ይድረስ ለኢህአዴጋዉያን “ወገኖቼ” – ይገረም ዓለሙ

መቼም ፈጣሪ ለሰው ልጆች ሁሉ የቸረውን ለእናንተም አለነፋጋችሁምና ሰዎች ናችሁ፤ የተገኛችሁት ከምታሰቃዩት ወይንም ጌቶቻችሁ ሲያሰቃዩት  ከምትሳለቁበት ሕዝብ መካከል ፣የተፈጠራችሁትመ እየገደላችኋት ካለው ወይንም አገዳዳይና አስገዳይ ሆናችሁ ከቆማችሁባት ሀገር ነውና የእናት ሆድ ዝንጉርጉር ሆኖ ብንለያይም ኢትዮጵያዊ  ናችሁ፡፡ እናም ለዚህ ነው ወገኖቼ ማለቴ፡፡ ይህች መልእክቴ የምትመለከተው ራሳቸውን ለወያኔ አስገዝተው ወገናቸውን በጠላትነት ፈርጀው ለደደቢቱ ውጥን ስኬት በሚችሉት አቅም በሀገርና በሕዝብ ላይ የዘመቱትናና፤ህሊናቸው የሚያምንበትን ሳይሆን ሆዳቸው የጠገበበትን የሚሰሩትን ነው፡፡

የቱንም ያህል ሥልጣን ወይንም ጥቅም ቢያውራችሁ  ከአይናችሁ እንዴት ጆሮአችሁን ታምናላችሁ? የቱንስ ያህል ጎመን በጤና ብሎ መኖርን ምርጫችሁ፣ አያያያዙን አይተህ ወደሚያደላው ማለትን የኑሮ መመሪያችሁ ብታደርጉ በኢትዮጵያውያን ላይ ባለፉት ሀያ አራት ዓመታት  የተፈጸሙና አሁንም በመፈጸም ላይ ያሉ በደሎች እንደምን አይታያችሁም? ጌቶቻችሁ የሚመጻደቁበትንና እናንተም የሚሉዋችሁን እንደወረደ እየተቀበላችሁ የምታስተጋቡለትን ሕገ መንግሥት ታውቁታላችሁ? ጆሮአችሁ የሚሰማው ይቅርና አይናችሁ የሚያየው ነገር ሁሉ ሕገ መንግሥቱን ባከበረ መልክ የሚፈጸም ነው? ወይንስ እንደ ንጉሱ አጎንብሱ ለማለት ባልፈቀደ ዜጋ ላይ የሚፈጸም ኢ-ሰብአዊም ሆነ ሕገ ወጥ ተግባር  ተገቢና ትክክል ነው ብላችሁ ታምናላችሁ? የነገሮች  ሕገ ወጥነት፤ የድርጊቶች ኢ-ሰብዊነት በራሳችሁ ላይ ካልደረሰ በስተቀር አያማችሁም አይሰማችሁም ማለት ነው፡፡ በርግጥ እንኳን እናንተ ጠቅላይ ምኒስትር ተብለው የተቀመጡት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንኳን ወያኔ የደደቢት ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ሲል የሚፈጽማቸውን ኢ-ሰብአዊ፣ ኢ-ዴሞክራሲያዊም ሆነ ኢ-ህጋዊ ተግባራት ለማስቆም አይደለም ለምን ብለው ለመጠየቅ አይችሉም፡፡ ከአቶ መለስ ወንበር ላይ ተቀምጠው ጠቅላይ ምኒስትር በተባሉ ሰሞን በአቶ መለስ ላይ ያዩት ሥልጣን በሳቸውም ላይ ያለ መስሎአቸው ይሁን  ወይንም እውነት ተፈታትናቸው በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ሲናገሩ ሰምተናቸው ነበር፡፡ በስም አንጂ በተግባር የሌሉት ሶስቱ የመንግስት ኃይሎች  ማለትም ሕግ አውጪው ሕግ አስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው  በጋራ ያካሄዱት በተባለ ስብሰባ ላይ  ከተሰብሳቢ ወንበር ላይ ተቀምጠው እይታቸውን ከበስተቀኛቸው ራቅ ብለው ወደሚታዩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በማድረግ «እንደ አስፈጻሚ አካል መሪ ከዳኝነት ሥርዓቱ ምላሽ የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ፤ ሕዝቡ በጣም በከፍተኛ ደረጃ  የሚያነሳቸው ጉዳዮች አሉ፤በዚህ ላይ የዳኝነት ሥርዓቱ እንዴት እያየው እንደሆነ፣ እንዴትስ እየፈታው እንደሆነ ምክር ቤቱም አስፈጻሚውን አካል የሚከታተለውን ያክል የዳኝነት ሥርዓቱን ይከታተላል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ በዚህ ላይ ማብራሪያ ቢሰጥ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱ አመራሮች እስከማውቀው ድረስ ጥሩ አመራሮች እንደሆኑ አውቃለሁ፣ ነገር ግን እሰከ ታች ድረስ በዚህ ደረጃ  ወርዶ የህዝቡን ፍላጎት፣ የሀዝቡን ጥያቄዎች፣ የህዝቡን አገልግሎት የማግኘት ጉዳይ፣ በተመለከተ እንዴት እያዩት እንዳለ  እንዴትስ ለህዝቡ መረጃ እየሰጡ እንዳለ ቢያብራሩና ብናውቀው የበለጠ ጥሩ ነው የሚል  ጥያቄ ላነሳ ፈልጌ ነው አመሰግናለሁ፡»ሲሉ በስም እንጂ በተግባር ኢትዮጵያዊ ካልሆነው ቴሌቪዢን ተመልክተናቸው ነበር፡፡ ጠየቁ እንጂ መልስ አላገኙም፣ ተናገሩ አንጂ ለተግባራዊነቱ አልተሰለፉም፤እንደውም የአቶ መለስን ራእይ ከማስፈጸም ውጪ የራሳቸው የሆነ ምንም እንደሌለ ነግረውን ለደደቢቱ የወያኔ ዓላማ መሳካት ከጳጳሱ ቄሱ እንዲሉ ሆነው እየሰሩ ነው፡፡ ቀድሞ አሳሪውም አሳሳሪውም ወንጃይ አስወንጃዩም ፈቺውም አስፈቺውም አንድ አቶ መለስ ነበሩ፣ በአቶ ኃይለማሪያም ሥልጣነ ዘመን ግን ብዙ መለሶች ተፈጥረው ሕዝቡን እያሰቃዩት ነው፡፡ አምናችሁም ይሁን  ሥልጣን ወይንም ጥቅም አሸንፎአችሁ አለያም ልኑር ብላችሁም ይሁን ዘር ከልጓም ይስባል ሆኖባችሁ ለወያኔ አርጋጅ አሸርጋጅ የሆናችሁ ከዚህችው ሀገር የተገኛችሁ ወገኖች በየግዜው የምናይ የምንሰማው ኢትዮጵያዊ ሆኖ መፈጠርን እስከመጥላት የሚያደርስ ከሰዋዊ ተግባር ያፈነገጠ ድርጊት እናንተን በማፈር ፋንታ የሚያኮራችሁ፤በማዘን ፋንታ የሚያስደስታችሁ፣ ለምን ብሎ ከመጠየቅ ካልሆነም ዝም ከማለት ይልቅ አበጀህ በለው ቀጥልበት በማለት ድጋፍ ለመለገስ የሚያበቃችሁ ምክንያቱ ምን ይሆን? እንዲህ የሆናችሁት ፈጣሪ ሳያዳላ የለገሳችሁን ሰዋዊ ተፈጥሮ ወደየት ጥላችሁት ነው? በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ወንድ ሴት ሳይባል በፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት፣ ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ዜጎች በተለያየ ግዜ ሲናገሩ ሰምተናል ተጽፎ አንብበናል፤በየወህኒ ቤቱ የሚፈጸሙ ኢ-ሰብአዊና ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በየግዜው እየሰማን ነው፡ለመሆኑ ሰይጣናዊ ስሜታቸውን ለማርካትና የበቀል ጥማታቸውን ለመወጣት ካልሆነ በስተቀር ወህኒ ቤት ያሉ ፍርደኞችን በማሰቃየት ጌቶቻችሁ የሚያገኙት ጥቅም ምንድን ነው? እናንተስ በዚህ ከማዘን መደሰታችሁ ከማፈር መኩራታችሁ ምን ይባላል፡፡ በጠያቂ ክልከላ ይታወቀ የነበረው የወህኒ ቤት ሕገ ወጥነት ምግብ ወደ መከልል ተሸጋግሯል፤መጻህፍት ጋዜጣም ሆነ መጽሄት በመከልከል የሚታወቁት የወህኒ ቤት ንጉሶች መጽኃፍ ቅዱስ መንጠቅ ደረጃ መድረሳቸውን ሰምተናል፤ የሀሰት ወንጀል ፈብርኮ አባይ ምስክር አሰልጥኖ ንጹሀን ዜጎችን ወንጀለኛ ማድረግ ስራው የሆነው የዐቃቤ ህግ ተቋም ዛሬም ራሱን ከሕግ በላይ አድርጎ ፍርድ ቤት ነጻ የሚላቸውን ሰዎች አለቅም  በማለት ተግባሩ እንደቀጠለ ነው፡፡የደህንነት ኃይሉ ራሱን የቻለ አድራጊ ፈጣሪ መንግሥት ከመሆን የሚገታው ሕግ አልተገኘም፡፡ እህሳ ይህን ተግባር ስትደግፉ ምክንያታችሁ ምንድን ነው ወይንስ ሁሉም የተቃዋሚዎች የውሸት ወሬ ነው ትላላችሁ፡፡ሌላው ቢቀር ነግ በእኔ ማለት እንዴትና በምን  ከውስጣችሁ ታጥቦ ወጣ፡፡ ከሎሌነት ወደ ሰውነት መሸጋገር ያሰባችሁ እለት፤ ጌቶቻችሁ በእናንተ ላይ ያላቸው እምነት የተሸረሸረ እለት፤ አገልግሎታችሁ ያበቃ እለት፤ ሳት ብሎ ያዳጣችሁ እለት ወዘተ ከእነዚህ በአንዱ ዛሬ በሌሎች ላይ ሲፈጸም አይታችህ እንዳላየ፣ ሰምታችሁ እንዳልሰማ የምታልፉት ወይንም በቻላችሁት ሁሉ የምትደግፉት ሕገወጥና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በእናተም ላይ ሊፈጸም እንደሚችል ነጋሪ ያስፈልጋችሁ ይሆን፡፡ ከብዙዎቹ ለምሳሌነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል አቶ ታምራት ላይኔን ከሩቁ  ከቅርቡ ግዜ  ደግሞ አቶ መላኩ ፋንታን ማስታወስ በቂ ይመስለኛል፤አዙሮ የሚያይ አንገት ላለው፡፡ የሚገደሉት የሚታሰሩት የሚሰደዱት የሚሰቃዩት ዜጎች ጌቶቻችሁ የሚሉትን እየተከተላችሁ ጸረ ሰላም አሸባሪ  ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ስለሆኑ ነው ትሉ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አይደለም መቃወም ሀሳብ የማቅረብ መብትም አቅምም የላችሁ ይሆናል፡፡በተቀዋሚነት ያስፈርጀናል ብላችሁ ትሰጉም ይሆናል፤ ጊቶቻችሁን አስተውላችሁ ተራመዱ እያሰባችሁም ተናገሩ እየዋሻችሁ አታሳፍሩን፤ እተደነባበራችሁ መሳቂያ አታድርጉን ለማለትስ አቅምም መብትም የላችሁ? ይህም ያስፈራችኋል? ክብዙው ትንሽ ላስታውሳችሁ አቶ መለስ ይህችን ዓለም በተሰናበቱበት ወቅት ሞታቸው ሲወራ እነ አቶ በረከት በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙን እየወጡ ሞታቸውን የሚመኙ ተቀዋሚዎች የሚያወሩት እንጂ ጠቅላይ ምኒስትሩ አልሞቱም አንደወም በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት አሉ፡፡ የራሳቸው መዋሸት አልበቃ ብሎ አዲስ አድማስ የሚባለው የቅዳሜ ሳምንታዊ ጋዜጣ አቶ መለስ በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና በቤተ መንግሥት ከትላልቆቹ ባለሥልጣኖቻችው ጋር እንደሚመክሩ በመግለጽ የውሸቱ ተጋሪ አንዲሆን አደረጉት፡፡ ጎበዝ ሞት እንዴት ይደበቃል፡፡ ጌቶቻችሁ ውሸት የባህሪያቸው በመሆኑ ሀፍረት ይሉ ነገር አያውቃቸውም፤ ከለማበት የተጋባበት እንዲሉ ሆኖ እናንተም  በዚህ ውሸት አልፈራችሁም፡፡ አትዋሽ ክፉ አትስራ ወዘተ የሚለውን ቅዱስ መጽኃፍ ጥለው ለዓላማህ ስኬት እስከጠቀመህ ድረስ ሁሉንም ሥራ ሁሉንም ተናገር የሚለውን የወያኔ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተቀበሉት አቶ ኃይለማሪያም ዋንኛ ዋሾ ሆነዋል፡፡ የዞን 9 ጦማሪያንን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥቄ ሲመልሱ በጦማሪ ስም ተከልልው ከአሸባሪ ድርጅት ጋር በመገናኘት በሽብር ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ለመሆናቸው በቂ መረጃ አለን በማለት በድፍረት ነበር የተናገሩት፡፡ ይህንንም የተቀዋሚዎች ወሬ ነው አንዳትሉ የታየ የተሰማው ከአልጀዚራ ቴሌቪዝን ነው( እናንት ምን ገዷችሁ እሱም የተቀዋሚዎች እጅ አለበት ትሉ ይሆናል) ታዲያ ጉዳያቸውን የያዘውና   በቀጠሮ ሲያንገላታቸው የቆየው ፍርድ ቤት  ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ አንደ ክሱ አግባብ አሸባሪ ለመሆናቸው አላስረዳም  በማለት  ሁሉንም ነጻ ያላቸው የአቶ ኃይለማሪያም በቂ ማስረጃ የት ገብቶ ነው!!  እናንተ ግን ይህም አላሳፈራችሁ፤ ዲያስፖራ በሚል መጠሪያ የሚታወቁትንና ከሀገራቸው ውጪ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አዲስ አበባ ጠርተው  የውሸት አጋሮቻቸው የሆኑ አርቲስቶች ከእንግዲህ ሻማ ለልደት ብቻ ነው በማለት በዋሹበት አዳራሽ ሰብስበው በምግብ እህል ራሳችንን ችለናል በማለት በረሀብ ላይ ድል መቀዳጀታቸውን አወጁ፡፡ከእውነት ጋር ሲጣሉ መጋለጡ ውሎ አያድርማና ይህን ብለው ብዙም ሳይቆይ የረሀብ ነገር መሰማት ጀመረ፡፡ የመቋቋም አቅም አለን በማለት ደግመው ዋሹ፣ ነገር ግን  ረሀብን በጉራ ማባረር በውሸት መቋቋም አይቻልምና መንግሥታቸው ለጋሾችን እየለመነ ነው፡፡ ለምን ይዋሻል? መሪ ዋሸ ነገር ተበላሸ ነው፡፡እናንተ ወገኖቼ ግን በዚህም አታፍሩም ፡፡ እንደው ህሊናችሁን ያደነዘዘው ልባችሁን ያደነደነው ምን ይሆን፡፡የኢህአዴግ አባል ስትሆኑ በወያኔ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስትጠመቁ የሚሰጣችሁ ሰዋዊ አስተሳሰብን የሚከላ ማደንዘዣ ይኖር ይሆን! ሁሉም አላፊ ነውና ዘለዓለማዊ ምድራዊ ኃይል የለም፤እናም ብትችሉ መልካም ነገር  ስሩ፤ ካልሆነም መጥፎ ስራ አትስሩ ለመጥፎ ሥራም አትተባበሩ፡፡

source  zehabesha.

posted tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s