‹ዛቻና ማስፈራራት ይገጥሙናል›› አቶ ዓሊ ሱሌማን፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር

‹‹ዛቻና ማስፈራራት ይገጥሙናል›› አቶ ዓሊ ሱሌማን፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌማን በፀረ መስና ትግል ውስጥ እየገጠማቸው ካሉ ችግሮች መካከል ‹‹ዛቻና ማስፈራራት›› እንደሚገኙበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጹ፡፡ 

አቶ ዓሊ የኮሚሽኑን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ለምክር ቤቱ ግንቦት 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ኮሚሽኑን እያጋጠሙ ስላሉ ዋና ዋና ችግሮች አብራርተዋል፡፡

የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ውስንነት፣ የሰው ኃይል ፍልሰት፣ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ኮሚሽኑ ለሚያቀርባቸው የማሻሻያ ሐሳቦች ተባባሪ አለመሆንና የመስክ ተሽከርካሪዎች እጥረት ኮሚሽኑን ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተቋሙ ትልቅ ኃላፊነት ጋር በማነፃፀር ገጠሙ የተባሉት ችግሮች ክብደት የሌላቸው ሆኖ እንደተሰማቸው የገለጹት የምክር ቤቱ አባልና የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አድሃኖ ቴድሮስ፣ የኮሚሽኑ ችግሮች እነዚህ ብቻ ከሆኑ የሚያስደስት ነው በማለት ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር አድሃኖ የሰጡት ጥያቄ አዘል አስተያየት ላይ ኮሚሽነሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ለምክር ቤቱ መቅረብ የሚገባ ነው ብለን ስላላመን እንጂ ዛቻና ማስፈራራት የመሳሰሉት ችግሮች አሉ፤›› በማለት ኮሚሽነር ዓሊ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የትኞቹ አስፈጻሚ አካላት ዛቻና ማስፈራራትን በኮሚሽኑ ሠራተኞች ላይ እንደሰነዝሩ አልገለጹም፡፡

ኮሚሽነሩ የአሥር ወር የአፈጻጸም ሪፖርታቸው የኮሚሽኑን የለውጥ ዕቅድ አፈጻጸም፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን መከላከል የሚያስችሉ ጥናቶችን በተለያዩ ተቋማት ላይ ማከናወኑን፣ በታላላቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የሚከናወን መደበኛ የመከላከል ሥራ፣ የሙስና ወንጀል ምርመራና ክስን የተመለከቱ አፈጻጸሞችን ዳሰዋል፡፡

አስቸኳይ የመከላከል ሥራዎችን በተመለከተ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታ ከኢንጂነሪንግ ግምት በላይ 80 ሚሊዮን ብር ዋጋ ላቀረበ ተጫራች ግልጽነት በጐደለውና ለአድልኦ ክፍት በሆነ መንገድ ከመሰጠቱ በፊት እንዲቆም መደረጉን፣ የኮንስትራከሽንና ቢዝነስ ባንክ 99 ጄኔሬተሮችን ለመግዛት ባወጣው የጨረታ ሰነድ የተመለከቱ የመገምገሚያ መሥፈርቶችን መሠረት ባላደረገና ግልጽነት በጐደለው ሁኔታ ከፍተኛ ዋጋ ያቀረበን ተወዳዳሪ አሸናፊ ያደረገ የግዥ ሒደት እንዲታረም በመደረጉ፣ 6.4 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ሀብት መዳኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የማሽነሪዎች ግዥ የጨረታ ሒደት ግልጽ ባልሆነ መንገድ ለአንድ ብቸኛ ተጫራች ዕቃውን እንዲያቀርብ የሰጠውን ውሳኔ እንዲሰርዝና ተስተካክሎ ጨረታው በድጋሚ እንዲወጣ መደረጉን፣ አስቸኳይ የመከላከል ሥራ ባሉት ሪፖርታቸው በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

የአሠራር ሥርዓት ጥናቶች ባሉት የሥራ ዘርፍ ደግሞ የንግድ ሚኒስቴር የቡና ምርት ኤክስፖርት ቁጥጥርና ክትትል ክፍልና በሌሎች መሥሪያ ቤቶች ላይ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ሰላሳ የቡና ላኪ ድርጅቶችን በናሙና በመምረጥ የአምስት ዓመታት የግብይት መረጃዎችን በመተንተን በአምስት ዓመት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላከ የቡና መጠን ውስጥ፣ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ቡና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አውቆት ስለመላኩ ማረጋገጫ እንዳልተገኘለት፣ በዚህም ምክንያት አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ልታጣ እንደምትችል በመጥቀስ ሚኒስቴሩ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግ ማሳሰቢያ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

ለምዝበራ የተጋለጡ ሀብቶችን ወይም የተመዘበሩትን በየዓመቱ ለምክር ቤቱ አባላት ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እንደሚያቀርብ፣ ኮሚሽኑ ያቀረበው ሪፖርትም ከዋናው ኦዲተር ጋር እንደተመሳሰለባቸውና ኮሚሽኑ ለምን ዕርምጃ እንደማይወስድ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል፡፡

‹‹ከኦዲተር መሥሪያ ቤት ጋር የተመሳሰለ ሥራ ብንሠራም ተልዕኳችን የተለያየ ነው፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹በእገሌ መሥሪያ ቤት ምርመራ ጀምረናል ማለት ስለማንችል በጥቅሉ ነው ሪፖርቱን ያቀረብነው፤›› ብለዋል፡፡ ሁሉንም ነገር ከሙስና ጋር ማያያዝ ወደ ሌላ ድምዳሜ ሊያደርስ ይችላል ሲሉ ድፍን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር ሙስና ፈጽመዋል ከተባሉ ባለሀብቶችና ድርጅቶች መካከል የተከሰሱት ጥቂቶቹ መሆናቸውን፣ ሌሎች 31 ድርጅቶች ያላግባብ ተለቀዋል ስለ መባሉ ተጠይቀው፣ ‹‹ሙስና መሆኑን አረጋግጠን የለቀቅነው የለም፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ የተጠቀሱት ድርጅቶች ያስገቧቸው ንብረቶች ሳይፈተሹ ያለፉበት ምክንያት ሥራን ለማቀላጠፍ ሲባል የተፈጸመ ግድፈት እንጂ፣ ሙስና ነው ብሎ ለመደምደም የሚያስቸግር ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s