ዘር ማጥፋት ያጠላባት ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ

መደፈር፣ ያሉበት ሥፍራ አለመታወቅ ብሎም መገደል ለማዕከላዊቷ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዜጐች የተለመደ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ንፁኃን እያለቁ ናቸው፡፡ ገዳዮች ደግሞ ከዕለት ዕለት ኃይል እያገኙ ነው፡፡

ሸማቂዎች በነገሡባት ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በሃይማኖት ተከፋፍለው የሚጨፋጨፉት ወገኖች፣ በተለይ ለንፁኃን ሕፃናትና ሴቶች ጦስ ሆነዋል፡፡ በአገሪቱ ምግብ ማግኘትም ከብዷል፡፡ የሚጠጣ ውኃም እንዲሁ፡፡ ቤት ውስጥ አድሮ አንገትን ለሰይፍ ከመስጠት አዳርን በዛፎችና በቁጥቋጦዎች ሥር ማድረግ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡  

በተለይ የሲሊካ አማጽያን የአገሪቱን መንግሥት አስወግደው ሥልጣን ከተቆጣጣሩበት ካለፉት አራት ወራት ወዲህ አገሪቷ ተፍረክርካለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ምድሪቱን በጣም አስጊ ሥፍራ ብሏታል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ 4.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጐችም የእምነት ግጭት ሰለባዎች መሆናቸውን አሳውቋል፡፡ በዓለም በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የተነፈገው ብጥብጥ የሰፈነባትም ሆናለች፡፡ ለዓመት በዘለቀው ብጥብጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሞቱ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወደ ጐረቤት ካሜሩን ተሰደዋል፡፡ አሁን ደግሞ እስከዛሬ ከነበረው ብጥብጥ የከፋ ዘር የማጥፋት አደጋ በአገሪቱ ላይ ተጋርጧል፡፡

ዘር ማጥፋት ባጠላባት ማዕከላዊት አፍሪካ ዋና ከተማ ባንጉዊ ሳይቀር ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ መገዳደል ተስፋፍቷል፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ዜጐች የምግብ ዋስትና ያጡ ሲሆን፣ ከ200 ሺሕ በላይ ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡ የአገሪቱ መሠረተ ልማት ወድሟል፡፡ የአገሪቱ ወታደሮች ተበታትነዋል፡፡ በመላ አገሪቱ የቀሩት 200 ፖሊሶች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ ፖሊሶች ደግሞ ሕዝቡን ለመከላከል አቅሙ የላቸውም፡፡ አገሪቱን የሚዳኛትም ጠፍቷል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞችም አገሪቱ ‹‹የባለ ብዙ ጭንቅላት ጭራቆች›› መናኸሪያ ሆናለች ብለዋል፡፡

‹‹በማዕከላዊት አፍሪካ ምንም የለም፣ የተቀናጀ የፀጥታ ኃይል የለም፣ ፖሊስ የለም፣ ፍትሕ የለም፣ ሥርዓት የለም፤›› ሲሉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊ ተናግረዋል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰጠው ምላሽም ደካማ ነው፡፡ ለዓመት ያህል የአገሪቱ ዜጐች በቆንጨራ ሲጨፈጨፉ፣ በጦር መሣሪያ ሲገደሉ፣ ሴቶች ሲደፈሩ እምቢ ያሉም ሲገደሉ፣ ሕፃናት ለውትድርና ሲመለመሉ፣ ሕዝቡ ሲራብ፣ ሲጠማና ሲሰደድ፣ በአገሪቱ ሥርዓት አልበኝነት ሰፍኖ ሸማቂዎች አገሪቷን እንዳልነበረች ሲያደርጉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት ምላሽ የረባ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ዜጐቿ ለጥቃት ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ከፈረንሳይ ወታደሮች ጋር በመሆን ግጭቱን ለማብረድ ከዓመት በፊት አገሪቱ ቢገባም፣ ችግሩን መቆጣጠር ተስኖታል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሳይማር ለማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እጁን ሳይዘረጋ ከርሟል፡፡

