የሃገራችን መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ተግዳሮቶች (ገለታው ዘለቀ)

በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ለማንሳት ስነሳ በ1994  ዓ.ም  የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በቤተ መንግስት ውስጥ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ሲወያዩ አንድ ምሁር የተናገረው ነገር ትውስ አለኝ። ትዝይላችሁ እንደሆነ የዚህ ምሁር ንግግር ብዙዎችን ኣስደምሞ ነበር። ለማስታወስ ያህል ይህ ምሁር ለራሳቸው ጠቅላይ ሚንስትር ለነበሩት ለአቶ መለስ እንዲህ ነበር ያለው።

“እዚህ አገር ሌላ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ተመስርቶ፣ ገበሬው ውስጥ ገብቶ ፋይዳ ያለው ለውጥ አይኖርም እርስዎ እያሉ። አይኖርም። ምክንያቱም እርስዎ እንዳይኖር ያደርጉታልና ነው። እስካሁን በዚህ ተሳክቶልዎታል በሚቀጥሉት ሃያ ኣመታትም ይህንኑ  ያደርጋሉ።”

የሚገርመው ይህ ምሁር ምንም ውስብስብ ነገር አልተናገረም። ብዙ ምጡቅ   አሳቦች በዚህ ስብሰባ ላይ ተነስተው ነበር። ይሁን እንጂ በተለይ የዚህ ምሁር ንግግር ግን ከተማሪው እስከ ምሁሩ፣ ከነጋዴው እስከ ሰራተኛውና ገበሬው ድረስ ኣስደንቆ ነበር። ለምን ብየ ጠይቄ አውቃለሁ። ሰው ሁሉ ይህን ምሁር ያደነቀበት ዋና ነገር ሁሉም በልቡ ጠቅላይ ሚንስትሩን እንዲህ ነበር የሚያውቃቸውና ነው። እሳቸው እያሉ መድብለ ፓርቲ አይኖርም የሚል እምነት በዚህ ሁሉ ሰው ልብ ውስጥ ስለነበር ነው።  አሁን ይህ ምሁር በሃቀኝነት ይህን ስሜት መግለጽ ሲችል ሁሉም እዎ!  አገኘኸው ኣይነት ነው የተደመመው። አንዳንዴ የውስጥን ስሜት በቅንነት  የሚገልጽ ሰው ሲገኝ ደስ እንደሚለን ነው ነገሩ። ምሁሩ እንዳለው አቶ መልስ ቅንነት  የጎደላቸው ናቸው ብሎ ህዝብ ያዝን ስለነበርም ነው። በርግጥ ከዚህ ምሁር የወጣው ይህ ቃል ቅንነትንና እውነትን ይዞ ስለነበር የብዙዎችን ስሜት በቀላሉ መግዛት ችሎ ነበር።

ያ ምሁር “እርስዎ እያሉ መድብለ ፓርቲ ስርዓት አይኖርም” አለ። አሁን አቶ መለስ ከዚህ ዓለም የሉም። ይሁን እንጂ ኣሳባቸውና ያፈሯቸው ደቀመዛሙርት ልክ እንደሳቸው ስለሆኑ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላም እነሆ ዛሬ ድረስ የዚህ የመድብለ ፓርቲ ጉዳይ እክሎች በዝተውበት ይኖራል። አቶ መለስ በኣካል ባይኖሩም አሉ ማለት ነው።

ያ ምሁርም ሆነ ብዙው ኢትዮጵያዊ በዚህች አገር በዚህ መንግስት ስር መድብለ ፓርቲ አድጎ ነጻ ምርጫ ተካሂዶ በውነት ያሸነፈው ስልጣን ይይዛል የሚለው እምነት በብዙዎች ዘንድ የወረደ ቢሆንም ግን ያሉትን ፓርቲዎች ወይ ተቀናጅተው ወይ አንድ የተሻለ ፓርቲ ጠንክሮ ወጥቶ ለመብታቸው እንዲያታግላቸው ይፈልጋሉ። እናም ዛሬ የብዙ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ የሆነው ጉዳይ ለምን አንድ ጠንካራ ድርጅት አይኖርም….? ለምን ተቃዋሚዎች ይበታተናሉ….? ለምን ህብረት አቃተን……? የሚል ነው። እንዴውም በአንድ ወቅት ህዝቡ ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ እያለ ብስጭት የተሞላበት ስሜትም አንጸባርቆ ነበር። በርግጥም መቶ የሚሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች የቀፈቀፍን እኛ ኢትዮጵያውያን ይህን በረከት አንለውም። ወደዚያ እሚታጠፈው ታጥፎ የሚከስመው ከስሞ የተወሰኑ ፓርቲዎች ይበቁናል። መቶ ፓርቲ ስሙንም ሸምድደን አንዘልቀው።

ከዚህ ከብዛቱም በላይ ግን የኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ስዓት ጉዳይ ከፍ ያሉ ችግሮች አሉበት።  በዚህች በዛሬዋ ጽሁፌም የገጠሙንን ለእኔ የታዩኝን ኣራት ጉዳዮች አንስቼ ችግሮቻችንን ለመዳሰስ እፈልጋለሁ።

ከዚያ በፊት ግን የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ሃይላት ደካማዎች ናቸው ይላል። ለምን? ሲባል አንዱ ኣዘውትሮ የሚያነሳው ጉዳይ አማራጭ ፖሊሲ የላቸውም የሚል ነው። ሌሎች አንዳንድ ሰዎችም በርግጥ ይህን አሳብ ይጋራሉ። እውነቱን ለመናገር መንግስት ግን ይህን አዘውትሮ የሚገልጸው ለኢትዮጵያ ህዝብ አይመስለኝም። ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ፣ለዲፕሎማቶች ነው። መንግስት ተቃዋሚዎች ኣማራጭ ፖሊሲ የላቸውም ብሎ ለህዝቡ ቢናገር ህዝቡ ጥያቄው የአማራጭ ኣሳብ ጉዳይ እንዳልሆነ ያውቃል። ኣማራጭ ኣሳብ የሚባለው ነገር በመጀመሪያ እውነተኛ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መኖርን ይጠይቃል። እውነተኛ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ባለበት ኣገር ኣማራጭ ኣሳቦች ህዝብ ጋር ወርደው በሃሳብ የበላይነት የያዘው የህዝብን ቀልብ ስቦ ተመራጭ ይሆናል። የህዝብን ቀልብ ስቦና ኣስደምሞ ስልጣን በማይያዝበት ኣገር ጥያቄው የህግን የበላይነት የማያከብሩ ስብስቦች ይውረዱና ለውጥ ይምጣና ደሞ ሌላውን እንሞክረው ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ በአሁኑ ሰዓት መንግስት ራሱ በሚያወጣቸው ህጎች ስለማይገዛ፣ ህግን ስለማያከብር፣ በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ የሰባዊ መብቶችን ራሱ መንግስት እንደፈለገ ስለሚጥስ ለውጥ እንፈልጋለን የሚል ነው። በመሆኑም ተቃዋሚዎች በነጻነት በማይንቀሳቀሱበት ኣገር ኣማራጭ ኣሳብ የላቸውም የሚለው ክስ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ሳይሆን ከፍ ሲል እንዳልኩት ለውጭው ዓለም ይሆናል።

ለነገሩ እኮ ኣንዳንዶቹ የተጠናከረ ባይሆንም ኣማራጭ ኣሳቦች ኣሏቸው።አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ጥሩ አማራጭ ኣሳቦች አሏቸው። መንግስትን በመሬት ፖሊሲ ዙሪያ ሲቃወሙና መሬት በመንግስትም በህዝብም በግልም መያዝ ኣለበት ሲሉ ኣማራጭ ኣሳብ ማለት ይሄ ነው።

