ራሳችንን ማታለል ካልፈለግን በቀር፣ አዲስ ነገር የለም በወያኔ ሰፈር |ይገረም ዓለሙ

ከሀያ ዓመታት በላይ ዜጎች በተለያየ መንገድ ሲጠይቁትና ሲጮሁበት የነበረን ጉዳይ ወያኔ ለመቶ በመቶ አሸናፊነቱ ማስቀየሻነት አዲስ አድርጎ ሲያመጣው አዲስ የሆነብ ሰዎች መኖራችን እየታየ ነው፡፡ አጥፊዎቹ ራሳቸው  የጥፋቱ አጥኚ ሆነው በመድረክ ሲያቀርቡት የሰማነው ሁሉም  አንድም አዲስ ነገር የለበትም፡፡በእለት ትዕለት ኑሮአችን የምናውቀው ፣በማነለብኝት ሲፈጸም የምናየው ወይ በራሳችን ወይ በዘመድ ጓደኛ አለያም በሀገር ልጅ ዜጋ ላይ ተፈጽሞ የምናውቀው ነው፡፡  ውጪ ጉዳይ ምኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ስለጥናቱ ተጠይቀው ለእኔ ምንም አዲስ ነገር የለውም ያሉት እውነት ነው፡፡

hailemariam desalegn

የመቶ በመቶ አሸናፊነት ያተኮሰውን የፖለቲካ አየር ለማቀዝቀዝ ይበጅ ከሆነ  ተብሎ በቀረበው ጥናት የተገለጹ ጉዳዮችን አስቀድመው ያመላከቱ፣ መፍትሄ የጠቆሙ፣ የተቃወሙ ወዘተ ዜጎች  ጸረ ሰላም ፤የቀድሞ ሥርዐት ናፋቂ፤ ትምክህተኛ በቅርቡ ደግሞ አሸባሪ ተብለው ተወግዘዋል ተከሰዋል በግፍ ታስረዋል፡፡ ይህን አላውቅም የሚል ይኖር ይሆን?

ሰውየው በደል ደርሶበት አቤቱታ ለማቅረብ ራፖር ጸኃፊ ጋር ይሄድና የደረሰበትን በደል እየዘረዘረ ለጸኃፊው ይነግረዋል፡፡ በስራው የተካነው ጸኃፊም የተነገረውን ከሽኖ ይጽፍና መጨረሻ ላይ ሲያነብለት ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል፡፡ ምን ሆነሀል የነገርከኝን እኮ ነው የጻፍኩት ሲለው ለካስ ይህን ያህል ተበድየ ነበር አለ ይባላል፡፡የደረሰበትን በደል በሌላ ሰው አንደበት ሲሰማው ገዝፎና ከፍቶ ታየው፡፡

እኛም ወያኔዎች የእኛን በደል በእነርሱ አንደበት ሲነግሩን አዲስ ሆኖብን ካልሆነ በስተቀር ከጥናቱም ሆነ ከውይይቱ የሰማናቸው ነገሮች ዶ/ር ቴዎድሮስ እንዳሉት  አዲስ ነገር ባለመሆናቸው  የወያኔን መለወጥ አይደለም በውስጣቸው ትንሽም የለውጥ ሀሳብ ስለመኖሩ አያሳዩም፡፡

በጥናቱም ሆነ በውይይቱ የችግሩ ምንጭ አልተገለጸም፤ስለሆነም ንቅናቄ ያሉት ቢፈጠር ዘመቻ የተባለው  ቢዘመት የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ ለምሳሌ በፍትህ  ጉዳይ ላይ የቀረበውን ጥናትና የተደረገውን ውይይት ስናይ (ተመጥኖ በኢቲቪ እንደቀረበለን)   ዳኞች ፣አቃቤያነ ህግ  ፣ማረሚያ ቤቶች  ወዘተ  የአዋጁን በጆሮ ይሉ አይነት በሆኑ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ተኮንነዋል፡፡ ነገር ግን  እነዚህ አካላት ይህን ለማድረግ የበቁት በፍትህ ሥርዓቱ ብልሹነት መሆኑ  አልተነሳም፡፡እናም ንቅናቄው ተነቃንቆ ዘመቻው ተዘምቶ ከየክፍሉ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ርምጃ ቢወሰድ እንኳን (ይህም ከሆነ ነው)  የሥርዓት ችግር በነካ ነካ ዘመቻ አይቀረፍምና  ለውጥ አይመጣም ፡፡

