ኢሕአዴግ ሆይ ስኬቶችህን ስትዘክር ጉድለቶችህንም ተመልከታቸው

ይኼ ጊዜ እንዴት ይሮጣል እባካችሁ? ሃያ ሦስት ዓመት የደቂቃዎች ያህል የማይቆጠርበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስላል፡፡

የዛሬ ሃያ ሦስት ዓመት ‹‹ብሶት የወለደው›› ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የተወለዱ ልጆች ለአቅመ አባትነትና እናትነት በቅተዋል፡፡ በፈጣኑ የጊዜ ባቡር ላይ ሆነን ያለፉትን ሃያ ሦስት ዓመታት የኋሊት ስንቃኝ የጊዜ መሮጥ ብቻ ሳይሆን፣ የድርጊቶችና የሁነቶች መለዋወጥም ይታወሰናል፡፡ ወይ ጊዜ?

ኢሕአዴግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሽግግር ኮንፈረንስ ጠርቶ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ብልጭታ ሲታይ፣ እጅግ በጣም ከተደሰቱ ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ ምንም እንኳ የሽግግር ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የገዘፈ ስም የነበራቸውን ኢሕአፓንና መኢሶንን አለማካተቱ እንደ ትልቅ ጉድለት ሆኖ ቢወሳም፣ በዚህች አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት የታየው ጅምር መልካም ነበር፡፡ የተለያዩ ፖለቲካዊ ዓውዶችንና ማኅበረሰቦችን እንወክላለን የሚሉ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች መታየታቸውም ብርቅ ነበር፡፡

እንግዲህ የኋሊት ተጉዘን ለመነሻ ያህል የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጥንስስ የነበረውን ያን ወቅት ስናስታውስና ከዚያ በኋላ እንደ አሸን ፈልተው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስናስብ፣ ዛሬ ላይ ሆነን ለመነጋገር የሚያበቃን አጀንዳ እናገኛለን፡፡ የሽግግሩ ዘመን እንዲያበቃ ያደረገው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ በኋላ በዚህ ሕገ መንግሥት ዋስትና ያገኙ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን መሠረት አድርገን የምንወያይባቸው ነጥቦችም አሉ፡፡

እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ መላ አገሪቱን ተቆጣጥሮ ሥርዓተ መንግሥቱን ሲዘረጋ በርካታ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ይናኙ ነበር፡፡ ከእነዚህም ጥያቄዎች መካከል ገንነው የወጡት የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ናቸው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሐሳብን በነፃነት  የመግለጽ መብትና የፕሬስ ነፃነት ፋና ወጊዎች ሲሆኑ፣ እነዚህን ተከትለው የሚመጡት የመደራጀት መብትና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አሉ፡፡ ከዚያም ሰዎች የመሰላቸውን አመለካከት በነፃነት እያራመዱ ለሚፈልጉት ወገን ድምፃቸውን የመስጠት መብት ደግሞ እንዲሁ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት በዲሞክራሲ የሐሳብ ገበያ ውስጥ በእጅጉ የሚፈለጉ ናቸው፡፡

