ከኔትዎርክ ቀውስ መላቀቅ ያቃተው ኢትዮ ቴሌኮም

ከኔትዎርክ ቀውስ  መላቀቅ ያቃተው ኢትዮ ቴሌኮም

ከኔትዎርክ ቀውስ መላቀቅ ያቃተው ኢትዮ ቴሌኮም

  •  22 February, 2014
  •  Written by  ናፍቆት ዮሴፍ እና መንግሥቱ አበበ

በግማሽ ዓመት ከ7ቢ. ብር በላይ ገቢ አግኝቻለሁ ብሏል

  • “መንግሥት፤ ቴሌ የምትታለብ ላም ናት ቢልም እየታለበ ያለው ህዝቡ ነው”
  • “እነ ቴሌና መብራት ኃይልን ይዞ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ላይ አደርሳለሁ ማለት ቅዠት ነው”
  • “ኢትዮ-ቴሌኮም በደረቅ ቼክ ማጭበርበር ወንጀል መከሰስ አለበት”
  • “መንግስት በቴሌ በኩል ኪራይ ሰብሳቢነቱን አስመስክሯል”

አቶ ሳሙኤል ማሩ ገንዘባቸውን በግል ባንክ ውስጥ ማስቀመጥ ከጀመሩ አራት ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ከሁለት ወር በፊት የአይሱዙ ሹፌር የሆነው ወንድማቸው ድንገተኛ አደጋ ይገጥመውና ቶሎ ድረስ ይባላሉ፡፡ ለክፉ ቀን ብለው ካጠራቀሙት ገንዘብ ላይ አንስተው ለወንድማቸው ሊደርሱለት ያደረጉት ሙከራ ግን አልተሳካም። ገንዘብ ያስቀመጡበት ባንክ ሲሄዱ “ሲስተም የለም፤ ምን እናድርግ?” የሚል ምላሽ ነው ያገኙት፡፡ “በጣም ደነገጥኩ፣ ወደ ሌላ ቅርንጫፍ እንድሄድ ተነገረኝና ቸርችል ጐዳና ወደሚገኝ የባንኩ ቅርንጫፍ ሄድኩኝ” ያሉት አቶ ሳሙኤል፤በሁለተኛው ቅርንጫፍም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ፡፡ በመጨረሻም መርካቶ ራጉኤል አካባቢ ወደሚገኘው ሌላው የባንኩ ቅርንጫፍ ሄዱ፡፡ ሆኖም እዛም እንዳልተሳካላቸው የሚገልፁት አቶ ሳሙኤል፤ለወንድማቸው አደጋ መድረስ እንዳልቻሉ ገልፀው “ያስቀመጥኩት ገንዘብ ለክፉ ቀን ካልደረሰ ለምን ባንክ ውስጥ አስቀምጣለሁ” ሲሉ የኔትዎርክ መጥፋት ያስከተለባቸውን ችግር ተናግረዋል፡፡
በአንድ ትልቅ የግል ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩትና የሆስፒታሉም ሆነ የራሳቸው ስም እንዲጠቀስ ያልፈለጉ  የህክምና ባለሙያ፤በሆስፒታላቸው ውስጥ “ቴሌ ሜዲሲን” የሚባል አሰራር ዘርግተው እንደነበር ይናገራሉ። በአገር ውስጥ ህክምናው ከሌለና ህመምተኞች ወደ ህንድና ታይላንድ ሄደው የመታከም አቅም ከሌላቸው በቴሌኮንፍረንስ ታካሚውን ከህንድና ባንኮክ ስፔሻሊስቶች ጋር በቀጥታ የሚያገናኝና የሚያወያይ አሰራር እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተሩ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ  የመጣው የኔትዎርክ ችግር አላሰራ ስላላቸው አገልግሎቱን ለማቆም መገደዳቸውን ገልፀዋል፡፡ “ዓለም አንድ መንደር እየሆነች በመጣችበት በዚህ ዘመን ሁሉም ስራ በስልክና በኢንተርኔት ነው የሚያልቀው” ያሉት ዶክተሩ፤በአገራችን ግን ቴክኖሎጂው እክል ስለገጠመው ብዙ ሥራዎችን እያስተጓጎለ እንደሆነ ጠቁመው፤ ቶሎ ታክሞ መዳን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
መኻል ፒያሳ፣ ኪዳነ ምህረት የጥርስ ህክምና አጠገብ ያሉ የኢንተርኔት ቤት ባለቤቶች በበኩላቸው፤ የተጠቃሚው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም በኔትዎርክ መንቀራፈፍና መቆራረጥ የተነሳ  ከሚሰሩበት ቀን የማይሰሩበት እንደሚበዛ ይገልፃሉ። “የምንጠቀመው ብሮድባንድ ኢንተርኔት በመሆኑ ብንሰራም ባንሰራም ለቴሌ መክፈላችን አይቀርም” ያለችው የኢንተርኔት ቤት ተቀጣሪዋ ሳራ፤አለቆቿ ስራውን ለማቆም እንዳሰቡና “ስራ ፈልጊ” እንደተባለች ገልፃለች፡፡
