የአዲስ አበባ መስፋፋት በተመለከተ የተሰጠ አስተያየት – ተፈራ ድንበሩ

ሰሞኑን የኦሮሞ ፈዴራሊስት ኮንግሬስ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በፖርቲው ስም ያወጡትን መግለጫ ይመለከታል። በመሠረቱ ፖርቲያቸው ሕዝባዊ ዓላማዎችን አንግቦ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ቢያነሣ መብቱ ስለሆነ እንደሕዝብ ፖርቲ የመንቀሳቅስ መብቱን ሊከበርለት ይገባል። ሆኖም በመግለጫው ላይ የሠፈሩት ሐሳቦች ኦሮምንና ኦሮሚያ የሚባለውን አዲስ አገር ከሌላው ሕዝብና አገር ለይተው አስቀምጠዋል፤ እንዲዚሁም የአዲስ አበባን ከፈዴራላዊ አመለካከት ጋር በሚቃረን ሁኔታ የከልሉ መብት ተጥሷል ብለው አቅርበውታል። ሆኖም መሠረታዊ ችግሩ ላይ ባለማተኮራቸው ኢሕአዴግ የሚፈልገውን ጨዋታ እየተጫወቱለት ነው። ይኸውም መንግሥት የአዲስ አበባን መስፋፋት ሰበብ አድርጎ ተጨማሪ ባለሥልጣናትን የሥርዓቱ ተገዥ ለማድረግ እና ተጨማሪ የሀብት መዝረፊያ መንገድ ለመክፈት፣ እንዲሁም የኦሮሞን ሕዝብ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል የማጥፋት ዘመቻ ነው ብለዋል። በዚህ አባባላቸው ባለሥልጣናትን የሥርዓቱ ተገዥ ማድረግም ሆነ ተጨማሪ የሀብት መዝረፊያ መንገድ የተባሉት የመቃወሚያ ነጥቦች በመሠረቱ የአዲስ አበባን መስፋፋት የሚቃወሙ አይደሉም። በመስፋፋቱ ሰበብ ይከተላሉ የተባሉት ችግሮች የሚያመለክቱት ውሳኔ ሰጭው መንግሥት ራሱ ሊታመን አለመቻሉን ነው እንጂ፤ ይህ መንግሥት ካልታመነ ደግሞ የሚወስደውን ትክክለኛ ይዘት ያላቸውንም ሆነ ትክክለኛ ይዘት የሌላቸውን አንድ ላይ ጭፍልቆ ሁሉንም መቃወም ነወይ የሚበጀው ወይስ ሌላ አማራጭ መውሰድ ? ስለአሜሪካ ያነሡት ጠቅላይ ግዛቶች /states/ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣን እንዳላቸው መጥቀሳቸው እንዳለ ሆኖ፤ በዘር /ethnicity/ የተመሠረተውን የኦሮሚያ ክልል ከዚያ ጋር ለማነፃፀር መሞከራቸው ወርቅንና ብረትን የማወዳደር ያህል ነው፤ ምክንያቱም ያ ሥርዓት ያለበትን አጠቃላይ ይዘት አብረው መውሰድ ስላለባቸው ነው። አሜሪካ በዘር፤ ቋንቋ፤ ሃይማኖት… ወዘተ ላይ የተመሠረተ ፈዴራሊዝም የላትም፤ አንድ አሜሪካዊ ከየትም ይምጣ የትም ይወለድ በየትኛውም ጠቅላይ ግዛት ተዘዋውሮ መኖር፣ መሥራት፤ ልጆቹን ማስተማር ይችላል፤ አሜሪካኖች በሁሉም ጠቅላይ ግዛትች የሚናገሩት ከቅኝ ግዛታቸው የወሰዱትን እንግሊዝኛን ሲሆን ያንን ቋንቋ በመጠቀማችው አደጉ እንጂ አልተጎዱበትም፤ ምክንያቱም ማንኛውም ቋንቋ (እንግሊዝኛ፣ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ጊዶልኛ፣ አገውኛ፣ ትግርኛ፣ ወዘተ ..) ለተገልጋዮቹ የመገናኛ መንገድ /medium of