ፖሊስ ሕጉ በሚፈቅድለትና ሙያው በሚጠይቀው አግባብ ሳይሆን በባለሥልጣናት ትዕዛዝ ሰዎችን እንዲያስር የሚፈቅደው፤ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ ሰዎችን ባለሥልጣናት በመገናኛ ብዙኃን  ወንጀለኛ ናቸው ለዚህም በቂ ማስረጃ አለን እያሉ ፍርድ ሲሰጡ የማይከለክለው ፤ ፖሊስና አቃቤ ሕግ እየተጋገዙ አባይ ምስክር አሰልጥነው ፍርድ ቤት ሲያቀርቡ የማይጸየፈው፣ዳኞች በስልክ እየታዘዙ ብይን ሲሰጡና ተጽፎ የተሰጣቸውን የፍርድ ቤት  ውሳኔ አድርገው ሲያነቡ የህግ ያለህ የማይለው፤ ነባር የህግ ባለሙያዎችን አግልሎ በለብ ለብ ስልጠና በተመረቁ ባለሙያዎች የተሞላው፤ በጥቅሉ ፍትህ የት እንዳለች የማያውቀው የፍትህ ሥርዓት ካልተለወጠ በስተቀር  እስከ ዛሬም ሆነ ዛሬ  የሰማናቸው  ጥናቶችም ሆኑ ውይይቶች ከፖለቲካ ቁማር ጨዋታነት ያለፈ ፋይዳ የላቸውምና እነርሱም በገዢነት እኛም በተገዢነት ከቆየን ከአመት ሁለት ዓመት በኋላም ተመሳሳይ ነገር እንሰማለን፡፡

ትናንትን መርሳትና አዲስ በሚመስሉ (አሰመስለው በሚያቀርቡል) ነገሮች ላይ ማተኮር አንዱ በሽታችን መሆኑ እንጂ፣ የዛሬ አስር ኣመት ቅንጅቶች   ሰሞነኛው ጥናት በገለጻቸው ዐቃቢያነ ህግ ከተከሰሱበትና በዚሁ ጥናት በተገለጹት አይነት ዳኞች የእድሜ ልክ እስራት ሊፈረድባቸው  ከባቀቻው ነገር አንዱ  የፍትሕ ሥርዓቱ ፍጹም ገለልተኛ ሆኖ ሊሰራ የሚያስችለው አደረጃጀት ይኑረው ብለው መጠየቃቸው ነው፡፡(  ይህ ጥያቄ ቅንጅቶች ፓርላማ ለመግባት ካቀረቡዋቸው ስምንት ጥያቄዎች አአንዱ ነው፡፡)  ይህንና መሰል  ጥያቄዎችን ወንጀል አድርገው ያቀረቡ ሰዎች (በአቃቤ ሕግ ስም ባለሥልጣኖች ) “ፓርላማ ለመግባት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ካልፈረሰ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ዓላማቸውን በኃይል ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል በማለት ነው በክስ መዝገቡ ላይ ያሰፈሩት፡፡

በጥናቱ በተገለጸውና በውይይት ተደረሰበት በተባለው ስምምነት መሰረት የተወሰኑ ዳኞች ዐቃቢ ሕጎችና የወህኒ ቤት ኃላፊዎች ላይ ጣት በመጠንቆል ለውጥ ይመጣል ብሎ ለማመን የዳዳው ሰው ካለ በወያኔ ሀያ አራት አመት አገዛዝ ውስጥ ያልኖረ መሆን አለበት፡፡ መፍትሄው ከመሰረቱ የፍትህ ሥርዓቱን መለወጥ ነው፤ ይህን ማድረግ ደግሞ በወያኔ ዘንድ ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ አይታሰብም ብቻ አይደለም የፍትህ ስርኣት ለውጥ እንዲኖር መጠየቅ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለማፍረስ መንቀሳቀስ በሚል ወንጀል ለወህኒ እንደሚዳርግ ከላይ አይተናል፡፡

የፍትህ ሥርዓቱ ገለልተኛ ሆኖ በፍጹም ነጻነት ሊሰራ በሚያስችለው መልኩ ይደራጅ የሚለው ጥያቄ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት ሲፈርስ ብቻ ነው ከተባለ (በክሱ እንደተገለጸው) አሁን ባለው ሕገ መንግሥት ሊኖር የሚችለው በጥናቱ የተገለጹ ጥፋቶችን ሊያስተናግድ የሚችል ነጻነት የሌለው በአስፈጻሚው አካል ተጽእኖ ውስጥ የወደቀ የፍትህ ሥርዓት ነው ማለት ነው፡፡ ሆን ብለው የማያምኑበትንና የማያደርጉትን ነገር እያወሩ ሲያደነባብሩን አብረን የምንደናበር፣ መለስ ብለን ማስታወስ እየተሳነን አዲስ ያልሆኑ ነገሮች  መልካቸውን ወይ መጠን ቅረጻቸውን ለውጠው ብቅ ሲሉ አዲስ የሚሆኑብን ሰዎች ለወያኔ የፖለቲካ ቁማር ጥሩ አጫዋች እየሆንን ነው፡፡

