ከጨርቁና ከቋንቋው በስተጀርባ – ይሄይስ አእምሮ (ከኢትዮጵያ)

ዛሬ እሁድ የካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም የወያኔ 40ኛ ዓመት ክብረ በዓል መዘምዘሚያ በወያኔው አባል በቱጃሩ አላሙዲን የሚሌኒየም አዳራሽ ውስጥ እየተከበረ ነው፡፡ ዘፈንና ደስታ አለቅጥ ሲበዛ የሚያስከትለውን ምልኪያዊ ሀዘን የተረዱ አይመስሉም፡፡

እኔ እንዳለመታደል ሆኖ የወያኔን ሚዲያ አልከታተልም – በሌላ ምክንያት ሣይሆን ለጤንነቴ ቅድሚያ ከመስጠት አኳያ ነው፡፡ ነገር ግን የሚከታተሉ ሰዎች ብዘውን ጊዜ  ምን እንደተላለፈ በመጠጥ ቤትና በሕዝብ መገናኛ ሥፍራዎች ይነግሩኛል፡፡ መስማት ባልፈልግም ጆሮየን መጠቅጠቅ አልችልምና እሰማለሁ፡፡ የዛሬውን አስደናቂ ወሬ የሰማሁት እንግዲህ ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ መሆኑ ነው፡፡

የወያኔ በዓል በትግራይ ውስጥ ከሁለት ወራት ላላነሰ ጊዜ በትግርኛም እንዳስፈላጊነቱ በዐማርኛም ተከብሯል፡፡ በመሠረቱ ወደ ስድስት ሺህ ገደማ በሚገመቱት የዓለም ቋንቋዎች ቢከበርም ግድ አይሰጠኝም ብቻ ሣይሆን የምከፋ አይደለሁም፡፡

ሰዎች እየተዘባበቱና በወያኔ እየቀለዱ ሲናገሩ እንደሰማሁት ደብረጽዮን የሚባለው የወያኔ ባለሥልጣንና ቱባ ካድሬ በዚህ የሚሌኒየም አዳራሽ የበዓሉ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ያደረገው ንግግር ሙሉ በሙሉ በትግርኛ ነው አሉ፡፡ እርግጥ ነው – በሕወሓት በዓል ላይ ሌላ ቋንቋ እንዲነገር መጠበቅ አግባብነት ላይኖረው ይችላል፡፡ መሠረታዊ ችግሩ ግን የአንድ ፓርቲ ወይም የነፃነት ግምባር የመላ ሀገሪቱን ሕዝብ እንደነሱው አጠራር ‹ሕዝቦች› ንብረት የሆነውን ሚዲያ በጉልበት አስገድዶ – ፕሮግራሞቹንም ሁሉ አስቁሞ – ለግል ጉዳዩ ማዋሉ ነው፡፡ ይህ ማንአለብኝነት ነገና ከነገ ወዲያ በታሪክም በወንጀልም የሚያስጠይቅ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ሌሎች “አቻ” ፓርቲዎች ወይም የ“ነፃነት ንቅናቄዎች” – ለምሣሌ እንደ ኦህዲድና ብአዴን እንዲሁም ደኢሕዲን የመሳሰሉት –  ይህን የመሰለ በጣም የተራዘመ ደማቅ ሀገራዊ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን፣ የገንዘብ መዋጮና “መንግሥታዊ” የበጀት ድጋፍ አላገኙም – ከአሁን ወዲያም ቢሆን ፍትሃዊ የድርጅቶች እኩልነት በተግባር እንዲታይ ወያኔዎች የሚፈቅዱ ከሆነና ሕወሓት እስከመጋቢት ድረስ የሚቆይ ከሆነ የፊታችን መጋቢት 17/2007 እንደሚከበር የሚጠበቀው የኦህዴድ የምሥረታ ወይም ከደርግ ምርኮኛ ብሔራዊ ዘማቾች በወያኔ ተጠፍጥፎ ለመናጆነት የተሠለፈበት በዓል በምን አኳኋን እንደሚከበር ለማየት በጉጉት እንጠብቃለን፡፡ ከህዝብ ብዛት አንጻር ወያኔ ትንሽ የመቶኛ ሥሌት ይዞ ሳለ በዚህ መልክ በዓሉን ማክበሩ ሀገሪቱንና ሀብቷን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ማድረጉን ያመለክታል የሚል ግምት ያስጨብጣል፡፡ ይህ አካሄድ ሀብቷን ብቻ ሣይሆን ከወያኔ በእጅጉ እንዲያውም በፍጹም ሊወዳደር በማይችል ሁኔታ ኆልቁ መሣፍርት የሌለው የሕዝብ ቁጥር ይወክላሉ የሚባሉ “አቻ” ግምባሮችንና ንቅናቄዎችን እንዲሁም ውዝዋዜዎችን በእግሩ ሥር አውሎ እንደፈለገው እየተጫወተባቸው መሆኑን ይጠቁማል – እንደአካሄድ፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ በጥገኛ ድርጅቶች ዘንድ ታላቅ የሀፍረት ምንጭ ሆኖ በታሪክ የሚመዘገብ ይመስለኛል፡፡

