ምን አስተሳሰብ ይሆን ወደ ተግባር የሚያሸጋግር?

ዶ/ር አበባ ፈቃደ

ጥንታዊት ቅድስት ኢትዮጵያ አገራችንን ከገጠማት ብሄራዊ ቀውስና ካንዣበበባት ሕልውናዋን ፈታኝ አደጋ ለመታደግ ምን መደረግ አለበት የሚለው ጥያቄ መመለስ ከመቸውም ግዜ በበለጠ የወቅቱ ዋናና አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑ ለሚመለከተንና ለምንቆረቆር ሁሉ አጠያያቂ አይደለም።TPLF, ወያኔ/የትግሬ ነጻ አውጭ ግንባር

እንደሚታወቀው ሁሉ ወያኔ ከውስጥና ከውጭ ግብረ አበሮቹ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ብሄራዊ ህልውና በማፍረስ፣ የህዝቧን አንድነት በማናጋት፥ ህዝቧን በባርነት ክልል በማጎር፣ አገራዊ ሉዓላዊነት የሌላት ቅኝ ተገዥ አገር ለማደረግ የጀመረውን የጥፋት መንገድ እያፋፋመ ቀጥሏል። አሁንም በህዝብ ላይ ግድያና የዘር ማጥፋትና እልቂት መፈጸም፣ ታዳጊ ልጆችን፥ ወጣቶቾን፥ ሴቶችን በአጠቃላይ የኢትዮጵያውያን የሰውነት ዋጋ ዝቅ በማደረግ በተለያየ መልክ ለዘመናዊ ባርነት ዳርጓል።

ወያኔ የኢትዮጵያን አርሶ አደር ገበሬ በተለይም አማራው ከመሬቱና ከኑሮው በማፈናቀል በአገሩ ውስጥ ተሰዶ፣ በድህነት ማቆ ለባእዳን ቅኝ ተገዥ አገልጋይ ማድረግን በሰፊው ቀጥሏል። ይህም ዕውነታ ለተጠቂው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ የተመዘገበና የታወቀ አሳዛኝ ሃቅ ነው። ስለዚህ የወቅቱ የትግል ጉዳይ ወያኔ በህዝብ ላይ የሚያደርሰውን በደልና ችግር ከማወቅና ከመተንተን አልፎ የችግሩን ምንጭና መንስዔ ማስወገድንና የተሻለ መፍትሄን መሻትን የሚጠይቅ ነው። ስለዚህም ከተለመደው ዘይቤ ወጣ ባለ መልክ መፍተሄ አዘል ውይይት ማካሄድ፤ ተገቢ ጥያቄውችን ማንሳትና መመርመር አስፈላጊ ነው። በተለይም በፖለቲካ መሪዎችና ምሁራን ዙሪያ ለረጅም ጊዜ የተንጸባረቁ አወዛጋቢና አደናጋሪ አስተሳሰቦች መኖራቸው ግልጽ ነው።

መጠያየቅ ያለብንም በብዥታ የጨፈገጉትን የፖለቲካ መርሃ ግብሮችና የትግል ስልቶችን ጥራትና እልባት የሚሰጥ አነሳሽ ውይይት እንዲጭር ነው። አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን የፖለቲካ ጽንሰ ሀሳቦችና አመለካከቶችን በጥልቀት ብንመረምር የትግሉ ሂደት ከሚሽከረከርበት አዙሪትና ከሚዳከርበት የአስተሳሰብ አረንቋ ሊወጣ ይችላል። ምንም እንኳ የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ በፊታችን የተጋረጡትን ወቅታዊ ጉዳዮችን በሙሉ ለመመለስና ለመተንተን ባይሆንም ለተግባር አነሳሻ የሆኑ ተገቢ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚጋብዝ ነው።

ወቅቱ ምን ይመሰላል?

በአሁኑ ወቅት በአገራችን ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ የበለጠ ህዝባዊ እምቅ ኃይልን ወደ ተግባራዊ የለውጥ ኃይል ለመቀየር የሚያስችሉ ነባራዊ ሁኔታዎች በህብረተሰቡ ውስጥ መኖራቸው በልዩ ልዩ መልክ እየተንጸባረቀ ነው። የወያኔ/ትግሬ ነጻ አውጭ ግንባር ኢሰብዓዊና ጸረ ኢትዮጵያዊ የጎሳ ክልል ሥርዓት ወደ ግባተ መሬቱ እያሽቆለቆለ የፍጻሜውን የመጀመሪያ ክፍል እየያዘ መምጣቱን የሚጠቁሙን በርካታ ሁኔታዎች አሉ። አንዱ ምልክት ዛሬ ወያኔ/የትግሬ ነጻ አውጭ ግንባር በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያደርሰው ጥቃትና ጥፋት በገጠጠ መልክ እያፋፋመ መምጣቱ ነው። ወቅቱ ወያኔ በጥላቻና በስግብግብነት የናረው ትዕቢቱ ለማይቀረው ውድቀት እያዘጋጀው መሆኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያመላክታል። የኢትዮጵያ ህዝብም የወያኔን ብልሹ ሥርዓት ለማስወገድ ያለው ቁርጠኝነትና ጽናት ከምንግዜም በበለጠ የአስተሳሰብ እምርታና ለተግባር ዝግጁነት እያገኘ በመምጣት ላይ መሆኑ ሌላው አመላካች ገጽታ ነው።

