ያገሬ ሰውና ያገሬ መንግስት ይመሳሰላሉ፤ ራሳቸውን ጠልፈው መጣል ይቀናቸዋል

  • .  ተመራቂ ወጣቶችን ወደ ቢዝነስና ወደ ሥራ ፈጠራ ለማነሳሳት የሚጣጣር መንግስት፤ የቢዝነስ ሰዎች “አጭበርባሪ፣ ስግብግብና ኪራይ ሰብሳቢ ናቸው” እያለ ያንቋሽሻቸዋል። እዚያው በዚያው የራሱን ጥረት ራሱ ያመክነዋል።
  • .   አገሪቱ ከድህነት ተላቃ ማደግ የምትችለው በትርፋማ የቢዝነስ ሰዎች ጥረት ነው የሚል መንግስት፤ የራሱን ንግግር ራሱ ያፈርሰዋል። ትርፍ ለማግኘት መስራትን ያብጠለጥላል – “የማስቲካና የከረሜላ አስመጪ” እያለ።
  • .  ሕይወቱ እንዲሻሻልና ኑሮው እንዲበለፅግ የሚመኝ ብዙ ሰው፤ ራስ ወዳድነትን ሳይሆን መስዋእትነትን፣ ከትርፋማነት ይልቅ ምፅዋትን ያወድሳል። ራሱን ያልወደደና ትርፋማነትን ያላከበረ ሰው እንዴት ሕይወቱን ያሻሽላል?
  • .  መንግስትን የማያምን የአገሬ ሰው፤ “ነጋዴዎች፣ የሸቀጥ እጥረትንና የዋጋ ንረትን ይፈጥራሉ” በሚለው ውንጀላ መንግስትን ሙሉ ለሙሉ ያምናል – እጥረት የተባባሰው በመንግስት የተያዙት ስኳር፣ ዘይትና ስንዴ ላይ ቢሆንም።

በአንድ በኩል፤ ስለ ብቃትና ስኬት ማውራት
እየተለመደ መጥቷል – ቢዝነስና ትርፋማነት፣ ሥራ ፈጠራና ኢንዱስትሪ፣ ሃብት ፈጠራና ብልፅግና… ዘወትር ስማቸው እየተደጋገመ ይነሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ ስኬት፣ ትርፋማነትና ሃብት ፈጠራ እየተንቋሸሹ፣ ምስኪንነት፣ ምፅዋትና አገልጋይነት ሲሞገሱና ሲወደሱ እንሰማለን። አዲስ ነገር አይደለም። “የዚህ አለም ደስታና ብልፅግና ረብ የለሽ አላፊና ረጋፊ ነው” ከሚለው ጥንታዊ የውድቀት ባሕልና አስተሳሰብ አልተላቀቅንም። ይህም ብቻ አይደለም። በዚሁ ኋላቀርነት ላይ፤ ባለፉት አርባ ዓመታት ሌላ መርዝ ተጨምሮበታል። “ከራሴ በፊት ለሰፊውና ለድሃው ሕዝብ መስዋእት ልሁን” የሚል የሶሻሊስቶች መፈክር፤ “ከራሴ በፊት ለእናት አገሬ፣ ለብሔር ብሔረሰቤ” የሚል የፋሺስቶች መዝሙር፣ ይሄውና አሁንም ድረስ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ስሜት ይኮረኩራል።
ምናለፋችሁ! ሁሉም ነገር የተቀየጠ ሆኗል፡፡ ስለ ብቃትና ስለ ስኬት የሚያወራ ሰው፤ ዞር ብሎ ምስኪንነትንና መስዋዕትነትን ያዳንቃል። ሃብት ፈጠራንና ቢዝነስን አበረታታለሁ የሚል መንግስት፤ ዞር ሳይል ባለሃብቶችን በሰበብ አስባቡ እየወነጀለ ቁምስቅላቸውን ያሳያቸዋል፤ “የሃብት ክፍፍል” እያለ በፖለቲካ ቋንቋ ጥንታዊውን የምፅዋት አምልኮ ይሰብካል። ሁለት ሱሪ ያለው አንዱን ያካፍል እንዲሉ፡፡
እናላችሁ፣ ራስን ጠልፎ የመጣል አባዜ የበረከተበት ግራ የተጋባ ዘመን ላይ ነው ያለነው። እየገነቡ የማፍረስ በሽታ! ብልፅግናን እየፈለጉ ራስ ወዳድነትን የማብጠልጠል ልክፍት! ይህንን በግልፅ የሚመሰክሩ አራት የሰሞኑ ዜናዎችን እጠቅስላችኋለሁ።

1. ተመራቂዎች ቢዝነስን ወይም አገልጋይነት?
