አርበኞች ግንቦት7 – ህዳሴም ሆነ ዉዳሴ ክህዝብ የሚደበቅ ምንም ነገር የለም!

Patriotic Ginbot 7 Movement for Unity and Democracyከሰሞኑ አገራችን ኢትዮጵያን በተለይም ብሄራዊ ጥቅሟንና ደህንነቷን በተመለከተ ሁለት አቢይ ዜናዎች የአገራቸን የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ጉዳዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸዉን አገሮች የአየር ሞገደች ተቆጣጥረዉት ነበር። ከእነዚህ ዜናዎች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብፅ የህዳሴዉን ግድብ አስመልክቶ ስምምነት ላይ ደረሱ የሚል ዜና ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ አለም አቀፍ ጋዜጠኞች የህዳሴዉ ግድብ የሚሰራበት ቦታ ድረስ ሄደዉ ባካሄዱት ጥናት መሠረት የህዳሴዉ ግድብ ፕሮጀክት ባጋጠመዉ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት የተነሳ እንዲዘገይ መወሰኑን የሚያወሳ ዜና ነዉ። አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚሰሩ ምንም አይነት ስራዎችና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ከየትኛዉም አገር መንግስትና መንግስታዊ ካልሆነ ተቋም ጋር ለሚደረጉ ስምምነቶችና ዉሎች ሁሉ ባለቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ነዉ ብሎ ያምናል፤ ስለሆነም አርበኞች ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያን ህዝብ ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ከሚመለከቱና በሚስጢር መጠበቅ አለባቸዉ ተብሎ ከሚታመኑ አንዳንድ ጉዳዮች ዉጭ ሌላ ምንም ስራ ወይም አለም አቀፍ ስምምነትና ዉል የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያዉቀዉና ሳይሰማዉ በድብቅ መደረግ የለበትም የሚል የጸና እምነት አለዉ። ሆኖም ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ አገዛዝ ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዢዎች በከፋ መልኩ የሚገዛ የጥቁር ፋሺስቶች አገዛዝ በመሆኑ የሚሰራቸዉ ስራዎችና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚፈርማቸዉ ዉሎችና ስምምነቶች የኢትዮጵያን ህዝብ ብሄራዊ ጥቅም የሚጻረሩና የሚጋፉ ድብቅ ስምምነቶች ናቸዉ።

ይህ የወያኔ መሪዎች ከኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ላይ ተሸሽገዉ የሚሸርቡት የድብብቆሽ ሴራ ዛሬ የተጀመረ አዲስ ክስተት አይደለም። ባለራዕዩ መሪ የሚል አላስፈላጊ የቅጽል ስም የተሰጠዉ መለስ ዜናዊ በ2004 ዓም ሐምሌ ላይ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ዜናዉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የተነገረዉ በነኀሴ ወር ማለቂያ ላይ ነበር እሱም ቢሆን ሞትን ያክል ነገር ደብቆ ማቆየት ስለማይቻል ነዉ እንጂ አይነግሩንም ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በሰሜናዊዉ የአገራችን ከፍል ወያኔ ከጎረቤት አገር ጋር የተዋዋለዉ መሬት ቆርሶ የመስጠት ዉል የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያዉቀዉና ሳይሰማዉ የተደረገ ዉል ወይም ስምምነት ነዉ።

አርበኞች ግንቦት ሰባት አገራችን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ብቻ ሳይሆን ከግዛቷ ተነስተዉ ወደ ጎረቤት አገሮች በሚፈሱ አለም አቀፍ ወንዞቿና በሌሎችም የአገር ዉስጥ ወንዞቿ ላይ ግደብ የመስራት ማንም ሊጋፋዉ የማይገባ የተፈጥሮ መብት አላት ብሎ ያምናል። በሌላ በኩል ደግሞ አባይን በመሳሰሉ ድንበር ዘለል ወንዞች ላይ የሚሰሩ ምንም አይነት የልማት ፕሮጀክቶች በዛቻና በማንአለብኝነት ሳይሆን በመግባባት፤ በመመካከርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በሚያዳብሩ መልኩ መሰራት አለባቸዉ ብሎም ያምናል። አርበኞች ግንቦት ሰባት ይህንን የሚለዉ ደግሞ መሠረታዊ ኑሯቸዉ በአባይ ወንዝ ላይ አገሮች ሊያደርሱ የሚችሉትን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ጫና በመፍራት ሳይሆን ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸዉ በፊት ፕሮጀክቶቹን አስመልክቶ ሊነሱ የሚችሉ ዋና ዋና ልዩነቶች መወገድ አለባቸዉ፤ ልዩነቶችን ለማስወገድ ደግሞ የተሻለና አዋጭ የሆነዉ አማራጭ ዲፕሎማሲ ነዉ የሚል ጽኑ አምነት ስላለን በቻ ነዉ።