ኢትዮጵያውያን የወያኔ ፖለቲካዊ ሆነ አስተዳደርዊ ምግባር ጎጂና ጨቋኝ ከመሆን በላይ መነሻ መሰረቱ ጸረ ኢትዮጵያ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ እየተገነዘብን የመጣንበት ወሳኝ ወቅት ነው። በተጨማሪም ይህን ሥርዓት ለማስወገድ በዋናነት ወሳኝ ኃይል ራሳችን መሆናችንና በራስ በመተማመን በውስጣችን ያለውን ኢትዮጵያዊ መንፈስ ይዘን መነሳት መሆኑን በጥልቅ እየተረዳን መጥተናል። ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦናዊ ኃይልና እምነትን ማእከል አድርገን መነሳት የድላችን ዋስትና ለመሆኑ ውስጣዊ እይታ ያገኘንበት የተስፋ ብርሀን መባቻ ላይ እንገኛለን። የወያኔ በውሸትና በጥላቻ የተመሰረተ የፖለቲካ ካብ፣ በኢትዮጵያዊ የነጻነት መንፈስና እውነት እንደሚናድና፣ ብሎም ህዝብ የሚፈልገው የፍትህ ሥርዓት እንደሚመስረት የሚያመላክት ተስፋ በህዘብ ውሰጥ የሰረጸበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

ዛሬ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሉዓላዊነትዋ የተጠበቀ አገር እንዳትሆንና ቀጣይ ህልውናዋን አስጊ ሁኔታ ላያ የጣላት የባእዳንን ጥቅም አስጠባቂ የሆነው የወያኔ የጎሳ ክልል ሥርዓት ስር በመውደቋ ምክንያት መሆኑን በስፋት የታወቀ እውነታ ነው። ወያኔ የተነሳበት ዓላማ መሰረቱ ታሪካዊ ውሸት በመሆኑ ተግባሩን የሚያከናውነው፣ ጥላቻንና ማጭበርበርን ያለ አንዳች ሃፍረት በመጠቀምም ቢሆንም ቀን በቀን እርቃኑን እየወጣ መጥቷል። ሆኖም ኢትዮጵያን ማዳንና ወያኔን የማስወገድን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ ተግባራዊ እርምጃን በተገቢው ጊዜ መውሰድንና አንቀሳቃሽን ሀሳብ በጊዜ በመፍጠር ከወቅቱ ጋር በፍጥነት መራመድን ይጠይቃል። በአሁኑ ጊዜ የምናራምደው ያልጠራ አስተሳሰብና የተደናገረ እርምጃ ወያኔን ማስወገድ የሚችል ጉልበት ሊፈጥር አይችልም፣ እንዳውም ትግሉን የባሰ አቅመ ቢስ ያደርገዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከሚታየው ወቅታዊ ሁኔታ አንደኛው ወያኔ የኢትዮጵያውያን የንቃት ቀልብ ለማሳትና ለማወናበድ የሚጠቀምበት በየአምስት አመቱ የሚያጮኸው ባዶ የምርጫ ቆርቆሮ ነው። አብዛኛው ወያኔን የሚቃወመው ወገን ደግሞ በተለመደው ማቀንቀኛ ነጥቦች ዙሪያ እንደገና ይሽከረከራል፣ በውይይት አረንቋ ውስጥ ባለባት ይረግጣል። ዘወትር ከሚነሱት መወያያና መከራከሪያ ነጥቦች ውስጥ ጥቂቶቹ፣ ህብረት ሰለመፍጠር፤ ሰል ትግል ስልት፣ በጦር ወይ ያለጦር መሳሪያ፣ ትግሉ በምን መርህ ነው የሚመራው? ምርጫውስ ምንድነው? ተቃዋሚው ማነው? ወዘተ ናቸው፣ ከነዚህም መሃል ለውይይት መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ አንድ ሁለቱን ጥያቄዎች በአጭሩ እንመልከታቸው።

ማነው ተቃዋሚ?

