ጠቦቱ በግ፤ ተመስገን ደሣለኝ – ከኢዩኤል ፍሰሃ

የኮከቦች ሳይንሳዊ ጥናት ወይም ሥነኮከብ አስትሮሎጂ ይባላል፡፡ ስለአስትሮሎጂ ያለህን አመለካከት ባላውቀውም የተወለድክበት ዕለት መጋቢት 27 ቀን ኮከብህ ኤሪስ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ ኮከባቸው ኤሪስ የሆኑት በጠቦት በግ ይመሰላሉ፡፡ ኤሪሶች ምን አይነት ስብእናን እንደተላበሱ ያነበብኩትን ላጫወትህማ፡፡ ‹‹ለተበደሉና ለተጨቆኑት ጥብቅና ይቆማል፡፡ ወንዱም ሆነ ሴትዋ ኤሪስ ኢ-ፍትሐዊ ነው የሚሉትን ነገር ሳይውሉና ሳያድሩ ይቃወማሉ፡፡ የሚመስላቸውን ከመናገርም ወደኋላ አይሉም፡፡›› (ፍካሬ ኢትዮጵያ፣ በአብነት ስሜ ገፅ 14) “የሚመስላቸውን ከመናገር ወደኋላ አይሉም” እንዲሁም “ኢ-ፍትሐዊነትን ሳይውሉና ሳያድሩ ይቃወማሉ” ተብሎ የተገለፀው አንተን በሚገባ ይገልፃል፡፡ ለተበደሉትና ለተጨቆኑትም ድምፅህን በማሰማትህ የተነሳ ወደ ወህኒ ተወርውረሃል፡፡ ‘ማረሚያ’ ሲሉ የሚጠሯቸው ማጎሪያዎቻቸው ከከተቱህ ድፍን አንድ ዓመት አስቆጠርክ፡፡ እኔም ይህን በማስመልከት ጥቂት ልፅፍልህ ወደድኩ፡፡ በቅድሚያ እንዴት እንዳወኩሁ ልተርክልህ ለጥቄ ደግሞ አንተን የምመለከትበት መነፅርን ምን እንደሚመስል አስቃኝሃለሁ፡፡ ወቅቱ 2003 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ መሆኑን አስታውሳለሁ፡፡ ያኔ የ19 ዓመት ታዳጊ የነበርኩ ሲሆን፤ ለፖለቲካ ብዙም ትኩረት አልሰጥም ነበር፡፡ ወላጅ አባቴ ዘወትር አርብ፣ አርብ ከእጁ የማትጠፋ አንድ ጋዜጣን ይዞ አየዋለሁ፡፡ የጋዜጣዋ ስም አይኔ ውስጥ ገባ፡፡ የጋዜጠዋ መጠሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ልናየው የምንሻው ነገር ነው፡፡ ‹‹ፍትሕ›› የሚል መጠሪያ ያላት ይህች ጋዜጣ አባቴ ዘንድ በብዛት ሳያት ጊዜ ስለጋዜጣዋ አስተያየቱን ጠየኩት፡፡ ‹‹ወደፊት ልትሻሻል የምትችል ጋዜጣ ትመስላለች፤ አንድ ደፋር ልጅ ነው ዋና አዘጋጇ፤ ድፍረቱ በእጅጉ ይገርመኛል፡፡›› በማለት አባቴ አስተያየቱን ሰንዝሮ ነበር፡፡ ፍስሃ ዳምጤን፣ በድፍረቱ ያስደመመውን ልጅ ፅሁፍ ላንብብ ብዬ ጋዜጣውን ከእሱ ተዋስኩ፡፡ ጋዜጣውን ገልጬ ወደ ገፅ 3 እንደዞርኩ አንድ ወጣት ፊትለፊት ያፈጥብኝ ጀመር፡፡ ወጣቱ በፎቶግራፉ ላይ እንደሚታየው አንገቱ ላይ ስካርፍ ጠምጥሟል፡፡ ከፎቶው በስተግርጌው ያለውን ስም አጤንኩት፡፡ ‹‹ተመስገን ደሳለኝ›› ይላል፡፡ የገፁ አናት ላይ ደግሞ ‹‹አንድ በሉ›› የሚል ፅሁፍ ሰፍሯል፡፡ የአምዱ ስም ነው አልኩ ለራሴ፡፡ እናም በአንድ በሉ አምድ ስር የወጣውን ፅሁፍህን አንድ ብዬ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ከፍትሕ ጋዜጣ አንስቶ ለእስር ከመዳረግህ ጥቂት ወራት በፊት የቆመችው ፋክት መፅሄት ድረስ ያደረከውን እልህ አስጨራሽ ጉዞ አብሬህ ተጉዤያለሁ፡፡ በዚህ መልኩ ከተዋወቅሁ በኋላ እንደ አባቴ ሁላ በድፍረትህ ተደምሜያለሁ፡፡ ሀሳብህን ስትገልፅ ፍርሃት ለሚባለው ነገር በርህን ጥርቅም አድርገህ መዝጋትህንም አስተውያለሁ፡፡ ሀሳቡን ሳይታክት የገለፀ ሰው ተብዬ ብጠየቅ፤ ከአንደበቴ በአምስት ፊደላት የተዋቀረ አንድ ቃል ይወጣል እሱም ተ.መ.ስ.ገ.