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብለክ እየተካሄደ ያለውን ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ ለማስቆምና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰጠውን ዘገምተኛ ምላሽ ለመቀልበስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፣ ‹‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለቀውሱ የሰጠውን ምላሽ እንዲያሻሽል ማንኛውንም ሊሆን የሚችል አማራጭ አደርጋለሁ፤›› ሲሉ የተሰሙትም ሰሞኑን ነው፡፡

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክን ለመታደግ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮችና ከሁለቱም አኅጉራት የተውጣጡ 30 መሪዎች ለሁለት ቀናት በብራሰልስ በመከሩበት ወቅት የአውሮፓ ኅብረት አንድ ሺሕ ወታደሮችን ለመላክ ቃል በገባው መሠረት ቢልክም አገሪቷን መታደግ አልተቻለም፡፡ ቀድመው የነበሩት ስድስት ሺሕ የአፍሪካ ኅብረት ወታደሮችም ቢሆኑ እንዲሁ፡፡ በመሆኑም በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ያለው ግጭት ዘር ማጥፋት ላይ እየደረሰ መሆኑን ባን ኪ ሙን አሳስበው፣ ‹‹ሕዝቡ ሰቅጣጭ ለሆነ ሞት ተጋልጧል፤›› ብለዋል፡፡

ስምንት ሺሕ የሚደርሱ የአፍሪካ ኅብረትና የፈረንሳይ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከዓመት ላላነሰ ጊዜ በአገሪቱ በተለይም በዋና ከተማዋ ባንጉይ ሰላም ለማስከበር ሲሠሩ የቆዩ ቢሆንም፣ ብዙ ለውጥ ማምጣት ስላልቻሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን በባንጉይ አካባቢ የሚኖሩ 19 ሺሕ ያህል ንፁኃን ዜጐችን ከአካባቢው ለማውጣት ተገዷል፡፡ 16 ሺሕ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ እየተባባሰ የመጣውን ግጭት በመሸሽ ከከተማዋ ወጥተዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ሰላማዊ ቤተሰቦች ከአገሪቱ የሚወጡበትን መንገድም እያማተሩ ነው፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር እየታጀቡ ከከተማዋ ባንጉይ ወደ ካሜሩን የሚያቀኑትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

ከዚህ ቀደም ከነበረው በከፋ ሁኔታ በተለይም በዋና ከተማዋ ባንጉይ አዲስ የተቀሰቀሰው ግድያ፣ ዘረፋና ሥርዓት አልበኝነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን አሳስቦታል፡፡ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት በተከሰተ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ባለመስጠቱ የሚተቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዛሬም ከዓመታት ዕልቂት በኋላ ነው ለማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ችግር ምላሽ ለመስጠት የተነሳው፡፡

የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የዘር ማጥፋት ይከሰታል ብለው ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ፣ ድርጅቱ ሰላም አስከባሪ ኃይሉን ወደ አገሪቱ ለመላክ ወስኗል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል የተነሳውን የዘር ማጥፋት ግጭት ለማብረድ ሰላም አስከባሪ ኃይሉን ለመላክ ከስምምነት ደርሷል፡፡

ድርጅቱ 1,800 ፖሊሶች፣ 20 ደንብ አስከባሪዎችን ጨምሮ 10 ሺሕ ወታደሮች እንደሚልክ ሲጠበቅ፣ ከዓመት በፊት ወደ አገሪቷ ሰላም ለማስከበር የገቡት የፈረንሳይ ወታደሮች ድጋፍ እንዲያደርጉለት ፈቅዷል፡፡

የአፍሪካ ኅብረትና የፈረንሳይ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የሚያደርጉት ሰላም የማስከበር ሥራ በአማፅያን ጫና ሥር ወድቋል ያለው ድርጅቱ፣ ወታደሮቹን ለመላክ ከመወሰኑ በተጨማሪ በአገሪቱ ያለው የሽግግር መንግሥት እስከ ጥር 2007 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲያካሂድ ጥሪ አቅርቧል፡፡

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s