የእምዬ ኢትዮጵያ ኑዛዜ – የመጨረሻው ደወል!

አርጤክስስ የሚባል ንጉሥ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባት አገሮች በሚገዛበት ዘመን፣ ሕዝቡዋ ከምድር ገጽ እንዲወገድ የተወሰነባት ስደተኛዋና ወላጅ አልባዋ የማደጎ ልጅ አስቴር የምትባል ሴት፣ በስደት ምድር ከግዞት ተላቃ፣ ከስደተኞች መንደር ወጥታ የንጉሥ ሚስት እና ንግሥት ለመሆን በታደለችበት ዘመን፣ ወገኖችዋ በተገኙበት ስፍራ ሁሉ እንዲገደሉ ተወስኖ፣ ግድያው ሊፈጸም ጥቂት ቀናት ሲቀረው፣ የንጉሡን የአሰራር ህግ ተላልፋ፣ በሕይወቱዋ ተወራረዳ፣ ብሞትም ልሙት ብላ፣ በነፍሱዋ ቆርጣ ንጉሱ ዘንድ ቀርባ፣ ስለ ሕዝቡዋ ጥብቅና ቆመችና፣ እኔ በሕዝቤ ላይ የሚወርደውን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ወይስ የዘመዶቼን ጥፋት አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ብላ ጠየቀች፣ ቀደም ሲል በንጉሡ ትእዛዝ የወጣው አዋጅ በአዋጅ ተሸሮ ሕዝቡዋም ከመገደል ተርፎ፣ ሕዝብዋ እንዲገደል ሊያደርግ የነበረው ክፉው ሐማ እና አስሩ ልጆቹ በስቅላት እንዲቀጡ ንጉሶ አዝዞ፣ ሕዝቡዋን ልታተርፍ የቻለችው ስደተኛዋ፣ ተራ ድሐዋ፣ ዘመድ አልባዋ፣ የማደጎ ልጅ አስቴር እንደነበረች፣ የክርስትና እምነት ሰነድ በሆነው መፅሐፍ ቅዱስ በመጽሐፈ አስቴር ላይ እንደተጻፈ ታሪክ ይነግረናል፡፡

እኛስ በስደት ምድር ያለን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ትውልድን አምጠን የወለድን እናቶች እና አባቶች፣ በምድራችን ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ ስደት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለረሐብ አደጋ መጋለጥ፣ በእስር ቤት ሲሰቃዩና ገና ሊገደል ያለውን ትውልድ እያየን፣ እኛ ግን በተሸለሙ ቤቶቻችን ውስጥ ተሸጉጠን፣ አፈራንው ባልንው ጊዜያዊ ሐብት እና ባካበትንው አውቀት ጉያ ውስጥ ተሸሽገን፣ በዝምታ የምናልፍበት ጊዜው አሁን ነውን? ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ የሚባል ቃል ተደጋግሞ ሲነገር እንሰማለን፣ እንድንትበባበር የሚያደርግን ነገር ምንድን ነው ከሚለው ይልቅ፣ እንዳንተባበር የሚያደርገን ነገር ምንድንን ነው ብለን ብንጠይቅ እና ለዛ ሕመም ፈውስ ብንፈልግስ? ማን እንዲያስተባብረን ይሆን የምንፈልገው? በፍርሐት ገመድ የተተበተበውን፣ የጋራ ማንነቱ የተዘረፈበትን፣ ከጎኑ ካለው ወገኑ ጋር በጠላትነት የሚተያየውን፣ እርስ በእርሱ እየተፈራራና ሳይተማመን የሚኖረውን፣ በእውነት እንዳያስብ፣ እውነትን እንዳይናገር፣ የተገደደውን፣ የሕሊናና እና የአካል እስረኛውን ሕዝባችንን ግን፣ እንደ ፖለቲከኛ አለያም እንደ ሐይማኖተኛ ሳይሆን እንደሰው ላስተባብርህ? ናልኝ ልጄ? ነይልኝ ልጄ? የሚል አስተባባሪ፣ ሽማግሌ፣ አዛውንት፣ እናት፣ አባት፣ አረጋዊት፣ወጣት፣ ካህን፣ ሼክ፣ ኢማም፣ አጥተን ይሆን? ወይስ እነርሱን ከመጤፍ የሚቆጥራቸው ትውልድ ጠፍቶ ይሆን?