ካዛንቺስ አካባቢ የኢንተርኔት አገልግሎት በመስጠት የሚተዳደሩት አቶ አውላቸውም የኔትዎርክ ችግር ራስ ምታት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡ ኢንተርኔት ቤቱን ከከፈቱ ሦስት ዓመት ቢሆናቸውም ከሦስቱ ዓመት አንዱን ዓመት እንኳን በወጉ አልሰራሁበትም ይላሉ፡፡ “ከዛሬ ነገ ይሻሻላል እያልኩ ብጠብቅም የኔትዎርክ ችግር እየባሰበት ድርጅቴ አፉን ከፍቶ እየዋለ ነው” የሚሉት አቶ አውላቸው፤ “ኢትዮ-ቴሌኮም በቂ መሰረተ ልማት ሳይዘረጋ፣ ሲምካርድና የኢንተርኔት አገልግሎት ፈቃድ መስጠቱ በደረቅ ቼክ እንደማጭበርበር የሚቆጠር ነው” ብለዋል፡፡ “አንድ ሰው በባንክ ሂሳቡ በቂ ገንዘብ ሳይኖረው ቼክ ቆርጦ ከሰጠ፣በደረቅ ቼክ ማጭበርበር ወንጀል ወደ ሰበር ችሎት ይቀርባል” ያሉት አቶ አውላቸው፤ “ቴሌም ከዚህ የተለየ ወንጀል እየሰራ አይደለም፤በቂ ኔትዎርክና መሰረተ ልማት ሳይዘረጋ አሁንም ሲምካርድ እየሸጠ ነው፤ ለኢንተርኔት አገልግሎትም ፈቃድ ይሰጣል” በማለት ወቅሰዋል፡፡
መንግሥት በኮንዶሚንየም ቤት፣ በሽልማትና በቦንድ ግዢ የግል ባንክ ደንበኞችን ወደ ራሱ በመሳብ በግል ባንኮች ህልውና ላይ ስጋት ፈጥሯል ያሉ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የባንክ ባለሙያ፤ ይሄም ሳያንስ የቀሩትን ጥቂት ደንበኞቻቸውን እንኳን በአግባቡ እንዳያስተናግዱ ኔትዎርክ ጫና እንደፈጠረባቸው በምሬት ገልፀዋል፡፡ “በአሁኑ ወቅት የግል ባንኮች ህልውና አደጋ ላይ ነው” ያሉት ባለሙያው፤ መንግሥት ችግሩን ለማቃለል እየሰራሁ ነው ቢልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት መምጣቱን ጠቁመው፣ ችግሩ የባንክ ሥራን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ከማሽመድመዱ በፊት እልባት ሊበጅለት ይገባል ብለዋል፡፡
የቀድሞ የኢዴፓ ሊቀመንበርና የባንክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤የቴሌኮም ችግር በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ይላሉ። “ባንኮች በኔትዎርክ መቆራረጥ በአግባቡ ማስተናገድ ካልቻሉ ደንበኞች በባንኮች ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ ይሄድና ባንኩ ውስጥ ከሚቀመጠው ገንዘብ ይልቅ በግለሰቦች ኪስ የሚንቀሳቀሰው ይበዛል፤ይሄ ደግሞ ለኢኮኖሚው ትልቅ ውድቀት ይሆናል” ብለዋል – አቶ ሙሼ፡፡
“እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የመዋቅር ችግር ባለባቸው አገራት ቴሌኮምን የማስተዳደር አቅም ያላቸው አመራሮችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው” ያሉት አቶ ሙሼ፤ መንግሥት የተወሰነ ድርሻ ይዞ ሌላውን ድርሻ ለግለሰቦች በመሸጥ ፉክክር መፍጠር አለበት ሲሉ ይመክራሉ፡፡ መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን በአግባቡ ለማስኬድ ከፈለገ ሦስት አማራጮች አሉት ይላሉ። አንደኛው ከላይ እንደተገለጸው መንግሥት የተወሰነ ድርሻ ይዞ ሌላውን ለግለሰቦች (ድርጅቶች) መስጠት ሲሆን ሁለተኛው፤ ተቋሙን ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ባለሀብቶች ማዞር ነው፣ሦስተኛው ደግሞ መንግስት በተጠናከረ አመራርና ከሙስና በፀዳ አሰራር የተሻለ አገልግሎት የሚሰጥበትን መንገድ ማመቻቸት ነው ሲሉ በዝርዝር ገልፀዋል፡፡ “በአሁኑ ጊዜ የኔትዎርክ መቆራረጥ ባንኮች ማግኘት የሚገባቸውን ያህል ገቢ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል” ያሉት ባለሙያው፤ ደንበኞችም ባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ በፈለጉት ሰዓት እንዳያገኙ እያደረጋቸውና ለጊዜ ብክነትም እያጋለጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“የኔትዎርክ ችግር በዚሁ ከቀጠለ የህብረተሰቡን በባንክ የመጠቀም ልማድ ያዳክማል፤ ኢኮኖሚው ላይም ኪሳራን ያመጣል” ያሉት አቶ ሙሼ፤ባንኮች ወደ ቀደመው የማኑዋል አሰራር እንመለስ ቢሉ እንኳን ማዕከላዊ የአሰራር ሲስተም እንዲከተሉ የሚያስገድደው የብሔራዊ ባንክ ህግ እንደሚከለክላቸው ገልፀዋል፡፡
