ለተስፋኪሮስ ኣረፈ የተሰጠ አስተያየት – አቻምየለህ ታምሩ

ተስፋኪሮስ «ሃገራችንን በዲፕሎማሲው መስክ ዋጋ እያስከፈሏት ያሉ የኢህኣዴግ ጭንጋፍ ኣስተሳሰቦች» በሚል ርዕስ በጻፈው አርቲክል ላይ አስተያየት እንድሰጥ ጋብዦኝ ነበር። ሙሉውን የተስፋኪሮስ አርቲክል ከዚህ ጽሁፍ ግርጌ ካለው የአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ ማንበብ ይቻላል። አርቲክሉን በሚመለከት ያሉኝን ሰፋ ያሉ አስተያየቶች ግን እነሆ!

 

አይተ ተስፋኪሮስ ያንተን ጽሁፍ ሁልጊዜ የሚያነብ ሰው አንተ ከተነሳህበት ሐሳብ ይልቅ ጎልቶ የሚታየው አንድ ነገር አለ። ይህም ከዋናው ጽሁፍህ ጭብጥ በላይ አትኩሮት በመስጠት ወያኔን «ከደሙ ነጻ ለማድረግ» ወይንም የወያኔን ኃጢዓት ለማቅለል በህይወት ያለውን ወያኔን ከሞቱት መንግስታትና መሪዎች «ክፋት» ጋር እያነጻጸርህ ወያኔን አጉልተህና አሳብጠህ የምታቀርበው ነገር ግፍዝ ነስቶ መታየቱ ነው። ይሄን ዘዴህን ብዙ ሰው ነቄ ያለው ይመስለኛል። ምናልባት እስካሁን ከምትታወቅበት ዘዴ ውጭ ወያኔን የምትታደግበት አዲስ ችሎታ ካለህ ሌላ ነገር ሞክር።

ለምሳሌ የጽሁፍህ ርዕስ « ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈሏት ያሉ የኢህኣዴግ ጭንጋፍ ኣስተሳሰቦች» ብለህ በጻፍከው ጽሁፍ ውስጥ «ኢህአዴግ» የሚለውን ስም አስራ አምስት ጊዜ በበጎና በተለሳለሰ ትችት ስጠቅስ «ኣፄ ምኒልክ» የሚለውን ስም ግን በጠጠረ ጥላቻና ትችት አስራ ስምንት ጊዜ ጠቅሰሀል። አንተ ለአጼ ሚንልክ ከዋናው የጽሁፍህ ርዕስ ትኩረት የላቀ ትኩረት የሚሰጥ ከሆነ ለምን የጽሁፍህን ርዕስ « ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈሏት ያሉ የኣፄ ምኒልክ ኣስተሳሰቦች» ብለህ አትቀይረውም ነበር? ይገርማል! ከዚህ በላይ ወያኔን እንዴት ትከላከለው? የቀበሮ ለምዱን አውልቆ በሰብዓ ቆዳው ወያኔን አደግድጎ ሌት ቀን የሚያገለግለው ዳንኤል ብርሀነ እንኳ ያንተን ያህል ወያኔን ከሞቱ ከመቶ አመታት በላይ ከሆናቸው መንግስታት ጋር እያነጻጸረ አያንቆለጻጽሰውም።

ለማንኛውም ለኔ አጼ ዮሀንስ ሰፊ አስተሳሰብ የነበራቸው ላገራቸው የወደቁ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ናቸው። አጼ ሚንልክ ደግሞ የአባቶቻቸውን የአጼ ቴወድሮስንና የአጼ ዮሀንስን ራዕይ ከግብ በማድረስ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያን ስልጣኔ መሰረት የጣሉ ታላቅና ብልህ መሪ ናቸው። ለዚህ ከገብረሕይወት ባይከዳኝ በላይ ምስክር የለም። አጼ ዮሀንስና ንጉስ ሚንልክ በጋብቻ የተዛመዱ፤ ልብ ለልብ የተሳሰሩ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት አብረው የተሰለፉ፤ ሰፊ የጋራ ራዕይ የነበራቸው ኋለኛው የቀዳሚውን ራዕይ ተቀብሎ በማስፈጸም የአንድ አገር ነገስታት መሆናችውን ያስመሰከሩ እንጂ ከደርግ በኋላ እንደመጣው ወያኔ ያለፈውን ሁሉ እንዳፈረሰውና የጠላት አገር እንደተረከቡ የሚያስቡ አንተና መሰል የወያኔ ሎሌዎች በምታቀርቡት ደረጃ የሚደባቡ ጠላቶች አልነበሩም። እድል አግኝተው ሚንልክና ዮኃንስ ተመልሰው ቢመጡና አንተና ሌሎች መሰሎችህ ያከማቻችሁትን የሁለቱን ጠላትነት ቢያዩ እንዴት ይታዘቧችሁ?