ለአገራችን መፍትሔ ሊያመጡልን የሚችሉ እና የተገባቸው ፖለቲከኞች ብቻ የሆኑ ይመስል፣ አይናችንን ከፖለቲከኞች ላይ ማንሳት አቃተን፣ ምናልባትም የችግሩ ዋነኛ ምንጭ እነርሱስ ቢሆኑስ? በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ደጋፊዎች ወይም ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ በሰላማዊ አለያም በትጥቅ ትግል አንዳቸው ሌላኛውን እስኪያሸንፉ ድረስ፣ እኛ ከሁለቱም ወገን የለንበትም፣ ፖለቲካ አንፈልግም፣ አያገባንም የምንልስ፣ እስከመቼ ነው የዜግነት፣ የሕሊና እና ሰው የመሆን ግዴታችንን የምንወጣው?

እውቀት አዳብረዋል ከሚባሉት ምሁራን ውስጥ ከጥቂቶቹ በስተቀር ከተራው ህዝብ ጋር ለመመካከር፣ ሌላውን በመናቃቸው፣ ከሰው ሁሉ እርቀው በመቀመጣቸው፣ ዝምታቸው በትውልድ ላይ ያደረሰውን ጉዳት የዘነጉት ይመስላል፣ ሰውን በሰውነቱ ከመናቅ ያነሰስ ምንኛ አላዋቂነትስ ይኖር ይሆን? ሕመማችን ነውና ፈውስ ያስፈልገናል፡፡

ዛሬ እንዲት ትግሪኛ ተናጋሪ እናት አንዱ ልጁዋ የወያኔ ፖለቲካ አራማጅ ሆኖ፣ ሌላኛው ደግሞ ያንን በጦርነት ለመዋጋት ኤርትራ በረሐ ገብቶ፣ ሊሞት አለያም ወንድሙን ሊገድል መሳሪያውን እየወለወለ እየሰማን፣ የዛች እናት ጭንቀት ካልተሰማን፣ አንዲት ኦሮምኛ ቁዋንቁዋ ተናጋሪ እናት አንደኛው ልጁዋ ኦሆዲድ ፣ ሌላኛዋ ልጁዋ ደግሞ ኦነግ ሆኖ አንዱ ሌላውን ሲያሳድድ ማየት፣ ማሕፀንዋን አጋርታ ወልዳ ላሳደገች እናት፣ ለየትኛው ልጅዋ እንደምታደላ ወላጅ ይፍረደው? አማርኛ ተናጋሪዋ እናት፣ እንዱ ልጁዋ የብአዴን ጉዳይ አስፈጸሚ ሆኖ፣ ከተከዜ ወዲያ ማዶ ባለው በረሐ ላይ ያለው ሌላው ልጅዋ ደግሞ አርበኞች ግንቦት ሰባት ሆኖ ወንደሙን ሊጋጠም ቀረርቶ ሲያሰማ፣ እናት ወደ ፈጣሪዋ እያንጋጠጠች፣ እባክህ አምላኬ አንዱ ልጄ ሌላውን ልጄን ሲገድል ከምታሳየኝ የኔን እድሜ አሳጠረህ ይህን ጉድ ሳልሰማ ወደ ቤትህ ሰብስበኝ እያለች ስትቃትት ይታያችሁ፡፡

በአገሪቱዋ ደርሶ አማራ፣ ትግሬና ኦሮሞ ብቻ የዛች አገር ምርጥ ዜጋ ይመስል ፣ለእነርሱ በስማቸው ድርጅት ተበጅቶላቸው ፣ሌላው ከሰማንያ በላይ ቁዋንቁዋ የሚናገረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ የደቡብ ሕዝቦች በሚባል አንድ ከረጢት ውስጥ የተካተተው ሕዝብ ኢሕዲግ የሚባል የውሸት ዣንጣላ ስር ተሸጉጦ፣   በነዚህ ከረጢቶች ውስጥ መካተት ያልቻለ ከተለያዩ ጎሳዎች ተቀላቅሎ የተወለደው ትውልድ ደግሞ የጋራ ከረጢት እሰኪገኝለት ድረስ የዚህ ሁሉ ሕዝብ እናት በየቤቱ በልጆችዋ መጎነታተል፣ በየቤተ እምነቱ እየሮጠች፣ ጸሎቱዋ ቢሰማ ለመክፈል የምትሳለው የስዕለት ዕዳ፣ መቼ እንደምትከፍለው በልማት በልጽጌያለሁ የሚለው የአገሪቱ ካዝና ብቻ ይመልሰው፡፡

የዚህ ሁሉ መከራ መሐንዲስ ነው የሚባለው ወያኔ ይውደም! ተብሎ ሲረገም፣ ሲወገዝ እና መፈክር ሲሰተጋባ፣አርባ አመት አለፈው፣ በእርግጥ ወያኔ የሚባለው ቡድን በእርግማን አለያም በትጥቅ ትግል ብቻ የሚወድም፣ አንድ ሥፍራ ውስጥ ተከልሎ የተቀመጠ ጠላት ይሆን? ወይስ መርዙን በትውልድ መሐል የረጨና ትውልድን ሁሉ የበከለ የመርዝ ብልቃጥ? አገርን ያህል ነገር እስከ መገንጠል ድረስ የሚፈቅድ ህግ ያወጣው የአገር ጠላት ወያኔ ብቻ ነው? ወይስ እኔ ከደሙ ነጻ ነኝ የሚል የወያኔ ወዳጅ የሆኑት መሐንዲሶችስ፣ እነርሱስ ለዛሬው መከራ ከተጠያቂነት ነጻ ናቸውን? ማንም ይህን መድፈር እና መነካካት ባይፈልግ፣ ይህ የሆነ እና እየሆነ ያለ ሐቅ ነውና የበሽታችንን ምንጩን አውቅን እውነቱን ተነጋግረን ልንፈውስ ይገባናል፡፡

ወያኔ በረሐ በነበረበት ዘመን ወዲ አማራ! እያለ ትግሪኛ የማይናገረውን ሕዝብ ሁሉ በወዲ አማራ ከረጢት ውስጥ ጨምሮ፣ በጥላቻ መርዙ ተከታዮቹን በወቅቱ እንደበከለው ሁሉ፣ ሌላው ከትገሪኛ ቁዋንቁዋ ተናጋሪነት ውጭ ያለው ኢትዪጵያዊ ደግሞ በተራው ወዲ ትግሬ! ብሎ ትግሬውን ሁሉ የመጥላት አባዜ ይዞት፣ ወያኔ በበከለው መርዝ ተነድፎ ወንደሙን እንዳያጠቃ እጅግ የሚያሳስብ ዘመን ላይ የተደረሰ ስለሚመስል፣ እንክርዳዱን ስንለቅም ስንዴውንም ከእርሱ ጋር እንዳንነቅለው ስጋት አለኝ እና የትውልድ እናቶች እና አባቶች ይህን እያየን በዝምታ ማለፍ፣ ትላንት በአውሮፓ ዘር እየለየ ያጨደው የናዚ ታሪክ ፣ በአፍሪካም የሩዋንዳ ህዝብ ታሪክ በእኛ ላይ ሳይደርስ ማርከሻውን በፍጥነት የምናፈላልግበት ጊዜው አሁን ነውና፣ ይህንን እያየን እና እየሰማን ችላ ብንል የዚህ ትውልድ ደም በእጃችን እንደሚሆን፣ ሳሳውቃችሁ ሰማይና ምድርን ምስክር አድርጌ ነውና ወገኔ ሆይ ችላ አትበል!