የወያኔ አገዛዝ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በ2011 ዓም የህዳሴዉን ግድብ ስራ ሲጀምር ከአራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ወይም 96 ቢሊዮን ብር በላይ የተገመተዉ ግዙፍ ግድብ ስራ ሙሉ በሙሉ ከአገር ዉስጥ የገንዘብ ምንጮች በሚገኝ ገንዘብ እንደሚሰራና አገዛዙ ግድቡንና የግድቡን ስራ አስመልክቶ ምንም አይነት ድርድር ከማንም አገር ጋር እንደማያደርግ ለለህዝብ ቃል ገብቶ ነበር። የግድቡ ስራ በተጀመረ በጥቂት አመታት ዉስጥ የግድቡ ግንባታ የአገሪቱን የካፒታል ጥሪት ሙጢጥ አድርጎ በመብላቱና በሌሎች በተጀመሩና ሊጀመሩ በእቅድ በተያዙ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በግልጽ የሚታይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማድረግ በመጀመሩ አለም ባንክ፤ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና አያሌ ኢትዮጵያዉያን ምሁራን የግድቡ ስራና ግድቡ ላይ የሚፈሰዉ የካፒታል ብዛት እንደገና እንዲታሰብበት ምክር ለግሰዉ ነበር፤ ሆኖም ምክሩ የተሰጠዉ የሚሰማ ጆሮ ለሌለዉ ለወያኔ ነበርና ሰሚ ታጣ። ዛሬ ግድቡ ከተጀመረና ወያኔም በህዳሴዉ ግድብ ላይ ከምንም ከማንም አልደራደርም ካለ ከአራት አመታት በኋላ አንደኛ የግድቡ ፕሮጀክት ስራ በገንዘብ እጥረት የተነሳ እንዲዘገይ ተደርጓል፤ ሁለተኛ ወያኔ የህዳሴዉን ገድብ አስመልክቶ ከግብፅና ከሱዳን መንግስታት ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ የፊታችን መጋቢት 14 ቀን ስምምነቱን ለመፈረም ጎንበስ ቀና እያለ ነዉ።

ለመሆኑ ይህ ወያኔ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር የህዳሴዉን ግድብ አስመልክቶ የሚፈራረመዉ የስምምነት ዉሳኔ ይዘት ምንድነዉ? ዉሳኔዉ በሦስቱ አገር መሪዎች ፊርማ ከመፅደቁ በፊት ለምንድነዉ የዉሳኔዉ ባለቤት የሆነዉ የኢትዮጳያ ህዝብ እንዲያዉቀዉ ያልተደረገዉ? ባለፉት አራት አመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ ምንም አይነት ገቢ ከሌላቸዉ ከተማሪዎችና ከአረጋዉያን ጀምሮ እስከ ቀን ሰራተኛዉ ድረስ ለህዳሴዉ ግድብ ግንባታ ገንዘብ አዋጣ ወይም ቦንድ ግዛ እየተባለ በሩ ያልተንኳኳ ኢትዮጵያዊ የለም። ታዲያ ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ገንዘብ ለዕድገቴና ለብልፅግናዬ መሠረት ይሆነኛል ብሎ የሚያሰራዉ ግድብ ስራዉ በገንዘብ እጥረት ሲተጓጎልና በዚሁ ግድብ ዙሪያ ከዉጭ መንግስታት ጋር አለም አቀፍ ስምምነቶች ሲደረጉ ምንም የማይነገረዉ ለምንድነዉ?