ሆኖም አንተ ያልከው «ከአፄ ዮሃንስ ወዲህ ግን ሃገራችን ኢትዮጵያ የተሟላ ሉኣላዊነትና ኣንድነቷ ኣጣጥማ ኣታውቅም።»ተራ ስህተትና የወረደ ወገንተኝነት ነው። ለምሳሌ [ለአክሊሉ ኃብተወልድና ለጓዶቹ ክብር ይግባቸውና] አጼ ዮሀንስ በዘመናቸው የኢትዮጵያ አካል ያላደረጉት የዛሬው ኤርትራ መሬት ሙሉ በሙሉ በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ ግዛት ነበር። እንደ አብነትም በአጼ ዮሀንስ ዘመነ መንግስት ምዕዋ የኢትዮጵያ አካል አልነበረችም፤ በአጼ ኃይለ ስላሴና በደርግ ግን የኢትዮጵያ አካል ነበረች። ጋምቤላና ሞያሌ፤ ኦጋዴንና አፋምቦ በአጼ ዮሀንስ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ አካል አልነበሩም፤ በአክሊሉ የረቀቀ ዲፕሎማሲ ጥረት ግን በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን የኢትዮጵያ አካል ሊሆኑ ችለዋል።

ሌላው «በኣፄ ምኒልክ ወቅት ኤርትራን ለጣሊያን ኣሳልፋ በመስጠት ሉኣላዊነትና ኣንድነቷ ገብራለች» ያልከው የወያኔ ፕሮፓጋንዳና ነጭ ውሸት ነው። ከፍ ብዬ ጠቆም እንዳደረግሁት በአጼ ዮኃንስ ዘመነ መንግስት የማይናቅ የኤርትራ መሬት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት አካል አልነበረም። ለምንድን ነው ዛሬ ኤርትራ ተብሎ የሚታወቀው መሬት ሙሉ በሙሉ የአጼ ዮኃንስ ኢትዮጵያ አካል እንደነበር ተደርጎ የሚቀርበው? ታሪክ የሚያውቅ የለም ለማለት ነው? በአጼ ዮሀንስ ዘመን ጣሊያን ከቆላው የኤርትራ ክፍል አልፋ ወደ ደጋው በመውጣት ሰፊ የኤርትራን መሬት በንጉሰ ነገስቱ ፈቃድ ይዛ ነበር። አጼ ዮሀንስ ጀግናው አሉላን ሳይቀር «ለምን ጥሊያንን ወጋህ?» ብለው ሲቀጡት፤ ጣልያን የልብ ልብ አግኝታ በመደሰት የመስፋፋት ምኞቷ እያየለ መጥቶ ብዙ ደጋማ የኤርትራ መሬቶችን መያዟ በአጼ ዮሀንስ ዘመን የነበረ እውነታ ነው። ለምን ይህንን አታነሳውም?