በመዲናዋ እየተበራከቱ የመጡ ህንፃዎች ለኔትዎርክ መቆራረጥ እንደምክንያት ሲጠቀሱ ቢቆዩም አቶ ሙሼ በዚህ አይስማሙም፡፡ “ደካማ የሆነ የመንግሥት መከራከሪያ ነው” ሲሉ የሚያጣጥሉት ባለሙያው፤ የኔትዎርክ ችግር የጀመረው ህንፃዎች ከመገንባታቸው በፊት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
መንግሥት ተገቢ አገልግሎት መስጠት ባቃተው ቁጥር “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ዓይነት ተራ ሰበብ እየፈጠረ ነው ያሉት አቶ ሙሼ፤ “እነ ኒውዮርክ፣ ዱባይ፣ ቻይናና ሌሎች የዓለም ከተሞች እስከ መቶና ከዚያ በላይ ርዝመት ያለው ፎቅ ቢኖራቸውም የኔትዎርክ ችግር አጋጠማቸው ሲባል አይሰማም። የእኛ አገር ህንፃ ከ20 ፎቅ በላይ ስላልሆነ ፈፅሞ ከኔትዎርክ ችግር ጋር አይገናኝም” ብለዋል፡፡
“ይልቅስ ለኔትዎርክ ተብሎ የተዘረጉት መሰረተ ልማቶች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም” ያሉት አቶ ሙሼ፤ በርካሽ ዋጋና በብደር ከወዳጅ አገር በሚገቡ ርካሽ ቴክኖሎጂዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረብ እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡
ከማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ በዲግሪ ተመርቆ በአንድ የውጭ ድርጅት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያነት የሚሰራው ወጣት ያሲን አብዱልመሊክ፤ ከአቶ ሙሼ ሃሳብ ጋር ይስማማል። የህንፃ ግንባታ ለኔትዎርክ መቆራረጥ በፍፁም ምክንያት አይሆንም ያለው ያሲን፤ ለኔትዎርክ መቆራረጥ መንስኤው ደረጃውን ያልጠበቀ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የተጠቃሚውን ቁጥር ያላገናዘበ መሰረተ ልማትና ከኃይል አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሆኑ አብራርቷል፡፡
መንግስት ቴሌኮምን ለግል ዘርፉ የማይሰጠው የምትታለብ ላብ ወይም የገንዘብ ማተምያ ማሽን ስለሆነ ነው እያለ መንግስት በተደጋጋሚ ይገልፃል። ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ ግን ከመንግስት አባባል ጋር አይስማሙም። “መንግሥት፤ቴሌ የምትታለብ ላም ናት እያለ ቢለፍፍም እየታለበ ያለው ግን ህዝቡ ነው” ባይ ናቸው፡፡ በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ “ሎጂስቲክስ” የሚባሉ ነገሮች አሉ የሚሉት ባለሙያው፣ እነዚህ ሎጂስቲክስ በሁለት እንደሚከፈሉ ጠቅሰው፤የትራንስፖርት፣ የባቡርና መሰል ትልልቅ ፕሮጀክቶች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እንደ ቴሌኮም፣ ኢንተርኔት የመሳሰሉትም ተገቢ አገልገሎት ላይ ከዋሉ በኢኮኖሚ ውስጥ እሴት በመፍጠር እድገት እንደሚያፋጥኑ ይናገራሉ። እነዚህ ሎጂስቲክስ በተገቢው መንገድ አገልግሎት ካልሰጡ ግን ባንኮች፣ ሆቴሎች፣ ሆስፒታሎች፣ አየር መንገዶችና መሰል ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ ብለዋል፡፡