የውጭ መንግሥታት ከምድራችን ጋር የተያያዘ ልዩ ልዩ አጀንዳና ጥቅም ስላላቸው፣ ምናልባትም አዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችን የሚፈልጉት አይጠፉም፣ መሳሪያ አምራቾችም ቢሆኑ የሚያመርቱትን መሳሪያ ማራገፊያ የንግድ ስፍራ ያስፈልጋቸዋል፣ የኛ ምድር ደግሞ ለዛ እየተመቻቸላቸው ነውና በእሳቱ ላይ ነዳጅ ከመጨመር የሚቆጠቡ አይመስለኝም፡፡

በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ በተበተንክበት አገር ሁሉ፣ የመደራጀት መብት አለኝ ብለህ የተለያየ ስም አውጥተህ የፖለቲካ ድርጅት ነኝ ብለህ ስትቁዋቁዋም፣ ባእዳን በገንዘብም በሞራልም የረዱህ የሚመስልህ ሁሉ ሆይ! እነርሱ የሚረዱህ ላንተ አስበው ሳይሆን ነገ የምታስፈጽምላቸውን አጀንዳ እንዴት እንደምታሰፈጸምላቸው ለማመቻቸት እያዘጋጁህ ነውና፣ የገንዘብም የሥልጣንም ጥምህን አቁምና፣ መስቀልኛ መንገድ ላይ ባለው ምድርህና ሕዝብህ ደም መነገድህን ትተህ ፣ ከተጸየፍክው ወንድምህ፣ እህትህ፣ የአገርህ ልጅ ጋር ለመቆራኘት ቀበቶህን አጥብቀህ እንዴት አድርገን ለጋራ ችግራችንን የጋራ መፍትሔ እንፈልግ እያልክ ምከር! አደራ ልጄ ሆይ! አለም አቀፉ ችግር እየተባባሰ ሲሄድ የተጠለልክበት ባዕድ አገርም የራሱ ችግር እየበዛ ሊሄድ ይችላልና፣ ከናቅህው እና ከተፀየፍክው ወንድምህ ጋር ይቅር ተባብለህ ታረቅ፣ አስታራቂ አትፈልግ፣ ኩራትና ትዕቢትን አስወግደህ ጥለህ፣ ከወንድምህ እና ከእህትህ ጋር ታረቅ! ሌላ አማራጭ የለህምና!

እኛ ራሳችን ከማንም አንበልጥም ወይም ከማንም አናንስምም የሚል ማንነት ማዳበር ያስፈልገናል፣ ሁሌ የበታችነት ስሜት ስለሚሰማን፣ ራሳችንንም ስለምንንቅ፣ ለችግራችን ሁሉ መፍትሔ ሌሎች እንዲያመጡልን እንፈልጋለን፣ ጥቁሮችን የሚጠላውን የነጮች ዘረኛ አመለካከትን እየተቃወምን፣ ነጮቾችን የሚጠላ ሌላ ዘረኝነት በውስጣችን አዳብረን ትዕቢት እና ጥላቻ በውስጣችን አርግዘን፣ ባገራችንም ዘረኝነትን እየተቃወምን፣ እኛው ዘረኞች ሆነን፣ ሌላውን ዘር እንጠላላን፣ በየጎጥ ድርጅታችን ዣንጥላ ውስጥ ለተሸጎጥን ሁሉ፣ የምነግራችሁ አንድ እውነት አለኝ፣ ይኀውም ቀደም ሲል በጎጥ ያደራጁን ሰዎች ወደ ሥልጣን መወጣጫ መሠላል ስላስፈለጋቸው፣ እነእርሱ እኛን በተገደበ  የጎጥ ወይም የሐይማኖት ድርጅት ከረጢት ውስጥ አሽገው አስቀምጠውን ከከረጢቱ ውጭ እንዳናስብ፣ ሌላውን እንዳንጠጋ፣ ከሌላው ጋር እንዳንነጋገገር፣ የሌላውን ሐሳብ እንዳንሰማ፣ አደንዝዘውን፣ እነርሱ ግን በስውር ከሁሉ ጋር ይወዳጁብናልና፣ ሕዝቤ ሆይ ንቃ! ከእንቅልፍህም የመባነኛ ጊዜው አሁን ነውና! 