ከዚያም አልፎ የትግራይ መሳፍንትና መኳንንት አጼ ዮኃንስ ወራሽ አድርገው የመረጧቸውን ራስ መንገሻን አንቀበልም ብለው መንገሻን ለመጉዳት ወደ ጣሊያን መግባታቸውንና ለጥሊያን የመሬት ገጸ በረከት በማቅረብ የአስመራና አካባቢዋን መሬት ለጥሊያን ያስረከቡትን ደጃች ደበብን፣ የአካለ ጉዛይን መሬት ለጥሊያን የሰጡትን ደጃች ባህታ ሐጎስን፣ ከረንንና ቦጎስን ለኢጣሊያ መንግስት እጅ መንሻ ያቀረቡትን ባላምባራስ ክፍለ እየሱስን ለምን አታነሳም? ነው ንጉስ ሚንልክ ሳይነግሱ የትግራይ መኳንንቶችና መሳፍንቶች ለጣሊያን ያስረከቧቸው አስመራንና አካባቢዋ፣ አካለ ጉዛይ፣ ከረንና ቦጎስን የኤርትራ አካል አልነበሩም?

ንጉስ ሚኒንልክ በደብዳቤ «የአገር ጥቅም አሳልፎ ሰጥቷል» እያልህ አጼ ዮኃንስን ከፍ ለማድረግ ስትጥር በደብዳቤ ሳይሆን ፊት ለፊት ተሰልፈው ቀለብ እየሰፈሩ፤ መንገድ እያሳዩ፤ ታማኝነታቸውን እያስረገጡ መቅደላ ድረስ ሰተት አድርገው የአጼ ቴዎድሮስን ገዳዮች የመሩትን የካሳ ምርጫን ጉዳይ ግን ማንሳት አትፈልግም። የንጉስ ሚንልክን ከአጼ ዮሀንስ በስተጀርባ መሄድ ሳታስተባብልና ሲባል ከሰማከውም ጨምረህ ስትናገር ፤ የካሳ ምርጫን ከአጼ ቴዎድሮስ ጀርባ መሰለፍ ማስተባበል ለምን አስፈለገህ? ለትውስታ እንኳ ያለፉትን መሪዎች ህጸጽ ስታነሳ ካሳ ምርጫ ለስልጣናቸው ሲሉ የሰሩትን ይህንን ትልቅ ስህተት መዝለሉ ጥፋታቸውን እንደማስተባበል አይቆጠርምን? በእውነቱ እንደዚህ አይነቱ አቀራረብ አይን ያወጣ ወገንተኝነት ነው። እኔ አጼ ዮሀንስም ሆነ አጼ ሚንልክን የማያቸው በእኩል አይን ነው፤ ሁለቱም ታሪካዊ መሪዎቼ ሲሆኑ በዘመናቸው የሰሩትን ጎደሎ ነገር ሳላዳላ በታሪክነቱ ብቻ ትምህርት ወስጀበት የማልፈው ጉዳይ እንጂ የኔን ስህተት ለማስተባበል የነሱን ስህተት ያለዘመኑ የማነሳባቸው የጠላት አገር መሪዎች አይደሉም። ሁለቱም ክብር ይገባቸዋል።

እንዳንተ አቀራረብ ከሆነ ግን ታሪክን ከኔ ምኞችና ፍላጎት አኳያ ብቻ እየተመለከትሁ፤ ጎጃምን ያጠፉትን አጼ ዮሀንስንና ንጉስ ተክለኃይመኖትን ጮመን ረግረግ በመክተት ኢምባቦ ላይ የረቱትን ንጉስ ሚንልክን በአገር ክዳት እየከሰስሁ ሳርውኃ ላይ ቤተሰቦቻቸውን ሳይቀር መስዕዋት ስላደረጉ አገር ወዳድ ንጉስ ተክለሀይማኖት ብቻ ናቸው ማለት ሊኖርብኝ ነው ማለት ነው። በፍጽም! እኔ እንዳንተ የኢትዮጵያን ታሪክ ከተወለድሁነት አካባቢ ፍላጎትና ምኞች አንጻር ብቻ እያየሁ ትልቁን ምስል በመሳት የተንሸዋረረ እይታ እንዲኖረኝ አልሻም።

«አፄ ሃይለስላሴ ከጨርጨር (ማይጨው ኣልደረሱም) ፈርጥጠው ከኣገር በመኮብለል ሃገራችን ለኣምስት ኣመታት በጣሊያን ቁጥጥር ስር ውላለች፣» ያልከው ቀይ ውሸትና የደርግና የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ነው። የዘውዴ ረታን በማስረጃ የታጨቀ «የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት» መጽሀፍ ያነበበ አንድ ሰው ይህንን ቀይ ውሸት ወይንም አደገኛ ውሸት አይዋሽም። ይህንን ቀይ ውሸትህን ለኛ መጽሀፍ ለምናነበው ሳይሆን ትግራይ ላሉ ህጻናት ንገርና በጥላቻ ቀስቅስበት። Otherwise, it is an insult to our intelligence.

