መንግሥት ተቃውሞውን ለማርገብ ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀም እነ አምነስቲ አሳሰቡ

ትላንት በአ.አ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

መንግሥት በኦሮሚያ የተነሳውን መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ለማርገብ ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠብ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ያሳሰቡ ሲሆን መንግሥት በበኩሉ፤ ሁኔታው ወደ ለየለት ሥርዓት አልበኝነት መቀየሩን ገልፆ ሁከቱን ለማስቆም የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
መድረክ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ ተቃውሞውን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት 32 ሰዎች በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ያስታወቀ ሲሆን አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሟቾች ቁጥር ወደ 40 እንደሚጠጋ ገልጿል። መንግሥት በግጭቱ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ቢያምንም የሟቾች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አልጠቀሰም፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች ሰሞኑን በጉዳዩ ላይ ባወጡት መግለጫ፤ መንግስት ተቃውሞ በሚያሰሙ አካላት ላይ ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠብ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት የዜጎችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና ሰላማዊ ተቃውሞ የማድረግ መብት ከማክበር ይልቅ ጉዳዩን ከሽብርተኝነት ጋር  ማያያዙ አግባብ አይደለም ብሏል አምነስቲ፡፡
“መንግሥት ተቃውሞ ያሰሙትን ሁሉ በሽብርተኝነት ፈርጇል” ያለው አምነስቲ፤ “ከህግ አግባብ ውጪ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈፀምን ግድያ ከማውገዝ ይልቅ ተቃዋሚዎቹን ሽብርተኛና ሀገር ሊበጠብጡ የተነሱ ናቸው ማለቱ አግባብ አይደለም” ሲል ተቃውሟል። የውዝግቡ መነሻ ከሆነው ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በ2006 ዓ.ም ተመሳሳይ ግጭት ተፈጥሮ የበርካቶች ህይወት ጠፍቶ እንደነበር ያስታወሰው ሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ፤ ያኔም ሆነ አሁን በተነሳው ተቃውሞ በርካቶች መገደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በተነሳው ተቃውሞ አብዛኞቹ የተቃውሞው ተሳታፊዎች ተቃውሞ ስላቀረቡ ብቻ ጉዳዩ ከሽብር ተቆጥሮ በሽብር እንደተፈረደባቸው የጠቀሰው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ በወቅቱ ታስረው የነበሩ ተማሪዎች በእስር ቤት ውስጥ ግርፋትና ስቃይ ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
ከሦስት ሳምንታት በላይ ለዘለቀው ተቃውሞ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎቹ ከመጠን በላይ ኃይል እንዳይጠቀሙ ሊከላከል ይገባ ነበር ያለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፤ ህግ የጣሱ አካላት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው ብሏል፡፡
መድረክም በበኩሉ፤ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆምና ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ካሳ ተከፍሎ ግድያውን የፈፀሙ ወገኖች በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ ከማስተር ፕላኑ ጋር ተያይዞ የተነሳው ተቃውሞ ባህርዩን ለውጦ ወደለየለት ሁከት  መቀየሩን ጠቁሞ የታጠቁ ኃይሎች ስርአት እናፈርሳለን እያሉ በመሆኑ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ በእነዚህ ኃይሎች የጥፋት እርምጃም የሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ፣ የመንግሥትና የህዝብ እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ አመራሮች ቤት ንብረት ወድሟል ያለው መንግሥት፤ የየወረዳዎቹ የመንግሥት አመራሮችና የፀጥታ አካላትም በግልፅ ጥቃት ተከፍቶባቸዋል ብሏል፡፡