የወያኔ መሪዎች ከሱዳንና ከግብጽ መሪዎች ጋር የህዳሴዉን ግድብ አስመልክቶ የተዋዋሉትን ዉል እንመራዋለን ብለዉ ከሚናገሩት ህዝብ ቢደብቁም ካርቱምና ካይሮ ወስጥ ሾልከዉ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግብፅ የህዳሴዉ ግደብ ፕሮጀክት ላይ የቁጥጥርና የማነጅመንት ድርሻ አንደሚኖራት እየተነገረ ነዉ። እንደዚህ አይነቶቹ ከዚህ ቀደም በፍጹም የማይሞከሩ ወይም የማይታሰቡ ናቸዉ ተብለዉ ሲነገሩ የነበሩ ስምምነቶችና ዉሎች ዛሬ ተደርገዉና የሶስትዮሽ ስምምነት ተደርሶባቸዉ በፊርማ የሚጸድቁት ግድቡን ሰርቶ ለመጨረስ የሚያስፈልግ ገንዘብ ለማግኘት ነዉ ወይስ ሌላ ድብቅ አላማ አለዉ? ደግሞስ ግድቡ የሚሰራዉ ለህዝብ ግድቡን የሚሰራዉም ህዝብ ሆኖ ሳለ ለምንድነዉ ይህ በዉድም በግድም ገንዘብ ካላዋጣህ ወይም ቦንድ ካልገዛህ እየተባለ ቀንና ማታ ሲጠየቅ የኖረ ህዝብ በዚህ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉ ዉሎችንና ስምምነቶችን እንዳያዉቅና ጭራሽ እንዳይሰማ የተደረገዉ? ካይሮና ካርቱም ዉስጥ እንደሚነገረዉ ግብፅ በህዳሴዉ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የማነጅመንትና የቁጥጥር ሚና ይኖራታል የተባለዉ ዜና እዉነት ከሆነ እኛ እራሳችን አገራችን ዉስጥ በምንሰራዉ ግድብ ግብፅ ሊኖራት የሚችለዉ የማነጅመንትና ቁጥጥር ድርሻ ዬት ድረስ ነዉ የሚሆነዉ …ለምንስ እንዲህ አይነት ሚና እንዲኖራት ተደረገ?

አርበኞች ግንቦት ሰባት የሶስቱ አገሮ መሪዎች ስምምነቱን በፊርማ ከማጽደቃቸዉ በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ ለእንደነዚህ አይነት ቁለፍ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለበት ብሎ ያምናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያን አስመልከቶ የሚደረጉ ምንም አይነት ዉሎችና ስምምነቶች ብቸኛዉ ባለቤት ነዉና ከዚህ ህዝብ ተደብቆ የሚደርግ ምንም አይነት ስምምነት ሊኖር አይገባም። ስለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህ ከዚህ በላይ ያነሳናቸዉ ጥያቄዎች ጥርት ባለ መልኩ እንዲመለሱለት የወያኔን አገዛዝ ማስጨነቅ አለበት፤ አለዚያ ይህ ጉዳይ ዉሎ ካደረ በኋላ የሚደረገዉ ሩጫ ሁሉ “ቁጭ ብለዉ የሰቀሉትን ቆሞ ማዉረድ ያቅታል” እንደሚባለዉ ይሆናል።