«ፕሬዚደንት መንግስቱ ሃይለማሪያም እንደ ኣፄ ሃይለስላሴ ፈርጥጠው ከኣገር በመኮብለላቸው ኤርትራ በህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (EPLF) እጅ ሙሉ በሙሉ ልትወድቅ በመቻሏ የኣፄ ሃይለስላሴን የዲፕሎማሲ ጥረት ኣፍር ድሜ ኣብልቶት ኤርትራ ዳግም ልትነጠል ችላለች።» ብለሀል ጥሩ፤ መንግስቱ ኤርትራን ለሻዕብያ ጥሎ ሲፈረጥጥ ወያኔ ኤርትራን ለኢትዮጵያ ለማድረግ ያደረገው ጥረት ምንድን ነው? ዛሬ ድረስ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብለው አይደለም እንዴ ስለኤርትራ ነጻነት አንደራደርም የሚሉን ወያኔዎች? ለምን መንግስቱ ስህተት ላይ ብቻ ቆመህ ወያኔን ከደሙ ንጹህ ታደርገዋለህ? እይታህ ወገናዊ ስለሆነ ላንተ የሚታይህና መሆን ያለበት አንድ ነገር ብቻ ነው፡- ይህም የታሪካዊ ስህተታችች ሁሉ ምንጮች ከትግራይ ውጭ የሆኑ መሪዎቻችን ብቻ ናቸው የሚለ ነው። ያንተ መነሻም መድረሻም ይህ ነው። መነሻውም መድረሻውም ለሚታወቅ አንድ አይነት «ትንተና» እንዳዲስ ነገር ለምን ትደጋግመዋለህ?

ሌላው ያንተ የተለመደ ነገር ደግሞ አጼ ሚንልክንና ወያኔን የምታወዳድረው ነገር ነው። ያንተ «ትንተና» አይን ያወጣ ወገንተኛነት የሚታይበት መሆኑን አንድ ማሳያ ልጨምርልህ። በዛሬው ጽሁፍህ «አጼ ሚንልክና ኢህአዴግ አንድና ተመሳሳይ ናቸው፤ የሚለያቸው ነገር የለም» ብለኸናል። ጥሩ! ታዲያ ይህን ነግረኸን ስታበቃ «ከትግራይ አይደሉም» ብለህ የምታስባቸውን አጼ ሚንልክን በጠላትነት ፈርጀህ በጥላቻ አፌር ድሜ ስታስግጣቸው በወያኔ የበላይነት የሚዘወረውን ኢህአዴግን ግን «እሱ ከስልጣን ከወደረ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች» እያልህ ለምን ጥብቅና ትቆምለታለህ? አጼ ሚንልክና ኢህአዴግ ላንተ አንድ ከሆኑ ለምን በሁለቱም ላይ የምታሳየው ፍቅርና ነቀፌታ እኩል አይሆንም? ለምን አጼ ሚንልክን አምርረህ እየጠላህ ኢህአዴግን አጣፍጠህ ታፈቅራለህ? ለዚህ ምክንያቱ አጼ ሚንልክ ወያኔ ጠላት ብሎ ሊፋለመው በረሀ ከወረደ ከየሸዋ አማራ በመሆናቸው ላንተም «ጠላትህ» ሆነው ስትዘምትባቸው ፤ ወያኔ ደግሞ አንተ ከበቀልህበት ከትግራይ በመሆኑ ነጻ አውጭህ ስለሆነ ብቻ የመጣ ከልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