ይጠቅመኛል ብለህ በተደራጀህበት ሐይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ማሃበራዊ ድርጅቶች ሁሉ ያሉ መሪዎችህን የሚገባቸውን ፍቅርና ከበሬታ አትንፈጋቸው፣ የማሰብ እና የመናገር ነጻነትህን ግን እንዲዘርፉህ አትፍቀድላቸው፡፡የምድረ ኢትዮጵያ ልጆች ሌላ አስታራቂ የለም እና እኛው እርስ እርሳችን እንታረቅ?

በውጭ ሶሰት ሚሊዮን ስደተኛ አለን ብለን እንኩዋን ብንገምት፣ እያንዳንዳችን በአገር ቤት በትንሹ እንኩዋን ሀያ ዘመዶች ቢኖረን፣ ድምሩ ወደ ስድሳ ሚሊዮን  የሚጠጋ ሕዝብ የእኛው ወገን እና ቤተሰብ  በአገር ውስጥ አለ ማለት ነው፣ እኛ በባእድ ምድር ቀን እና ሌሊት እየተጋን፣ ካፈራንው ጥሪት፣ እኛ በልተን እያደርን እነእርሱን እንዴት ዝም እንላለን እያልን፣ በአገር ቤት ላሉ ወገኖቻችንን በመጠኑም ቢሆን በኢኮኖሚ ደግፈን፣ ወላጆቻችንን ጡረን፣ ወንድም እህቶቻችንን አስተምረን፣  ለአገሪቱዋ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በመሆን የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆነን አገር እየገነባን እያለን፣ በውጭ ያለንውን የምድረ ኢትዮጵያ ልጆች ከእርሱ ጋር ተባበብረው ለልማት አጀንዳው ተባባሪዎች ከሆኑት ውጭ ያለውን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ፣ የአባትነት እና የእረኝነት ሥልጣኑን በገዛ እጁ ያስነጠቀውን፣ ልጆቹን እንደ አመላቸው መዳኘት ያልቻለውን መንግስት ተብዬውን፣  በየእስር ቤቱ ስላጎረው ሕዝብ፣ በየጊዜው ስለሚገድለው ሕዝብ፣ ከአገር ስለሚያሰድደው ሕዝብ፣ ስለሚጠፋው ሕዝብ፣ በረሐብ ስለሚያልቀው ሕዝብ፣ በእጅህ የትውልድ ደም አለና፣ ለፍርድ ልትቀርብ፣ ከሥልጣንህም በሰላማዊ መንገድ ወደህና ፈቅደህ ልትወርድ፣ የአገሪቱ ሕዝብ ወዶ ለመረጠው፣ ሁሉን ሰብሳቢ፣ ጥበበኛ፣ ሩህሩህ፣ ታጋሽ አመራር ልታስረክብ ይገባል! ብለን ልናሳምነውም ልናስገድደውም ይገባል፡፡

