ወይ እነሱ ወይ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለንም” | በ4 ፖሊሶች የተደበደበው ሰው | ከያሬድ ሹመቴ

ካዛንቺስ ቶታት ፊትለፊት ጫጫ ኮርነር የተባለ ቤት በር ላይ የፒያሳ ታክሲ ለመያዝ ከምሽቱ 3:30 ገደማ በርካታ ሰዋች መሀል ቆሜያለሁ። 4 ፖሊሶች ደግሞ አለፍ ብለው ቆመዋል። እድሜው ወደ 30ዋቹ መጨረሻ የሚሆነው አንድ ሰው በፌስታል የተቋጠረ ነገር ይዞ አቀርቅሮ ይጓዛል። ፖሊሶቹ አጠገብ ሲደርስ በመሀላቸው አቋረጠ። ከመሀላቸው ልጅ እግር የሆነው ፖሊስ ሰውየውን ጎትቶ ወደ ኋላ መለሰው። “አቤት?” አላቸው ሰውየው። “ለምንድነው በመሀላችን ያቋረጥከው?” አለው። “አላየኋችሁም ይቅርታ” “እንዴት አላየኋችሁም ትላለህ” አለው ሌላው “ምን አጠፋው” ብሎ መለሰ “ፖሊሶች እኮ ነን” አለው አንዱ “ፖሊስ ማለት ህዝብ ነው” አለ ቆፍጠን ብሎ “አንተማ ሌላ ተልዕኮ አለህ” ልጅ እግሩ ተናገረ። “በስህተት በመሀላችሁ በማለፌ ነው ተልዕኮ ያለኝ?” ታክሲ ለመሳፈር የተሰበሰበው ሰው ከንፈሩን እየመጠጠ ፖሊሶቹን በትዝብት ሲመለከት አንደኛው ፖሊስ “በቃ ና” ብሎ ወደፊት ጎትቶ ሲወስደው ሁሉም ተከተሉት። ከፊት 2 ከኋላ 2 ሆነው ሰውየውን ይዘውት ሲሄዱ ታክሲ ተራው ላይ መቅረት አላስቻለኝም። ተከተልኳቸው። ከፊት ያሉት ሁለቱ ፖሊሶች እንደ ጓደኛ እያወሩት ይሄዳሉ። ወደ ፈንድቃ ባህል ምሽት ጋር ከመታጠፋቸው በፊት አንድ የብረት ፍርግርግ አጥር ያለው ጊቢ በር ከፍተው ገቡ። ኮምዩኒቲ ፖሊሲንግ የሚባል ቢሯቸው ነው። የቢሮውን በር ከፍተው ሶስቱ ፖሊሶች ወደ ውስጥ ይዘውት ሲገቡ አንደኛው በረንዳው ላይ ቆሞ አካባቢውን ይቃኛል። እኔም እንዳያየኝ ካንትራት ታክሲ አስቁሜ ዋጋ መደራደር ጀመርኩ። ፖሊሱ ሰው አለማየቱን አረጋግጦ ወደ ውስጥ ሲገባ፥ ታክሲውን ይቅርታ ብዬው ወደ አጥሩ ተጠጋሁ። የጊቢው አጥር እና ቢሮው ብዙም ርቀት የሌለው በመሆኑ በድንብ ይታያል። የበረንዳው መብራት እንደበራ ሲሆን ከፍተው የገቡትን ቢሮ መብራት አላበሩትም። ጨለማው ክፍል ውስጥ ሰውየው በመስኮቱ በኩል ከውጭ በሚገባው ብርሀን ይታየኛል። ከመቅጽበት በሩ ተከፍቶ አንደኛው ፖሊስ ወደ ውጭ ወጣ። በረንዳው ላይ ቆሞ አላፊ አግዳሚውን መቃኘት ሲጀምር እኔም ታክሲ ጠባቂ መስዬ ቆምኩ። የሰውየውን ጩኸት ሰማሁት። የዱላ ድምጽ እና የሰውየው ጩኸት መንገደውኛውን ፊቱን ቢያስዞረውም ፖሊሱ አይኑ ፈጦ ሁሉንም ሰው ያይ ስለነበር ደፍሮ የቆመ የለም። ጨለማ ቤት ውስጥ ለሚቀጠቀጠው ምስኪን ሰው አንጀቴ አረረ። ማድረግ የምችለው ነገር ምን እንደሆነ ጠፋኝ። የሰውየውም ድምጽ እና የዱላ ውርጂብኝ እየበረታ ሲሄድ አልቻልኩም። በፍጥነት ወደ 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሮጥኩ። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ፖሊስ መምሪያ (6ተኛ) አሁን ካለሁበት ብዙም ርቀት የሌለው በመሆኑ በፍጥነት ደረስኩ። ጨለማ የወረሰው ግቢ ውስጥ ተረኛ ጥበቃ ፖሊሶች አግኝቼ አዛዦች ካሉ ብዬ ጠየቅኩ። “ማንም የለም ለኛ ንገረን” አሉኝ “አይ ሀላፊ ነው የምፈልገው” አልኳቸው። ሀላፊዎች የሉም ግን የመረጃ ክፍል ሄደህ ማነጋገር ትችላለህ አሉኝና ቢሮውን አመላከቱኝ። ጨለማውን ኮሪደር አልፌ አንደኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው መረጃ ክፍል ደረስኩ። አንድ ፖሊስ ብቻውን በርካታ የራዲዮ መገናኛ የድምጽ መሳሪያዎች ፊቱ ተደርድረው አንድ መዝገብ ላይ የሆነ ነገር እየፃፈ አገኘሁት። “አስቸኳይ ጥቆማ ለመስጠት ነው” አልኩት። “ምን ልታዘዝ” አለኝ። ፖሊሱ በጣም ትሁት ነው። የሆነውን በሙሉ ነገርኩት። ተናደደ። በሬዲዮው መገናኛ የተለያዩ ኮዶችን እየጠራ የፖሊሶቹን ማንነት ለማጣራት ሞከረ። ተረኛ የጣቢያ አዛዡን ሞባይል ስልክ ቁጥር ጠይቆ ደወለ። “ሀሎ … የት ነው ያለኸው?… 26 ያሉት ለምንድነው ሰው የሚደበድቡት?… ሰዋች በአካል መጥተው አባሎች ሰው እየደበደቡ ነው ብለው እየተናገሩ ነው። ጠቋሚ ሰዋቹ ‘በመሀላችን ለምን አለፍክ ብለው ነው የሚደበድቡት’ ነው የሚሉኝ…ፈጥነህ ድረስ…ቦታው ላይ ሂድ። ሰውየው ካለ ወደ ቤቱ የሚሄድበትን ወይም ወደ ህግ የሚሄድበት ነገር አድርግ። ህግ ከጣሰም በህግ ነው መቀጣት ያለበት እንጂ እንዴት በዱላ ይቀጣል?… እንደሰው አያስቡም እንዴ? ለምን አትነግሯቸውም? ሰው ለምን በመሀል አለፍክ ተብሎ ይደበደባል?… …በባህላችን በሰው መሀል እንደማይታለፍ አስተምረኸው ታልፋለህ እንጂ ሰውን በዱላ ነው እንዴ የምታስተምረው?… እኔ ጋር ነው ያሉት የጠቆሙኝ ሰዋች… ምን?…ለምንድነው ወዳንተ ጋር የምልካቸው?… ወዳንተ ልኬ ደግሞ ልታስደበድባቸው ነው? ቶሎ ሂድና ያለውን ውጤት እኔ ጋር መጥተህ ንገረኝ።” ስልኩን ዘጋውና አመስግኖ አሰናበተኝ። የሰውየው ነገር መጨረሻ አሳስቦኛል። እንደገና በሩጫ ትቼው ወደ ሄድኩት የኮምዩኒቲ ፖሊሲን ቢሮ አቅጣጫ ሄድኩኝ። መታጠፊያው አካባቢ ስደርስ ይህ ሰው እያነከሰ እና እየተንፏቀቀ ወደ እኔ አቅጣጫ ሲመጣ አየሁት። ያለቅሳል” ወይኔ” እያለ ግንባሩን ይደበድባል። “አይዞህ” አልኩት። “እባክህ ደግፈኝና 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ አድርሰኝ” አለኝ። የሆነውን በሙሉ እንዳየሁ ነገርኩትና ደግፌው ወደ ጣቢያው