋሉ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዩኒቨርስቲው እስካሁን ወደ 20 ሚሊዮን ብር መክሰሩንና ህንፃዎቹን ለማደስ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠብቀው ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው አመራር፣ የመምህራርንንም ሆነ የሌሎች ሠራተኞችን ቅሬታ ለመስማትና መፍትሄ ለማበጀት ዝግጁ አይደለም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በዚህም የተነሳ በተለይ ወጣቶችና ትዳር ያልያዙ መምህራን በአስተዳደራዊ ችግር እየተማረሩ በየጊዜው ሥራቸውን እየለቀቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ሁለት ምክትል ዲኖችም ከመማረራቸው የተነሳ የአገልግሎት ክፍያ ሳያገኙ ሥራቸውን ጥለው እንደወጡ ገልፀዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ በበኩላቸው፤ ሠራተኞች የሚለቁት የተሻለ ደሞዝ ሲያገኙ እንጂ በአስተዳደራዊ ችግር እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ አስተዳደራዊ ችግር እንዳለ የሚያወሩት የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰራተኞች እንደሆኑም ገልፀዋል – ፕሬዚዳንቱ፡፡ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ በአገር ውስጥ ካሉት ምርጥ ዩኒቨርስቲዎች ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ዶ/ር ባይሌ፤  የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በቀጥታ ከዩኒቨርስቲው በርካታ ምሩቃንን እንደሚቀጥሩ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው አመራር የትምህርት ዝግጅት፣ ከአስተዳደር ሙያ  ጋር ስለማይገናኝ ዘርፈ ብዙ አስተዳደራዊ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው በሚል የተነሱ ቅሬታዎችንም ፕሬዚዳንቱ አይቀበሉትም። “ማንኛውም ሰው የመጀመርያ ድግሪውን በየትኛውም ዘርፍ ሊሰራ ይችላል፤ ለምሳሌ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር የመጀመርያ ድግሪ ከአመራር ጋር የተገናኘ አይደለም” ያሉት ዶ/ር ባይሌ፤ አንድ ሰው ተመራማሪ መሆኑ ከአመራርነት አያግደውም ሲሉ ተሟግተዋል፡፡ እኔ የፊዚክስ ሰው ስለሆንኩ መምራት አልችልም ማለት አይደለም ያሉት ዶ/ሩ፤ ይሄ የሚያሳየው የቅሬታ አቅራቢዎቹን አላዋቂነት ብቻ ነው ብለዋል፡፡ የፕሬዚዳንቶቹን አለመግባባትና መዘላለፍ በተመለከተ ሲያስረዱም ፤ በሃሳብ አለመግባባትና የሃሳብ ልዩነትን እንደተራ ጠብ ማየት የግንዛቤ ችግር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ዋናው ለአላማ መሥራት እንጂ የሰዎች ግንኙነት መሆን የለበትም  ብለዋል፡፡
ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ለመምህራን የተገዙትን ቤቶች በተመለከተ ሲመልሱም “ዩኒቨርስቲው ቤት ለመግዛት ብር ከፈለ እንጂ ቤት አይገነባም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ መረጃ ሰጪዎቹ ያለ እውቀት ወሬ ይዘው የሚሮጡ በመሆናቸው ነው እንጂ ችግሩ የተከሰተው በቤቶች ልማት አቅም ማነስ እንደሆነ ተረጋግጦ፣ ዩኒቨርስቲው የቤቶቹን የማጠናቀቂያ  ሥራ ለመሥራት ውሳኔ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ዩኒቨርስቲው የገዛውን ይሄንኑ ኮንዶሚኒየም ለመምህራኑ ሳያስረክብ በመቅረቱ  ዩኒቨርስቲው ለ20 ሚሊዮን ብር ኪሳራ መዳረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s