“የኔትዎርክ መቆራረጥ ኅብረተሰቡ በሞባይልና በኢንተርኔት የመጠቀም እምነቱን ስለሚሸረሽር ትልቅ ጉዳት አለው” ያሉት ባለሙያው፤ ይህም አጋጣሚና እድልን ያለመጠቀም (opportunity cost) ከሚባለው ውስጥ እንደሚመደብ አብራርተዋል፡፡ “ቴሌ ደረጃውን ያልጠበቀ አገልግሎት እየሰጠ ህዝቡን እያለበው ነው” የሚሉት ኢኮኖሚስቱ፤ “በአንድ ስልክ ማለቅ የሚገባው ጉዳይ በአስር ስልክ እያለቀ ባለበት ሁኔታ መንግሥት ያለተቀናቃኝ የያዘውን ተቋም በመጠቀም ኪራይ የመሰብሰብ ስራውን አስፋፍቶ መቀጠሉ፣ ተመጣጣኝና ተገቢ አገልግሎት ሳይሰጡ ገንዘብ ማጋበስ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል፡፡ መንግስት በቴሌ በኩል ኪራይ ሰብሳቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በቴሌኮም ላይ ለሚታየው ችግር መፍትሄው ዘርፉን ለግል ባለሃብት ማዛወር ነው የሚሉት ባለሙያው፤  መንግሥት ፈቃድ በመስጠትና መሰል ሥራዎች ብቻ በርካታ ገቢዎች ሊያገኝ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ቴሌኮምን ለግል ባለሃብት የማያዛውረው ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለመሰረተ ልማት ሥራዎች ስለሚፈልገው እንደሆነ በየጊዜው ይገልፃል፡፡ በሌሎች አገሮች እንዲህ ዓይነት ተቋሟት ለግለሰቦች የሚዛወሩት መንግሥት ገንዘብ ጠልቶ አይደለም የሚሉት ባለሙያው፤ ይልቁንም የተሻለ ገንዘብ የሚገኘው ዘርፉ ወደ ግል ባለሃብት ሲዛወር መሆኑን ስለሚያምኑ ነው ብለዋል፡፡
“እንዲህ ዓይነት ተቋማት ወደ ግል ዘርፍ ሲዛወሩ ፉክክር ይኖራል፣ ፉክክር ሲኖር ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ይፈጠራል፣ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሲኖር ተጠቃሚው ይበዛል፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ በዋነኝነት ተጠቃሚው መንግሥት ይሆናል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡ እንደ እነቴሌኮምና መብራት ኃይል የመሳሰሉ  ተቋማት በመንግሥት ተይዘው አገሪቱን በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ ማቀድ ቅዥት ነው የሚሉት ባለሙያው፤ እንዲህ ያሉ እቅዶችን እውን የሚያደርገው የግሉ ዘርፍ እንደሆነ የሌሎች አገራት ተሞክሮ ያረጋግጣል ብለዋል፡፡
የመሰረተ ልማት መስፋፋቱ በጎ ጅማሮ ቢሆንም ጥንቃቄ ስለሚያንስው በአብዛኛው ለሙስና የሚጋለጥበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ያለ ጨረታ፣ ያለ ውድድርና በተድበሰበሰ መንገድ ጥራት የሌላቸው ዕቃዎች እየገቡ ችግር የሚፈጥሩት በውስጡ ሙስናና ሙሰኞች ስላሉ ነው ያሉት ባለሙያው፤“ይህን በድፍረት የምነግርሽ ጉዳዩን በደንብ ስለማውቀው ነው” ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ “ከሙስና ጋር በተያያዘ ለማስፋፊያ ስራ የሚመጡ ድርጅቶች ሳይናበቡ የየራሳቸውን ሲስተም ስለሚጭኑ በቴሌኮም ሰርቪስና በኔትዎርኩ ላይ ከፍተኛ ጫናና ችግር ይፈጥራሉ” በማለትም አብራርተዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮ-ቴሌኮም ሰራተኞችን በመከለስና በመፐወዝ፣ በቴክኒክ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን በርካታ ሰራተኞች በመቀነስ ከስራው ጋር ትውውቅ የሌላቸውን ሰራተኞች መቅጠሩ አሁን ላለው የቴሌኮምና የኔትዎርክ አጠቃላይ ችግር የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል የሚሉ በርካታ ወገኖች አሉ፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው በዚህ አስተያየት ይስማማሉ። “ይኼ ምንም ጥርጥር የለውም፣ በወቅቱ የመጣው የፈረንሳይ ኩባንያም ቢሆን የሞባይል ቁጥር መሙያ፣ ካርድ መሙያና ቀላል ነገሮችን በተለይም ማርኬቲንግ ላይ ከመስራት ባለፈ ቴክኒክ ላይ እንዲሰራ አልተፈቀደለትም” ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ኢትዮ ቴሌኮም በወቅቱ ሳያስብና ሳያቅድ የአሰራር ለውጥ ማድረጉ የአመራር ችግር ፈጥሯል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ “የተሻለ ሰው ሳይዘጋጅ ዲግሪ የለህም፣ የትምህርት ደረጃህ በቂ አይደለም” በማለት ብዙ ልምድና የቴክኒክ እውቀት የሌላቸውን መቅጠሩም አሁን ላለው ችግር አንዱ መንስኤ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