በኣስራ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባት ምርጫ ወቅት ቅንጅት ያን ያህል ህዝባዊ ተቀባይነት ያገኘው ህዝቡ የቅንጅትን ማኒፌስቶ ኣንብቦ ስለጨረሰ ኣይደለም። በዚያች ስድስት ወር ውስጥ ቅንጅት ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ስለሰራም ኣይደለም። ህዝቡ በሃይል ለውጥ ፈልጎ ነበር። በኣንዳንድ ቦታዎች በቅንጅት ተወካይና በኢህዓዴግ ተወካይ መካከል ምርጫ ሲካሄድ ህዝቡ ለመመረጥ ኢህዓደግ ኣለመሆን ብቻውን በቂ ነው ይል ነበር። ይሄ የሚያሳየው ለውጥን በጣም ከመሻት የመጣ ምርጫም ነበር። አንደኛው ይሄ ነው። ሌላው ደግሞ የለሂቁ ክፍፍል መቀነስና ዘግይቶ የታየው ህብረት ነበር የኢትዮጵያን ህዝብ በተስፋ ባህር ላይ እንዲያ ያንሳፈፈው።

ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓቱ እንቅፋቶች እንመለስና ርግጥ ነው ተቃዋሚዎች ብዙ መሰናክል ኣለባቸው። ጥንካሬና ህብረት ተስኗቸዋል። አቶ መለስ ቢሞቱም የመድብለ ፓርቲ ጉዳይ እያደር ቁልቁል ሆኗልና ለዚህ መሰረታዊ ችግሮች ናቸው ያልኳቸውን ዝቅ ሲል እኔም ላቀብል።

  1. የህወሃት የጠለፋ የትግል ስልት

ህወሃት (ኢሃዴግ) ተቃዋሚዎችን የሚያጠቃበት ስልት በኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ የመድብለ ፓርቲ የማሰናከያ ድንጋይ ነው። ህወሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ደርግን ለመጣል ይጠቀም ከነበረባቸው ዘዴዎች መካከል ሰርጎ መግባት፣ ማታለል፣ መደለል፣ የስነ-ልቡና ጦርነቶችን ማድረግ ዋና ዋና  ዘዴዎቹ ነበሩ። እነዚህን ስልቶች ዛሬም መድብለ ፓርቲ ስርዓት መስርቻለሁ በሚልበት ስርዓት ውስጥ ይጠቀምባቸዋል። ህወሃት ኣዲስ ኣበባን ከተቆጣጠረ በሁዋላ ሌላ ቀዝቃዛ ጦርነት ከፍቶ ነው የሚኖረው። ዋናው ኣንዱ ችግሩ ህወሃት ራሱን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን የሚያየው እንደ ዘውግ ተቆርቋሪ ማህበር በመሆኑና ለኢትዮጵያ የሚበቃ ወይም ኢትዮጵያን የሚሸፍን ዓላማ ስለሌለው በመድብለ ፓርቲ ውስጥ የውነት መጫወት ኣይችልም። ብሸነፍም ልሸነፍ ብሎ ለመወሰን ቢያንስ ኣገራዊ ድርጅት መሆንን ይጠይቃል። የሌሎቹ “የኢህዓዴግ” ኣባል ፓርቲዎችም ለህወሃት ተገዢ ከመሆን ባሻገር እንደዚሁ ተመሳሳይ ተፈጥሮ ነው ያላቸው። ለዚህ ነው እነዚህ ድርጅቶች የህይወት ታሪክ ውስጥ ጥርት ያለ ርእዮት የማይታየው።