ባለራዕዩ መሪ ሙትቻው ሟች መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት ስለ ሰንደቅ ዓላማ ሲጠየቅ – መጥቀስ ይቻላል –  “ባንዲራ ጨርቅ ነው፡፡ ምሥጢሩ ያለው ከባንዲራው በስተጀርባ ነው” ብሎ ነበር፡፡

መለስ በዚህ ንግግሩ ብዙ ተተችቷል፡፡ እንደኔ ግን ትክክል ነበር፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ከጨርቅ ውጪ ከብረት ወይም ከእንጨት ተሠርቶ ሲውለበለብ አይቼ አላውቅም – እናም ከዚህ እሳቤ አንጻር መናገር ፈልጎ ከሆነ ስህተት አልነበረውም፡፡ ችግሩ የሚመስለኝ ከአመለካከትና ከንግግሩ በስተጀርባ ካለው ፍላጎት ነው – እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ “intention” የሚሉት፡፡ እንደሚመስለኝ እርሱ ማለት የፈለገው “ሕወሓት ለ‹ሀገሪቱ› የፈጠረላት ባንዴራ ከጥንቱ ባንዴራ የተለዬ ነው፡፡ የጥንቱ ባንዴራ ብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በኃይል ጨፍልቆ የግዛት አንድነት ለመመሥረት የሚጥርን ሥርዓት የሚወክል ሲሆን አዲሱና እኛ ሕወሓቶች የሠራነው ባንዴራ ግን የሀገሪቱ ዜጎች በፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ ሁኔታ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ፈጥረው የሚኖሩበትን ፍትሃዊ ሥርዓት የሚወክል ነው፡፡ ስለሆነም የጥንቱ ባንዴራ ከጨርቅነት ያለፈ ትርጉም ስለሌለው ከጨውና ስኳር መቋጠሪያነት ባለፈም ተቀዳዶ ቢጣልና ቢቃጠልም ሲያንሰው ነው” ነው፡፡ መለስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንደማይወድ እንዲያውም እንደአባቱ ገዳይ ያህል እንደሚጠላው የታወቀ ነው፤ የኢትዮጵያን ስም እንኳን በአግባቡ ለመጥራት ሲጠየፍ እንደነበርና ኢትዮጵያን መጥቀስ በሚኖርበት ዐረፍተ ነገር ሁሉ “ሀገሪቱ” እያለ በመጥራት ምድራዊውንና የሥልጣን ዘመኑን በአንድ ቅጽበት እስካጣበት ወቅት ድረስ በጥላቻ ናውዞ ይህችን ዓለም የተሰናበተ የመርገምት ፍሬ ነው፡፡ ስለዚህ ጨርቅ ቀርቶ ከዚያም ባለፈ ሊያስከፋ የሚችል ቃል ሊናገር ይችል ነበር፡፡ በንግግር ለማስቀየም ደግሞ እንደመለስ ዘርፋጭ ዓለማችን እስካሁን ያፈራች አትመስለኝም፡፡ እነሂትለርም የዚህን ቆሻሻ ሰውዬ ያህል እንደልባቸው ተናጋሪዎች አይመስሉኝም – መጠነኛም ቢሆን የተወሰኑ የሞራል ዕሤቶችን የሚያከብሩ ይመስሉኛል፡፡ ይሄ የኛው ጉድ  ግን ለይቶለት ከሁሉም ሃይማኖታዊና ሞራላዊ ማዕቀፎች ያፈነገጠ ነበር፡፡