ተቃውሞ ማለት አንድ ህዝብ ሆነ ግለሰብ ህልውናውና ደህንነቱን፣ ነጻነቱንና ደስታውን ፤ የተፈጥሮም ሆነ የዜግነት መብቱን የሚጻረርና የሚጎዳ ነገር ሁሉ ሲፈጸምበት አለመቀበል ማለት ነው። በፓለቲካና በማህበራዊ ህይወት በቀላሉ ሲተረጎም ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ ማለት ወያኔና ግብረአበሮቹ በአገር ላይ የጫኑት የጎሰኛ ጨቋኝ ሥርዓት ህዝብንና ሀገራዊ ህልውናን የሚጎዳ በመሆኑ አንቀበለውም፣ እንቃወማለን ማለት ነው። ይህም የተቃውሞ ትግል ኢትዮጵያዊነትን በመደገፍ እና ጸረ ኢትዮጵያዊነትን በመቃወም ላይ ያማከለ ነው። ስለዚህም መቃወም ሲባል ምንንና ለምን ብሎ መጠየቅ ዓላማና ግብን የሚያስማማ እይታና አቋም እንዲኖረን ይርዳል። ማነው ተቃዋሚ፣ ለምንስ ግብ በተቃዋሚነት ተስልፏል ብሎ መመርመርም የጋራ ግብን፣ የትግል አሰላለፍ እንዲሁም የድርጅቶችን የትብብርና የህብረትን ሂደት በተመለከታ ጠቃሚና ወሳኝ ግንዛቤን ያስጨብጣል።

የወያኔ/ትግሬ ነጻ አውጪ ግንባር የፖለቲካ መርህና ዓላማ የኢትዮጵያን ነጻ አገራዊ ግዛታዊ ሉዓላዊነት፣ የህዝቧን አንድነትና ብሄራዊ ህልውናን የደፈረና የሚቀናቀን ነው። ኢትዮጵያዊ መለያ ቅርሶች፣ ተቋሞችና፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መሰረት የሆኑትን የማህበረሰብ አካላትን የሚያዳክምና የሚያፈርስ ኃይል በመሆኑ ይህን የሚቃወም የተቃዋሚ ወገን አለ። ይህ የተቃዋሚ ረድፍ ኢትዮጵያዊነትን ማእከል ያደረገ ብሄራዊ አንድነትን የሚያቀነቅን አገራዊ ህልውና ለድርድር አይቀርብም፣ በአገር ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ችግር ኢትዮጵያንና ህዝቧን በማያጠፋ መንገድ ፖለቲካዊ ማህበራዊ ፍትሀዊ መፍትሄ ማግኘት እንደሚቻል የሚያምንና የሚታገል የተቃዋሚ ክፍል ነው። ይህ ተቃዋሚ ኃይል በአብዛኛው ያልተደራጀው ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብን ስሜትን ያንጸባርቃል፣ አገር ወዳድ ምሁራን፣ ጥቂት ድርጅቶችንና ሰብስቦችን ያጠቃልላል።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ አገራዊ ሉዓላዊነት፣ በብሄራዊ ህልውናና፣ በህዝቧ አንድነት ላይ ቅድመ ሁኔታ የሚያስቅምጥ ሆነ ለድርድር የሚያቀርብ፣ ጎሳዊነትና አገራዊ ስሜትንና ዋጋን በእኩል ደረጃ ወይም በተቀናቃኝነት የሚመለከት የተቃዋሚ ረደፍ ነው። ይህ የተቃዋሚ ክፍል ምንም እንኳ ለይስሙላ በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን ቢሉም አገራዊ ይዘት ያላት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከጎሳና ከቋንቋ ማህበረሰብ ለይቶ ማየት ይሳነዋል፤ የማንነት ስሜትን በተመለከተ ጎሳን ከአገር የሚያስቀድም የተቃዋሚ ክፍል ነው። ይህም ቡድን አሁን ያለውን ወያኔን መቃወም ላይ ብቸኛ ትኩረት ይደረግ በሚል ሽፋን ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮችን አድብስብሶ ኢትዮጵያዊነትን የሚጻረር ጽንሰ ሃስብን በውስጡ አዝሎ የሚጓዝ የተቃዋሚ ሰብስብ ነው።

