‹‹ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ካላቆመች ወታደራዊ ኃይል እጠቀማለሁ››

ሞርታዳ ማንሱር፣ የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ 

በግብፅ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን በዕጩነት ያቀረቡት የሕግ ባለሙያው ሞርታዳ ማንሱር፣ ‹‹ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ካላቆመች ወታደራዊ ኃይል እጠቀማለሁ፤›› በማለት አስጠነቀቁ፡፡

አወዛጋቢና ስሜታዊ እንደሆኑ በይፋ የሚታወቁት የሕግ ባለሙያና ከሳምንት በፊት ደግም ዛማሌክ ለተባለው ታዋቂ የግብፅ እግር ኳስ ቡድን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ማንሱር፣  ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፉት ባለፈው እሑድ ፕሬዚዳንታዊ ውድድርን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ጦነርት በመክፈት የግብፅ ሕዝብን ጥቅም እንደሚያስከብሩም ተናግረዋል፡፡ የዓባይ ወንዝን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 የተፈረሙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ማንሱር፣ ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት ወደጎን ብላ ግንባታውን መቀጠሏን ተቃውመዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያና ግብፅን ከማግባባት የተቆጠቡ ዓለም አቀፍ ተቋማት አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በአቋሟ ፀንታ ግድቡን መገንባት ቀጥላለች፡፡ ኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም እንዳላት በመግለጽ ግብፅን እያስፈራራች ነው፡፡ ነገር ግን ግብፅም ወታደራዊ አቅም አላት፤›› ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጀርባ እስራኤል እንዳለች የተናገሩት ማንሱር፣ ይህ ቢሆንም የግብፅን የውኃ ድርሻ ለመገደብ የሚደረግ ጥረት ለግብፃውያን የሞትና ሽረት ጉዳይ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ወደ ግድቡ የጦር ጄኔራሎቻቸውን ወስደው እየፎከሩ ግብፅ ከመጣች የሚሉ ከሆነ ግብፅም ጄኔራሎችና ተዋጊ ጄቶች እንዳላት ይወቁ፡፡ ግብፅ ጠብታ ውኃ እንዲጎድልባት አትፈቅድም፡፡ በዚህ ጉዳይ አንደራደርም፡፡ ይህ ለግብፃውያን ሞትና ሽረት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለግብፅ ፕሬዚዳንትነት ራሳቸውን በዕጩነት ያቀረቡት ማንሱር ገና ወደ ውድድር ለመግባት የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኮሚሽንን ይሁንታ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው ማንሱር የኮሚሽኑን ይሁንታ እንኳን ማግኘት ቢችሉ የሚወዳደሩት በቅርቡ ከግብፅ መከላከያ ሚኒስትርነትና ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምነት ከለቀቁት ፊልድ ማርሻል አልሲሲ ጋር መሆኑን የጠቆሙት መገናኛ ብዙኃን፣ በፕሬዚዳንትነት የመመረጥ ተስፋ እንደሌላቸው የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል፡፡

በግብፅ እ.ኤ.አ. በ2012 በተካሄደው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ማንሱር ራሳቸውን በዕጩነት አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኮሚሽኑ ተቀባይነት አለማግኘታቸው አንዱ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ አራት ጊዜ ለፓርላማ ቢወዳደሩም ማሸነፍ የቻሉት ግን አንድ ጊዜ መሆኑን፣ እንዲሁም ሰውየው በጣም ስሜታዊና ግልፍተኛ መሆናቸው በቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ጭምር መረጋገጡ በምክንያትነት የተጠቀሱት ናቸው፡፡

ማንሱር ግልፍተኛና ስሜታዊ ቢሆኑም፣ በርካቶች የግብፅ አመራሮች በግልጽ አያወጡትም እንጂ በዓባይ ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው በተደጋጋሚ የሚነገር ከመሆኑም ባሻገር፣ ከዓመት በፊት የግብፅ ፕሬዚዳንት በነበሩት መሐመድ ሙርሲ ጊዜ  በግብፅ በቀጥታ ቴሌቪዥን እንዲህ ዓይነቱ ማስጠንቀቂያ መተላለፉ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ግን ከግብፅ በኩል በቀጥታ ጥቃት ይሰነዘራል ብለው አይገምቱም፡፡  የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ባለፈው ሳምንት በዚህ ጉዳይ ላይ በፓርላማው ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለዚህ የጠቀሷቸው ምክንያቶች ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እያካሄደች የምትገኘው ከዓለም ተደብቃ አለመሆኑንና የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ዜጎች  በግድቡ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ መሆናቸው ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማንኛውንም ጥቃት የመመከት ዝግጁነት እንዳለው ግን አረጋግጠዋል፡፡

የማንሱርን ንግግር በተለያዩ ድረ ገጾች የተከታተሉ ግብፃውያንና ኢትዮጵያውያን ስሜቶቻቸውን በድረ ገጾቹ ላይ አስፍረዋል፡፡ ‹‹ጥሩ ፕሬዚዳንት የሚለካው በመደራደር አቅሙ፣ ትዕግሥቱና ዕውቀቱ ነው፡፡ ኃይል የመጨረሻ አማራጭ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ግድብ በላይ የሚያስጨንቀን የውስጥ ጉዳይ አለ፤›› የሚሉ የግብፃውያን አስተያየት አዘል ሙግቶች በግለሰቡ ላይ ተሰንዝረዋል፡፡

በኢትዮጵያውያን አንባቢያን በኩል እልህ የተጋቡ የሚመስሉ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያና ግብፅ ቢተባበሩ ሁለቱም ይጠቀማሉ፣ ነገር ግን ግብፅ እንደ ማንሱር ከወሰነች ሁሉቱ አገሮች ይጎዳሉ ብለዋል፡፡ ግብፅ በግድቡ ምክንያት የውኃ አቅርቦት እንደማይስተጓጐልባት ይልቁንም ከዚህ ግድብ በሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንደምትሆን የገለጹ አሉ፡፡

የግብፅ ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች ተለዋዋጭ አቋም በየጊዜው እየተንፀባረቀ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከግድቡ ቦንድ በመግዛት የግድቡ ግንባታ ማኔጅመንት ላይ ለመሳተፍ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰጠው ምላሽ የግድቡ ባለቤት ኢትዮጵያ ስለሆነች ይልቁንም ግብፅ ወደ ድርድሩ መመለስ ይሻላታል ነበር የተባለው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s