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት መግለጫ፤ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች ስርአት አልበኝነት መስፈኑን ጠቁመው አስፓልቶች መቆፈራቸውን፤ ፋብሪካዎችና የገበሬ ማሳዎች ላይም ጥቃት እየተፈፀመባቸው እንደሆነ በመግለፅ መንግስት ይሄን ሁከት ለማስቆም አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ተቃውሞው አቅጣጫውን እየቀየረ መሆኑን አስረድተው፤ መንግስታቸው ተከታታይ እርምጃ እንደሚወስድና ሀገሪቱን የማረጋጋት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
ተቃውሞውን ተከትሎ በሶስት የኔዘርላንድ የአበባ እርሻዎች ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸውና ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ እንደወደሙ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ያስታወቀ ሲሆን ዳንጎቴ ሲሚንቶም የጥቃቱ ሰለባ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ ለነዚህ የልማት ድርጅቶች አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጿል፡፡  በወንጪ ከተማ የሚገኘው የሶላግሮ ኢንዱስትሪም ፤ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመበት አስታውቋል፡፡
ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘው ተቃውሞ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የኦሮሚያ አካባቢዎች በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ግጭቱ ማየሉን መንግስት ያስታወቀ ሲሆን በኢጃጂ፣ በግንደበረት፣ በአምቦ፣ ወሊሶ፣ አርሲ ዶዶላ፣ ሜታ ሮቢ፣ ሙገር፣ ሃረማያ፣ አወዳይ፣ ደምቢዶሎ፣ ዲላላ፣ አይራ ጉሊሶ፣ ነጆ፣ ዪብዶ፣ መቱ፣ ወንጪ፣ ቡራዩና ሱሉልታ በመሳሰሉት አካባቢዎች ሁከቱ መቀጠሉንና በአብዛኞቹ ከተሞችም የፀጥታ ኃይሎችና ተቃዋሚዎች መጋጨታቸውን ገልፆ ነበር፡፡
መንግሥት በሰጠው መግለጫ፤ ግጭቱን ተከትሎ በሰዎች ላይ ከደረሰው ሞት በተጨማሪ ከፍተኛ የንብረት ውድመት የደረሰ ሲሆን ባንኮች፣ የግል ድርጅቶች፣ የእርሻ ማሳዎች፣ የመንግሥት አስተዳደር ፅ/ቤቶች፣ የወረዳና ቀበሌ አመራር መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ፍ/ቤቶች  እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ እስረኞች ከማረሚያ ቤት እንዲያመልጡ ተደርጓል ብሏል – መንግሥት፡፡
ተቃውሞው ሲጀምር በተማሪዎች ይሁን እንጂ አርሶ አደሮችና ሰራተኞች በስፋት እንደተቀላቀሉት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ግጭቱ ባየለበት የደቡብ ምዕራብና ምዕራብ ኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ህብረተሰቡ ወደየከተሞቹ የሚያስገቡ አውራ ጎዳናዎችን በድንጋይና በእንጨት በመዘጋጋት፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ ጥረት እያደረጉ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ከአዲስ አበባ በ20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሱሉልታ ከተማ በተነሳው ተቃውሞ ወደ ጎጃም መውጫ መንገድን በመቆፈር እንዲዘጋ መደረጉ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትላንትና ጠዋት ተቃውሞ ተነስቶ የነበረ ሲሆን በፌደራል ፖሊስ ሃይል መገታቱን ምንጮች ገለጹ፡፡ ለተቃውሞው መነሻ ነው የተባለው ሃሙስ ሌሊት ፖሊስ 2 ሴት ተማሪዎችን  ከዶርም እያለቀሱ ወዳልታወቀ ቦታ መውሰዱ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በነጋታው አርብ ጠዋት ተማሪዎች በሰልፍ ወደ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ቢሮ በማምራት፣ሌሊት የተወሰዱት ጓደኞቻችን የት ገቡ ሲሉ ፕሬዚዳንቱን የጠየቁ ሲሆን  አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ምንጮች ተናግረዋ

ል፡፡ በዚህ የተናደዱት ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ከግቢው ለመውጣት ሙከራ ቢያደርጉም ፖሊስ ደርሶ እንዳገታቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም ከፖሊስ ጋር የተፈጠረ ግጭት አለመኖሩን የዩኒቨርሲቲው መምህራን ነግረውናል፡፡ ትላንት ከሰዓት በኋላ ግቢው ጭር ብሎ እንደነበር የታወቀ ሲሆን ለጥቂት ሰዓታትም ከዩኒቨርሲቲው እስከ አሜሪካ ኤምባሲ መንገድ ተዘግቶ ነበር ተብሏል፡፡

addisadmassnews

posted tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s