የደብረጽዮን የትግርኛ ንግግርም ከመለስ የሰንደቅ ዓላማን ምንነት አገላለጽ ብዙም ለይቼ አላየውም፡፡ መለስ የኢትዮጵያን መለያ የሦስት ቀለማት ኅብር በሰም ለበስ ቅኔ “ጨርቅ” ሲል ለማዋረድ መሞከሩ ይህም ሰው – ደብረጽዮን – በሚሌኒየም አዳራሽ ለተሰበሰበው፣ ኢትዮጵያንም እንደሚወክል ለሚታመንና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚተላለፍ የቀጥታ ሥርጭት በትግርኛ – ሊያውም ያለ አስተርጓሚ – መናገር የፈለገው  የተለዬ  “ኢንቴንሽን” በወያኔያዊ ልቡ ስላረገዘ እንጂ አንድምታውን አጥቶት አይደለም – የተወሰኑ ምናልባትም ብዙዎቹን የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ አባላት በንዴት ለማንጨርጨር የታሰበ ድርጅታዊ ተልእኮን ለማሣካት ፈልጎ መሆን አለበት – በዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ ኦሮሞም በሉት ጉራጌ፣ ደራሳም በሉት ሽናሻ፣ ጠምባሮም በሉት ሃዲያ፣ ከምባታም በሉት ወላይታ፣ ጀምጀምም በሉት ኮንሶ፣ ጉሙዝም በሉት ኣሪ፣ በርታም በሉት አኝዋክ፣ፃማይም በሉት ሱርማ … ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ – በአዳራሹ ውስጥ ተገኘም በቲቪ ተከታተለም ከትግርኛ ይልቅ በአማርኛ እንደሚግባባ ትግሬ ብቻ ሣይሆን መላው ዓለም ያውቃል፡፡ By the way – በፈረንጅኛው ብራቀቅ ማን ይከለክለኛል –  አሁንም ልድገመውና  By the way የዋሽንግተን ዲሲ አምስተኛው የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን እየመረራቸውም ቢሆን ወያኔዎች ሊያስታውሱት ይገባል – “የሚንቁሽ ዕግርሽ ሥር ወድቀው ይሰግዱልሻል” የተባለችው እምዬ ማርያም ብቻ እንዳልሆነች ልብ ይሏል – ዐማርኛም ገና ምን ዓይታችሁ – ጽላት እስኪቀረጽለት ድረስ በኢትዮጵያ ምድር ከፍ ያለ ሥፍራ ያገኛል – ዐማራ የሚባሉ የወያኔ የዕልቂት ሰለባዎች ከምድረ ገጽ ቢጠፉ እንኳን ዐማርኛ አይጠፋም – በዚህ ላይ ወረድ ብለን ተጨማሪ ነጥቦችን እንመለከታለን፡፡

ይህ ሰው – ደብረጥዮን – በዚህ ድርጊቱ ትግርኛ ተናጋሪውን ማስደሰት ይፈልጋል – ቢያንስ የዋሁን ክፍል፤ ትግርኛ ተናጋሪውን ማስደሰት የሚፈልገው ደግሞ በትግርኛ ፕሮግራም በሚሰራጭ የቴሌቪዥንም ሆነ የሬዲዮ ሥርጭት ሣይሆን ብሔራዊ ሥርጭት የሚካሄድበትን ዋና መስመር በማቋረጥ መሆኑን ያውቃል(ሉ)፤ ጀጋኑ ወዲታት ተጋሩ – ወየንቲ አዲ ትግራይ ኸምዚ’ኢና – ጋና ነርዕዮም ኢና… ይህች ትንሽዬ የዱባ ጥጋብ ከዚህ የምታልፍ መልእክት የላትም – እነዚህን ነፍጠኞች ገና እናሳያቸዋለን እያሉ ይመስላል – እነዚህ ከሙት መንፈስ ጋር ተፋላሚ ዶንኪሾቶች፡፡ በዚህ ሂደት ዐማርኛ ተናጋሪውንና ለጊዜው ማንኛውም ነገር ቢጠበስ ቢገነተር ምንም የማይመስለውን – የማይሞቀውን የማይበርደውን – ከርታታ ዜጋ ብቻ ሣይሆን መላዋን የሀገሪቱን ሕዝብ “ገዢህ እኔ ሕወሓት መሆኔን ሳትወድ በግድህ ዕወቅ፤ ምንም ብታስብ ምን ከኔ በላይ ጌታ ሊኖርህ አትችልም!” የሚል ውስጠ ወይራ መልእክት ለማስተላለፍ የፈለጉ ይመስላል – ቀላል ሰው ከዚህ የሚያልፍ አስተሳሰብ ሊኖረው አይችልምና፡፡ እንጂ ያ በሚሌኒየም ተሰበሰበ የተባለው ሰው ሁሉ ዐማርኛ ቋንቋን አጣርቶ አያውቅም ማለት ማሞ ቂሎን መሆን ነው፡፡ ዐማርኛን እንኳን አዲስ አበቤ ይቅርና እኔም አውቃለሁ ብዬ እንቀባረራለሁ – ከትግራይ ከመጣሁ ከ27 ዓመታት በኋላ፡፡ በአንድ ቋንቋ ውስጥ 50 ዓመትም ኖረህ እኮ ላታውቀውና ላትናገረው ትችላለህ፡፡ የበረከት ስምዖን ወላጆች ጎንደር ውስጥ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ኖረው በዐማርኛ ይቸገሩ እንደነበር በሕይወት ካሉም እንደሚቸገሩ ሰምቻለሁ፡፡