ዘንድሮ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚመረቁ ከ50ሺ በላይ ወጣቶች፣ ከመንግስት ሳይጠብቁ፤ በራሳቸው መንገድ ሕይወታቸውን የሚያሻሽል ሥራ (ቢዝነስ) እንዲፈጥሩ ምክርና ማሳሰቢያ ከመንግስት ባለስልጣናት ሲጎርፍላቸው ሰንብቷል። ቀላል ምክር አይደለም። ጉዳዩ፤ የድህነትና የብልፅግና፤ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው – ለእያንዳንዱ ወጣት። ስንቱ የጨነቀው ወጣት፣ ድንበርና እየዘለለ፣ ኬላ እየሰበረ፣ የበረሃውን ንዳድ የባህሩን ውርጭ እያቆራረጠ የሚሰደደው ለምን ሆነና! ጉዳዩ፤ የኢኮኖሚ እድገትና የኢኮኖሚ ቀውስ ጉዳይ ነው – ለመንግስት። በየአቅጣጫው በርካታ አገራት ሲተራመሱ የምናየው፣ በርካታ መንግስታት ሲቃወሱና ሲፈናቀሉ የምንመለከተው ለምን ሆነና! የጎሰኝነት ጡዘትና የሃይማኖት አክራሪነትን ጨምሮ፤ ከዘመናችን ሶስት ዋና ዋና ቀውሶች መካከል አንዱ፤ ወጣቶችን ተስፋ የሚያስቆርጥ የኢኮኖሚ ቀውስ ነው – በገናና የሚፈጠር የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ፡፡ እናም፤ ተመራቂ ወጣቶች ለስራ ፈጠራና ለቢዝነስ እንዲነሳሱ፣ ከመንግስት በኩል ምክርና ማሳሰቢያ እየተደጋገመ ቢሰነዘር አይገርምም። ብልህነት ነው፤ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ።
ታዲያ፤ ተመራቂዎቹ ወጣቶች ይህንን እጅግ ትልቅ ምክር ሰምተው፤ የራሳቸውን ቢዝነስና ንግድ ቢፈጥሩ፣ አድናቆትና ክብር ያገኛሉ ማለት አይደለም። ጉዳዩ የሕይወትና የሞት፣ የብልፅግናና የቀውስ ጉዳይ ቢሆንም ያን ያህል ክብደት አይሰጠውም።
እንደ ትልቅ ነገር ተቆጥሮ ክብር የተለገሰውና በስፋት የተለፈፈው ጉዳይ ምን እንደሆነ ልንገራችሁ። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ በክረምት ወራት ጊዜያቸውን ለህዝቡና ለአገር መስዋእት በማድረግ፣ ለበጎ አድራጎት ስራ ይሰማራሉ የሚል ዜና አልሰማችሁም?
በእርግጥም፤ የከፍተኛ ትምህርት አላማ፤ የራሳቸውን ቢዝነስ እየከፈቱ ራሳቸውን የሚጠቅሙ ተመራቂዎችን ማፍራት ሳይሆን፤ አገሪቱን በተለያዩ ሙያዎች የሚያገለግል የሰው ሃይል ማፍራት ነው  – የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ። ያ ሁሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪ፤ በክረምት ወራት መስዋእትነት፣ አንዳች ጠብ የሚል ቁም ነገር አይሰራ ይሆናል። ዋናው ነገር፤ ለየራሳቸው በሚጠቅም ስራ ላይ ሳይሰማሩ የክረምቱን ጊዜ (መስዋእት ማድረጋቸው) ማቃጠላቸው ነው። ቢረባም ባይረባም፤ ለቢዝነስ ሳይሆን ለአገልጋይነት መሰማራታቸው ነው – አድናቆትን የሚያተርፍላቸው።
በአጭሩ፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ የመንግስት ጥገኛ ከመሆን ይልቅ በስራ ፈጣሪነት ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ መንግስት ማሳሰቢያ ሲሰጥ መሰንበቱ ብልህነት ነው። ተመራቂዎች ሥራ መፍጠር ካልቻሉ፤ ሥራ አጥነትና ተስፋቢስነት እየተስፋፋ አገሪቱ ልትቃወስ ትችላለቻ። ይህን አደጋ በመገንዘብ፤ ተመራቂዎች የየራሳቸውን ሕይወት ለማሻሻል ከሁሉም በላይ ለሥራ ፈጠራ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ሲመክር የሰነበተ መንግስት፤ ያንን ምክር ለማምከን ሲጥር መሰንበቱ ነው ችግሩ። የአገርና የህዝብ አገልጋይ መሆን ከሁሉም የላቀ ክብር እንደሚገባው በመግለፅ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የክረምት ጊዜያቸውን “ለበጎ አድራጎት ሥራ” መስዋእት እንዲያደርጉ መንግስት አሰማርቷቸዋል። ራስን ጠልፎ የሚጥል ቅይጥ አስተሳሰብ ይሉሃል ይሄ ነው፡፡

2. የመንግስት የጅምላ ንግድ – ነጋዴዎችን ለማበረታታት ወይስ ለመጣል?