communication/ እንጂ ሐጢአት የለበትም፤ የአሜሪካ ጠቅላይ ግዛቶች (United States) የተፈጠሩት በታሪካዊ/ፖሊቲካዊ/ ጅኦግራፊ እንጂ በዘር ወይም በቋንቋ አይደለም። ኦሮሚያ ግን በቋንቋና ዘር አገርን እና ሕዝብን በመከፋፈል ሕዝብን ለያይቶ ለሚገዛው ኢሕአዴግ መንግሥት በመሣሪያነት እያገለገለ ነው። መቀላቀልንና ማንነትን የማጣት ጥያቄም ከጠባብ ብሔርተኝነት የሚመነጭ አመለካከት ነው፣ ምክንያቱም መነጣጠልን /isolationism/ የሚከተል ጎታች አስተሳሰብ ነው፤ ባለፉት 40 ዓመታት እንኳ እንዲህ ያሉ የውስጥ ችግሮች ባይኖሩብን ኖሮ የት መድረስ እንችል እንደነበር በአንፃሩ የበለፀጉ አገሮችን ታሪክ አነፃፅሮ በማየት መቀላቀልን /integration/ ለሕዝቦች መቀራረብና ማኅበራዊ ፍቅር ተጠቅመውበት እነሆ በእድገት ላይ አተኩረውና ከኛ ልቀው የሚገኙትን ምእራባውያን አገሮች አንጋጠን ልናያቸው ችለናል። ወረድ ብሎ ደግሞ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ውስጥ ላሉ ከተሞች ዕቅድ የማውጣት አቅሙም ሥልጣኑም የለውም ሲሉ፤ በሌላ በኩል ግን ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የቀረጥ ገቢ እንድታገኝ ተጠይቆ ለረዥም ጊዜ ሳይፈጸም መቆየቱን ጠቅሰዋል፤ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ አዲስ አባባም ሆነ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች በኦሮሚያ ሥር መሆናቸውን እንደሚቀበል ነው፤ ይህ ከሆነ የማካለል ተግባር የተፈጸመው በዚያው በኦሮሚያ ሥር ስለሆነ መሬት ተወሰደብን የሚለው ጥያቄ ትርጉም ያጣል።

በአገራችን ድልድይ አይሠራብን፤ መንገድ አይገነባብን፤ የአስኳላ ትምህርት ቤት አይከፈትብን፤ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአንድ … ዘመን የነበሩ ሲሆን፤ በአንፃሩ መንገድ በመሬታችን ካላለፈልን፤ ድልድይ ካልተሠራልን፤ ትምህርት ቤት ካልተከፈተልን በማለት ትግል የተደረገበትም ዘመን ነበር። እድገት አይደረግ ብሎ መሟገት ተገቢ አይደለም፤ ሆኖም ግንባታ ሲፈጸም የሕዝብ መብት እንዲከበር፤ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሕዝብ በተወካዩ አማካይነት በተገቢው ሁኔታ እንዲሳተፍ፤ እንዲሁም ግንባታው የሚያፈናቅለው ወገን ካለ ተገቢው ካሣ እንዲከፈለው ማድረግ የወግ እና ፍትሐዊ ነው። ቀጥሎ የተመለከተው ደግሞ አንዱን አካባቢ ከሌላው ጋር የመቀላቀል ተግባር የምእራባውያን እንጂ የኛ አይደለም “ ” ብለዋል። ይህ አባባል እኛ እርሻ የምናርሰው በሞፈርና ቀንበር ስለሆነ ትራክተርና ኮምባይን ሀርቨስተር አያስፈልገንም፤ ዲሞክራሲ የሚባል ነገርም በግሪክ ተፈጥሮ ምእራባውያን የሚጠቀሙበት ሥርዓት