የጀመርኩትን ርዕሰ ጉዳይ በሚመለከት ንግግሩ ሣይሆን ከንግግሩ በስተኋላ ያለው ነገር ነው ለትርጉም ወሳኙ ብዬ ማመን እፈልጋለሁ፡፡ ወያኔ ዐማርኛን አሽቀንጥሮ መጣል ይፈልግ ነበር – ግን አልቻለም – አይችልምም፤ በምን አቅሙ? እየጠላውና እያንገሸገሸውም ቢሆን እስካሁን ለአገዛዙ ተጠቅሞበታል፤ እምትንጠራወዝ እስትንፋሱ ለይቶላት እስክትወጣና ወረደ መቃብር እስኪገባ ድረስም ይጠቀምበታል፡፡ ዐማርኛን ለማጥፋት – ልክ ዐማራ ተብለው የተፈረጁትን ሰዎች ለማጥፋት እንደሞከሩት  – ወያኔዎች ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም – ዐማርኛም ልክ እንደድመት ባለዘጠኝ ነፍስ ሆኖ ግና ክፉኛ ተገዳደራቸው – ሕይወት ያላቸው ተናጋሪዎቹ ሲሸነፉ ግዑዙ ቋንቋ አሸነፋቸውና ሥነ ልቦናዊ የበታችነት ህመማቸውን በየመድረኩ ያዝረከርክባቸውና ለሣቅ ለሥላቅም ይዳርጋቸው ገባ፡፡ ተጋሩ ወንድሞቼንና እህቶቼን የሌሎችን ብሔርና ብሄረሰቦች ስም እየሰጡ፣ ቋንቋቸውንም እንዲማሩ እያደረጉ ብዙ ሥውር ሥራዎችንና ሤራዎችን እንዲሠሩ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ነገር ግን እንደዐማርኛ የመሰለ የመግዣ መሣሪያ ሊያገኙ አልቻሉምና እስካሁን ከመድረክ ሊያገልሉት አልተቻላቸውም – ዐፄ ዮሐንስም በዚሁ መሣሪያ ነው አሉ ጎጃምን፣ ወሎንና ጎንደርን አንቀጥቅጥው የገዙት፡፡ በመሆኑም እየጠሉትም ቢሆን፣ ኦሪጂናል ተናጋሪዎችን እያጠፉም ቢሆን፣ ዐማርኛ መናገርን እንደነውር እንዲቆጠር በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ እየሠሩም ቢሆን፣ የቋንቋው ባለቤት እንደሆነ የሚነገርለትን ማኅበረሰብ እየናቁና እያንቋሸሹም ቢሆን፣ በትዕቢትና ዕብሪት ተወጥረው የነሱን ቋንቋና ባህል በሌሎች ላይ ለመጫን እየተንደፋደፉም ቢሆን …  የዐማርኛ ቋንቋን ግን እንደመሣሪያነቱ ሲጠቀሙበት ባጅተዋል፡፡ ምርጫ ስለሌላቸውም ነው፡፡

