ብጥብጥ በመፍጠር የተጠረጠሩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ክስ ተመሠረተባቸው

-ሦስት የፓርቲው አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተጠቆመ

በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በተመለከተ ሕዝቡ ሐዘኑን ለመግለጽና የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለማውገዝ፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በተደረገው ሠልፍ ላይ፣ ብጥብጥ

እንዲፈጠር አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው በታሰሩ ሰባት የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና በሁለት ግለሰቦች ላይ ግንቦት 4 እና 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የተከሰሱት ‹‹ስብሰባን ወይም ጉባዔን ማወክ ወንጀል›› በሚል ሲሆን፣ ክሱ የተመሠረተው በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ቂርቆስና መናገሻ ምድብ ችሎቶች ነው፡፡

በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ የተመሠረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወይንሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬና ማስተዋል ፈቃደ ሲሆኑ፣ ቤተልሔም አካለወርቅ የምትባል ግለሰብ በክሱ ተካታለች፡፡

በመናገሻ ምድብ ችሎት ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ የተመሠረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ደግሞ መሳይ ደጉሰው፣ ብሌን መስፍንና ተዋቸው ዳምጤ ናቸው፡፡ ማትያስ መኩሪያ የሚባል ግለሰብም አብሯቸው ተከሷል፡፡

በቂርቆስ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ግለሰቦች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ)ን ማለትም በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን፣ እንዲሁም አንቀጽ 490(3)ን ማለትም፣ በቡድን ሆኖ ስብሰባን ወይም ጉባዔን ማወክ የሚለውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

በመናገሻ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ግለሰቦችም፣ ከላይ ከተጠቀሱት የወንጀል ሕግጋት በተጨማሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 487(1ሀ)ን ማለትም፣ ‹‹የማነሳሳት ጠባይ ያላቸው የሐሳብ መግለጫዎችን፣ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ ወይም ስብሰባ ላይ ሕገወጥ ለሆነ ድርጊት የሚያነሳሳ ወይም የዛቻ ጠባይ ያለው የንግግር መግለጫ ወይም ምስል ያዘጋጀ፣ ያስፋፋና ያሠራጨ ወይም ያሰማ›› የሚለውን መተላለፋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ ወይንሸት ሞላ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥትን ክብርና ሰብዕናን፣ እንዲሁም ከሕዝብ የተሰጠውን የአመራርነት አደራ የሚያንቋሽሽና የሚያጎድፉ ቃላት እያወጣች በመጮህና በማስተጋባት፣ ሠልፍ ለወጣው ኅብረተሰብ መግለጿን ክሱ ያስረዳል፡፡

ተከሳሽ ዳንኤል ተስፋዬ አንደኛ ተከሳሽ የተናገረችውን እየደገመ ‹‹ናና ናና መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ናና›› ማለቱንና ተከሳሽ ኤርሚያስ ፀጋዬ ‹‹ወያኔ አሳረደን ወያኔ አሳረደን›› በማለት እየተቀባበሉና ሕዝቡ እንዲቀበል ሲያደርጉ እንደነበር በክሱ ተጠቁሟል፡፡ በሠልፉ ላይ ጋዜጠኞች ካሜራ ይዘው ሲንቀሳቀሱና ወደ እነሱ ሲቀርቡ ‹‹ሌባ ሌባ›› በማለት ድንጋይ በመወርወርና እነሱ የሚሉትን ሕዝቡ እንዲያስተጋባ ሲያነሳሱ እንደነበርም በክሱ ተብራርቷል፡፡

ቤተልሔም አካለወርቅ የተባለች ተጠርጣሪ እጆቿን እያጣመረች ‹‹ታስረናል፣ የታሰሩ ይፈቱ፣ ፍትሕ የለም›› እያለች ስትጮህ፣ ሁሉም ተጠርጣሪዎች እሷን በመቀበልና በእጃቸው ምልክቱን በማሳየት ሕዝቡ እንዲያስተጋባ በማድረግ ሠልፉን ያወኩ መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች ተመሳሳይ ድርጊቶችን በመፈጸም ‹‹ስብሰባን ወይም ጉባዔን ማወክ ወንጀል›› ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

በቂርቆስ ምድብ ወንጀል ችሎት ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ የቀረበባቸው ዋስትና ተከልክለው ለግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ተቀጥረው ወደ ማረሚያ ቤት ወርደዋል፡፡ በመናገሻ ምድብ ወንጀል ችሎትም ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ የተመሠረተባቸውም ዋስትና ተከልክለው ለግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ተቀጥረው ማረሚያ ቤት ወርደዋል፡፡

በሌላ በኩል ሦስት የፓርቲው አባላት መሆናቸው የተጠቆመው ናትናኤል ያለምዘውድ፣ ሜሮን አለማየሁና ደብሬ አሸናፊ ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ፣ በፖሊስ ታስረው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ ለምንና በምን ምክንያት በፖሊስ ሊወሰዱ እንደቻሉ ከፖሊስ ለማጣራት በተደረገው ጥረት፣ ፖሊስ ምንም የሚያውቀው እንደሌለ አስታውቋል፡፡

 http://www.ethiopianreporter.com/
post tigi flate

Leave a comment