እንጂ የኛ አይደለም፤ አያስፈልገንም … የሚያሰኙ መሠረታዊ ስህተቶች ውስጥ ይጥለናል። ወደእውነተኛው ፊዴራሊዝም መመለስ ይገባናል በማለት ያስቀመጡት መደምደሚያ ራሱ አጠያያቂ ነው፤ ምክንያቱም በአገራችን የነበረው ፊውዳሊዝም ከዚያም የኮሚኒስት አቅጣጫን ይዞ የነበረው ፍጹም ማእከላውነትን የተከተለ አሪስቶክራቲክ አመራር የነበረ ሲሆን፤ ኢሕአዴግም በስም ፀረ -ኮሙኒዝም ቢመስልም ከደርግ የቀዳውን ኮሚኒስታዊ የአወቃቀር ሥርዓት የተከተለ አምባገነናዊ ሥርዓት ስለሆነ እንመለስበት የሚሉት ፊዴራሊዝም ሁሉቱንም አይመለከትም። ከዚያ በፊት የነበሩት የኦሮሞ አፍ ሲነገርባቸው የነበሩት ግዛቶች ጅማ፤ ሊሙ -እናርያ፤ ጎማ፣ ጉማና ጌራ በሁለት ትውልድ ውስጥ በሚለካ ጊዜ ውስጥ የነበሩ ታዳጊ ፊውዳላዊ አመራር ይከተሉ የነበሩ ትናንሽ የጊቤ አካባቢ መንግሥታት ነበሩ እንጂ አሁን አሮሚያ ከተባለው ክልል ጋር የማይመጣጠኑ ስለሆነ ፊዴራላዊ ይዘትም ፅንሰ -ሐሳብም አልነበራቸውም፤ እነሱም ቢሆኑ በግዛት ስፋት ለማደግ እርስበርሳቸው ሲዋጉ የነበሩ እንጂ ፊዴራሊዝምን አያውቁትም። ሆኖም እንመለስበት የሚሉት መቼ ሥራ ላይ የዋለ ፈዴራሊዝም ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ስለሆነም አዲስ አበባ ኦሮሚያ የሚባል መንግሥት ከመፈጠሩ በፊት የነበረችና የሁሉም ኢትዮጵያውያን መገልገያ ዋና ከተማ /metropolitan city/ መሆኗ መታወቅ አለበት። የፖርቲው አመለካከት ችግር ሊንፀባረቅ የቻለው ከርዕዮተ ዓለማቸው ጋር ከሞቱ 60 ዓመታት ካለፋቸው ጆሲፍ ስታሊን እና ብላድሚር ኤሊኽ ሌኒን ለብሔረሰቦች ችግር መፍቻ ተጠቅመውበት የነበረውን ያውም ፖላንድ ላይ ተሞክሮ ጆርጅያ ላይ የከሸፈውን ፅንሰ -ሐሳብ /defunct theory/ መመሪያቸው በማድረጋቸው ነው፤ የኢሕአዴግም አመሠራረት ይህንኑ ጽንሰ -ሐሳብ የተከተለ ነው። ብሔርተኝነት አልፎ አልፎ በታዳጊ አገሮች የሚገኙ ጠባብ ብሔርተኞች የተወሰኑ ሕዝቦችን በቋንቋና ዘር ለይተው እንደፈረስ በመጋለብ የሥልጣን ጥማቸውን የሚያረኩበት ያረጀ ፅንሰ -ሐሳብ ሲሆን ኢምፔሪያሊስቶችም ትናንሽ አሻንጉሊት መንግሥታትን በመፍጠር አገሮችን አያዳከመው በእጅ አዙር የሚቆጣጠሩበት ዘዴ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ለሕዝቦች የጋራ እና የእኩልነት እድገት፣ ብልፅግናና ማኅበራዊ ግንኙነት እውነተኛ ወደሚሉት ፊዴራሊዝም ለመምጣት የሚታሰብ ከሆነ አገርን በመልክ – አምድር /ጂኦግራፊያ/ አቀማመጥ ላይ ባማከለ ሥልት ማዋቀር እንጂ ተስማምተው ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦችን በዘርና ቋንቋ ከፋፍሎ በማለያየት አይደለም፤ ሕዝቦች ሁሉ ተባብረው ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ መንግሥት