የዛሬ ሃያ ሦስት ዓመት መሠረት የተጣለለት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምን ያህል ተራምዷል? የአመለካከት ልዩነት ምን ያህል ተከብሯል? የመደራጀት መብትስ? ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እያፍታታን እናያለን፡፡ ኢሕአዴግ ሁሌም በእጅጉ የሚመካበትና በአርዓያነት የሚጠቅሰው የልማት አጀንዳን ያህል ትኩረት ያላገኘው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አሁንም የወቅቱ ትኩሳት ነው፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ግስጋሴው የዓለምን ቀልብ የመሳቡን ያህል፣ የፖለቲካው መስክ በአሉታዊ ገጽታው ብዙ እያነጋገረ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ባገኘበት አገር ውስጥ በጠላትነት ያስፈርጃል፡፡ ገዥው ፓርቲ ተቀዋሚዎቹን በአገር ጠላትነት ሳይቀር ሲፈርጃቸው፣ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ ከዚያ ጠንከር ባለ አገላለጽ ይወነጅሉታል፡፡ የፖለቲካው ሥነ ምኅዳር መጥበቡ ብቻ ሳይሆን አስፈሪ እየሆነ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ዲሞክራቲክ የሆነች ፌዴራላዊ አገር እየገነባሁ ነው ቢልም፣ ጭፍን ጥላቻና ጠባብነት የአገሪቱን ፖለቲካ ወሮታል፡፡ ኢሕአዴግ ሲመቸው በዘዴ ካልተመቸው ደግሞ በጉልበት መንበሩን እያፀና ሲሄድ፣ ከእሱ በተቃራኒ የተሠለፉ ኃይሎችና ደጋፊዎቻቸው የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው እየጠበባቸው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን መንግሥት በማስተዳደሩ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው ዕድሎች መኖራቸው ባይካድም፣ ፓርቲንና መንግሥት መለየት እስከማይቻል ድረስ ከሚዲያ ጀምሮ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትን የግሉ አድርጓቸዋል፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያግዛሉ ተብለው ተስፋ የሚጣልባቸው የሲቪል ማኅበረሰብና የተለያዩ ተቋማት አቅማቸው እየተዳከመ የሉም የሚባሉበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡

በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የወጡት የፕሬስ ሕግ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግና የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ በአገሪቱ የፖለቲካ ድባብ ላይ የራሳቸውን ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ ምንም እንኳ የሕጎቹ አስፈላጊነት ባይስተባበልም፣ ሕጎቹ በውስጣቸው የያዙዋቸው ዓላማዎችና በሰፋት የሚታዩባቸው ክፍተቶች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚያኮማትሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ በመውጣቱ በበኩሌ ምንም ቅሬታ ባይኖረኝም በሕጉ ውስጥ የተሰነቀሩ አንቀጾችና ያሉት ክፍተቶች ‹‹ጎመን በጤና›› የሚያሰኙ ናቸው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡንና የግሉ ፕሬስን የሚያደነዝዙት ሁለቱ ሕጎችም በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮችን አቅፈዋል፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ፈተና ውስጥ ሲገባ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩ ከመጣበቡም በላይ አስፈሪ ይሆናል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቱንም ያህል ድክመት ቢኖራቸውም መኖራቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹ባለመታደል ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሉም›› ከሚል ይልቅ፣ ፓርቲዎቹ ተጠናክረው በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ዕድል ቢያመቻች በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የሚስተዋለው ጨለምተኛነትና ፅንፈኝነት ፈር ይይዝ ነበር፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠፍንገው በተያዙበት ሁኔታ ውስጥ አማራጭ አምጡ ብሎ መጠየቅ ከባድ ነው፡፡ በሚገባ ተንቀሳቅሰው አባላት ካላፈሩ፣ ለሥራቸው የሚያወጡት የገንዘብ ድጋፍ ካላገኙ፣ ለሰላማዊ ፖለቲካ ትግል የሚያስፈልገው ሰላማዊ ድባብ ካልኖራቸው እንኳን አማራጭ ሐሳብ ሊያመጡ ህልውናቸውም ያሰጋል፡፡

ኢሕአዴግ በአገሪቱ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ሕዝባዊ ድርጅቶችና መሰል ቦታዎች በስፋት ተንሠራፍቶ አባላትን ሲመለምልና ደጋፊዎችን ሲያፈራ ተቃዎሚዎቹ ይኼንን ዕድል እንዳያገኙ ከተደረጉ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከየት ይመጣል? ከታች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ በገዥው ፓርቲ ብቻ በቁጥጥር ሥር የዋለ መዋቅር ለተቃዋሚዎች ቦታ ከሌለው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት ይገነባል? አማራጭ ለሚጠይቅ ሕዝብ እኮ በብቃት የተደራጀ ፓርቲ መኖር አለበት፡፡ ይህ በሌለበት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እየተሠራ ነው ቢባል ከማስገረም አልፎ ያሳዝናል፡፡

