– የከተማ አውቶቡስ ድርጅት 16 ቁጥር አውቶቡስን ከሥምሪት ማገዱ ተጠቃሚዎችን አስቆጣ

– ‹‹አደጋውን እያየን ዝም ማለት የለብንም››      የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ከመርካቶ እስከ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ድረስ አገልግሎት እንዲሰጥ አሰማርቶት የነበረውን 16 ቁጥር አውቶቡስ፣ ከሥምሪት ማገዱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን አስቆጣ፡፡

ድርጅቱ በበኩሉ አደጋውን እያየ ዝም ማለት እንደሌለበትና ለጊዜው አገልግሎቱን ለማቋረጥ መገደዱን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ከመርካቶ በተለምዶ አዳራሽ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ተነስቶ በሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ፣ በጊዮርጊስ ውቤ በረሃ፣ መነንና ሽሮ ሜዳን አካሎ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ላይ ጉዞውን የሚያበቃው 16 ቁጥር አውቶቡስ፣ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ ዕድሜ ማስቆጠሩን የሚናገሩት የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች፣ ድርጅቱ አገልግሎቱ እንዲቆም ማድረጉ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡

ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በደረሰው አደጋ የሞቱት ስምንት ሰዎችና ጉዳት የደረሰባቸው ከ30 በላይ ግለሰቦች ሁኔታ አስደንግጦት ሊሆን ይችላል በሚል የአገልግሎቱ መቋረጥን ለሳምንት ያህል መታገሳቸውን የገለጹት ተጠቃሚዎቹ፣ ቀናት እየጨመሩ በመሄዳቸው ምክንያቱን ለማጣራት ሲሞክሩ፣ ድርጅቱ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡

አውቶቡሱ የተሰማራበት መንገድ ከፍተኛ የሰዎች ምልልስ ያለበት መስመር ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በንግድ ቦታነት ከሚታወቁ አካባቢዎች አንዱ የሆነው ሽሮሜዳም የሚገኝበት መሆኑን የገለጹት ተጠቃሚዎች፣ የአውቶቡሱን ብዛት በመጨመር አገልግሎቱን በማስፋፋትና ኅብረተሰቡ ከትራንስፖርት ችግር እንዲላቀቅ ማድረግ ሲገባው፣ ድርጅቱ አገልግሎቱ እንዲቆም ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. የደረሰውን አደጋ በሚመለከት ድርጅቱ ያሰማራውን አውቶቡስ ሁኔታ ማለትም የነበረበትን የቴክኒክም ሆነ የአሽከርካሪ ችግር በማጥናት ማስተካከል ሲገባው፣ አገልግሎቱን በማቋረጥ ኅብረተሰቡን ለእንግልት ማጋለጡ ተገቢ አለመሆኑን ተጠቃሚዎቹ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አውቶቡስ በጥቂት ወራት ብቻ ለበርካታ ሰዎች መሞት፣ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የዳረገ መሆኑን ያስታወሱት ተጠቃሚዎቹ፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ አውቶቡሶች የሚያደርሱት ጉዳት በንፋስና ሌሎች ምክንያቶች መሳበቡ አንሶ፣ በተገለበጡበትና ጉዳት ባደረሱበት አካባቢ አገልግሎት መስጠት ማቆሙ መፍትሔ እንደማይሆን አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ የአውቶቡሶቹን ሁኔታ በደንብ በመፈተሽና ብቃት ያላቸው አሽከርካሪዎች በማሰማራት አገልግሎቱን መስጠት እንደሚገባው ተናግረው፣ በተለይ 16 ቁጥር አውቶቡስ በተሰማራበት መንገድ ብዙ ደካማ አዛውንቶች፣ እንዲሁም ተማሪዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ድርጅቱም ሆነ የሚመለከተው የአስተዳደሩ አካል፣ አገልግሎቱ እንዲጀመር እንዲያደርጉላቸው ተጠቃሚዎች ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በድሉ አሰፋ፣ 16 ቁጥር አውቶቡስ አገልግሎቱን እንዲያቋርጥ የተደረገበትን ምክንያት ተጠይቀው፣ ክረምቱ ከባድ ስለሆነና በተለይ ከሽሮሜዳ እስከ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለው መንገድ ጠባብነት ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንገዱ ጠባብ ከመሆኑም በተጨማሪ ወቅቱ የፍልሰታ በዓል በመሆኑ ብዙ ሕዝብ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ አገልግሎት መስጠት አስቸጋሪ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

አውቶቡሱ ሰፊ ቦታ የሚፈልግ በመሆኑና መንገዱ ደግሞ ጠባብ በመሆኑ እግረኞችና አውቶቡሱ በአንድ መንገድ የሚሄዱ ከሆነ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል የገለጹት አቶ በድሉ፣ ‹‹ይኼንን አደጋ እያየን ዝም አንልም፤›› ብለዋል፡፡ ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. የደረሰው አደጋ ከላይ በጠቀሱት ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕዝቡ ሽሮሜዳ ድረስ በእግሩ ከተጓዘ ሽሮሜዳ ላይ ብዙ አማራጮች እንዳሉት የገለጹት አቶ በድሉ፣ ስለቀጣይ የሥምሪቱ ጉዳይ ቆም ብለው ማሰብ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል፡፡ የቴክኒክ ችግር የገጠማቸው ከ200 በላይ አውቶቡሶች ስለመቆማቸው ተጠይቀው፣ ‹‹ስለሁሉም ነገር ቆም ብለን እያየንና ለማስተካከል እየሞከርን ነው፡፡ የቴክኒክ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማስተካከያ እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ በሥምሪት ላይ ስንት አውቶቡሶች እንዳሉ ተጠይቀው፣ ወቅቱ ክረምት ስለሆነና ብዙ ተጠቃሚዎች ስለሌሉ በአገልግሎት ላይ ያሉት አውቶቡሶች ቁጥር 650 መሆኑን አስረድተው፣ ከመስከረም 2007 ዓ.ም. በኋላ ተጨማሪ 100 አውቶቡሶች እንደሚሰማሩ አክለዋል፡፡ የቆሙት አውቶቡሶች 200 ሳይሆኑ 80 መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ከመርካቶ እስከ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት የተሰማራው 16 ቁጥር አውቶቡስ፣ ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ ባደረሰው አደጋ 8 ሰዎች መሞታቸውንና ከ30 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን፣ እንዲሁም በስምንት ተሽከርካሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s