በድጋሚ ሄድኩ። ፖሊስ ጣቢያው ጊቢ ውስጥ እንደገባን ሰውየው የቢሮው በረንዳ ላይ ተቀመጦ ለቅሶ እና የህመም ሲቃውን ቀጠለ። እኔን ያስተናገደኝ ፖሊስ እና የደወለለት ፖሊስ ተከታትለው መጡ። የሰውየውን ስም ጠየቁት “ዘላለም” አለ እያለቀሰ። ዘላለም ብሶቱን በእንባ እና በለቅሶ መናገር ጀመረ።” “እኔ እኮ የተከተልኳቸው የናንተን ልብስ ስለለበሱ ነው። የፖሊስ ልብስ ባይለብሱ ኖሮ ጨለማ ክፍል ውስጥ ተከትያቸው እገባ ነበር? ህግ ቦታ እየወሰዱኝ ነው ብዬ ነው አምኜ የተከተልኳቸው። ምን አደረግኳቸው? ምን በደልኳቸው? አያውቁኝ! አላስቀይምኳቸው። ምን በድዬ ነው ምን አጠፋሁ ባልኩ የሚሰባብሩኝ?” እንባውን እየዘረገፈ ሲቃ እየተናነቀው ሲናገር ሀይለኛ ቁጣ እና ሀዘን ሆዴ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ ጉሮሮዬን ሳግ ተናነቀኝ። “ምን አድርጌ ነው። ለልጄ ልብስ እና ጫማ ገዝቼላት እንቅልፏን ሳትተኛ ልድረስ ብዬ ስሮጥ ጠልፈው ይቀጥቅጡኝ?!። እግዚአብሔር ፍርድ ይሰጣል እኔ ምንም አልልም እንባዬን እሱ ያብሰዋል። ምንም መናገር አልችልም ሌላ።” ፖሊሶቹ የተመታውን እንዲያሳያቸው ባትሪ ወደ እግሩ አበሩ። ግራ እግሩ ክፉኛ አብጧል። እንባው እንደጎርፍ እየወረደ ለቅሶውን ቀጥሎ እያነከሰ ከተቀመጠበት ተነሳ። ፖሊሶቹ ነገ መጥተህ ክስ መስርት አሉት። “እኔ ክሴ ለእግዜር ነው። እሱ ፍርድ ይስጥ። ብቻ ወይ እነሱ ወይ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለንም። አንዳችን ሀገር ክደናል። አይ ኢትዮጵያ! የፖሊስ ልብስ ለብሰዋል ብዬ ተከትዬ ስደበደብ እውነት ሀገር አለኝ እላለሁ? ነገም አልመጣም እናንተ ከሰማችሁኝ ይበቃኛል። ምን ፍርድ አገኛለሁ ብዬ ነው?” እንባውን እየጠራረገ ወደ ቤቱ ለመሄድ እያነከሰ መራመድ ጀመረ። ፖሊሶቹ ስልኩን ተቀበሉት። በነጋታው እንዲመጣ ቢለምኑትም ምንም ፍትህ ተስፋ እንደማያረግ ነግሯቸው እንባውን እያዘራ መሄድ ጀመረ። ከፖሊሶቹ ጋር ተሰናብቼ ደግፌው አብረን መሄድ ጀመርን። ግማሽ መንገድ ሸኘሁት። “ወይ እነሱ ወይ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለንም” የሚለውን ቃል እየደጋገመ እንባውን እያፈሰሰ ወደ ቤቱ በእየተሳበ ሄደ። ፡።።። ሀቀኛ ፖሊሶች ካላችሁ ልብሳችሁን አስከብሩ። ።።።። እነዚህን 4 ፖሊሶች በህግ ተጠያቂ ይሆኑ ዘንድ ይህንን መልዕክት Share በማድረግ ሀላፊነትዎን ይወጡ። ።።።። ዘላለምን ግን ቸር አምላክ ምህረቱን ያውርድለት።

poseted tigi felat

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s