መንግስት፣ ሶስተኛውን የጅምላ ንግድ ማዕከል በመርካቶ ሲከፍት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ዋና አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረአብ፤ የግል ባለሃብቶች ወደ ዘመናዊ የጅምላ ንግድ እንዲሸጋገሩ ለማሳየትና ለማነሳሳት ይጠቅማል ብለዋል። የጅምላ ንግድ በመንግስት ሳይሆን በባለሃብቶች እንዲካሄድ እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል። (አማካሪው ለምን እንዲህ አሉ? የባለሃብቶች የግል ኢንቨስትመንት፣ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ዋነኛ ሞተር ነው። የቢዝነስ ሰዎች ሃብትን ይፈጥራሉ፤ ራሳቸውን ለመጥቀምና ትርፍ ለማግኘት ሲጣጣሩ፤ ሌላውም ሰው ይጠቀማል በሚል እምነት ነው)።
በሌላ በኩል እስከአሁን ሶስት የመንግስት የጅምላ ንግድ ማዕከላት እንደተከፈቱና ተጨማሪ ማዕከላትን በመክፈት አገልግሎቱ እንደሚስፋፋ የገለፁት የንግድ ሚኒስትር፤ ዋነኛ አላማው በነጋዴዎች አማካኝነት የሚፈጠረውን የሸቀጥ እጥረትና የዋጋ ንረት መከላከል እንደሆነ አስታውቀዋል። (ለምን የቢዝነስ ሰዎችን መወንጀል አስፈለገ? መንግስት በገፍ የብር ኖት ከማሳተም ከተቆጠበ ወዲህ የዋጋ ንረት ረግቧል – ከ2003 ወዲህ ። መቼም ቢሆን፣ የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በመንግስት እንጂ በነጋዴዎች ወይም በቢዝነስ ሰዎች አማካኝነት አይደለም። እንዲያም ሆኖ፤ በተገኘው ሰበብ የግል ቢዝነስንና ንግድን መኮነን የአገራችን ነባር ባህል ነው። እናም መንግስት፣ “የግል ቢዝነስ፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ የቀውስ አደጋ ነው። የቢዝነስ ሰዎች፤ ለአገር ልማት ሳይሆን ትርፍ ለማግኘት ይሰራሉ” በሚል እምነት ዘወትር ተመሳሳይ ውንጀላ ያዘንብባቸዋል)

3. ፎቀቅ ያላለውን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት – ባለሃብቶችን ማነሳሳት ወይስ ማብጠልጠል?