ግብፅና ሱዳን የረጂም አመታት ወዳጅነትና አመታት ያስቆጠረ ወተዳራዊ ስምምነት ያላቸዉ ተጎራባች አገሮች ናቸዉ። እነዚህ ሁለት አገሮች በቅርቡ ከወያኔ ጋር የደረሱበትን ስምምነት “የግብፅን ፍላጎት የሚያረካ” ስምምነት ነዉ እያሉ ካርቱምና ካይሮ ዉስጥ አስተያየት በመስጠት ላይ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን ሁሉም ነገር ህዝብ እንዳያዉቀዉ በሚስጢር መያዙ እየታወቀ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት “አዲስ ምዕራፍ” ተከፈተ እያለ የፈረደበትን የኢትዮጵያ ህዝብ መሸንገል ጀምሯል። በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ ሱዳንና ግብፅ በቅርቡ ካርቱም ላይ የደረሱበት ስምምነት እዚያዉ ካርቱም ዉስጥ የፊታችን ሰኞ በሦስቱ አገሮች መሪዎች ፊርማ ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አል ሲሲ የዉጭ ጉዳይና የዉኃ ኃብት ልማት ሚኒስተራቸዉን አስጠርተዉ ሦስቱ አገሮች የደረሱበትን ሰነድ መርምረዉ ሪፖርት እንዲያቀርቡላቸዉ ማዘዛቸዉ ከወደ ካይሮ ተደምጧል። እንግዲህ ይታያችሁ እኛ ኢትዮጵያዉያን የሦስቱ አገሮች ስምምነት ምን እንደሆነ እንኳን ሳናዉቅ ግብፅ እሷ እራሷ የደረሰችበት ስምምነት አልጥም ብሏት ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጣት ጠይቃለች። ይህ የሚያሳየን አገሮች ለብሄራዊ ጥቅማቸዉና ደህንነታቸዉ ምን ያህል እንደሚጨነቁና አርቀዉ የሚመለከቱ አስተዋይ መሪዎች ደግሞ የሚጨንቃቸዉና የሚያሳስባቸዉ ይህ አሁን የሚመሩት ህዝብ ብቻ ሳይሆን ወደፊት በተከታታይ የሚመጣዉ ትዉልድ ጭምር መሆኑን ነዉ።እኛ ኢትዮጵያዉያን ግን ለእንደዚህ አይነት መሪዎች አልታደልንም። የኛ መሪዎች እንኳን ለሚመጣዉ ትዉልድ ሊጨነቁ ለዛሬዉም ትዉልድ “እኛ ከሞትን ሠርዶ አይበቀል” የሚሉ ስግብግቦች ናቸዉ።

ወያኔ ከራሱ ዉጭ ማንንም የማይሰማ፤ልዩነትን የማያስተናግድና የሌሎችን ሃሳብ ከሱ ሀሳብ የተሻለ መሆኑን እያወቀም ቢሆን የማይቀበል ችኮ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቶናል። ዛሬ ላይ ቆመን ወደ ኋላ ዞር ብለን የትናንቱን ስንመለከት ወያኔ በህዳሴዉ ግድብ ዙሪያም ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ያሳየን ይህንኑ ችኮነቱንና “እኔን ብቻ ስሙ” ባይነት ዕብሪቱን ነዉ። በተለይ የህዳሴዉን ግደብ በተመለከተ አባይ ወንዝ ላይ የሚገነባዉ ግድብ ከዚህ ቀደም በማንም ኢትዮጵያዊ ያልታሰበና የልተወጠነ ፍጹም አዲስ የሆነ ወያኔ ለኢትዮጵያ ያበረከተዉ ገጸ በረከት መሆኑን ለማሳየት ብዙ ጥሯል፤ አንዳንድ የዋሆችን ደግሞ አሳምኗል።ወያኔ ሁሌም ቢሆን ጥረቱና ፍላጎቱ እራሱን ከብጤዉ ከደርግ ጋር እያወዳደረ የተሻለ ሆኖ ለመታየት መሞከር ነዉ እንጂ የተሻለ ስራ መስራት ስላልሆነ በህዳሴዉ ግድብ ላይም አብዛኛዉን ግዜ ያጠፋዉ “አባይን የደፈረ” ተብሎ ለመጠራት ስለሆነ ዛሬ ግድቡ ግንባታዉ አልቆ አገልግሎት መስጠት በሚጀምርበት ወቅት የግድቡ ስራ ከመጀመሩ በፊት ተሰርተዉ ማለቅ የነበረባቸዉን ስራዎች እየሰራ ነዉ።