ን የሚል ነው፡፡ በዚህ ድርጊትህ ከወገቤ ጎንበስ በማለት እጅ ነስቼያለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሃሳቤን በድፍረት እንድገልፅ የተነሳሽነት ስሜት በመላ አካላቶቼ ላይ እንዲሰርፅ አድርገሃልና በድጋሚ እጅ እነሳለሁ፡፡ በዓለም ላይ ሶስት ዓይነት ጋዜጠኞች እንዳሉ አንድ ቦታ ማንበቤን አሰታውሳለሁ፡፡ የመጀመሪያዎቹ አለቆቻቸውን ምን ልፃፍ ብለው የሚጠይቁት ናቸው፣ ሁለተኞቹ ጌቶቻቸውን እንዴት እናስብ ብለው ይጠይቃሉ፤ በሶስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጡት ሁለቱንም ጥያቄዎች ለራሳቸው የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ አንተ ሶስተኞቹ ምድብ መሆንህ ጥርጥር የለውም፤ ለዚህ ደግሞ ከፅሁፎችህ በላይ አንዳች አስረጂ ነገር ማቅረብ አይቻልም፡፡ በፃፍካቸው ፅሁፎች ላይ በተደጋጋሚ ‹‹ጉዟዬ እስከ ቀራኒዮ ነው›› ትል ነበር፡፡ ለእኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህን ያልከው ሃሳቤን በነፃነት በመግለፄ የተነሳ ሊመጣብኝ የሚችለውን ማንኛውም ዓይነት መከራ፣ በሙላ ተቋቁሜ መሄድ እስካለብኝ መንገድ ድረስ እሄዳለሁ፤ እጅግ ከከፋም ሞትንም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ የሚለውን ለማመላከት ይመስለኛል፡፡ ቃሉን ከማለት ባለፈ ተግብረኸዋል፡፡ ፈረንጆቹ “Actions do speak louder than words” ይላሉ፡፡ ተግባራቶችህ ከቃሎችህ በላይ ተናግረዋል፡፡ ቃልህ የእምነትህ ዕዳ ሆኖብህ ፍዳን እየተቀበልክ ትገኛለህ፡፡ ሃሳብህን ሳታክት በመግለፅህ ብቻ አያሌ መከራዎችን ተቀብለሃል፡፡ ከቤተሰብ፣ ከወዳጅና ከአድናቂዎችህ ነጥለው ግዞት ወስደውሃል፡፡ በዚህ ሳይበቃቸው ደግሞ አይንህን ለማየት ከሸገር እስካለህበት ዝዋይ ድረስ የሚመጡትን ወዳጆችህን የአይናችሁ ቀለም አላማረኝም ብለው ይመልሷቸዋል፡፡ ወላጅ እናትህ በመጦሪያ እድሜያቸው ያንን አድካሚ መንገድ እንዲጓዙ ፈርደውባቸዋል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ህክምናህ እንዳታገኝም አድርገውሃል፡፡ ይህን ሁላ መከራ ለመቋቋም የሚያስችል ደንዳና ልብ እንዳለህ ስመለከት ምንኛ እንደቀናሁብህ ቃላትን ተጠቅሜ ለማስረዳት ያዳግተኛል፡፡ ይህ ሁላ መከራ ግን ያጠነክርህ እንደሆነ እንጂ ቅንጣት ታክል ከዓላማህ እንድታፈገፍግ እንደማያደርግህ መናገር እችላለሁ፡፡ የሚደርስብህን ነገር ሁላ ተቋቁመህ ዳግመኛ ድምፅ አልባ ለሆኑት ድምፅ እንደምትሆን አልጠራጠርም፡፡ ተሜ ሆይ በርታ እንዳልልህ በርታ ሳልልህ የጠነከርክ ወዳጄ ነህ፤ ፅናቱን ይስጥህ እንዳልልህም ፅናትህን ተላብሰሃል፤ ስለዚህም አንድ ነገር ቃል ልግባልህ፡፡ አረረም፣ መረረም ሃሳቤን ሳልታክት እንደምገልፅ ቃል እገባልሃለሁ፡፡ ቃል ከመግባቱ ባለፈ ተግብረው እንደምትለኝ እገምታለሁ፡፡ አዎ ልክ ነህ፤ ቃሌን ከማለት ባለፈ ለመተግበር አብዝቼ እታትራለሁ፡፡ ዜጎቿ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ የምትወተውተዋ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ውለታህን እንደማትዘነጋው ከቶም አልጠራጠርም፡፡ ይህቺን ኢትዮጵያ በጋራ እንደምናያት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

posted tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s