አሁን አጼ ሚንልክንና ወያኔን «እኩል አጥፍተዋል» ብለህ ሁለቱም «ይመሳሰላሉ» ወዳስባሉህ የውጫሌና የአዲስ አበባ ስምምነቶች ልመለስ። ሁለቱንም ስምምነቶች ያነበበ ሁሉ እንደሚያውቀው ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት በማወጇ የተነሳ ፈርሰውና ሞተው የተቀበሩቱ የአዲስ አበባና የውጫሌ ስምምነቶች ጥሊያን ከኤርትራ ስትለቅ ኤርትራ ወደ እናት አገሯ ኢትዮጵያ እንደምትመለስ እንጂ ነጻ አገር እንደምትሆን አይደነግጉም። ላንተ አጼ ሚንልክና ወያኔ ወይንም ባንተ አገላለጽ ኢህአዴግ በአጥፊነታቸው «አንድ አይነት ከሆኑ» ለምን በውጫሌና በአዲስ አበባ ስምምነት መሰረት አጼ ሚንልክ ጣሊያን ከኤርትራ ስትወጣ ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ትመለሳለች ብለው እንደተስማሙትና እንደተደራደሩት ሁሉ ወያኔም ከሻዕብያ ጋር ተደራድሮ ኤርትራን ወደ እናት አገሯ አላስመለሰም? የአጼ ሚንልክ ስምምነቶችኮ [ ልብ በል፡ የውጫሌ ስምምነት በአድዋ ጦርነት ምክንያት፤ የአዲስ አበባ ስምምነት በሙሶሎኒ ወረራ የተነሳ ፈርሰው NULL AND VOID ሆነዋል] ጥሊያን ከኤርትራ ስትወጣ ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ የሚያስመልሱ እንጂ ነጻ አገር እንድትሆን የሚያደርጉ አይደሉም። እና እንዴት ሆኖ ነው ጥሊያን ከኤርትራን ከወጣች በኋላ ነጻ አገር እንድትሆን ያደረገውን ወያኔንና ጥሊያን ከኤርትራ ከወጣች በኋላ ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ እንደምትመለስ አድርገው ስምምነት የፈረሙትን አጼ ሚንልክን አንድ የምታደርጋቸው?

«የኣፄ ምኒልክ ኣድናቂ ሆኖ ኢህኣዴግን መውቀስ በDouble Standardነት ያስከስሳል/ያስገምታል» ያልከውም ሎጂክ የሌለው ባዶ ነው። እንዳንተ እይታ «አጼ ሚንልክ የሰሩትን ተመሳሳይ ስህተት» ወያኔ ሲደግመው ሁለቱንም እኩል ተሳስተዋል ማለት ከሆነ ይህ ሊሆን የሚችለው አንድም ታሪክ በሌለበት ሁኔታ ነው ሁለትም የታሪክን ትምህርት ጥቅም ካለመገንዘብ የሚመነጭ ወገናዊ አስተያየት ብቻ ነው የሚሆነው። የአጼ ሚንልክ ስህተት ለወያኔ ጥፋት ማስተባበያ ተደርጎ ሊቀርብ አይችልም። ወያኔኮ የተረከበው አገር እንጂ የጠላት ምድር አይደለም። አገር ከተረከበ ደግሞ ያለፈው ስህተት ማረም እንጂ ዛሬ ሊደግመው አይገባም። የተረከበውን አገር የጠላት መሬት አድርጎ ከቆጠረው ግን ያለፈውን ስህተት ዛሬ ለምንፈጽመው ጥፋት ማጽጃ በማድረግ የምንመዘው መጫዎቻ ካርድ ይሆናል። ለማንኛውም ወያኔ ስልጣን ሲይዝ የጠላት አገር የተረከበ ባይመስለው ኖሮ የአጼ ሚንልክ «ስህተቶች» ያልካቸው በሙሉ በወያኔ ሊታረሙ ይችሉ ነበር።