አጥፊነትን አምኖ ለውጥን ከልብ ሽቶ የሚደረግ ጥናት የሚካሄደው በገለልተኛ ወገን ነው፡፡በዛ መልኩ የሚካሄድ ጥናት በሽታውን ከነሰንኮፉ ለመንቀልና ችግሩን ከመሰረቱ ለማስወገድ ያስችላል፡፡ ሰሞኑን እንደሰማነው አይነት የጥፋቱ አካል ራሱ አጥኚ ሆኖ ሲሰማራ አንድም ለማስመሰል እንጂ ለውጥ ከመፈለግ አለመሆኑን ያሳያል፡፡ ለውጥ ቢፈለግም ደግሞ እንደታየው የሚየቀርበው የጥናት ውጤት “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” አንዲሉ አይነት ስለሚሆን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አይፈይድም፡፡

ችግሩ በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ያለው ችግር በችግሩ ፈጣሪዎች የማይታወቅ መሆኑ ሳይሆን  ችግሩ ራሱ የእድሜ ማረዘሚያ መድሀኒት ተደርጎ መወሰዱ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት፣ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት ከአምባገነን አገዛዝ ጋር ሆድና ጀርባ ናቸው፡፡ በመሆኑም ነው በተለይ በየምርጫዎች ማግሥት የሰሞኑን አይነት ነገር እየነገሩን የለውጥ ንቃናቄ እንፈጥራለን በችግሮቻችን ላይ እንዘምታለን እያሉን እኛ እያሞኙ እነርሱ ከደደቢቱ ዓላማቸው ዝንፍ ሳይሉ በመንገዳቸውም የሚቀጥሉት፡፡

ዛሬ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የማይሰማው በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ፋክልቲ ዲን የነበሩት ፕ/ር ጥላሁን ተሾመ በኢትዮጵያ የፍትሕ አስተዳደር ችግሮችና የፖሊስ ነጥቦች በሚል ርዕስ ለውይይት ባቀረቡት የጥናት ጽሁፍ (ወረቀቱ ላይ ቀንና ዓ.ም ባይገለጸም ከ10 ዓመታት በፊት ነው፡፡)

“የሕግ የበላይነት መግለጫ ዓይነተኛው መንገድም ይህ መንግሥት ለዳኝነቱ ሥርዓት የሚኖርበት ተገዢነት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ይህን ከባድና አልፎ አልፎም መስዋዕትነት የሚጠይቅ ተልእኮ ይወጡ ዘንድ በሕገ-መንግሥት የተረጋገጠ ነጻነት፣ለሕግ ልዕልና የቆመ የፖለቲካ ሥርዓትና በሕግ ልዕልናም ከአንጀታቸው የሚያምኑ ፖለቲከኞችና መሪዎች መኖራቸው አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ የሚዋቀረው የፍትሕ ሥርዓትም ስለ ዳኝነት ነጻነት ምንነት በቅጡ የተረዱ ራሳቸውን ለሕግ እንጂ ለማንም ተገዢ የማያደርጉ ከአድርባይነትና ከምግባረ ብልሹነት የፀዱ እና አስፈላጊ ሲሆንም ለዚህ ክቡር ዓላማ የሚፈለገውን መስዋዕትነት ለመክፈል የዓላማ ጽናቱ ያላቸውን አባላት በውስጡ የያዘ  ሊሆን ይገባል” ብለው ነበር፡፡ ሰሚ አላገኘም እንጂ፡፡

ዛሬ የይስሙላ ለቅሶ ዋይ ዋይ እያሉ  እውነት መስሎን ደረት አየደቃን እንድናላቅሳቸው የሚከጅሉት ሰዎች እውነትም መንገድም እኛ ብቻ ነኝ ብለው የሚያምኑ ምክር የማይሰሙና ለውጥ የማያስቡ በመሆናቸው እንጂ በሁሉም ዘርፍ በርካታ ምሁራን ጠቃሚ ምክር ለግሰዋል፤ አዋጪ የሆነ መንገድ አመላክተዋል፤ መፍትሄ ጠቁመዋል፤ ከእነዚህ አንዱ የሆኑት ፕ/ር

ጥላሁን ከላይ የገለጽኩትን የጥናት ጽሁፍ ያጠቃለሉበት መልእክት ዛሬም ከአስራ ምናምን አመታት በኋላ ሰሚ ቢያገኝ አዲስ ነው፡፡ ይህን ነበር ያሉት፡፡

“የፕሮፓጋንዳ ፍላጎታችንን ለማርካት ብለን ሳይሆን፣የግል ወይንም የቡድን ዓላማዎቻችንን ለማራመድ ብለን ሳይሆን፣ ከሌሎች የህግ ሥርዓቶች ለመፎካከርና እንዲህ ነን ለማለትም ሳይሆን ፣ታግለንለታል እየታገልንለትም ነው ለምንለው ሕዝባችን መብትና ነጻነት ብለን የፍትህ ሥርዓታችንን እንደገና የምንፈትሽበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ጀንበሯ ልትጠልቅብን ሩብ ሰዓት ብቻ ቀርቷታልና፡፡”

አዎ ከዚህ በመለስ የሚደረገው ጨዋታ ሁሉ ተጨፈኑ  ላሞኛችሁ ነው፤መሞኘት አለመሞኘት ደግሞ የግለሰቡ መብት ነው፡፡

posted tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s