በመሆኑም ኣውራው ፓርቲ ህወሃት ፖለቲካን ከማህበራዊ ማንነቱ ጋር ኣጣብቆ ስለያዘ በቀላሉ ለሃሳብ ፍጭት እጅ ስለማይሰጥ ተቃዋሚ የሚባሉትን ሁሉ በጠላትነት ያያቸዋል። እናም በደርግ ጊዜ ይጠቀምበት የነበረውን ስልት ተግባራዊ እያደረገ ተቃዋሚዎች እንዳያድጉ ያደርጋል። ከተራ ኣባል እስከ ኣመራር ድረስ በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ዘንድ ሰላይ እየሰገሰገ ህብረት እንዳያድግ፣ ህዝባዊ ሰላማዊ ትግሎችን እንዳይመሩ እያደረገ ያሸመደምዳቸኣል። ህወሃት ለብዙ ዓመት የዳበረ የጠለፋና ቆረጣ ልምድ ስላለው ተቃዋሚውን በቀላሉ ይጠልፈዋል። ኣንዱና ትልቁ ለሰላማዊ ተቃዋሚዎች ኣለመጠንከር ምክንያት ይሄ ነው። በነገራችን ላይ ህወሃት እንዳይጠነክሩ የሚያደርገው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ብቻ ኣይደለም። ኣጋር ድርጅቶቹንም ነው። እነ ብዓዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴግ ጠንካራና በራስ የሚተማመኑ እንዲሆኑ ኣይፈልግም። ይህን ቢያደርግ የሃገሪቱ የፖለቲካ ኣቅጣጫ እስካሁን ይቀየር ነበር። ነገር ግን እነዚህን ኣጋር ድርጅቶቹንም ጠልፎ ይዟቸዋል። ኢሃዴግ የተባለው ድርጅት እውነተኛ ማንነቱ ይታይ ቢባል ህወሃት ነው። ኢሃዴግ የህወሃት የፌደራል ስም ነው። ይሄ ማለት የኦህዴድ የደህዴግና የብአዴን ኣባላት ጨዋዎች ናቸው ማለት ኣይደለም። እነሱ ለግል እድሎች (Opportunities) መስፋት ሲሉ የህወሃትን የበላይነት ተቀብለው በሃገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳያድግ እያደረጉ ያሉ ናቸው። ተራው ኣባል ግራ ቢጋባም ከላይ ያሉት ግን በተለያየ ስልት የተያዙና ለህወሃት የበላይነት የሚሰሩ ናቸው። በኣጠቃላይ ህወሃት በስልጣን ለመቆየት ኣሳብን ወይም በኣሳብ በልጦ መገኘትን መሰረት ኣድርጎ ኣይኖርም። ዋናው እምነቱ ጠለፋ ነው። ኣጋር ድርጅቶችን መጥለፍና በራሱ እዝ ስር ማድረግ፣ ፕሬሱን መጥለፍ፣ ሰላማዊ ትግሉን መጥለፍ፣ ውጭ ያለውን ተቃዋሚ መጥለፍ…..ሁሉንም መጥለፍ…. ነው አዋጭ የትግል ስልት አድርጎ የሚኖረው። ስለዚህ በሃገራችን መድብለ ፓርቲ ስርዓት ኣድጎ እንዳናይ የሚያደርገን ይሄ የጠለፋ ጉዳይ ነው። ኢሃዴግ “ንብ” ነኝ ሲል የንብን የህብረት ስራ ያስታውሰናል። ኣውራው ኣለ። ሌሎች ደግሞ ውሃ ቀጂና ዘበኞች ናቸው መሰለኝ። ኣውራው ህወሃት ቢሆን እነ ኦህዴድ ብአዴንና ደህዴግ ዘበኞችና ውሃ ቀጂዎች ሆነው ይኖራሉ። ይሄ መለወጥ ኣለበት። በዚያች ድሃ ኣገር፣ ሁላችን ድሆች ሆነን እንዲህ ያለ ጅማሮ የትም ኣያደርሰንም።በህብረተሰቡም ውስጥ ይህ ነገር የተለየ ኤነርጂን እየፈጠረ ወደአልሆነ አቅጣጫ ስለሚመራን ቶሎ መቆም አለበት።

  1. የፖለቲካ ውቅር (Political setup)