ሌላው የተቃዋሚ ዘርፍ ከወያኔ መሰረታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና ፍልስፍና ጋር የማይታረቅ ተጻጻሪ ልዩነት የለውም። የወያኔን የፖለቲካ ፍልስፍናን ይጋራል። ጥቂቶችም የወያኔ አካል የነበሩ በይዘት ሳይሆን በመልክ ብቻ የተለዩ፤ በተለያየ ደረጃ ከወያኔ ጋር አብረው ጸረ ኢትዮጵያ ተግባሮችን የፈጸሙ ግለሰቦችና ስብስቦችን የሚያካትት ተቃዋሚ ረድፍ ነው። ይህ የተቃዋሚ ዘርፍ ከወያኔ ጋር ያለው ልዩነት በወያኔ የፖለቲካ ፕሮግራም መሰረታዊ ሀሳብ ላይ ሳይሆን በመለስተኛ አስተዳዳራዊ ልዩነቶችና የግል የሥልጣንና የጥቅማጥቅም ቅራኔወች ላይ የተመሰረተ ነው። በተጨማሪም በወያኔ ምንነትና ማንነት ላይ የተዛባና የተለሳለሰ አመለካከት ያለውና፣ ወያኔ በየጊዜው እንደ ድሪቶ እየለጣጠፈ የሚፈጥራቸውን ተቃዋሚ ተብየ ድርጅቶችን፣ ያካትታል። እነዚህም በአብዛኛው በወያኔ ፓርላማ ውስጥ አባል ከመሆን ሌላ መሰረታዊ የህዝብ ጥቅም ማስፈጸም የማይችሉ፤ በጎሳ ማንነት ላይ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱትንና፣ በፖለቲካ የዋህነትና ግንዛቤ ማነስ ምክንያት በወያኔ በጎ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ናቸው።

በአጠቃላይ በርካታ የተቃዋሚ ክፍሎች አንኳር በሆኑ የመርህ ጉዳዮች ላይ ግልጽ አቋምና አሰላለፍ ይዘው የተደራጁ ስላልሆኑ፣ መነሻ መሰረታቸውና መድረሻ ግባቸው የማይጣጣም የተዘበራረቀ የትግል ስልት ላይ ተመስርተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። በሌላ አባባል የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅና የማያስጠብቅ (አጥፊና ጠፊ) በአንድ ላይ ተቀናጅቶ ለመታገል የሚደረገውን ተደጋጋሚ ሙከራን ይመለከታል። ይህም አላሻቂ፤ ፍሬ ቢስ ጉዞ መሆኑን ላለፉት 24 አመታት ተመልክተናል፤ በአንድ ሃሳብና በአንድ ልብ ላይ መሰረት ያደረገ ተግባር እንዳይፈጠር ካደረጉት ነገሮች መካከል አንደኛውና ዋናው ይህ ሂደት ነው። ወያኔን የተቃወመ ወይም የጠላ ሁሉ የኢትዮጵያ ደጋፊ ወይም ወዳጅ ነው ማለት አይደለም። ስለዚህም ዛሬ ካለንበት ሁኔታ አንጻር ተቃዋሚው ማነው? ምንድነው የሚቃወመው? ምርጫውስ ምንድነው? ብለን በጥሞና ብንመረምር፤ ተቃዋሚዎች የቆሙበት መሰረታዊ ሃሳብና የመታገያ መርሆዎች ላይ የበለጠ ግንዛቤና የተሻለ አማራጭና ተግባራዊ መንገዶችን እንድናገኝ ይረዳናል።

ምርጫውስ ምንድነው?

የሰው ልጅ የጋራ ሆነ የግል ህይወቱን የሚመራውና የሚያከናውነው፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ከፉውን ከደጉ፣ የሚፈልገውን ከማይፈልገው፣ መካከል አንዱን ከአንዱ በመምረጥ ነው። በኑሮ ሂደት ውስጥ ማንኛውንም ነገር አውቅንም ሆነ ሳናስተውል ያለምርጫ የምንሰራው አንዳችም ነገር የለም። መምረጥ ወይም ምርጫ የሚለው ተግባረ ሃሳብ በጥቅሉ ሰውን ከሌሎች ፍጡሮች ሁሉ ልዩ ከሚያሰኙት አእምሮው የሚያመነጨው ሥነ ልቦናዊ ባህሪያት ዋናውና አንደኛው ነው። ምርጫ የተፈጥሮ ሕግና ባህሪ ቢሆንም፤ ለምን? እንዴት? ምንን መምረጥ የሚለው ግን ጊዜና ቦታ የፈጠራቸው በሰው ልጅ የዘወትር ነባራዊ ሁኔታዎች የሚወሰን ይሆናል።