ባለሃብቶች ከንግድ ቢዝነስ ባሻገር፣ ወደ ማምረቻ (ወደ ማኑፋክቸሪንግ) የኢንዱስትሪ ቢዝነስ እንዲገቡ ለማነሳሳት፣ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በወዲያኛው ሳምንት ለሁለት ቀናት ገለፃ ሲሰጡ ውለዋል። ለምን? የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ በሚል ያዘጋጁት ሰነድ እንደሚለው፤ በግል ኢንቨስትመንት እንጂ በሌላ መንገድ ስኬታማና ትርፋማ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት አይቻልም። እናም ፋብሪካዎች በትርፋማነት እንዲስፋፉና እንዲያድጉ፤ የስራ እድሎች በብዛት እንዲከፈቱ ከተፈለገ፤ የቢዝነስ ሰዎች በዚሁ መስክ እንዲሰማሩ ማግባባት ያስፈልጋል – የተለያዩ እንቅፋቶችንና መሰናክሎችን በማስወገድ።
የማኑፋክቸሪንግ ቢዝነስ፤ አርቆ አሳቢነትንና ፅናትን፣ ለአመታት የሚዘልቅ ጥረትንና የፈጠራ ትጋትን ይጠይቃል። ይህንን የማሟላት ችሎታ ያላቸው ደግሞ የመንግስት ቢሮክራቶች ሳይሆኑ የቢዝነስ ሰዎች ናቸው። በወዲያኛው ሳምንት የተዘጋጀው ገለፃም ከዚሁ እምነት ጋር ይያያዛል። የመንግስት ባለስልጣናት እንዲህ አይነት እምነት ከያዙ፤ “እውነትም ለቢዝነስ ስራና ለቢዝነስ ሰዎች ትልቅ ክብር አላቸው” ያስብላል። ግን፤ ወዲያውኑ አፍርሰውታል።
አክብሮትን ሳይሆን ተቃራኒውን ስሜት ለማሳየት ጊዜ ያልፈጀባቸው የመንግስት ባለስልጣናት፤ “የአገራችን ባለሃብቶች፣ በአጭር ጊዜ እና በቀላሉ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘት ይፈልጋሉ” ሲሉ ከዘለፋ ወዳልተናነሰ ቅኝት የተሸጋገሩት በዚያው ገለፃ ላይ ነው። የንግድ ስራ ቀላል ነው? ቀላል ቢሆን፣ ለምን የመንግስት ባለስልጣናትና ቢሮክራቶች በንግድ ስራ አይሳካላቸውም? ለምን ደርግ አልተሳካለትም፣ ዛሬም መንግስት የገባበት የንግድ ስራ በሙሉ፤ በሙስናና በሸቀጥ እጥረት ሲበላሽ የምናየውኮ አለምክንያት አይደለም። የስንዴ እጥረት፣ የዘይት እጥረት፣ የስኳር እጥረት… እነዚህ በመንግስት የተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ፤ የንግድ ቢዝነስ ቀላል እንዳልሆነ የሚመሰክሩ ናቸው። የመንግስት ባለስልጣናት ይህንን የአደባባይ እውነት ለማገናዘብ ፍቃደኛ አይመስሉም።
ይልቁንስ ትርፋማነትንና ቢዝነስን የሚያንቋሽሽ ነባር የአገራችንን ባህል ይዘው ማራገብንና መዛትን መርጠዋል። የቢዝነስ ሰዎች በተለመደው የንግድ ሥራ “ኪራይ ሰብሳቢ” ሆነው ለመቀጠል እንጂ ወደ አምራች የኢንዱስትሪ ቢዝነስ ገብተው “ልማታዊ ባለሃብት” ለመሆን የማይፈልጉ ከሆነ፤ ብድር አያገኙም ሲሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል። “የቢዝነስ ሰዎች፣ በጥረት ሃብት መፍጠር አይፈልጉም። በቀላሉ ትርፍ ለማጋበስ እንጂ ለአገር ልማት አስተዋፅኦ የማድረግ ሃሳብ የላቸውም – ከረሜላና ማስቲካ አስመጪ ሁላ!” …
ራስን ጠልፎ መጣል፣ እየገነቡ ማፍረስ ይሏል ይሄው ነው ብሎ ማንኮታኮት ነው፤ የቅይጥ ኢኮኖሚ ባህርይ፡፡

4. የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ – የዋጋ ንረትን ይፈጥራል ወይስ አይፈጥርም?
ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ስለተጨመረ፣ የዋጋ ንረት እንደማይከሰት የገለፁት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር፤ የደሞዝ ጭማሪው በጥናት ላይ የተመሰረተና በበጀት የተያዘ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል – ለደሞዝ ጭማሪ ተብሎ የብር ኖት ህትመት በገፍ እንደማይካሄድም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝም እንዲሁ፣ ተመሳሳይ መከራከሪያ በማቅረብ፣ የዋጋ ንረት የሚፈጠርበት አንዳችም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለም ብለዋል። በእርግጥም፤ መንግስት የብር ኖቶችን በገፍ ከማሳተም እስከተቆጠበ ድረስ፤ የዋጋ ንረት አይፈጠርም። ትክክል ነው። እንዲያም ሆኖ፣ በዚህችው አጋጣሚ፣ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን ሳይወነጅሉ ለማለፍ አልቻሉም። “ስግብግብ ነጋዴዎች የዋጋ ንረት እንዳይፈጥሩ ክትትልና ቁጥጥር ይካሄዳል፤ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” በማለት ደጋግመው ተናግረዋል።
ዜጎች በሥራ ፈጠራና በምርታማነት ኑሯቸው እንዲሳካ፣ የቢዝነስ ሰዎች በትርፋማነት ኢንዱስትሪ እያስፋፉ እንዲከብሩ፤ በአጠቃላይ ለሃብት ፈጠራና ለብልፅግና ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጥ የሚገልፅ መንግስት፤ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን ማጣጣል መደበኛ ስራው ሲሆን ምን ይባላል? “ራስን ጠልፎ የመጣል አባዜ” አይደለምን?
“ጥቃቅንና አነስተኛ” በሚል የተለያዩ የቢዝነስ ሥራዎችን የጀመሩ በርካታ ወጣቶች፣ “ገበያ አጣን” በማለት በተደጋጋሚ ለመንግስት አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ሳታውቁ አትቀሩም፡፡ መንግስትም፤ “የገበያ ትስስር እፈጥርላችኋለሁ” እያለ በርካታ ፕሮጀክቶችን ያለጨረታ ለዚህኛውና ለዚያኛው ሲቸር ቆይቷል፡፡ ግን ለሁሉም ጥቃቅን ተቋማት ከዓመት ዓመት ችሮታ ማዳረስ አይቻልም፡፡ “የገበያ ትስስር እፈጥርላችኋለሁ” የሚለው ፈሊጥ እንደማያዋጣ  ቀስ በቀስ የተገነዘቡ ባለስልጣናት አሁን አሁን የሚሰጡት ምላሽ፤ “ከመንግስት ችሮታ የምትጠብቁ ጥገኞች መሆን የለባችሁም” የሚል ሆኗል።
እውነትም፣ የቢዝነስ ሰዎች እንጂ ቢሮክራቶች ለዘለቄታው የሚያዋጣ የገበያ ትስስር የመፍጠር አቅም የላቸውም። የቢዝነስ ሰዎች ገበያ የሚያገኙትና ትርፋማ የሚሆኑት ለምንድነው? አንዴ ሁለቴ፣ ይሄንን ወይም ያንን በማጭበርበር ለማምለጥ የሚሞክሩ የቢዝነስ ሰዎች መኖራቸው አያጠራጥርም። ነገር ግን፣ ብዙም አይራመዱም። ስኬታማ መሆን የሚችሉት፣ በተወዳዳሪነት ብቃት ነው።  የመንግስት ባለስልጣናት ይሄንን አያጡትም። “ጥቃቅንና አነስተኛ” የቢዝነስ ተቋማትን ለሚመሰርቱ ወጣቶችም ይህንኑን ሲነግሯቸው ሰምተናል – “በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ስታቀርቡ ነው ገበያ በማግኘት ትርፋማና ስኬታማ መሆን የምትችሉት” በማለት።