እንዴት? ትሉኝ ይሆናል፣ መልሱ መጀመሪያ ትውልድ አገራችን፣ ዘር ማንዘሮቻችን በደምና በአጥንታቸው የገነቡዋት አገር መሆንዋን፣ እኛም ሳንወድ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ አለያም በማሐበራዊ ችግር ምክንያት ተገደን ተገፍተን የወጣንና መብታችንን ተዘርፎ በባእድ ምድር የምንከራተት ሕዝቦች መሆናችንን ስናምን፣ የዛች ምድር ትውልዶች እና ባለመብቶች መሆናችንን ስናምን፣ እና የተነጠቀብንን መብት ማስመለስ እንችላለንም ብለን ስናምን፣ ለዚህም ወፍራም እውነት ጨክነን ስንነሳ ብቻ ነው! ይህንን ሀቅ የባዕድ ምድር ማንነታችን ከቀጠለብን ማንነት ጋር አዋህደን፣ እየካድንው ያለውንማንነታችንን እንቀበል ፣ እንመንበትም፣ እነ አሜሪካም፣ እነ አውሮፓም፣ እነቻይናም፣ እነ አረብ አገሮችም፣ እነ እንተናም እነ እንቶኔም እንኩዋን ያገባናል ብለው፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ይፈተፍቱ የለምን? እኛማ ደምና አጥንታችን ከዛች ምድር አፈር የበቀልንማ እንዴታ አያገባን? እንግዲያውስ ለዚህ መልካም ስራ መተባበበር የምትፈልግ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኤትዮጵያዊ ሁሉ መልካሙን እጆቻችንን እና ቅንነት የተሞላበት ልባችንን ጨክነን እናያይዝ! የምላችሁ ትውልድን እንዳማጠች እናት፣ ትውልድን እየገበሩና ገና ሊገብሩ ባሉ የትውልድ ወላጆች ስም በመማፀንም ነው?

እኔ አንዲት ድሐ የጠለቀ እውቀት የሌለኝ ተራ ትንሽ እናት ነኝ ፣ አንድ ነገር ግን አውቃለሁ፣ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ ክልል ውስጥ በመገኘቴ፣ በፖለቲካ ጦስ እስከዛሬ ድረስ ከትውልድ ምድሬ ላይ ትውልድ ሲያልቅ፣ በተለይ ክፉና ደጉን ጠንቅቆ የማያውቅ፣ በትኩስ ስሜት የሚነዳውን ወጣቱን ትውልድ በምድሪቱዋ የፈለቀ ፖለቲካ ድርጅት ሁሉ መሳሪያ ሲያደርገውና ማገዶ እያደረገ ሲያስጨርሰው፣ እንደ በግ እየተነዳ ሲታረድ፣ ባለፉት አርባ ዓመታት በተለይም ባለፉትሀያ አራት ዓመታት ደግሞ እጅግ በከፋ መልኩ አይቻለሁና፣ ይህ እርግማንና እርኩሰት እየቀጠለ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ እያየሁ ዝም ማለት ትውልድን እንዳማጠች እናት አይሆንልኝም፣ እኔ በሕዝቤ ላይ የሚወርደውን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ወይስ የዘመዶቼን ጥፋት አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ብዬ ለመነሳት ሰው መሆኔ ብቻ፣ እናት መሆኔ ብቻ ግድ ይለኛል፣ ሰው በሐይሉ አይበረታምና ያበረታኝ እና ያስጨከነኝም እግዚአብሔር ክብሩን ይወሰድና ወገኔ ሆይ ችላ አንበል!