ወያኔ/የትግሪ ነጻ አውጭ ግንባር የተነሳበት ዓላማ መሰረቱ ውሸት በመሆኑ የቀን ተቀን ተግባሩም የሚያከናወነው፣ ሃሰትን፣ ማጭበርበርን ያለ አንዳች ሃፍረት በመጠቀም ነው። ከነዚህም ውስጥ አንዱ እውነትን ለመሸፈን የሚጠቀመበት ይኸው የይስሙላ ምርጫ ነው። እንዳለፉት ምርጫወች ሁሉ የዘንድሮ የወያኔ ምርጫም ይህንኑ ሥርዓት የማገልገያ ሂደት ነው፤ የህዝብን አእምሮ ለመስለብና ህሊናን ለማጉደፍ የሚገለገልበት ዘዴም ነው። ሆኖም ግን ለወያኔ ትእይንት ተዋናኝ በመሆን በመቃወም ሆነ በመደገፋ ጉልበትን ከማባከን ይልቅ የህዝቡን እውነተኛ ምርጫ እውን ሊያደርግ የሚችል በኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ መንገድ መቀየስ አስፈላጊ አማራጭ ሊሆን ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 24 አመታት እንዳሳየው አሁንም ወያኔ ካቀረበው ምርጫ ውስጥ የሚያማርጠው ነገር ስለሌለው አለመምረጥን ምርጫው ሊያደርግ ይገባል።

በውድም ሆነ በግድ የሚሳተፉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ይህን የቧልት ምርጫ ወደ የእውነት ምርጫ ለመቀየር የሚያስችል ኃይልና አቅም ካላቸው በምርጫው መሳተፉ አይከፋም ነበር፣ ሆኖም ግን የተቃዋሚ አቅምን በተመለከተ ወቅታዊው ተጨባጭ እውነታው ከዚህ የራቀ ነው። ስለዚህ የትግሉ ተግባራዊ ቅደም ተከተልና ወደፊት ህዝባዊ ኃይልን ለመገንባት እንዲቻል፣ በወያኔ የግፍ አሰራርና አፈና አቅም ቢስ የተደረጉት ተቃዋሚ ድርጅቶች መጀመሪያ ከህዝቡ ጋር በመቆራኘት አቅም ማዳበሩ ላይ ማተኩር የተሻለ ምርጫ ሊሆን ይገባል። እውነተኛ የመምረጥ ሆነ የመመረጥ ኃይል የሚመነጨው ከህዝብ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በእርግጥ ምርጫ አለው፣ ይህም ወያኔን አለመምረጥ ነው።

የትግሉ መሪዎችና ምሁራን

በፊታችን የተደቀኑትን ወቅታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በተለይ ምሁራንና ሊሂቃኑ፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ታጋዮችና በአጠቃላይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከተለመደው አካሄድ ለየት ባለ መንገድ የጋራ አስተሳሰብን የሚፈጥር ተጨባጭና አሸጋጋሪ ውይይት ማካሄድ ቀዳሚነት ያለው ተግባራችን ሊሆን ይገባል። ውይይቱም በቅድሚያ በመሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦችና የፖለቲካ እይታዎች ላይ ያተኮረ፤ በተግባር የሚተረጎም የነጠረ መርህና ሀሳብ ላይ የተመሰረተ የትግል መሳሪያ መቅረጽ የሚያስችል መሆን ይኖርበታል። ይህም የጠለቀና የሰላ ሀሳብ የተወሳሰበ አገራዊ ችግርን የመፍታትና የተቆላመመውን የትግል መንገድ ለማቃናት የሚያስችል የኃይል ምንጭ ይሆናል፣ አንቀሳቃሽ ራእይና የዓላማ ጽናትንም ይወልዳል። ይህን አስተሳሰብን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችለውና የሚጠበቅበት የምሁሩንና ሊሂቃኑ ክፍል መሆኑ ቢታወቅም ጥያቄው ይህን ኃላፊነት በአግባቡ ተውጥቷል ወይ፤ ካልሆነስ ምንድነው ምክንያቱ? ነው።

