የውቤ በረሃ ተፈናቃዮችና አስተዳደሩ ተፋጠዋል

በአራዳ ክፍለ ከተማ ከጊዮርጊስ ወደ አፍንጮ በር በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የውቤ በረሃ ከአስፋልት በታች ነዋሪዎች፣ የክፍለ ከተማው አስተዳደር ‹‹የገባልንን ቃል አጥፏል›› በሚል፣ ‹‹ዕጣ አውጡ›› የሚለውን የአስተዳደሩን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተፋጠዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ከ514 በላይ አባወራዎችን በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የክፍለ ከተማው አስተዳደርና የወረዳዎቹ ተወካዮች ሰብስበዋቸው ቦታው ለልማት እንደሚያስፈልግ ሲነግሯቸው፣ አራት ኪሎና ልደታ ከተገነቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በዕጣ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር ነዋሪዎቹ ያስታውሳሉ፡፡

በመሆኑም ኮሚቴ በማቋቋም ከዓመት በላይ ጉዳዩን ሲከታተሉ ቆይተው ሰሞኑን ዕጣ ማውጣት እንዳለባቸው ተነግሯቸው ሲሄዱ፣ ዕጣ የሚያወጡት ለአራት ኪሎና በልደታ ሳይሆን ገላን ለተገነቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች መሆኑን ሲያውቁ፣ ‹‹ዕጣ አናወጣም›› በማለት መቃወማቸውን ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ ነሐሴ 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በቅድሚያ አቅመ ደካማ ለሆኑ 35 አባወራዎች ዕጣ ሲያወጡ ሳይቱን ማየታቸውንና ‹‹የተገባልን ቃል ከአካባቢያችሁ ሳትርቁ በቅርብ ባሉ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ትገባላችሁ የሚል ነው፤›› በማለት አስተዳደሩን መቃወማቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹እኛ ጥያቄያችን የፖለቲካ አይደለም፡፡ እኛም ሆንን ልጆቻችን ሰላም ፈላጊዎች ነን፤›› የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ዓመቱን ሙሉ በአግባቡ እየተሰበሰቡና ከወረዳው አመራሮች ጋር ሲመካከሩ ቆይተው፣ ቅድሚያ ለፈረሰባቸው 50 ነዋሪዎች ጀሞ ሳይት ቤት ሰጥተው ሲያስገቡ፣ ‹‹የቅርቡ ሳይት ስላልደረሰልን ነው›› በማለት አታለዋቸው፣ አሁን ደግሞ እነሱን ‹‹ገላን ሳይት ትገባላችሁ›› በማለት ወደ አመፅና ሁከት ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል፡፡

ከ217 በላይ አባወራዎች (አብዛኛዎቹ አዛውንቶች ናቸው) የከተማውን ከንቲባ ለማነጋገር ጥረት ሲያደርጉ ለነሐሴ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. የተቀጠሩ ቢሆንም፣ በዕለቱ ሊያነጋግሯቸው አለመቻላቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸው፣ አሁንም የሚጠይቁት ከዓመት በፊት በተገባላቸው ቃል መሠረት በቅርቡ በተገነቡ አራት ኪሎና ልደታ ሳይቶች ዕጣ እንዲወጣላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በገላን ሳይት ከዚህ ቀደም የፈረንሳይ ነዋሪዎች እንዲገቡ ተጠይቀው ‹‹አንቀበልም›› ማለታቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ከስምንተኛ ክፍል በላይ ትምህርት ቤት ሳይኖርና በቂ ጤና ጣቢያ እንኳን በሌለበት አካባቢ እንዲገቡ ማስገደድ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ አስተዳደሩ በገባላቸው ቃል መሠረት ሊፈጽምላቸው እንደሚገባም አክለዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ነዋሪዎቹን በመከፋፈልና ልጆቻቸውም በማያውቁት የፖለቲካ ድርጅት ‹‹አባል ናችሁ›› በማለት ለማስፈራራት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹ይኼ ለማንም አይበጅም፣ ልጆቻችንም ሆኑ እኛ የምንፈልገው መብታችን እንዲከበር ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማና የከተማው አስተዳደር ኃላፊዎች፣ ነዋሪዎቹ እያቀረቡ ባሉት ተቃውሞ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት ‹‹ሥልጠና ላይ ናቸው›› በሚል አልተሳካም፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s