ከሁሉ በላይ ግን እናንተ ወያኔዎች ላገር ጉዳይ ሲባል እንኳ እንዲገባችሁ የማትፈልጉትና እንዲገለጥላችሁ የማትፈልጉት ነገር ለሁላችንም ግልፅ የሆነ አንድ ነገር አለ። አጼ ሚንልክ «ተሳስተው ተዋዋሏቸው» የሚባሉ ስምምነቶች በሙሉ በስምምነቱ ፈራሚ በሆነው በሌላኛው ወገን ወይንም በጥሊያን ጦረኛነት ስምምነቶቹ ተሽረው ሙሉ በሙሉ NULL AND VOID ሆነዋል። አጼ ሚንልክን ለማጥቃትና ኢትዮጵያን ለመጉዳት ታስቦ ካልሆነ በስተቀር በአድዋ ጦርነትና በሙሶሎኒ ዳግም ወረራ ወደ መቃብር የገቡ የአጼ ሚንልክ ስምምነቶች ህይወት እንዳላቸው ሰነዶች ለክርከር የሚቀርቡ አይደሉም። አንድ የኢትዮጵያ መንግስት ነኝ የሚል አካል የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ እና NULL AND VOID የሆነ ስምምነት እየጠቀሰ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለጠላት እኩል አይመለከትም። ወያኔ ያደረገው በዚያው በአጼ ሚንልክ ዘመን NULL AND VOID የሆኑ ስምምነቶችን ነፍስ ሰጥቷቸው ኢትዮጵያ እንድትጎዳ ማድረግ ነው። ልብ በል! ያጼ ሚንልክ ስህተት ስምምነቶች NULL AND VOID በዚያው በራሳቸው በአጼ ሚንልክ ዘመን ነው። የተወሰኑት ስምምነቶች ደግሞ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን በድጋሜ ሲወርር በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን መንግስት ፈርሰዋል። እነ አክሊሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተከራክረው ኤርትራን ሲያስመልሱ ባደረጉት ክርክር ወቅት ጥሊያን NULL AND VOID የሆኑ ስምምነቶችን አልጠቀሰችም፤ እንደማይጠቀሱ ታውቃለችና፤ ከጦርነት በኋላ ከጦርነት በፊት የነበረ ስምምነት NULL AND VOID እንደሆነ ያውቃሉና።

እና አንተ ዛሬ ሚንልክ «ይሄን አድርጎ» እያልህ የምትከሰው የወገንተኛ ክስ ባጠቃላይ NULL AND VOID የሆነና ለወያኔ ጥፋት ማጣፊያ በምንም መልኩ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል አይደለም። NULL AND VOID ሆኖ ወደ መቃብር የወረደን የአጼ ሚንልክና የጥሊያን ስምምነት ወደ ጠረጼዛ ዙሪያ መመለስ ማለት ኢትዮጵያን ለመጉዳት ከመፈለግ ውጭ በምንም መልኩ በተለይ በኢትዮጵያ በኩል ባለ ወገን እንደመከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም። ሆኖም ግን የወያኔ የጥላቻ ሀመም ተሻካሚ ስለሆንህ ደንቆሮዎቹ ወያኔዎች የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት ከመቃብር ቆፍረው ያወጡትን NULL AND VOID የሆነ የአጼ ሚንልክ-ጥሊያን ስምምነቶች ህይወት እንዳላቸው ሁሉ በማስረጃ እየጠቀስህ ወያኔን ለመከላከል ትከራከርባቸዋለህ! ይህን አይነቱን በሞተ ኃሳብ የሚደረግና ትርጉም የሌለው ፖለቲካ ጨዋታ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ «የሙታን ፖለቲካ» ይለዋል። አንተም የዚህ የሙታን ፖለቲካ ተጋሪ ነህ። ባትሆን ኖሮ NULL AND VOID የሆነ የኢትዮጵ ጥሊያን ስምምነት እያነሳህ «ጣሊያን በውጫሌ ውል ያገኘችው ኣልበቃ ብሏት እየተንፏቀቀች ተጨማሪ መሬቶችን መያዝ ጀመረች፡፡ ኣፄ ምኒልክም ዝም በሏቸው እያሉ ከውሉ ውጪ የተያዙ መሬቶች በኋላ የውጫሌ ውል በጣሊያን ኣገር ሲፈረም በጊዜያዊነት በውሉ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል ( እነዚህ የውሉ ኣካል ያልሆኑና በጊዜያዊነት የተቀጠሉት ኢህኣዴግ በድርድሩ እንዴት እንዳስተናገዳቸው ኣይታወቅም-» በማለት ቁም ነገር የሰራህ አይመስልህም ነበር።