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ የፖለቲካው ውቅር ነው። በመሰረቱ ኢትዮጵያ በብሄር ላይ የተመስረተ ፖለቲካ ካማራት በኮንፌደራል የመንግስት ውቅር ነው መተዳደር ያለባት። በርግጥ ይህ ጥያቄ የማንም እንዳይደለ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በብሄር ላይ የፖለቲካ ቤትን ኣቁም እንደገና መድብለ ፓርቲ ስርዓትን ኣራምዳለሁ ማለት ኣንዱን በሬ ወዲህ ኣንዱን በሬ ወዲያ ኣጣምዶ እርሻ ልጀምር እንደማለት ይቆጠራል። መድብለ ፓርቲ ስርዓትና የብሄር ፖለቲካ ኣብረው ኣይሄዱም። የብሄር ፖለቲካ ባለኣንድ ፓርቲ ገዢነትን የሚያበራታት ስሜት ያለው ነው። ሰማኒያ የሚሆኑ ብሄሮች ሰማኒያ የፖለቲካ ድርጅት ኣቋቋሙ ማለት መድብለ ፓርቲ ስርዓት እውን ሆነ ማለት ኣይደለም። መድብለ ፓርቲ ስርዓት ማለት በኣንድ ብሄራዊ የፖለቲካ ማንነት ስር የተሰባብሰቡና የጋራ ትልቅ ግብ ያላቸው ነገር ግን በፖሊሲና በኣይዲዮሎጂ የሚለያዩ ድርጅቶች ኣሳብ እያፋጩ በፖሊሲ ብልጫ እየተመረጡ የጋራ ኣገር የሚያሳድጉበት ስርዓት ነው። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ኣሁን የለም። ብሄራዊ ማንነት በኣካባቢ የፖለቲካ ማንነት እንዲዋጥ ስለሚደረግ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ኣይኖርም። መንግስት ለኣንዳንድ የህብረ ብሄር ድርጅቶች ፈቃድ ሰጥቶና እድገታቸውን አየከረከመ የሚያኖራቸው ኣንዱ በስልጣን ላይ ያቆየኛል የሚለው እምነቱ ስለሆነ ነው። ብዙሃኑን ለመያዝ፣ ግጭቶችን ለመቀነስ ነው። ከዚህ ውጭ ኢትዮጵያ በኣሁኑ ሰዓት መድብለ ፓርቲን የሚያስተናግድ ሲስተም ኣልቀረጸችም።  ብሄራዊ ድርጅቶች የቆሙት ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ስላላቸው እንጂ ሲስተሙ እየጠለፈ የሚጥል ነው።

  1. የፖለቲካ ባህላችን

በእኔ እምነት ይህም የተወሰነ ተጽእኖ የፈጠረ ቢመስለኝም እንደ ዋና ችግር ግን ኣላየውም። በርግጥ ነው በተለይ ቀደም ያለው ትውልድ እስካሁን የግራው የፖለቲካ ተመክሮ ተጽእኖ ፈጥሮበት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የተለወጡና በኣዲስ መንፈስ የተነሱ ደግሞ አሉ። ያልተለወጡትና ዛሬም በድሮ በሬ ለማረስ የሚሹቱ አነሱ በርግጥ እርስ በርስ ሲጠላለፉ ይታያል። ይሄ መቀረፍ ያለበት ችግር ነው። ለኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መሽመድመድ ግን እንደ ዋና ምክንያት ኣይታይም። ያም ሆኖ ግን የፖለቲካ ባህላችን ሊያድግ የሚገባው ብዙ ነገር ኣለውና በመድብለ ፓርቲው ስርዓት እድገት ላይ የተወሰነ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። ከዚያ ውጭ መንግስት ራሱ ተቃዋሚውን የፖለቲካ ባህላችን ደካማ ነው እያለ ቅስማቸውን ለመስበር እንደሚሰራ ይታወቃልና ፓርቲዎች ባህላችን ጥሩ ኣይደለም እያሉ ራሳቸውን ማፍረስ ለመንግስት እድሜን ከመጨመር ሌላ ኣይጠቅምም።እሚስተካከለውን ማስተካከል መድብለ ፓርቲን የሚሸከም ልብና ትከሻን ማዳበር ያስፈልጋል።