ይሄ ምክር፣ አማራጭ የሌለው ትክክለኛና የሚያዋጣ ምክር ነው። በሌላ አነጋገር፤ ዋጋ በማናር ለማትረፍ የሚሞክር ነጋዴ፤ ገበያተኛ እየሸሸው ይከስራል እንጂ አይሳካለትም። በሌላ አነጋገር፣ ነጋዴዎች የዋጋ ንረትን መፍጠር አይችሉም። ይህንን የሚያውቁና የሚናገሩ ባለስልጣናት፤ ዞር ብለው “ነጋዴዎች የዋጋ ንረትን ይፈጥራሉ” የሚል ውንጀላ ሲሰነዝሩ ምን ይባላል? በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለተሰማሩ ወጣቶች የሰጡትን ምክር፣ መልሰው ይንዱታል። “እንዳሻችሁ ዋጋ በማናር ገበያ ማግኘትና ትርፋማ መሆን ትችላላችሁ” የሚል የውሸት ምክር እንደመስጠት ቁጠሩት – እውነተኛውን ምክር የሚያፈርስ።
በአጠቃላይ፤ ዛሬ ዛሬ ለወሬ ያህል ደግ ደጉን ማውራት ተጀምሯል። ብቃትና ስኬት፣ ትርፋማነትና ብልፅግና፣ ምርታማነትና ስራ ፈጠራ፣ መጣጣርና የራስን ሕይወት ማሻሻል የሚሉ ቃላት ባገሬ ሰዎች አንደበት ዘንድ እየተዘወተሩ ነው። የመንግስት ባለስልጣናትም እንዲሁ፣ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ ኢንዱስትሪን ማበረታታት፣ የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እያሉ ሲናገሩ እንሰማለን። ጥሩ ነው። ግን “ወሬ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ የስኬት ወሬ፣ በተግባር የማይሳካው፤ አብዛኛው የአገሬ ሰውም ሆነ የመንግስት ባለስልጣናት፤ በገዛ አንደበታቸው ለሚናገሩት “የስኬት ሃሳብ”፤ እምብዛም ክብር ስለሌላቸው ነው። ከብቃትና ከስኬት ይልቅ፤ አቅመ ቢስነትንና ምስኪንነትን፤ ከትርፋማነትና ከብልፅግና ይልቅ ምፅዋትንና ችግር መጋራትን፤ ከስራ ፈጠራና ሕይወትን ከማሻሻል ይልቅ መስዋእት መሆንና አገልጋይነትን ያደንቃሉ – ያገሬ ሰውና ያገሬ መንግስት።
ከ“ትርፋማነት” እና ከ“ምፅዋት” መካከል የትኛውን ነው “በጎ አድራጎት” በማለት የምናሞግሰው? ያገሬ ሰው በአብዛኛው፤ የ“ምፅዋት” አወዳሽ ነው – “ሁለት ጫማ ያለው አንዱን ይመፅውት” ይባል የለ! መንግስትንም ብታዩት፣ ከዚህ የተለየ አይደለም።
መንግስት አገሬውን ይመስላል። መቼም፤ ለኢትዮጵያ ተብሎ፣ ከሌላ ፕላኔት ልዩ መንግስት አይመጣም። ያገራችንን መንግስትና ገዢ ፓርቲ ተመልከቱ። የመንግስትን ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ሌሎች ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችንም ጠይቋቸው። ባትጠይቋቸውም ይነግሯችኋል። ለድሆች የቆሙና “ለዝቅተኛው ሕብረተሰብ” የወገኑ መሆናቸውን በኩራት የሚናገሩት የአገራችን ፓርቲዎች፣ የምፅዋት አድናቂዎች ናቸው – ከራሳቸው ኪስ በማይወጣ ገንዘብ ድሆችን በመደጎም ተአምረኛ ለውጥ እናመጣለን ብለው የሚያልሙ።
ከሁሉም ፓርቲዎች አፍ የማይጠፋ፣ እንደ ፀሎት ቀን ከሌት የሚደጋግሙት “እጅግ የተከበረ ቅዱስ መፈክር” ቢኖር፤ “የሃብት ክፍፍል” የሚለው ፈሊጥ ነው። ያው “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ይመፅውት” ከሚለው ስብከት ጋር ይመሳሰላል። ግን ይብሳል። “ምፅዋቱ” በፈቃደኝነት የሚፈፀም ሳይሆን በሕግ የታወጀ ግዴታ እንዲሆን ያደርጉታል። ለነገሩ፤ አቅመቢስነትንና ምስኪንነትን፤ ምፅዋትንና ጥገኝነትን አስበልጦ የመውደድና የማምለክ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በተቃራኒው፤ ብቃትንና ስኬትን፣ ትርፋማነትንና ብልፅግናን የማጣጣል፤ ከዚያም አልፎ የማንቋሸሽና የማውገዝ ዝንባሌ ይታከልበታል። “ራስ ወዳድነት”ን እንደ ስድብና ኩነኔ የምንቆጥረው ለምን ሆነና?  “ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ አጭበርባሪና ስግብግብ ነጋዴዎች” የሚለው የአገራችን የተለመደ አባባል የዚህ ዝንባሌ መለያ ታፔላ ነው። “የሃብት ልዩነት ሰፍቷል” የሚለው ውግዘትም እንዲሁ።