ቋንቋ የራሱ ህግ አለው፡፡ ማንም እንደፈለገ በዐዋጅ “ይህ ብሔራዊ ይሁን ፤ ያኛው ግን ከዛሬ ጀምሮ ብሔራዊ አይሁን”ማለት አይቻለውም፡፡ እንዲህ ቢቻል ኖሮ የዛሬዋ ዓለማችን የጋራ መግባቢያ ቋንቋ እንግሊዝኛ መሆኑ ቀርቶ የቻይናውያኑ መንደሪን ቋንቋ በሆነ ነበር፡፡ እንደገናም እንዲህ ቢቻል ኖሮ የኢትዮጵያ የጋራም በሉት የሥራ ቋንቋ ኦሮምኛ በሆነ ነበር – እነዚህ ቋንቋዎች በአፍ መፍቻነት እንደሚናገራቸው የሕዝብ ብዛት ቢሆን ኖሮ በየተገለጹበት አድራሻ ኦፊሴላዊ ቋንቋ ከመሆን የሚያግዳቸው አንድም ነገር ባልነበረ፡፡ የሚያግዳቸው ግን የታጠቀ ጉልበተኛ ወያኔን መሰል ውድብ ሣይሆን የማኅበረ-ኢኮኖሚውን መስተጋብራዊ ትስስር ተከትሎ በዘመን ማሕፀን የሚወለደውና የሚያድገው ሥነ ልሣናዊ ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ እንጂ በቡድኖች ፍላጎት ቢሆንማ ኖሮ የኢትዮጵያ የጋራ ቋንቋ በአሁኑ ወቅት ትግርኛ ከሆነ ቢያንስ 24 ዓመታትን ባስቆጠረ ነበር፡፡ በዶክተር ተብዬዎች የወያኔ አቀንቃኞች የተጻፉ ብዙ ቅዠቶችን አንብቤያለሁ – ለምሣሌ ዐማሮች አናሳ(minority) ጎሣ እንደሆኑ፣ ትግሬው ብዙኃን(majority) እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ትግርኛ እንደሆነ ወዘተ.፡፡

ዐይናችንን እንጨፍንና በተመስጦ ጥቂት እናስብ፡፡ ዐማርኛ ባይኖር ኖሮ አገው ከአደሬው፣ ትግሬው ከቆቱው፣ ከፊቾው ከጉራጌው፣ ኑዌሩ ከሽናሻው፣ ሶማሌው ከኢሣው፣ አፋሩ ከከምባታው፣“ዐማራ”ው ከኦሮሞው፣… በምን ይግባቡ ነበር? ከ80 በላይ ቋንቋዎች በሚነገሩባት ድሃ ሀገር ስንት ብሄራዊ ቋንቋ ማበልጸግ ይቻላል? ከዚህ አኳያ የአፍ መፍቻን ቋንቋን ለአካባቢያዊ አገልግሎት እያዳበሩና እየተገለገሉ ለቅርስነትም እያቆዩ ሁለተኛ ቋንቋን (ተፈጥሯዊ ህግን እስከተከተለ ድረስ ማንኛውም ቢሆን ግዴለኝም) በጋራ ማዳበርና መጠቀም ማንን ይገድላል? በኢትዮዮጵያ ሁኔታና ለኔ እንደሚመስለኝ ይህን የዘመናት የታሪክ ሽመና ያወሳሰበውን ሥነ ልሣናዊ ቁርኝት በ40 ዓመት አይደለም በ400 ዓመትም ቢሆን መበጣጠስ አይቻልም – እርግጥ ነው እዚህና እዚያ በማቆሳሰል የተወሰነ ሰምበርና ጠባሳ ማኖር ይቻል ይሆናል፡፡ አለበለዚያ የኅልውና ጉዳይ ስለሆነ ምድረ ወያኔ ሁላ ጥላቻው እያንዘረዘራትም ቢሆን ዐማርኛዋን እየሰለቀች የአፓርታይድ ሥርዓቷን ትቀጥላለች – የቀብር ሥነ ሥርዓቷ እስኪፈጸም፤ ለነገሩ ዕድር የሌላት ሆና እንጂ ወያኔ እኮ ከሞተች ሰንብታለች – በሕይወት ያለች እየመሰለቻቸው ግን ሰዎች ይፈሯታል – የማይሞት አፏንና የውርድንበር አስደንጋጭ ተግባሯን እያዩ፡፡ ዐማርኛ ቋንቋን በሚመለከት ወያኔ ዕቅዱ ተሣክቶለት ዐማራ የሚላቸውን ወገኖች ከምድረ ገጽ ማጥፋት ቢቻለው እንኳን ዐማርኛን ከጋራ ቋንቋነት አንዲት ጋት እንዲያፈገፍግ ሊያደርገው አይችልም፡፡ ወደሽን ቆማጢት እንዲሉ ነው፡፡ በመሠረቱ ዐማርኛ ብሄራዊ ሆነ አልሆነ ለዐማርኛ ተናጋሪዎች የሚፈይደው ነገር ያለ አይመስለኝም፤ በመንግሥት ደረጃ ከታወጀባቸው የዕልቂት ዐዋጅና ተግባራዊ ማሳደድስ መቼ አስጣላቸው? ቋንቋቸው ብዙኃንን በድልድይነት በማገልገሉ ሳቢያ እንደውለታ ተቆጥሮ ከወያኔ ጭፍጨፋና እንግልት ሊታደጋቸው የሞከረ ማን ነው?

