የውሸት ችርቻሮ ይቁም! በአንዲት ዜና 15 ውሸቶች

በአበበ ገላው

በኢትዮጵያ የሚታተመውና በድረ ገጽ አማካኝነት የሚነበበው “አዲስ አድማስ” በመባል የሚታወቀው ሳምታዊ ጋዜጣ እጅግ ሃላፊነት የጎደለው የፈጠራ ወሬ በዜና መልክ ሰሞኑን አስነብቧል። በዘባው መሰረት ለደህንነቴ ስለሰጋሁ ቤቴን ለቅቄ ከዋሽንግተን ዲሲ እርቄ በሁለት የደርግ አየር ወለዶች እየተጠበኩ በአንድ “ቪላ” ውስጥ እንደምኖር ይሄው “ጋዜጣ” ነግሮናል። ከዚህም በተጨማሪ 250ሺ ዶላር በሽልማት ቃል እንደተገባልኝና ከዚሁም 120ሺ ዶላር ባንክ ማስገባቴን “ዜናው” ያትታል። ዜና ተብዬዋ ከአስራ አምስት በላይ ውሸቶችን በማካተት ወደር ያልተገኘላት ልብ ወለድ መሆንዋ ብዙም አያጠያይቅም።
እውነታው ግን ህወሃቶች በአሜሪካን ሀገር አንገት አቀርቅረው ተሸማቀውና ከህዝብ አይን ተደብቀው መኖራቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው። እኔ በዚች ታላቅ ሃገር ተደብቄ ሳይሆን በነጻነትና በኩራት ነው የምኖረው።
ሰሞኑን በተቀነባበረ መንገድ በህወሃት የዜና አውታሮች እየተፈበረከ ካለው የሀሰት ውንጀላና በሬ ወለደ ወሬ አንጻር የአዲስ አድማሱም ዘገባ ሆን ተብሎ ዋናውን ጉዳይ በርካሽ ውሸትና ወሬ ለማድበስበስ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑ ማንም ሊዘናጋ እይገባም። ጥያቄው የገንዘብ፣ የቪላ፣ የአጃቢና ተራ መሰል ጉዳዮች አለመሆኑ በግልጽ እየታወቀ በአለም መሪዎች ፊት የተስተጋባው የኢትዮጵያ ህዝብ መሰሪ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት የፋሺስታዊው ስራትን ኪስራ የበለጠ ከማጋለጥ ያለፈ ፋይዳ የለውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የመብትና የክብር መሆኑ ግልጽ ነው።
በቅርቡም የNational Press Club አባልነቴና “የጋዜጠኛ ፈቃዴን” መሰረዙ፣ የአሜሪካ መንግስት በአቶ መለስ ላይ ያሰማሁት ተቃውሞ እንዳበሳጨው በህወሃት የተፈበርኩ ዜናዎች በሙሉ ሃሰት መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። በአሜሪካ ትልቁ የጋዜጠኞች ማህበር ናሽናል ፕሬስ ክለብ ፕሬዚዳንት የሆኑት ቴሬሳ ዌርነር በስርአቱ ደጋፊዎች በኔ ላይ የቀርቡላቸውን በርካታ ውንጀላዎች መርምረው ውድቅ ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል። ማህበሩም የኔን እውነተኛ ጋዜጠኛነት ጥያቄ ውስጥ እንደማያስገባና ከጎኔ እንደሚቆም አረጋግጠውልኛል።
ህወሃት የሚያወራው ከዚህ ሃቅ የራቀ ስለሆነ አለኝ የሚለውን የእገዳ ወይንም የተግሳጽ መረጃ ይፋ እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ ለመጠየቅ እወዳለሁ። ይሁንና ትልቁ ችግር በነበረከት ስምኦንና በብርሃነ ገብረክርስቶስ የሚሰራው የከሰረ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መረጃ ነጥፎበት ባዶ ሀሰት ችርቻሮ ውስጥ መግባቱ ነው።
በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ብርሃነ ገብረክርስቶስ የአሜሪካ መንግስት በየትኛውም ስብሰባዎቹ ላይ “ግለሰቡ” እንዳይገኝ ወስንዋል ያሉት እንደተለመደው ቅጥፈት ሲሆን፣ የአሜሪካ ህገመንግስትን First Amendment የሚጻረር መሆኑን አለመገንዛባቸውን ያሳያል። ያም ሆነ ይህ ህወሃት ውሸት መቸርቸሩን አቁሞ እውነትን ለመጋፈጥ ቢደፍር መልካም ነው።
——————-


ጋዜጠኛ አበበ ገላው በደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል (ውሽት)