የዘመናዊ ትምህርት ወደአገራችን በምዕራብያውያን በኩል የገባው ኢትዮጵያ ከሚደርስባት ተደጋጋሚ ጥቃትና ሌሎችንም ችግሮች ለመወጣት ይረዳታል ብሎ በማሰብ ነበር። ሆኖም ግን በተደጋጋሚ ሊገዟትና ሊያንበረክኳት የሚፈልጉት የውጭ ኃይሎች በተለይም ምዕራባውያን ይህን ያገኙትን አጋጣሚ ለስውር ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ትምህርተ ስርዓቱን ተጠቀመውበታል። ምንም እንኳ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ባይሆንም ወደፊት የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ያስከተለውን ጥቅምና ጉዳት ሰፊ ጥናትና ምርምር እንደሚያስፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። በዘመናዊ ትምህርት አማካኝነት ያልተመረመረ እንዲሁ በግርድፉ የገባው የምዕራባውያን ፍልስፍና አስተሳሰብንና እምነትን ስለነበረ ለዛሬ አገራዊ ውድቀት ከፍተኛ አስተዋጽዎ አድርጓል፤ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ ማንነትና ምንነት ትክክለኛና የተሟላ እውቀት የሌለው የተማረ ማህበረሰብን ፈጥሯል። በዚህ መልክ የተማረ ከፍል ደግሞ ለማንኛውም ተጽኖና፣ ባህላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ምቹ ይሆናል። በጎደለው ቦታ ጽንፍኛ፣ ጸረ የራስ ማንነትና የተዛባ ኢትዮጵያዊነት ይተካል። ለምሳሌ አሁን ለደርስንበት የፖለቲካ ቀውስ ማዕከል የሆነው አንደኛው የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ በሚል ሽፋን የተጠነሰሰው የውሸት የኢትዮጵያ ታሪክ የዚህ ውዝግብ ውጤት ነው። በኢትዮጵያዊነት ላይ የንቀትና የራስ ጥላቻ አስተሳሰብ ሰርጎ የገባው በዚሁ በምዕራብያውያን ዘመናዊ ትምህርትና አመለካከት አማካኝነት ነው። በተለይ ሙሉ በሙሉ ለጥፋት መሳሪ የሆነው፣ በጸረ ኢትዮጵያና ጸር አንድነት፣ በብሄረሰብና ጎሳዊ አስተሳሰብ የታነጸውና በተገንጣይነት የተሰለፈው ምሁር ነው። ይህ የተማረ ክፍል የባእዳንን የረጅም ጊዜ ፍላጎትና ጥቅም አስከባሪ የሆነው አሁን በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተፈናጠጠው ወያኔና ተመሳሳይ አስተሳሳብ ያላቸው ተባባሪ ምሁራንን ይጨምራል። ሌላው ለረጅም ጊዜ በአገራችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ ያላስተዋለውና የተዘናጋው ሆኖም የኢትዮጵያዊ ብሄራዊ ስሜቱ ጨርሶ ያልተሟጠጠበት አገር ወዳድ ምሁሩ ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ የሚገኘው ደግሞ በመሃል የሚዋልለው ምሁራዊ ባህሪያትን የተራቆተው በራሱ ሚና ላይ ገለልተኛ የሆነው ሆድ አደሩን ምሁር ይጨምራል።

አንድ ምሁር ዝንባሌውና ታማኝነቱ ለአስተሳሰብ፣ ለጥበብና ለዕውቀት ነው። ህብረተሰቡን ከችግር መንጥቆ ለማውጣት የሚሰራና የማይሰራውን መሳሪያ በመለየት ለለውጥ የሚያመቹ ሁኔታዎች ይፈጥራል፤ ጊዜና ቅድም ተከተል ጠቃሚነትን ላይ ሙሉ ግንዛቤ አለው። እውነተኛ ምሁር የመመርመርና የመፈተሽ ችሎታ ያለው፣ ለሌላው የማይታየውን ማየት የሚችል የህብረተሰብ ክፍል ስለሆነ ኢትዮጵያዊ አጀንዳንና አመለካከትን ቀርጾ የመስጠት ኃላፊነት ይጠበቅበታል። ባጠቃላይ ምሁር ያለፈ ታሪክ ላይ መሰራታዊ ዕውቀት ያለው፣ የዛሪውን በትክክል የተገነዘበ፣ የወደፊቱን አቅጣጫ የሚያመላክት ችሎታ አለው ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ በቀጥተኛነት እውነትን ከዕውቀት ጋር፣ ታሪክን ከተጨባጥ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማቀነባበር ለጋራ መፍትሄ የሚሆኑ ሃሳቦችን በነጻነት በማፍለቅ ለአገር እና ለህዝብ ጠቃሚ ተግባሮችን ያከናውናል። አገር ወዳድ ምሁር ህዝብን ወደፊት ከሚመጡ ስውር ጥቃቶች ይከላከላል፣ ጠላት ወይም ተቀናቃኝ ኃይል የፈጠረውን መንገድ እንደ አማራጭ ተቀብሎ መሄድ ተሸናፈነትን እንደሚያስከትል ይጠቁማል፣ በሀሳብ ይመራል። ምርጫ በሌለበት ቦታ አማራጮችንና የሚቻሉ መንገዶችን ይፈጥራል። ሆኖም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህ አይነት የምሁር ክፍል ለጊዜው በቁጥር አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአቅምና በጥንካሬ የሚገባውን ሁሉ ለማድረግ ብዙ ውጣ ውረዶች ይጠብቁታል።

እና ምን ይደረግ?

ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታም ባልደበዘዘ ራስን ማእከል ባደረገ መነጸር ማየት ለሂደትም ለመጨረሻ ውጤትም መሰረት ነው። ስለዚህም በውስጣችን ያለው የታመቀ የለውጥ ኃይል እውን የሚሆነው ወደ አዲስ ምእራፍ የሚያሸጋግር እውነትንና እውቀትን መሰረት ያደረገ ተግባራዊ መልስ ለጥያቄዎቻችን ስንሰጥና፤ የተቆላለፉና የጓጎሉ ሃሳቦች ሲፍታቱ ነው። ይህ ደግሞ የሚሳካው በተዝረከረከ፣ ትኩረት የለሽ በሆነ ዋና ጉዳዮችን ነካክቶና ሸፋፍኖ በሚያልፍ የውይይት ባህል አማካኝነት አይደለም። ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ለምሳሌ ተሸፋፍነው ከሚታለፉት ብዙ ጉዳዮችና ጥያቄዎች ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ፣ ከየት ተነስተን የት እንደምንደርስ አቅጣጫ ሰጭ ጠቋሚ የመድረሻ ሃሳብ በግልጽ አለመኖሩ አንደኛው ነው። ወያኔን የምናስወግደው በሌላ ወያኔን መሰል፣ ጸረ ኢትዮጵያ መንፈስ ባለው ኃይል ለመተካት አይደለም። ወያኔ ላይ ብቻ እናተኩር በሚል አባባል አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተፈላጊውን ትኩረት እንዳንሰጥ ያደርገናል። ስለዚህ በአገር ህልውና ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች መሰረታዊ ናቸውና ከወዲሁ የትግሉን አላማና ግብ ማወቅ የግድ ነው (ደርግ ይውደቅ እንጂ ሁሉ አልጋ ባልጋ ነው ያሉን፣ ይኸው ለዛሬ ውድቀት አድርሶናል፣ መደገም ግን የለበትም)።

የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችና እንዲሁም በተማረው ክፍል በሚታየው የማሰብ ስንፍናና ንዝህላልነት ምክንያት ጭቆናን የሚያላምዱ ንግግሮች፣ አእምሮን የሚሰልቡ ዘይቤዎች እንደ ዋዛ በግልጽና በስውር በማወቅና ባለማወቅ እንዲስፋፋ እያደረግን ነው። በድብስብስ ሁሉም በየፊናው በሚችለው ከሚፈለገው ጋር ይታገል፣ ሁሉም ጠጠር ይወርውር፣ የተቃዋሚ ተቃዋሚ አንሁን፣ ከሰይጣንም ጋር ቢሆን መተባበር (የሰይጣን ባህሪ አጥፊ እንጂ አልሚ ስላልሆን የተባበረውንም መልሶ እንደሚያጠፋ አልተገነዘብንም ማለት ነው)አማራጭ የለንም ወዘተ የሚሉት አስተሳሰቦች የትግሉ መሪ ሃሳብ መሆናቸው ያሳስባል፣ ያሰጋል። ከላይ ላዩ ሲታዩ ጉዳት የሌላቸው ቢመስሉም ተቃዋሚውንና ትግሉን አደናጋሪ አሰላለፍና ስልትን እንዲከተል ያደርጋሉ፣ አድርገዋልም። አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች የሃሳብና የአቅጣጫ ጥራትን በተመለከተ ለሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ከመስጠትና ራስን ከመፈተሽ ይልቅ በሆይ ሆይታና በጫጫታ፣ በተዋከበ ጭፍን የቡድን ደጋፊና ተቃውሚነት ጎራ ዙሪያ በመመደብ የጋራ አገራዊ ጉዳይን በጠባቡ ይወስኑታል። ይህም በመሆኑ ትግላችንን የሚያሰምር የሚያጠነክርና የበሰለ ውይይት እንዳናደርግ ከማስተጓጎሉም ባሻገር አዲስና የተለየ ሃሳብን በተቀናቃኝነትና በጠላትነት በማየት እንድንፈራረጅ ያደርገናል። የዚህ አይነት ምሁራዊ የፖለቲካ ሂደት ከአወንታዊው አሉታዊው አስተዋጽዎ እንዳመዘነ ዛሬ አገራችን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ይመሰክራል። ይህንን ሁኔታም መቀየር የሚችለው፣ ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳትና በመመለስ አሸጋጋሪ ድልድይና የትግሉ ቁልፍ አካል አገር ወዳድ ምሁሩ ነው።