ኢሕአዴግ ባለፉት ሃያ ሦስት ዓመታት የመንግሥት ሚዲያውን በቁጥጥሩ ሥር አውሎ የራሱ ልሳን አድርጎታል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖር የሚታወቀው እንደ አማራጭ በሚታየው የግሉ ፕሬስ አማካይነት ነው፡፡ የሚዲያ ፍትሐዊነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫ በቀረበ ቁጥር እየተቆነጠረ የሚሰጠው የአየር ሰዓት ብቻውን እርባና የለውም፡፡ ይኼ ዓይነቱ አሠራር ሐሳብ በነፃነት እንዳይንሽራሸርና የዲሞክራሲው ጉዞ ስኬታማ እንዳይሆን ትልቅ አስተዋድኦ አበርክቷል፡፡ ነጋ ጠባ የአንድ ወገን ድምፅ ብቻ በሚሰማበት አገር ውስጥ ስለ ዲሞክራሲ እንዴት ተደርጎ ማሰብም መናገርም ይቻላል?

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አደጋ ወስጥ ሲወድቅ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከማንም በላይ ኃላፊነት ሊኖረው የግድ ይለው ነበር፡፡ ሌሎች ወገኖች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አንዳንድ የማይመቹዋቸው አንቀጾች ላይ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ‹‹ፀረ ሕገ መንግሥት›› ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጣቸው መብቶች ሲሸራረፉ መጠበቅ ካልተቻለ ደግሞ ተጠያቂነት ያመጣል፡፡ እዚህ አገር ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት ከሚቸራቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የሕግ የበላይነት ነው፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ደግሞ ወደድንም ጠላንም መከበር አለበት፡፡

ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት መከተሏ የግድ መሆን ያለበት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ የበርካታ ብሔርና ብሔረሰቦች አገር ከአሃዳዊ ሥርዓት ተላቃ ፌዴራላዊ ሥርዓት መከተልዋ የሚደገፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ሰፍኖ የነበረው አድልኦና መገለል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መጥፋት የሚችለው በፌዴራል ሥርዓት ብቻ እንደሆነ ያለውን ሁኔታ በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ ፌዴራላዊ ሥርዓት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ካልተቃኘ አደጋ ይሆናል፡፡ ዲሞክራሲ የፌዴራል ሥርዓቱ መሠረት መሆን አለበት ሲባል ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍሉ በሕጋዊ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን ላልተገባ ዓላማ ባዋልነው ቁጥር ግን ችግሮች ይባባሳሉ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ለመታዘብ እንደቻልነው የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ምላሹ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስለማይቀርብ ግጭቶች ይነሳሉ፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች ከአቀራረባቸው ጀምሮ እስከ መልስ አሰጣጣቸው ድረስ ኢዲሞክራሲያዊ በመሆናቸው የሰው ሕይወት ሲቀጠፍ፣ ንብረት ሲወድምና መደናገጥ ሲፈጥር በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክፍተቶችና የተሸፋፈኑ ችግሮች እየተጠራቀሙ በሄዱ ቁጥር ነገን ተስፋ እንዳናደርግ ያደርጉናል፡፡ ከሰሞኑ በኦሮሚያ አካባቢ የተነሱ ግጭቶችም ይህንኑ አመለካች ናቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አደጋ በተደቀነበት ጊዜ ሁሉ ለፊዴራል ሥርዓቱ ግንባታ አዋኪ የሆኑ ችግሮች ያገጥማሉ፡፡ አንዴ ብልጭ ሌላ ጊዜ ድርግም ለሚሉ ችግሮች መፍትሔው ዲሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ማለባበስና ማደባበስ የትም አያደርስም፡፡ ከጥፋት በስተቀር፡፡

