ባለሥልጣኑን በመቃረን ክፍለ ከተማው ልኳንዳ ነጋዴዎች ላይ ግብር መወሰኑ ቅሬታ አስነሳ

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የማኅበሩ አባላት በነፍስ ወከፍ ከ500 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ እንዲከፍሉ የተጣለባቸው የግብር ውሳኔ ፍትሐዊነት የጐደለው፣

ገቢያቸውንና አቅማቸውን ያላገናዘበ መሆኑን ገለጸ፡፡ ይህ ዓይነቱ ውሳኔም እንዲነሳ አለበለዚያም እንዲታረም በፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለአገር ውስጥ ታክስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት አቤቱታ አቀረበ፡፡ ዳይሬክቶሬቱም በጉዳዩ ላይ ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ 

ማኅበሩ በዋና ሥራ አስኪያጁ በኩል መጋቢት 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጻፈው ደብዳቤ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የክፍለ ከተማውን ውሳኔ ፍትሐዊነት የጐደለው ነው ለማለት ያበቃው፣ ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ የልኳንዳ ነጋዴዎች ላይ የሚጣለውን የግብር አወሳሰን በተመለከተ የሚያጠና ቡድን አቋቁሞ ባለበት፣ ቡድኑም ጥናቱን ባላጠናቀቀበትና ውጤቱም ገና ባልታወቀበት ወቅት በቅድሚያ ውሳኔው በመተላለፉ ነው፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በክፍለ ከተማው ከሚገኙ ነጋዴዎች መካከል በስድስት የልኳንዳ ነጋዴዎች ላይ የግብር ውሳኔ የወሰነባቸው ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ በቫት ማሽን እንደሠሩ ታስቦ፣ ፍሬ ግብር አሳንሶ በማሳወቅ፣ በጊዜ ባለመክፈልና መዝገብ ባለመያዝ በሚል ምክንያት መሆኑን ደብዳቤው አመልክቷል፡፡ በተጠቀሰው ዘመን ግን ዘርፉ በቫት እንዳልታቀፈ፣ ነጋዴዎቹም በዘመኑ በነበረው የግብር ስሌት መሠረት የሚጠበቅባቸውን ሲከፍሉ መቆየታቸውን ደብዳቤው ጠቅሷል፡፡

አቶ የኋላእሸት በጋሻው በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለአገር ውስጥ ታክስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር፣ ማኅበሩ ያቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ከሪፖርተር በስልክ ተጠይቀው፣ ደብዳቤው ከመዝገብ ቤት ገና እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የደብዳቤውን ይዘት ከተረዱ በኋላ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የጥናት ቡድኑ መሪ አቶ ወንድምአገኝ ካሳዬ እንደገለጹት ከሆነ፣ ጥናቱ እንዲካሄድ ያስፈለገው ከልኳንዳ ንግድ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች በመኖራቸው ነው፡፡ ከችግሮቹም መካከል የግብይት ሥርዓቱ በሕግ ሊመራ አለመቻሉ፣ የሽያጭ መረጃ አለመኖር፣ የምርት መጠኑ አለመታወቅ (ከአንድ በሬ፣ በግና ፍየል የሚወጣው ሥጋ ስንት ኪሎ እንደሆነ በአግባቡ አለመታወቅ)፣ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ብዙዎቹ የልኳንዳ ነጋዴዎች አንድ ኪሎ ሥጋ እስከ 150 ብር ከፊሎቹ ደግሞ እስከ 100 ብር እንደሚሸጡና ይህ ዓይነቱም የሽያጭ አለመመጣጠን በግብር አጣጣሉ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ መሆኑን ከቡድኑ መሪ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ነጋዴዎቹ የግብር ውሳኔውን ላሳለፈው ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ቅሬታቸውን ሳያቀርቡ፣ ጉዳዩን በቀጥታ ወደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለአገር ውስጥ ታክስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለምን ማቅረብ ፈለጉ? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ‹‹ነጋዴዎቹ በየስማቸው ቅሬታቸውን ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለማቅረብ ሲሞክሩ አንቀበልም የሚል መልስ ስለተሰጣቸው ነው፤›› በማለት የማኅበሩ ነገረ ፈጅ አቶ አየለ ሣህሌ መልሰዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የደንበኞች አገልግሎት የነጋዴዎችን ቅሬታ ለመቀበል አለመፈለጉን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኛ፣ ‹‹ቅሬታ አንቀበልም የሚል አካል የለም፡፡ ይህም ሆኖ ግን አቀራረቡ ራሱን የቻለ ሒደት አለው፡፡ በዚህ ሒደት ቅሬታ ያለው ሰው በመጀመሪያ ለደንበኞች አገልግሎት ጉዳዩ እንደገና እንዲታይለት የሚገልጽ ጥያቄ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ የደንበኞች አገልግሎትም ጉዳዩን በኮሚቴ ያይና ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ግለሰቡ ውሳኔው ካላረካው ከተጠየቀው ግብር ውስጥ 50 በመቶ ያህሉን በቅድሚያ ከፍሎ ቅሬታውን ለግብር ይግባኝ ሰሚ ሊያቀርብ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ከስድስት የልኳንዳ ነጋዴዎች መካከል ሒደቱን ተከትለው ለደንበኞች አገልግሎት ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሁለት ብቻ መሆናቸውንና የእነዚህም ቅሬታዎች በኮሚቴ ከታየ በኋላ ውሳኔ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም በአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች መካከል የግብር አወሳሰንን በተመለከተ ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡ በተለይ ልኳንዳ ቤቶች በስፋት በሚገኙባቸው የከተማዋ አካባቢዎች ላይ የሚነግዱ ልኳንዳ ነጋዴዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር የግብር ዕዳ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን፣ ይህንን በመቃወምም ሥራ ለማቆም እንደሚገደዱ ያስጠነቀቁ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

የነጋዴዎቹ ቅሬታ የመነጨው ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ከፍተኛ ግብር ተጥሎብናል ከሚል መነሻ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ከአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አገኘሁት ባለው መረጃ ላይ ተመርኩዞ ባሰላው ስሌት መሠረት ሊከፈለኝ ይገባል ያለው ከፍተኛ ግብር ተቀባይነት በማጣቱ፣ ውሳኔውን በመቀየር የጥናት ቡድን ሰይሟል፡፡ የጥናት ውጤቱም እየተጠበቀ ነው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s