ፈሪሐ እግዚአብሔር የሆነው ሕዝባችን በየቤተ እምነቱ እግዚኦ ሲል ከረመ፣ ምነው እግዜር ጨከነክብን? ይላል፣ እርሱ ነው እኛ ለበጎ ነገር ላለመተባበር የጨከንን? ላለመዋደድ የጨከንን? ይቅር ላለመባባል የጨከንንን? እኛስ የራሳችንን ጥፋት በማመን ራሳችንን ተጠያቂስ በማድረግ ለምን አንጀምርም? ለዚህ በጎ ስራ እንነቃቃ እና ለተግባርም እንጨክን? ላለፉት በሺህ የሚቆጠሩ ዘመናት ተዋደን፣ ተዋልደን በፍቅርና በመግባባት፣ በደስታና በሐዘን ጊዜ ሁሉ እንደተቃቀፍንው፣ እስላም ክርስቲያን ሳንል፣ ወንድ ሴት ሳንል፣ ተምሬያለሁ፣ አልተማርኩም ሳንል፣ እበልጣለሁ፣ አንሳለሁ ሳንል፣ ሰው የሆንን ከዛች ምድር የወጣን ሰው ሆይ! እኔ ታዲያ ምን ማድረግ እችላለሁ? ሳንል፣ ነገር ግንሁላችን በጋራ እንችላለን!  በሚል መንፈስ በመነሳት በምድራችነ ላይ ባለ ክፋት ላይ ሁሉ እንዝመትበት?

የተሰረቀብንን ሠላም ፣ፍቅር፣ አብሮ መብላት፣ ደስታና ችግርን በጋራ መካፈል፣ ውበታችን ነውና ምርኮአችንን እናስመልስ? ማንም አይሰጠንም፣ ማንንም መለምን አያስፈልገንም፣ ቀድሞም የኛው ነበር፣ አሁንም የእኛው መሆን አለበት፣ ከተደበቀበት እናውጣው? ግልፁም ስውሩም ዓላማችንና ግባችን የተፈወሰች ኢትዮጵያን እና የተፈወሰ ትውልድን ማየት እና ማሳየት ይሁን?  እንፈወስም ዘንድ ውሸትን ሁሉ አስወግደን እርስ በእርሳችን እውነትን እንነጋገር? ለብዙ ዘመናት ውሸትን እንድንናገር እና ውሸት እንድናስብ ተደርገን ስለተቀረጽን፣ መጀመሪያ ከዚህ እስር ቤት ራሳችንን ነፃ እናውጣ? ብዙዎቻችን ፈሪዎች ሆነናል፣ ፈሪ የሆንው ደግሞ ለራሳችንም ለሰውም ስለምንዋሽ ነው፣ የፈሪ ሰው ደግሞ ፍቅሩ ፍፁም አይደለም፣ይህ ደግሞ የዘላለም ባርነት ስለሆነ፣ ስላለፈው ውሸታችን ምንም ማድረግ ባንችል እንኩዋን፣ ከአሁን በሁዋላ ላለመዋሻት ራሻችንን እናለማምድና፣ በዚህ ትውልድ የማትረፍ ስራ ላይ እንረባረብ? በምድራችንምብሔራዊ እርቅ እና ሠላም እንዲፈጠር፣ የተበደለ እንዲካስ እና በዳይ ለበደሉ ተመጣጣኝ ፍርድ እንዲያገኝ ሁኔታዎችን እናመቻች?

በአገር ውስጥም በውጭም ላላችሁት ፖለቲከኞች!  እኛ በባዕድ ምድር ተበትነነን ያለን መጻተኛ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች ልናስገድዳችሁ ነውና እጆቻችሁንም፣ ልባችሁንም አዘጋጁ! በፖለቲካ እና በሐይማኖት ድርጅት ስም የምትነግዱም እናንተም እጃችሁን እና ልባችሁን አጥሩ? እንግዲህ የሚያስተባብረን እስኪገኝ ለዘመናት ከምንጠብቅ፣ እኔ አንዲት ተራዋ ድሐዋ እናት ደፍሬዋለሁና አግዙኝ? ይህን ሐላፊነት የሚወጣ ብቁ ወገን እስክናገኝ ድረስ ፖለቲካውንም፣ ኢኮኖሚውንም፣ ህግና ሥርአቱንም እኛ እንደሚሆን እናደርገዋለን ችሎታ አለን የምትሉ ሁሉ፣ እውቀታችሁን ሰማይ ቤት ስትሄዱ አትጠቀሙበትም እና ፣ በምድር የተቀጠረላችሁ እድሜ አሰኪደርስ ድረስ ለዚህ መልካም ስራ ጨክኑና!እነሆ አለን! ትሉን ዘንድ እናንተንም በወለደች እና ትውልድን ባማጡ እናቶች ስም አማጸናችሁዋለሁና ሴትም ወንድም ሳትሉ ተዘጋጁ፣ በአድራሻችን አግኙንም?