መንግስት፤ የሙያና የቢዝነስ ሰዎች፣ በየመስኩ ፋብሪካ እየከፈቱ የኢንዱስትሪ ምርትን እንዲያስፋፉ ይመኛል። ምኞቱ እውን ሊሆን የሚችለው፤ የቢዝነስ ሰዎች ስኬታማና ትርፋማ ሲሆኑ ነው። ነገር ግን፤ የቢዝነስ ሰዎች ከሌላው ሰው የበለጠ ሃብት ማፍራታቸው መንግስትን አያስደስትም። “የሃብት ልዩነት”ን በደስታ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም። በደስታ ይቅርና፤ በዝምታ ወይም በቅሬታ ለመቀበልም አይፈልግም። “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” የሚለው ነገር አለ።
በፖለቲከኞቹ ቋንቋ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” ማለት፤ ከታታሪ የፈጠራ ሰው (ማለትም ከስኬታማና ከትርፋማ ሰው) ሃብት በመውሰድ፤ ሃብትን በኪሳራ ለሚያባክንና ሃብትን ለማያፈራ ሰው መስጠት ማለት ነው። “ፍትሃዊ” ማለት፤ ሁሉንም ሰው እኩል ለማድረግ ፈጣን ሯጮችን ማንቋሸሽ፤ ቀን ከሌት ሲሰሩም፤ “አሸናፊ ለመሆን የሚመኙ በስግብግቦች” እያልን መወንጀል፤ ስኬታማዎች ወደ ፊት እንዳይራመዱ ቅልጥማቸውን ሰብሮ ማሳረፍ፣  ፈጣን ሯጭ ያልሆነውም ሰው እንዳይጣጣር ማባበል እንደማለት ነው።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከመንግስት የተለየ አስተሳሰብ የለውም። ብቃትንና ስኬትን ከምር የሚፈልጉ ሰዎች፤ በብቃት የላቀ ስኬታማ ሰው ሲያጋጥማቸው በአድናቆትና በክብር ያሞግሱታል፤ በአርአያነቱም መንፈሳቸውን ያነቃቃሉ። ብዙ የአገሬ ሰዎች ግን፣ ቀልባቸው የሚማረከው አቅመቢስና “አለም በቃኝ” ብሎ ራሱን የጣለ ምስኪን ሲያጋጥማቸው ነው። ትርፋማነትንና ብልፅግናን የሚፈልጉ ሰዎች፤ ሃብትን በማፍራት የበለፀገ ትርፋማ የቢዝነስ ሰው ሲያጋጥማቸው፤ ውስጣቸው በአድናቆት ይሞላል፤ ታሪኩን ለማወቅ ይጓጓሉ። አብዛኛው የአገሬ ሰው ግን፤ የቢዝነስ ኩባንያን ሳይሆን የእርዳታ ድርጅትን፣ ለትርፍ የተቋቋመ ፋብሪካን ሳይሆን በበጎ አድራጎት የተተከለ ችግኝን በማስበለጥ እንደ ቅዱስ ነገር ያያል።
በአጭሩ፤ በነባር ተራ ቃላት፣ በተድበሰበሱ ምሁራዊ ሃረጋት ወይም በተሰለቹ ፖለቲካዊ አባባሎች ልዩ ልዩ ቀለም ብንቀባውም፤ አብዛኛው የዘመናችን አስተሳሰብ ከጥንታዊው የኋላቀርነት ባህል ብዙም አይለይም። “የዚህ አለም እውቀትና ሙያ እንደ ብናኝ ክብደት የሌለው፤ የዚህ አለም ደስታ እንደ ጤዛ ውሎ የማያድር፤ የዚህ አለም ስኬትና ብልፅግና እንደ ሸክላ ተሰባሪ፤ የዚህ አለም ኑሮና ምቾት እንደ ቅጠል ረጋፊ” … ከሚል የውድቀት ቅኝት አልተላቀቅንም። ራሳችንን ጠልፈን የመጣል አባዜ የተጠናወተንም በዚህ ምክንያት ነው። ይህንን ካስወገድን፤ የብቃትና የስኬት፣ የሥራ ፈጠራና የትርፋማነት፣ የሃብት ፈጠራና የብልፅግና ጉዟችንን የሚያሰናክል ከአቅም በላይ የሆነ እንቅፋት አይኖርብንም። ለነገሩ ብዙም ሊያከራክረን አይገባም ነበር፡፡ ምፅዋት የሚኖረው እኮ፣ በቅድሚያ የሃብት ፈጠራ ሲኖር ነው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s