ወያኔዎች እውነተኛ ማንነታቸው ድንገት ብልጭ ሲልባቸው ልክ እንደዛሬው በዐማርኛ ተናጋሪ ኅብረተስበ መካከል – ሳይቸግር ጤፍ ብድር እንዲሉ –  በትግርኛ መቀናጣት ያምራቸዋል – እኔ እንደታዘብኩት ትርፉ ትዝብትና መሣቂያና መሣለቂያ መሆን ነው፡፡ በዚህ ድርጊት ትግርኛ አልከበረም – ዐማርኛም አልተዋረደም፤ የተከበረም ሆነ የተዋረደ ካለ ወያኔ መንደር ውስጥ የሚገኝ ሸውራራና ከፋፋይ አመለካከትና አስተሳሰብ ነው፡፡ በመሠረቱ ቋንቋ እስከዚህ ድረስ ለሥነ ልቦናዊ ቀውስ የሚዳርግ ነገር አይደለም፡፡ ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ እንጂ የበታችነት ስሜት ጭቅቅትን በሰፊው ሕዝብ ላይ ለማራገፍ የሚዳክሩበት አቢይ ጉዳይ አይደለም፡፡ የማይምነት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ብዙኃኑ የሚናገረውንና የሚግባባበትን ቋንቋ አስትቶ ወደጠበበ ዐውደ ልሣን የሚያወርድ ምንም ምክንያት የለም፡፡ እርግጥ ነው – በአሁኑ ወቅት ትግርኛ የገዢው መደብ ቋንቋ መሆኑ በስፋት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ለምሣሌ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ነገ የዳዋሮ ማኅበረሰብ አባል ወደ ሥልጣን ቢመጣ ዳዋሮኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ይሆናል ማለት አይደለም – ሊሆን አይችልም ማለቴ ሣይሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን እውነቱ እንደዚያ አለመሆኑን ለመጠቆም ብዬ ነው፡፡ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ቋንቋ የራሱ ህግና ሥርዓት ያለው እንጂ ገዢዎች እንደፈለጉ የሚዘውሩት እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም ደብረጽዮንና በረከት እንዲሁም ሌሎቹ ወያኔዎች እየዳከሩበት የሚገኙት የኢትዮጵያን ሕዝብ የጋራ ቋንቋ የማጥፋትና ወደቀደመው የባቢሎን ዘመን የመመለስ ዕቅድ እንዲህ በቀላሉ ይሣካላቸዋል ብሎ ማመን የዋህነት ይመስለኛል፡፡ እንደኔ እንዲያውም የተቃጠለ አየር ከሰውነቷ እንዳይወጣ ጥረት አድርጋ ነገር ግን ያልተሣካላት ሴትዮ “ውይ! መንግጌ አባስኩሽ!” እንዳለችው እነዚህ ወያኔዎችም ዐማርኛን ለማጥፋት ባደረጉት ጥረት ይበልጥ ተፈላጊነቱን ሣይጨምሩት የቀሩ አይመስለኝም፡፡ እንዴ፣ ቋንቋ እኮ ከእስክርቢቶና ከወረቀት የማይበልጥ ወይም የማያንስ ተራ የመግባቢያ መሣሪያ ነው እንጂ እስከዚህ ድረስ አቅልን ስተው የሚራኮቱበት ነገር አይደለም – በቃ፣ ተራ ነገር ነው፤ ከዚያ አስበልጦ ማየት በሽታን መግዛት ነው – ልክ እንደወያኔ፡፡ ትግርኛ ተናገርክ ዐማርኛ፣ ጦጥኛ ተናገርክ ዝንጀሮኛ፣ አፋርኛ ተናገርክ ኦሮምኛ ዋናው በመግባቢያ መሣሪያነቱ መጠቀም እንጂ “የኔ”ና “ያንተ”ን ምን አመጣው? ያንተ የሆነ የነሱም ነው፤ የነሱ የሆነም ያንተ፡፡ Why should we really over-politicize languages? Personally, I do not see any difference between ‘my’ language and any of the tools I use in my daily life. Aha! I now vividly remember that Esperanto was a failure due to the selfish motive of humans! Hey, let’s get enlightened, please.