  1. የግል ዝንባሌዎች

ኣንዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ኣለመጠናከር አስተዋጾ ያደረገው ጉዳይ ደግሞ  ፖለቲካ በሃገራችን ውስጥ ሙሰኛ ስለሆነ ነው። ከፍተኛ የሚባሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድሎችን ሁሉ ዘርፎ ይዟል። በተለይ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የትምህርት እድልን ሳይቀር ዘርፎ የወሰደ በመሆኑ ፖለቲካው ሙሰኛነቱ ጫፍ ረግጧል። ስኮላርሺፕ ለማግኘት፣ በስራ ላይ እድገት  ለማግኘት፣ የተሻለ ኑሮ ለመኖርና በተሰብንና ዘመድን ለመርዳት፣ ወደ ፖለቲካ ጠጋ ማለት ኣዋጭ ነው። ፖለቲካው እነዚህን ኦፖርቹኒቲዎች መዝረፉና ሙሰኛ መሆኑ ያመጣው ኣንዱ ችግር እድሎች በጠበቡበት ድሃ ኣገር የሚኖሩ ዜጎችን እድል ፍለጋ ሳያምኑበትም ቢሆን ወደ ፖለቲካ እንዲሳቡ ያደርጋል። ከመንግስት ጋር ኣጎብድደው እየሰሩ የተሻለ ትምህርት ለማግኘት ይጥራሉ። ኣንዳንዶች ደግሞ ገዢው ፓርቲ ደመወዝ እየቆረጠላቸው በተቃዋሚ ስም መንግስትን የሚደግፉም ይኖራሉ። ይህ ችግር በሰፊው በአገር ደረጃ ሲታይ ፖለቲካችን ጥሪ ባላቸው ኣስተዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን በብዙ እድል ፈላጊዎች የተጠቀጠቀ ሰሚያደርገው ኣጠቃላይ ፖለቲካችንን ጨዋታውን ኣበላሽቶብናል ይመስለኛል። ፖለቲካው ከመንግስትም በላይ ሆኖ ፓርቲ መንግስትን ሳይቀር ውጦ በሚኖርበት ኣገር፣ ፖለቲካው እንዲህ በሰፊው እድሎችን ሁሉ ከየሲቪል ሰርቪሱ ሰርቆ በሚኖርበት ኣገር፣  መድብለ ፓርቲ ኣፈር ይበላል። ፖለቲካም ኣያድግም።

ማጠቃላያ

እነዚህ ከላይ የጠቃቀስኳቸው ችግሮች ለሃገራችን መድብለ ፓርቲ ስርዓትና ለፖለቲካችን  እንቅፋቶች ናቸው ብለናል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ብዙዎቻችን ጠንካራ ፓርቲ ባለመኖሩ በጣም እናዝናለን። ለምንድነው ጠንካራ ፓርቲ የፈለግነው?  በአሁኑ ሰዓት ለምን ጠንካራ ፓርቲ ፈለግን? ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲስ ማለት ምን ማለት ነው?። መድብለ ፓርቲ ስርዓት በጠፋበት ኣገር ጠንካራ ፓርቲ ስንል በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ጽህፈት ቤት እየከፈተ የጦፈ የቢሮ ስራ የሚሰራ፣ ብዙ ኣባላት የመዘገበ ወዘተ ከሆነ  ስህተት ነው። ላም በሌለበት ኩበት ለቀማ ማሰብ ነው። እንዲህ ዓይነት ጥንካሬ የሚያስፈልገው መድብለ ፓርቲ ስርዓት ባለበት ምህዳሩ ባለበት ኣገር ነው። የኣሁኑ ትግል ከዚህ ይለያል። ትግሉ የነጻነት ትግል ነው። መድብለ ፓርቲ ስርዓትን ከምር ለመጀመር ነው ትግሉ። ለዚህ ደግሞ ብዙ ኣባል የመዘገበ ብዙ ቢሮ ያለው ድርጅት ሳይሆን የሚያስፈልገን ኣንድ ሰውም ሊበቃን ይችላል። ትግልን የሚመራ ኣንድ የነጻነት ታጋይ ሊበቃ ይችላል። በአሁኑ ሰዓት የተነሳውን የኦሮምያ ኣመጽ የትኛው ጠንካራ ፓርቲ ነው የቀሰቀሰው? ማንም ፓርቲ ኣይመራውም። ህዝብ ነው ያስነሳው።