“ጥሩ የሚሰሩትን እየለቀቀ ያልተሻለ ማምጣት፣ “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” ዓይነት ችግር እየፈጠረ ነው” ያሉት ባለሙያው፤ ይህ በቴሌ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም የሚከሰት በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሌለ ኔትዎርክ ከጊዜ ወደጊዜ የሞባይል ባንኪንግ አዳዲስ አገልግሎት እያስተዋወቀ መሆኑን የሚናገሩ አስተያየት ሰጭዎች፣ የባንኩ አካሄድ ግራ እንዳጋባቸው ይገልፃሉ።  የባንኩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፤ በኔትዎርክና በስልክ የሚሰጡ አገልግሎቶችን መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ ባንኩ ችግር ሲያጋጥመው ለዚህ ተግባር ተብለው የተመደቡ ሠራተኞች ስላሉ ለእነሱ በመንገር ችግሩን እንደሚፈቱ ተናግረዋል፡፡ የባንኩ ሥራ ከመብራት ኃይል ጋር የተያያዘ መሆኑንም ጠቅሰው፣ኤሌክትሪክ ሲጠፋ ኤቲኤም ማሽኖች ስለማይሠሩ፣ ሕዝቡ መብራት ያለበት እየፈለገ ይጠቀማል ብለዋል፡፡ ከሁለቱ መ/ቤቶች ጋርም በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
በቴሌ የማስፋፊያ ስራ ላይ ለመሳተፍ የተፈራረመውና ከዚህ ቀደም የተሰጠውን ፕሮጀክት ሰርቶ ያስረከበው የቻይናው “ዜቲኢ” ኩባንያ፤ በኔትዎርክ መቆራረጥ ችግር ዙርያ ላቀረብንለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ከዚህ በፊት የሰራው ፕሮጀክት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ከዓለም ባንክ እውቅና እንደተሰጠው ጠቅሶ ኩባንያው ለኔትዎርክ መቆራረጥ ችግር ተጠያቂ እንዳልሆነና ይሄ የሚመለከተው ኢትዮ ቴሌኮምን እንደሆነ ገልጿል፡፡
ህዋዌ የተባለ ሌላው የቻይና ኩባንያ ከወራት በፊት የማስፋፊያ ስራ ለመስራት ከቴሌ ጋር የተፈራረመ ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያ ላነሳነው ጥያቄ “እኛ ስራ አልጀመርንም፣ የሰራነውም ስራ ስለሌለ ስለጉዳዩ አስተያየት መስጠት አንችልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ በሰጠው መግለጫ፤  የኔትዎርክ ችግሩን በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታ ያስታወቀ ቢሆንም ብዙዎች ግን እምነት ያደረባቸው አይመስልም፡፡
የሞባይል አገልግሎት በ1991 ዓ.ም ሲጀመር የተጠቃሚው ቁጥር 36 ሺህ የነበረ ሲሆን አሁን ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 27.1 ሚሊዮን ማድረሱን በቅርቡ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 26.2 ሚሊዮኑ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ናቸው – የድርጅቱ መረጃ እንደሚጠቁመው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት አላማም የደንበኞቹን ቁጥር  ወደ 39 ሚሊዮን ለማድረስ ሲሆን አሁን ያለውን 64 በመቶ የመገናኛ መሰረተ-ልማት በትራንስፎርሜሽን ዓመቱ መጨረሻ ላይ ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ይዟል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s