በአገሪቱ የፖለቲካ አየር ውስጥ ከሚዋኙ ዋነኛ ችግሮች ውስጥ በገዥው ፓርቲና በተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጀቶች መካከል ያለው የተበላሽ ግንኙነት ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ለሥልጣን በሚያደርጉት ፉክክር ሕዝብን ማዕከል ማድረግ የተሳናቸው ይመስላሉ፡፡ ሁለቱ ወገኖች ወደ ሕዝብ ሲቀርቡ የሚመዘኑት በሰነቁት ሐሳብ ወይም ተስፋ መሆን ሲገባው የተወዳዳሪነት ስሜት ጠፍቶ በጠላትነት ይተያያሉ፡፡ ‹‹የእኔ አጀንዳ ካንተ በዚህና በዚያ ምክንያት ይሻላል›› ከማለት ይልቅ ‹‹አገር አጥፊ››፣ ‹‹የአገር ጠላት›› እየተባባሉ ለዓመታት ዘልቀዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በጨዋነት ተቀምጦ ለመነጋገር ይቅርና ለህልውናቸው ዕውቅና ሲሰጣጡ እንኳን አይታዩም፡፡ በፊት ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ ተቀዋሚዎችን ‹‹ግማሽ መንገድ›› ሄዶ እንደሚቀበላቸው ይናገር ነበር፡፡ አሁን ግን ፈጽሞ አይሰማም፡፡ እንደ ገዥ ፓርቲነቱ አገርን የመምራት ኃላፊነት እያለበት ተቃዋሚዎችን አግባብቶ ወደ መወያያ ጠረጴዛው ማምጣት ነበረበት፡፡ ‹‹ከእኔ ይቅር›› በማለት ተነሳሽነቱን በመውሰድ የመወዳደሪያውን ሜዳ ማስፋት ሲገባው፣ የተቃዋሚዎች  ሜዳ ዘወትር እየጠበበ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ ላይ ተቃዋሚዎችም የሚቻላቸውን ሁሉ በማድረግ የመጫወቻ ሜዳው እንዲሰፋ ማድረግ ሲገባቸው፣ ኢሕአዴግን በማጥላላትና በማንቋሸሽ ላይ ብቻ ማተኮራቸው ያስወቅሳቸዋል፡፡ አንዳንዴ አንገትን ደፋ በማድረግ የልብ መሥራት እንደሚቻል ማወቅ ለምን እንደሚጠፋባቸው ግራ ያጋባል፡፡ ከድንፋታና ከፉከራ በመላቀቅ የሠለጠነ ፖለቲካ መምራት ካቃታቸው በጣም አሳሳቢ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ባለፉት ሃያ ሦስት ዓመታት በተጓዘባቸው ወጣ ገባ መንገዶች ላይ ስኬትን ብቻ አስመዝግቤያለሁ ቢል ማን ይቀበለዋል? ለዘመናት ተኝታ የነበረችን አገር ከእቅንልፏ ቀስቅሶ እያለማት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ልማቱ ከአገርና ከአኅጉር አልፎ በዓለም ደረጃ መነጋገሪያ መሆኑን ማንም አይክድም፡፡ ነገር ግን ይህ የልማት ጅምር በተሳካ ሁኔታ ይቀጥል ዘንድ አገራዊ መግባባት ሊኖር ይገባል፡፡ አገሪቱ በመንገድ፣ በባቡር፣ በኃይል ማመንጫዎች፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ በግብርና፣ በማዕድናት፣ በስኳር፣ በሲሚንቶ፣ ወዘተ ከፍተኛ እመርታ ስታሳይ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ግንባታ መጨንገፍ አይኖርበትም፡፡ በቅርብ ዓመታት መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ ለማሠለፍ የተጀመረው ጥረት በዲሞክራሲ ሲደገፍ ውጤቱ ያማረ ይሆናል፡፡

ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት ግንኙነት ሐሳቦቻቸውን በነፃነት ያንሸራሽሩ፡፡ የፓርቲ ፖለቲካንና የአገርን ጉዳይ ይለዩ፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታቸው ሲሉ አገርንና የፓርቲን ጉዳይ መቀላቀል አይገባቸውም፡፡ ሐሳብ በነፃነት በተንሸራሸረ ቁጥር ሕዝብና አገር ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ዲሞክራሲ የሐሳብ ገበያ ነው የሚባለው ከተለያዩ ወገኖች በተለያዩ ዕይታዎች የሚቀርቡ ሐሳቦች ለአገር ዕድገት ጠቃሚ በመሆናቸው ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ጭፍንነትና ፅንፈኝነት ፖለቲካውን በክለውታል፡፡ አሁንም ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተነሳሽነቱን በመውሰድ ይኼንን ደስ የማይል ድባብ መለወጥ አለበት፡፡

አገሪቱ ውስጥ ከሚታዩ አስከፊ ተግባራት አንዱና ዋነኛው ሙስና ነው፡፡ ሙስና አገሪቱን እንደ ነቀዝ እየበላት ነው፡፡ በአንድ ሌሊት ሚሊየነሮች የሚፈጠሩበት ምክንያትም ሙስና ከመጠን በላይ በመስፋፋቱ ነው፡፡ የአገርና የሕዝብ ንብረት ሲባክን ተቆርቋሪ ሳይኖር፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ገንዘብ ሲዘረፍ ወይም ኦዲት ሳይደረግ ሲቀር፣ በቡድን የተደራጁ ኃይሎች የአገር ሀብት ሲያወድሙና ሲዘርፉ እንዴት ዝም ይባላል? ከድህነት ለመላቀቅ አሳሯን በምታይ አገር ውስጥ በኔትወርክ የተሳሰሩ ኃይሎች እየከበሩ ብዝኃኑ ሕዝብ በኑሮ ውድነት ሲጠበስ እናያለን፡፡ ፀረ ሙስና ትግል ተጀምሯል ተብሎ አንድ ሰሞን ሸብ ረብ ይባልና ከዚያ በኋላ ፀጥ ይባላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ቆራጥነትና ወኔ ያልተላበሰ ፀረ ሙስና ትግል ዘረፋ ካላስቆመ ምን ይፈይዳል? ‹‹ሙስና የአገር ጠላት ነው›› የሚለው መፈክር ብቻውን የትም አያደርስም፡፡ ትግሉ ሁሉንም ወገን አሳታፊ ካልሆነ ዘመቻው አፍአዊ ሆኖ ይቀራል፡፡ በአንድ ጀንበር በልፅገው የምናያቸው የዘመናችን ‹‹ከበርቴዎች›› ጉዳይ አንድ መላ ካልተፈለገለት ሙስና ሥርዓቱን ገዝግዞ ይጥለዋል፡፡

በተቻለኝ መጠን አጠር አጠር በማድረግ ዋነኛ የምላቸውን ጉዳዮች ባነሳም፣ በርካታ የሚቀሩ ጉዳዮች እንዳሉ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ ያለፉትን ሃያ ሦስት ዓመታት ሲገመግም ችግሮቹን ጭምር ማየት ይኖርበታል፡፡ በተለይ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጠቃሚ የሆኑት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተቀዳሚ መሆን አለባቸው፡፡ ልማቱ ተሳክቷል የሚባለው እነዚህ በኩር ጉዳዮች ትኩረት ሲቸራቸው ብቻ ነው፡፡ ልማትን ከዲሞክራሲ ወይም ዲሞክራሲን ከልማት ያስቀደመ አካሄድ የትም አያደርሰንም፡፡ ኢሕአዴግ ሆይ ስኬቶችህን ስትዘክር ጉድለቶችህንም ተመልከታቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s