አሁን እኛ ጠንካራ ፓርቲ የምንለው በምርጫ ያሸንፍልናል ሳይሆን ሰላማዊ ትግልን ይመራል ብለን ኣስበን ከሆነ ትክክል ነው። ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው ከድርጅታዊ ጥንካሬው በላይ የጥቂት ኣመራሮቹ ቁርጠኝነት ይበልጥብናል። እነዚህ ድርጅቶች ኣባላት ምዝገባ ላይ ጊዜ ማጥፋት የለባቸውም። ሁሉም በልቡ ኣባላቸው ነው። ለዚህ ነው ኣንድ ጊዜ ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ሲጠራ ያን ያህል ሰው የወጣው። በልቡ ኣባል ሆኖ የጨረሰውን ሰው ፎርም ካላስሞላን ብሎ ጊዜ ማጥፋቱ ዋጋ የለውም። ይልቅ ህዝቡን በሰላማዊ መንገድ ለመብቱ እንዲታገል ማድረግ ነው። ይህን ግፍ የጠገበ ህዝብ ስለነጻነት ልናስተምረው፣ ስለለውጥ ጥቅም ልናስተምረው ኣያሻም። የሚያስፈልገው ትግልን የሚመሩ የነጻነት ታጋዮችን ማፍራት ነው።

ጠንካራ ፓርቲ ቢኖረን መልካም በሆነ። ነገር ግን በተለይ በሃገር ቤት ይህን ኣይነት ፓርቲ በኣሁኑ ሰዓት መጠበቅ ችግር ኣለው። ዋናው ማወቅ ያለብን ነገር ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ኣላቸው። ባይመዘግቡትም፣ የድርጅት ኣባል ኣድርገው መታወቂያ ባይሰጡትም ህዝቡ ኣባል ሆኖ ጨርሷል። በመሆኑም ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁኑ ፈጣን ምልሽ የሚሰጠው ሰፊ ህዝብ ኣለ። ህዝባዊ ተቃውሞዎችን መምራት የሚችል የተሰጡ መሪዎች ያሻናል። በዚህ ጊዜም ጠንካራ ፓርቲ ስንል የላይኛውን መሪዎች የመስዋእትነትና የቆራጥነት መንፈስ የሚመለከት ነው። ጠንካራ መሪዎች ብቅ ሲሉና ተቃውሞዎችን ሲመሩ ህዝቡን ለመብቱ ሲያታግሉት ያን ጊዜ ብዙዎችን ውጦ ጠንካራ ፓርቲ ወጣ ይባላል። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን ማድረግ ያለብን መልካም ራእይ ያላቸውን ፓርቲዎች ውጤት ተኮር እንዲሆኑ መከታተል ጠቃሚ ነው። መቼም ጠንካራ ፓርቲ ሁሌም እንሻለን። ይሁን እንጂ የአሁኑ አንገብጋቢ ጥያቄያችን የህዝቡን መብት የሚያስመልሱ ቆራጥ የነጻነት ትግል መሪዎችን ነው። ስለዚህ ህዝቡ መረዳት ያለበት ነገር ጣንካራ ፓርቲ መጠበቁ ጊዜ ይወስዳል። የፓርቲውም ቁጥር ገና ሊጨምር ይችላል። አሁን የሚያስፈልገው ዜጎች ለነጻታቸው፣ ለመብታቸው በራሳቸው መቆምን ነው። ህዝባዊ እምቢተኝነቶች መሪዎችን ያፈራል። ታላቁ መሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ የነጻነት ትግል ውጤት ነው፣ ከህዝብ ትግል መሃል የወጣ ነው። ማርቲን ሉተር ሳይሆን ትግሉን ያፈራው ትግሉ ነው ማርቲን ሉተርን ያፈራው። ኔልሰን ማንዴላ በራሳቸው አንደበት እኔ የደቡብ አፍሪካዉያን የትግል ውጤት ነኝ ብለዋል። መሪ የሚያፈራ ትግል ማድረግ አለብን። ኢትዮጵያን በተሻለ አቅጣጫ መምራት የሚችሉ ብዙ ልጆች አሉ። ጭቆና ተጭኗቸው ይሆናልና እነዚህን መሪዎች የህዝብ ትግል ያወጣቸዋል። በሌላ በኩል ፓርቲዎችም በቆራጥነት ትግሉን ምሩ፣ ህዝቡን ለመብቱ አታግሉት። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ።

posted by tigi flate

ecadforum com

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s