እንዲፈጠር በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፖርቲዎች በጋራ የአገር ጉዳይ ላይ መተባበር ነው የሚያስፈልጋቸው፤ በትግል ወቅት በጋራ የአገር ጉዳዮች ላይ መተባበር ያልቻሉ ፖርቲዎች የፌዴራላዊ ፅንሰ -ሐሳብን ተከትለናል ለማለት አይችሉም፤ ምክንያቱም ሊያስተባብራቸው በሚገባ የጋራ ትግል ላይ ያልተባበሩ ፖርቲዎች የዕድል ጉዳይ ሆኖ በእውነተኛ ፊዴራሊዝም የሚሳተፉበት ሁኔታ ቢያጋጥማቸው እንኳ ተግባራዊ የማድረግ ልምዱም ብቃቱም ስለማይኖራቸው ነው። በትግሉ ወቅት ሕዝቦችን በእኩልነት የማያይ ፖርቲ ሥልጣን ላይ ሲወጣ ቀድሞ ያላሳየውን ባህርይ ከየት ሊያመጣ እንደሚችል አሳማኝ አይደለም። ከላይ የተጠቁሱት ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆኖ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በአንድነት የሚያይ ወገን የአዲስ አበባን መስፋፋት አንደችግር እይመለከትም፡፡ ስለዚህ ጥያቂያችሁ ወደትክክለኛ ፊዴራሊዝም እንዲያመራ ፖርቲያችሁ በዘር ሳይሆን በጂኦግራፊ፤ ወይም ዘርና፤ ሃይማኖትና ቋንቋን በማይለያይ አገር -አቀፋዊ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ቢሆን ሕዝቦች ሳይለያዩ የተሻለ ልማት፤ ፍትሐዊ አመራር እና ኅብረት ሊያመጡ የሚችሉ መሪዎችን በመምረጥ ላይ ብቻ ያተኩራሉ። ብሔርተኛነት ሕዝቦችን ያራርቃል፤ እርስበርስ መተማመንን ያጠፋል፡፡ ነገር ግን ሕዝቦች ሲተባበሩ የጋራ ችግራቸውን በጋራ ማስወገድ ስለሚችሉ ዲሞክራሲ እውን ለማድረግ የተመቻቸ ይሆናል፤ ሰላም ይፈጠራል፤ አገርም ትበለጽጋለች። በትሐት የሚመራውና የአሻንጉሊቶች ጥምረት የሆነው ኢሕአዴግ እንደሆነ እንኳን መሬት ማካለል፣ የማከራየትም፤ የመሽጥም፤ የመስጠትም ተግባር ፈጽሟል፤ እንኳን መሬት ዛፍ አስቆርጦ ሽጧል፤ የአገር ሀብት የሆነን የወርቅ ማዕድን ሽጧል፤ የሚጠቅመው ሆኖ ካገኘው በ 24 ሰዓት ውስጥ የፈለገውን ሕግ ያወጣል፤ ለሕግ ተገዥ አይደለም፤ ከሕግ በላይ እንጂ። ፈዴራል የሚባሉ ክልሎች ስማዊ /symbolical /እንጂ እውነተኛ ፈዴራል ስለአይደሉ ጥያቄ የቀረበበት ጉዳይ የበሽታው ምልክት ላይ እንጂ በበሽታው በራሱ ላይ ስላልሆነ ችግሩ ትክክለኛ መንግሥት የማምጣቱ ጉዳይ ነው። በአንድ በኩል በዘር ላይ የተመሠረተን አከላለል ተቀብለው የከፋፋዩን እና ጨዋታ እየተጫወቱ በሌላ በኩል ፍትሕ ተጥሷል ማለት ለአንበሳ ጊደር ሰጥቶ አንበሳውን ሥጋ ስጠኝ እንደ ማለት ነው። ስለዚህ ድካማችሁ ውጤታማ እንዲሆን ትግላችሁ ሕዝቦችን ያማከለ ከብሔርተኛነት ነፃ የሆነ ፕሮግራም ቢቀይስ እና ዋናው ችግር ላይ ቢያተኩር ይመረጣል።

ተፈራ ድንበሩ

posted by tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s