በቅርቡ አንድ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች ቡድን ግድቡ የሚሰረባት ቦታ ድረስ በመሄድ የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ በተመለከተ ጥናት አትንቶ የግድቡ ስራ በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት የተነሳ ይዘገያል ብሎ ሪፖርት ማቅረቡ የሚታወስ ነዉ። ጉዳዩን በቅርብ ለምናዉቀዉ ለኛ ለኢትዮጵያዉያን ግን እዉነቱ ከዚህ በላይ ነዉ። የህዳሴዉ ግደብ የሚዘገየዉ በገንዘብ እጥረት ብቻ አይደለም። የዚህ ትልቅ ፕሮጀክት ድህረ ጥናት ሁኔታዎችን የላጤነና ቅደም ተከተሎችን ያላገናዘበ ጎደሎ ጥናት ነበር፤ ከዚህ በተጨማሪ ሩጫዉና ግርግሩ የተጀመረዉ የህዳሴዉን ግደብ የመሰለ ግዙፍ የ96 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት በይድረስ ይድረስ ሰርቶ ለመጨረስ ነበር።

የብዙ አለም አቀፍና የአገር ዉስጥ ኤክስፐርቶች ግምት በግልጽ እንደሚጠቀመዉ የህዳሴዉን ገድብ ግንባታ ጨርሶ አግልግሎት የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ፕሮጀክቱ በዕቅድ ከተያዘለት በጀት ከሃምሳ በመቶ በላይ ሊያስፈልገዉ ይችላል። ይህ ደግሞ ዛሬ ወያኔን ስለምንቃወም የምናወራዉ ተራ የፕሮፓጋናዳ ጨዋታ ሳይሆን የዛሬ አራት አመት ወያኔ ከበቂ ጥናትና ዝግጅት ዉጭ አባይን እገድባለሁ ብሎ ሲፎክር የዛሬዋ ቀን እንደምትመጣ አዉቀን በተከታታይ ያስጠነቀቅነዉ ማስጠንቀቂያ ስለሆነ ነዉ። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ወያኔ አስቀያሚ መልኩን ለማሳመር ሲል ብቻ በኢትዮጵያ ህዝብ ገንዝብና ጉልበት የህፃን ጨዋታ መጫወቱን ነዉ። ሆኖም ዛሬ የሚያስፈራን ይህ ወያኔ የተጫወተበት መጠነ ብዙ የህዝብ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ግድቡን ሰርቶ ለመጨረስ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት የሚያደርገዉ አጉል መቅበዝበዝ ነዉ። በእኛ እምነት የህዳሴዉ ግደብ ተሰርቶ ሲያልቅ ኢትዮጵያን ከጥገኝነት ነፃ ማዉጣት ነዉ ያለበት እንጂ ሌላ አላስፈላጊ የሆነ የፖለቲካ ጥገኝነት ዉስጥ ይዞን መግባት የለበትም። ለዚህም ነዉ አርበኞች ግንቦት ሰባት ወያኔ፤ ግብፅና ሱዳን በአባይ ወንዛችን ላይ የሚሰራዉን ግድብ አስመልክቶ ደረስን የሚሉትን ስምምነት ምኑም ሳይደበቅ ለኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ መነገር አለበት እያለ ህዝብንም ወያኔንም የሚያስጠነቅቀዉ። የግብፅና የሱዳን መንግሰታት አገራቸዉ ዉስጥ ህዝብ የሚወዳቸዉ ወይም የሚጠላቸዉ መንግስታት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም ከዉጭ መንግሰታት ጋር በሚያደርጉት ምንም አይነት ድርድርና ዉይይት ሽንጣቸዉን ገትረዉ የሚቆሙት ለአገራቸዉ ጥቅም ብቻ ነዉ እንጂ ሌላ ከህዝብና ከአገር የተለየ አጀንዳ የላቸዉም። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ አገዛዝ በተለይ ባለፉት ሃያ አራት አመታት ብቻዉን ስልጣን ተቆጣጥሮ የኖረዉ ህወሓት ግን ከኢትዮጵያ ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም የተለየ የራሱ የሆነ አጀንዳ አለዉ። አርበኞች ግንባት 7 ህወሓትንና ይህንን ከህዝብና ከአገር የተለየ አጀንዳዉን የማቆሚያዉ ግዜ ዛሬ ነዉና ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፤ ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ፤ እዉቀት ያለህ ደገሞ በእዉቀትህ ነገ ሳይሆን ዛሬ ህዝባዊዉን ትግል ተቀላቀል እያለ አገራዊ ጥሪ ያስተላልፋል።

http://ecadforum.com/

post tigi late

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s