የኢትዮጵያ ሕዝብ የቋንቋም ሆነ የዘር ሐረግ ልዩነት እንደማይበግረው በቅርቡ ያዩታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለመሠሪ ተልዕኮና ለአፍራሽ ውጤት ሣይሆን ለእውነተኛው መግባቢያነት ትግርኛም ሆነ ሌላው ቋንቋ ሁሉ በመገናኛ ብዙኃናችን በተፈለገው ጊዜና በተፈለገው መጠን ሲነገር የሚያዳምጡበት ጊዜ ብዙም ሩቅ አይመስለኝም፡፡ ይህችኛዋ የደብርጽዮኒቷ የሚሌኒየም አዳራሽ ትግርኛ ግን “ኢንቴንሽኗ”(ድብቅ አጀንዳ) ትገባናለችና የ“ሲምፕል ሣይኮሎጂ” ሰለባዎች እንዳንሆንላቸው እንጠንቀቅ፤ ወያኔዎችና ሼሪክ አበጋዞቻቸው ሕዝብን ከሕዝብ ለማቃቃር ብቻ ሣይሆን በለዬለት የሁለትና ሦስት ጎራዎች ውጊያ አሠልፈው ለማጨራረስም የማያቅማሙ አረመኔዎችና ኃላፊነት የጎደላቸው ፍጡራን በመሆናቸው ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን እኛ ሕዝቡ ነን፡፡ ቀላሎች ቀላል ሊያደርጉን አይገባቸውም፡፡ ሤራቸውን ለማክሸፍ ሕዝቡ በቶሎ መንቃት ይኖርበታል፤ በጥቃቅን መደለያዎች – ሆድን በማይሞሉ የወያኔ የማስመሰል ቅራቅንቦዎች መታለል የለብንም – በሚጨበጥ ነገር እንጂ መሬት ባልረገጠ የስሜት ዐውሎ ነፋስ እንዳንነዳ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ከነዚህ አዛኝ ቅቤ አንጓቾች ተንኮል ራሳችንን እንጠብቅ፤ ትግሬውን ያስደሰቱ መስለው ለመታየትና በእግረ መንገድም ስንጥቃቱን ለማስፋት በሚያከናውኗቸው ከፋፋይ ተግባራት ሳንሞኝላቸውና ብዙም ፊት ሳንሰጣቸው በጋራ የጋራ ቤታችን የምትሠራበትን መንገድ እናመቻች፡፡  ትግሬው ወገን የወያኔን ጠባብ ዓላማ ይረዳና ከሰፊው ወገኑ ሊለያየው የሚችልን ይህን መሰል ላይ ላዩን ሲያዩት ምንም ነገር ያልሆነ የሚመስል በጥልቀትና በጥሞና ሲያዩት ግን ሥነ ልቦናዊ መደላድል የረገጠ የከፋፋይነት ሤራ ያለው ተንኮል ተገንዝቦ ተቃውሞውን በግልጽ ማሰማት አለበት፡፡ “የእስካሁኑ መሠሪ አካሄድ ይብቃ” ብሎ እነዚህን የእፉኝት ልጆች ሊታገላቸው ይገባል፡፡ ሌላውም ወገን በዚህ ዓይነት መሠሪ አካሄድ ብዙም ሳይከፋ ለመጨረሻው አርማጌዴዌዎናዊ ድል ይዘጋጅ፡፡ የመጨረሻው መጨረሻ ደወል ሊደወል የቀረው ጊዜ ብዙ ሩቅ አይመስለኝም፡፡ እስከዚያው በያለንበት ሰላም ያቆየን፤ የሀገራችንን ትንሣኤም በቅርብ ያሣየን፤ አሜን፡፡

http://www.zehabesha.com

post tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s