Saturday, 09 June 2012 06:49 administrator
ባለፈው ወር ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተሳተፉበት የG8 ስብሰባ ላይ የተገኘው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ጠ/ሚኒስትሩን በተቃውሞ ከንግግራቸው እንዳቋረጣቸው ከተሰማ በኋላ በርካታ ድጋፎች የጐረፉለትን ያህል ከተቃውሞና ከነቀፋም አልዳነም፡፡ ተቃውሞውን አሰምቶ ሲቀመጥ በአራት የአሜሪካ ፖሊሶች ከአዳራሹ እንዲወጣ የተደረገው ጋዜጠኛ አበበ ገላው፤ ፖሊሶች እስር ቤት እንዳልወሰዱትና ምንም የድብደባ ሙከራ እንዳላደረሱበት ከሚሰራበት ኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ መናገሩ ይታወሳል፡፡ G8 ስብሰባ ላይ ያሰማውን ተቃውሞ በታንዛኒያ በተካሄደ ተመሳሳይ ስብሰባ ላይ ለማድረግ እቅድ እንደነበረው የጠቆመው ጋዜጠኛው፤ ችግር ሊያደርሱብኝ ይችላል በሚል ፍራቻ እንደተወው አክሎ መግለፁም ይታወቃል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጋዜጠኛው ጉዳይ ላይ ለሁለት ተከፍለዋል የሚሉ ምንጮች፤ አንደኛው ወገን ጋዜጠኛውን እንደ ጀግና በመቁጠር በሙገሳና በገንዘብ ሽልማት ሲያንበሸብሸው (ውሽት) ሌላኛው ወገን በጠላትነት ስሜት የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄደበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ጋዜጠኛውን እንገድልሃለን በሚል የሚያስፈራሩ ሰዎች እንዳሉ የጠቆሙት ምንጮች፤ ደህንነቱን ለመጠበቅ ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦችም መኖራቸውን ተናግረዋል (ውሽት) ፡፡ ጋዜጠኛ አበበ ገላው በአ.አ ዩኒቨርሲቲ በህግ (ውሽት) ከተመረቀ በኋላ “ኢትዮጵያን ሔራልድ” ጋዜጣ ላይ ለበርካታ (ውሽት) አመታት እንደሰራና በኋላም ወደ ለንደን መሄዱን ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ ከለንደን ወደ አሜሪካ የገባው ጋዜጠኛ አበበ፤ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ በመግባት መሳተፉንም (ውሽት) እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የኢሳት ቴሌቪዥን ተባባሪ መስራችና አዘጋጅ እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛ አበበ ገላው ተቃውሞውን ካሰማ በኋላ በአራት (ውሽት) የአሜሪካ ግዛቶች ጥሪ ተደርጐለት ንግግሮች ማድረጉን የጠቆሙት ምንጮች፤ በሲያትል የተካሄደውን ስብሰባ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና አንባቢ የነበረችው ንግስት ሠልፉ (ውሽት) እና የኢቴቪ ዜና አንባቢ የነበረው መኩሪያ ገ/ሚካኤል (ውሽት) እንዳስተባበሩት ገልፀዋል፡፡ የአበበ ገላውን ተግባር እንዳደነቁ የተናገሩት በሲያትል የሚኖሩት አቶ ገ፤ ጋዜጠኛው የጀግና ተግባር መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩን “አምባገነን” በማለት እንዳሳጣቸው በመጥቀስ፡፡ እዚያው ሲያትል ነዋሪ የሆኑት አቶ ከበደ ግን የአቶ ገን ሃሳብ ይቃወማሉ – “ጀግና ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው” በማለት፡፡ “እኔ ለምን ተናገረ አይደለም ያልኩት፤ ሆኖም የሰደበው ኢትዮጵያን እንጂ ጠ/ሚኒስትሩን አይደለም” ብለዋል፡፡ መቃወም ከፈለጉ ኢህአዴግ መቃወም ይችላሉ ያሉት ግለሰቡ፤ “እሱንም በሚዲያ ማለትም በኢሳት በየቀኑ ሲተቹ እናያለን፡፡ ዛሬ የተለየ ነገሩ ምንድነው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ገ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፡፡ “ይልቁኑ መመስገን አለበት፤ ችግራችንን ተናግሮ አገራችንን በቅጡ እንድናይ አድርጐናል፡፡ አሜሪካም በነፃነት እንድንኖር ትፈቅዳለች” ብለዋል፡፡ አገሪቷ ላይ መኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ ለመኖር ምክንያት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ገ፤ የጋዜጠኛው ድምጽ ለጥያቄያችን መፍትሔ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ከበደ በበኩላቸው፤ “አገርን ሰድቦ ሌላ አገር ጥገኝነት መጠየቅ መዋረድ ነው” ይላሉ፡፡ ጋዜጠኛው ጠ/ሚኒስትሩ ላይ ባሰማው ተቃውሞ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሽልማት መንበሽበሹን የሚቃወሙት አቶ ከበደ፤ ድሮም ጋዜጠኛው ሲናገር ይሄንን እንደሚያገኝ ያውቃል ብለዋል፡፡ አቶ ገ ግን ለጋዜጠኛው የሰጠነው ያንሰዋል ባይ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ችግሮች መኖራቸውን ማንም አይክድም ያሉት አቶ ከበደ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር የሚፈታው አንድ ግለሰብ በአገር ላይ በፈፀመው ውርደት ሳይሆን በጋራ በምንሰጣት ጥቅም ነው ይላሉ – ሁሉም ለአገራቸው ምን እንደሰሩ ይጠይቁ በማለት፡፡ ጋዜጠኛ አበበ ይሄን ተቃውሞ በማሰማቱ ብቻ እንገድልሃለን እያሉ የሚያስፈራሩትና የሚዝቱበት ጥቂት አይደሉም የሚሉት አቶ ገ፤ ለአምባገነንነታቸው ይሄ በቂ ምስክር አይደለም ወይ ብለዋል፡፡ “አሜሪካ ያለ ኢትዮጵያዊ ከኃ/ስላሴ ጀምሮ ሲቃወም የኖረ ነው፡፡ ሰው ፍፁም ይመስለዋል፡፡ ስህተቱን አይቀበልም፤ ተደላድሎ እየኖረም ችግር ይፈጥራል፡፡ ትክክለኛ ተቃዋሚዎች ጥቂቶች ናቸው” ያሉት አቶ ከበደ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ይሄ ተደረገ ብሎ ለመረበሽ እና ሠልፍ ለመውጣት የሚደረገው ሩጫ ለአገር ግንባታ ቢውል የተሻለ ውጤት ይገኝ ነበር” ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
ጋዜጠኛ አበበ ገላው በአሁኑ ሰአት ከሚኖርበት አፓርትመንት በመልቀቅ (ውሽት) በአንድ ቪላ ውስጥ የገባ ሲሆን (ውሽት) ሁለት የደርግ አየር ወለዶች በፈቃደኝነት ደህንነቱን ለመጠበቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት እየጠበቁት እንደሆነ የአሜሪካ ምንጮች ጠቁመዋል (ውሽት) ፡፡
በ15 ግዛቶች ንግግር እንዲያደርግ የተጋበዘው ጋዜጠኛው (ውሽት) ፤ እስካሁን ወደ ዋሺንግተን ለመሄድ አለመድፈሩን (ውሽት) የጠቆሙት ምንጮች፤ ምክንያቱ ደግሞ በዲሲ በርካታ የኢህአዴግ ደጋፊዎች በመኖራቸው (ውሽት) እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በፈፀመው ተግባር አድናቆታቸውን ለጋዜጠኛው የገለፁ ደጋፊዎች፤ 250ሺ ዶላር ሊሰጡት ቃል እንደገቡለት (ውሽት) ሲታወቅ እስካሁን 120ሺ ዶላር በእጁ እንደገባ ምንጮች ጠቁመዋል (ውሽት፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ለሁለት ተከፍለው መቆራቆሳቸውን ቀጥለዋል ነው የተባለው (ውሽት) – በተቃውሞና በድጋፍ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s