እስቲ ማን ይሙት በአድዋ ጦርነት NULL AND VOID የሆነው የውጫሌ ስምምነት ኤርትራን ነጻ ለማውጣትና የኤርትራ መሬት ለመስጠት ሲባል ከመቃብር ተቆፍሮ ኢትዮጵያዊ የሆነ ወገን ይወጣል? ያውም ስምምነቱ ጣሊያን ኤርትራን ለቅቃ ስትወጣ ኤርትራ ወደ እናት ወደ ኢትዮጵያ ትመለሳለች እያለ? እስቲ የትኛውን የውጫሌ ስምምነት አንቀጽ ጠቅሶ ነው ወያኔ ጥሊያን ከኤርትራ ለቅቃ ስትወጣ ኤርትራ ነጻ መውጣት አለባት ብሎ ከኢትዮጵያ ለማስገንጠል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደብዳብ የጻፈው? የውጫሌ ስምምነትኮ አነ አክሊሉ ኃብተወልድና ወልደ አብወልደ ማሪያም በተባበሩት መንግስታት ፊት ቆመው ክርክር ሲያደጉ አልተነሳም፤ ምክንያቱም በአድዋ ጦርነት ምክንያት ስምምነቱ NULL AND VOID እንደሆነ ይታወቃልና።

ለምን ሲባል ነው NULL AND VOID የሆነ ስምምነት ከመቃብር ተቆፍሮ አክሊሉና ወልደአብ ለክርክር ሳያቀርቡት መለስና ኢሳያስ ለድርድር ያቀረቡት? ኢትዮጵያን ለመጥቀም ነው? ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው ታሪካዊ በደል መለስም ኢሳያስም ኤርትራዊ ሆነው ካልቀረቡ በስተቀር በኢትዮጵያ በኩል NULL AND VOID የሆነ ስምምነት ከመቃብር ተቆድሮ በመውጣት የኤርትራን ህልውና ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ ጥቅም ላይ አይውልም። ይህንን ወያኔ ከቃብር አውጥቶ ነፍስ የዘራበትን የውጫሌ ስምምነት ነው እንግዲህ አጼ ሚንልክ በአድዋ ጦርነት ወደ መቃብር ካወረዱት ጋር እኩል ዋጋ ሰጥተህ አጼ ሚንልክንና ወያኔን የምታመሳስላቸውና ሞቶ የተቀበረውን ስምምነት ነፍ እንዳለው ቆጥረህ በስምምነቱ ውስጥ «ኤርትራ ከጥሊያን በኋላ ነጻ አገር ትሁን» የሚል አንቀጽ ያለው ይመስል ወያኔ ኤርትራ ነጻ አገር እንድትሆን መወሰኑን ያጼ ሚንልክ ጥፋት ነው እያልህ የምትከራከረው። እስቲ አጼ ሚንልክ ተሳሳቱት የምትለውን ኤርትራን የጥሊያን የመስጠት ጥፋት ወያኔ ለማረምና ኤርትራን ወደ እናት አገሯ ለመመለስ ያደረገው አንድ ጥረት ንገረኝ ?

በመጨረሻ « ኣፄ ምኒልክ ኣባይን ላለመገደብ ተስማምተዋል» ያልከውም ያው የለመድነው የፈጠራ ክስና በሬ ወለደ ሲሆን ወያኔ ባለፈው ሳምንት ከግብጽና ሱዳን ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ወደፊት የአባይን ውሀ ግድቡን ላለመሙላት ሰበብ ሲፈልግ «የቀድሞው መሪዎች በተስማሙት ስምምነት የተነሳ ነው ግድቡ የማይሞላው» የሚለውን ካርድ ለመምዘዝ የታለመ ስለሆነ ጊዜው ሲደርስና ስበቡ ሲጎነጎን እመለስበታለሁ።

posted by tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s