እናንተ የማትሰሩ፣ ወይ የማታሰሩ፣ በየመንደሩ እየዞራችሁ አሉባልታ ብቻ የምታናፍሱ፣ እግዚአብሔር ይፈውሳችሁና ከሚሰሩም ጋር ያቀላቅላችሁ! በምድራችን እና በሕዝባችን ላይ የተለያየ የፖለቲካና፣ የሐይማኖት ቡድኖች አመለካከትንና፣ ዘመን አመጣሸ የማይረባ ባህልን በትውልዳችን ላይ ማራገፊያ አድርገን ምድራችንን ስንበክል የነበርን የውጭ አገር ዘመነኛዎች፣ እስቲ አሁን ደግሞ ፣ መልካምነትን፣ ትህትናን፣ በጎነትን፣ ታራቂነትን፣ ፍቅርን፣ ወደ ትውልደ አገራችን ፈሰስ(ኢነቨስት) እናድርግ? የምድራችን ከፉዎች መሄጃ ስለሌላቸው የባሰ ክፉ ሆነው ሕዝባችንን ከመጨረሳቸው በፊት፣ እኛ በፍቅር እናንበርክካቸው? ከእኛም ጋር የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር አብሮን ይሁን!

በትውልድ ምድራችን ያላችሁ ሕዝባችን ሆይ! የተበተኑት ልጆቻችን፣ እኛ እና አያት ቅድመአያቶቻቸው በገነባንው ምድር ባየተዋር አይሁኑብን? ብላችሁ መንግስታችሁን አስገድዱልን አደራ?

እናንት ወጣት ትውልድ! ፖለቲከኞች እና ሐይማኖተኞች አጥብበው በሰፉላችሁ ከረጢት ውስጥ አንገባም በሉ! መጀመሪያ ሰው ነኝ ከዛ ደግሞ ኢትዮጵያ በምትባል ምድር የተለያያ ቁዋንቁዋ ከሚናገሩ ሕብረሰተብ የተወለድኩ ውብ ሰው ነኝ ብላችሁ፣ ሲንከባለል የመጣው መርዝ እንዳይበክልላችሁ ተጠንቅቁ!

ክርስቲያን ሆይ! ለእስልምና እምነት ተከታይ ወንድምህ ዘብ ቁም! የእስልምና እምነት ተከታይ ሆይ! ለክርሰቲያን ወንድምህ ዘብ ቁም፣ እምነት የሌለህ እምነት ላለው ወገንህ ጠበቃ ሁን፣ ለራስህ ብቻ ዘብ መቆምን አቁም! ሁላችን በእግዚአብሔር አምሳል እኩል ተፈጥረናልና!

እኔ ሐይማኖተኛ ነኝ ፖለቲካ አያገባኝም ብለህ ራስን የምትሸነግል ሆይ! አንተ ነጻ ሳትወጣ ሌላውን ነጻ ማውጣት አትችልም እና ራስህነ ከውሸት ጭንብል አላቅቅ! ፖለቲከኛ የግድ መሆን የለብህም፣ ነገር ግን በርታ ሰው ግን ሁን!አንተም እንደ እኔ፣ አንቺም እንደ እኔ በሕዝቤ ላይ የሚወርደውን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ወይስ የዘመዶቼን ጥፋት አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? በሉ! እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው። የያዕቆብ መልእክት4፣17 ዝም ብንል ግን እግዚአብሔር ለምድራችን ፈውስ ከየትም ሥፍራ ያመጣልና ለእናንተ ግን ወዮላችሁ!

posted by tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s