ትኩረት በህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድ ላይ ይሁን!!!

ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ መንታ መንገድ ላይ ትገኛለች። በአንድ በኩል ህወሓት እና አገልጋይ ድርጅቶቹ በተለይም ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድ የተነሳባቸው ሕዝባዊ ተቃዉሞ ለመሸፈን የሕዝብ ለሕዝብ ጠብ ለመጫር የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው። በየተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ዘርን መሠረት ያደረጉ ስድቦች፣ ዘለፋዎችና ጥቃቶች እንዲኖሩ በካድሬዎቻቸውና በቅጥረኞች አማካይነት እየጣሩ ነው። በዚህ እኩይ ተግባር ውስጥ ባለማወቅ በስሜት ብቻ የሚነዱ የወያኔ ደጋፊ ያልሆኑ ወገኖችም እየተሳተፉበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በዘውግም ይሁን በአገር ደረጃ የተደራጁ የፓለቲካ ድርጅቶች መሪዎች የጋራ ጠላቶቻችን ወያኔና ግብረአበሮቹ ስለመሆናቸው የጠራ አቋም እየያዙ ነው። ወያኔና ግብረአበሮቹን ለማስወገድ በጋራ መታገል የሚያስፈልግ መሆኑ እና ከወያኔ አገዛዝ በኋላ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አገር የመገንባት የጋራ ኃላፊነት ያለብን መሆኑ ሰፊ ግንዛቤ እያገኘ መጥቷል።

ይህ መንታ መንገድ በሁሉም ቦታ በባሰ ኦሮሚያ ውስጥ ጎልቶ እየታየ ነው። በኦሮሚያ አካባቢዎች የሚደርሰው ጥቃትና መፈናቀል ያስቆጫቸው ወጣቶች የሚያደርጉት ፍትሃዊ ተቃውሞ ቀጥሏል። በአምቦ፣ በነቀምት፣ በጊምቢ፣ በሀረር፣ እና ሌሎችም አካባቢዎች በተለይም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሥርዓቱን በመቃወማቸው ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል። በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ የእንተባበር ጥሪዎች ጎልተው እየተሰሙ ነው። በኦሮሚያ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎች ከጎናቸው እንዲቆሙ የኦሮሞ ተማሪዎች ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አቅርበዋል። የሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎችም ከኦሮሞ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጎን ቆመዋል። ይህ ተስፋ የሚሰጥ እና መበረታታት ያለበት ነገር ነው። ሆኖም ግን ከዚሁ ጎን ለጎን ህወሓትና ኦህዴድ የሕዝቡን ጥያቄ ወደ ዘር ግጭት ለማዞር እየሠሩ ነው። በተማሪዎች መፈክሮች ውስጥ ዘርን ለይተው የሚያንቋንሽሹ መልዕክቶች ሰርገው እንዲገቡ እየተደረገ ነው። ኦሮሞ ባልሆኑ በተለይም በአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው። የወያኔ ጆሮ ጠቢዎችና ካድሬዎች በስሜት የተገፋፉ ወጣቶችን ወደ ዘር ግጭት እየመሯቸው ነው።ይህ እጅግ አሳሳቢና በአስቸኳይ መቆም የሚኖርበት ነገር ነው።

ከመንታ መንገዶቹ ለአገርና ለወገን እንዲሁም ለወደፊቱ ትውልድ ደህንነት የሚበጀውን የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ እና የመተባበርን መንገድ መርጠን እርምጃችንን ካላፋጠንን አሁን የደረስንበት ደረጃ እጅግ አስጊ ነው። ማሰብ፣ ማስተዋል እና ጠላትን መለየት በሚያፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው የምንገኘው። ድሃ አማራ ለድሃ ኦሮሞ ወገኑ ብቻ ሳይሆን የትግል አጋሩ ነው። ኦህዴድ ውስጥ ያሉ የወያኔ አገልጋዮች ደግሞ ኦሮሞች ስለሆኑ የድሃ ኦሮሞ ወዳጆች አይደሉም። እነሱ የወያኔ ተቀጥላዎች ናቸው። የትውልድ መንደራቸውን ሳይቀር አዘርፈው የሚዘርፉ ስግብግቦች ናቸው።

የኦሮሞ ሕዝብ ትግል በወያኔ እና ተቀጥላዎቹ ድርጅቶች እንጂ በአማራና በኦሮሞ ወይም በኦሮሞና በትግሬ ሕዝብ መካከል አይደለም። የአማራ ሕዝብ ትግል በወያኔ እና ተቀጥላዎቹ ድርጅቶች እንጂ ከማንኛውም አካባቢ ሕዝብ ጋር አይደለም። ወደ እርስ በርስ ቅራኔ ሊዘፍቁን የሚፍጨረጨሩትን ህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድን ከሕዝብ መነጠል መቻል አለብን። እዚህ እኩይ ኃይሎች ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ፍትህና ሰላም ማግኘት አንችልም። እዚህ እኩይ ኃይሎች እርስ በርሳችን ሊያጫርሱን እየሠሩ መሆኑን አውቀን ኃይላችንን በማስተባበር እንመክታቸው።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በማናቸውም የኢትዮጵያ ግዛት የሚደርስን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በፍጹም ቁርጠኝነት በጋራ እንታገል፤ በስሜት ከተሞሉና ለእርስ በርስ ግጭቶች ከሚዳርጉ ነገሮች እንቆጠብ፤ አርቆ አስተዋይነትና ታጋሽነት በተላበሰ መንገድ የጋራ ጠላቶቻችን በሆኑትን በህወሓት እና አጫፋሪዎቹ ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደህዴድ ላይ በጋራ እንነሳ ሲል ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ያደርጋል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s