ከንግድ ባንክ መጠኑ ያልተገለጸ ገንዘብ መጥፋቱ ተጠቆመ

‹ተሰርቋል ሳይሆን የሆነው ነገር ሌላ ነው›› የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፊንፊኔ ቅርንጫፍና ከዋናው መሥሪያ ቤት ፋይናንስ መቆጣጠሪያ፣ መጠኑ ያልተገለጸ ገንዘብ መጥፋቱን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንም የጠፋም ሆነ የተሰረቀ ገንዘብ እንደሌለ፣ ነገር ግን አንድ የባንክ ሠራተኛ በቁጥጥር ሥር ውሎ የባንኩ ትራንዛክሽን እየተመረመረ መሆኑን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለይ የፊንፊኔ ቅርንጫፍ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ መሰረቁን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ የባንኩን አሠራርና ሲስተም በደንብ በሚያውቁና ከሌሎች ሠራተኞች የተሻለ ደረጃና ዕውቀት ባላቸው ገንዘቡ በተለያየ ዘዴ መውጣቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ የባንኩ የበላይ ኃላፊዎች ጉዳዩን በሚስጥር ይዘውና የተወሰኑ ሠራተኞች እንዲታሰሩ በማድረግ በምርምራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ ቅርንጫፎች ከአንዱ ሒሳብ ወደ ሌላኛው በማንቀሳቀስና በሐሰተኛ ሰነድ ሒሳብ በመክፈት የተለያዩ ስርቆት የሚፈጸም ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን ረቀቅ ባለ ዘዴ ጠቀም ያለ ገንዘብ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይኼ የሚሆነው ልምድ ያላቸው ሠራተኞች ባልጠበቁትና ባልገመቱት ሁኔታ ከኃላፊነታቸው እየተነሱ ልምድ የሌላቸውና በቅርብ ጊዜ ቅጥሮች እየተተኩ በመሆኑ፣ ሌሎቹም ‹‹ነገ የምነሳ ከሆነ ለምን ዛሬ አልጠቀምም?›› በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ የወንጀል ድርጊቱን ለመፈጸም ሳይነሳሱ እንዳልቀሩ ምንጮቹ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ምንጮች የሚጠቁሙት ነገር ቢኖር ቄራ አካባቢ ከሚገኘውና በአገሪቱ ያሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች (832 ናቸው) ሒሳብ የሚወራረድበት ከዋናው መሥሪያ ቤት ፋይናንስ መቆጣሪያ፣ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ መጥፋቱን ነው፡፡ በሚስጥር የተያዘው የዚህ ገንዘብ መጥፋት ውስጥ ለውስጥ እየተጣራ መሆኑንና ወደ ሌላ ክልል ቅርንጫፎች ገንዘቡን አስተላልፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ሁለት ሠራተኞች መታሰራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከንግድ ባንክ ጠፍቷል ስለተባለው ገንዘብና መጠን እንዲገለጽ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮሙዩኒኬሸን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እንደተናገሩት፣ ከፊንፊኔ ቅርንጫፍ ተሰርቋል የተባለው ገንዘብ አልተሰረቀም፡፡ ነገር ግን አንድ የፊንፊኔ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ እረፍት ወስደው ጠረፍ ላይ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ሱዳን ጠረፍ በፀጥታ ኃይሎች የተያዙት ሠራተኛ በመኖራቸው አራት ሚሊዮን የሚደርሱ ትራንዛክሽኖች እየተፈተሹ መሆናቸውን እንጂ ባንኩ ተሰርቋል ተብሎ ሪፖርት የተደረገ ነገር እንደሌለ አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል፡፡ ዝም ተብሎ እየተጣራ እንጂ ችግር ተፈጥሯል በሚል የቀረበ ሪፖርት አለመኖሩንም አክለዋል፡፡ ከዋና መሥሪያ ቤት የፋይናንስ መቆጣጠሪያ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ ጠፍቷል ስለመባሉ ሥራ አስኪያጁን አነጋግረው፣ ምንም የጠፋ ገንዘብ እንደሌለ እንደነገሯቸውም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ ሌሎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ሒሳቡን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ መዝጋት ቢኖርበትም፣ እስካሁን ድረስ አለመዘጋቱም ተጠቁሟል፡፡ አቶ ኤፍሬም ግን ይኼንንም ‹‹ሐሰት ነው፤ ባንኩ ሒሳብ የሚዘጋው በሲስተም ስለሆነ በወቅቱ ተዘግቷል፤›› በማለት አስተባብለዋል፡፡ ሁሉም ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች በአዲሱ በጀት ዓመት ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ከ500 በላይ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በኔትወርክ ሲስተም የተያያዙ በመሆናቸውና በተለይ በዚህ ወቅት ከሒሳብ መዝጋት ጋር በተገናኘ በቀን ከ300,000 በላይ ትራንዛክሽኖች ስለሚካሄዱ ሲስተሞቹ ላይ ችግር የተፈጠረ ቢሆንም፣ ሒሳቡ ግን በአግባቡ መዘጋቱን አስረድተዋል፡፡ ሒሳብ ከተዘጋ በበጀት ዓመቱ ምን ያህል እንዳተረፈ፣ ምን ያህል ተቀማጭ እንዳለውና ትርፍና ኪሳራውን እንዲያስረዱ ተጠይቀው፣ የባንኩ የሒሳብ ቀመር ለጊዜው በእጃቸው ላይ የሌለ ቢሆንም፣ በዘጠኝ ወራት ሪፖርቱ ባንኩ እንደገለጸው ሁሉ ትርፉ እንደጨመረ፣ ተቀማጩም ከፍ ማለቱንና ቅርንጫፎቹም ወደ 832 መድረሳቸውን አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል፡፡

ባንኩ ለጊዜው ባለው ከፍተኛ ትራንዛክሽን የሲስተሞች እርስ በርስ የመናበብ ችግር አገልግሎቱ የቀነሰ ቢሆንም፣ በፍጥነት ወደ መደበኛ አገልግልቱ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና የሦስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሾፌሮች ወደ መቀሌ ለሥራ በሄዱበት ወቅት ተገቢ ያልሆነ ነዳጅ ተጠቅመዋል በሚል በተፈጠረ ውዝግብ፣ የደመወዛቸውን 20 በመቶ የገንዘብ ቅጣትና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ አስተዳዳራዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s