ስለዚህ የታመቀ የለውጥ ኃይል እውን የሚሆነው ወደ አዲስ ምእራፍ የሚያሸጋግር ዕውነትን፣እውቀትንና ጽናትን አቀናጅቶ በሚጓዘው አገር ወዳድ ምሁሩ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚደረገው አጠቃላይ አገር አድን ትግል ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሲካተት ነው። ይህም ኢትዮጵያውያንን በማይከፋፍል መንገድ በኃይማኖት፣ በጎሳ ወዘተ በመሳሰሉ ማንነቶች ዙሪያ ባላጠነጠነ አገራዊ የፖለቲካ አደረጃጀት በአንድነት ማህበራዊ አቅሙን አካቶ ሲነሳ ነው። የወቅቱም ጥሪ ወያኔን መቃወም ብቻ በቂ አለመሆኑን የተገነዘበ፣ በራሱ የተማመነ አገራዊ ኃይሎችን አስተባብሮ የሚንቀሳቀስ፣ ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ያደረገ የነጻነት ንቅናቄን መመስረት፣ ማጠናከርና ማስፋፋት ነው። የማይቻል ነገር እንደሌለ የተገነዘበ ኢትዮጵያዊ ልበ ሙሉነት ይኖረዋል። ማህተመ ጋንዲ የእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝን ለማንበርከክ እንዴት ይቻልሃል ተብለው ሲጠየቁ፣ አቅምና ኃይል ለጊዜው ባይኖረንም እንችላለን ብለን ካመን አቅምና ኃይል ማግኝት አይሳነንም (“if I have the belief that I can do it, I shall surely acquire the capacity to do it even if I may not have it at the beginning” Gandhi) ብለው ነበር መልስ የሰጡት። እንዳሉትም የእንግሊዝን ቅኝ ግዛት አንበረከኩ። ዛሬ እኛም በማንኛውም መንገድ ታግለን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ድል የማናደርግበት ምንም ምክንያት የለም። ያአሸናፊነት እምነትን በህሊና ውስጥ መያዝ ለድል የሚያበቃ አንደኛው አስተማማኝ መንገድ መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው። ምን ይደረግ ለሚለው ጥያቄ የበርካት አገር ወዳድ መልስ ለኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት ንቅናቄ በአንድ ልብ ኃይልን አካቶ መነሳት መሆኑ ይንጸባረቃል። ስለዚህም ወያኔ/ የትግሬ ነጻ አውጫ ግንባር በአገርና በህዝብ ላይ የሚያደርሰው ሁለገብ ጥቃት ስለሆነ፣ ይህን አደጋ የሚመክት ተመጣጣኝ ሁለገብ ትግል በተገቢው ጊዜና ቦታ ማራመድ ወሳኝ ተግባር ነው።

በተጨማሪም የሰው ልጅ አካላዊ ህይወት ብቻ ያለው ፍጡር ሳይሆን መንፈሳዊና የማይታዩ ረቂቃን ኃይሎች ያሉት ተፈጣሪ ብቻ ሳይሆን የመፍጠር ኃይልና ችሎታ በወስጡ ያዘለ መሆኑን የሰው አዕምሮ የደረስንበት ንቃተ ህሊናና የምንኖርበት የዓለም ሥልጣኔ ምስክር ነው። ስለዚህ እኛም በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርን በመሆናችን፣ እስከዛሬ የኖርንበትን እውነታና ዓለማችንን እንደፈጠርን ሁሉ የወደፊቱንም መፍጠር እንችላለን። ይህ የሚሆነው ግን በመጀመሪያ ራስን በማወቅና በራሳችን ላይ ስንተማመን ነው። ራሳችን ስናውቅ የማንነት ዕውነተኛነትን እናገኛለን፣ ይህ እውነት በውስጣችን ሲሰርጽ ፍርሃትን እናሸንፋለን፤ ያን ጊዜ ነጻነት፣ ደስታና ሁለንተናዊ እድገትንም መጎናጸፍ እንችላለን። ጥንታዊ ጠቢባን የእውቀት ሁሉ መሠረት መጀመሪያ ራስን ማወቅ ነው ይላሉ። ምናልባት ይህን አባባልን ከተግባርና እምነት ጋር ብናዋህደው ወደ ተፈላጊው ተግባር ያሸጋግረን ይሆን? በእኔ በኩል በእርግጥ

http://www.ethiopiazare.com

post tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s