የበእውቀቱ ስዩም፣ የተስፋዬ ገብረአብና የእኛ ኢትዮጵያ

(ዮሴፍ ወርቁ ደግፌ)

«ነፍጠኞች የሴቶቻችንን ጡት እኛ ከበግ ላይ ጸጉር እንደምንሸልተው እንዲያ ነበር የሚቆርጡት። እነዚህ ሰዎች በግ ሲያርዱ በስመአብ ብለው ይጀምራሉ። የሴቶቻችንን ጡት

ሲቆርጡ ግን በስመአብ አይሉም። ግን ሀይማኖት አለን ይሉናል»
(ተስፋዬ ገብረአብ “የቡርቃ ዝምታ”)

«…ባጠቃላይ በሚኒልክ ተፈጸመ የተባለው ያኖሌ ጡት ቆረጣ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሰነዶች ላይ ያልተመሰረተ ለመሆኑ ይህ በቂ ማስረጃ ይመስለኛል። በአርሲ ታሪክ ዋና ባለሙያ የሆነው ፕሮፌስር አባስ ገነሞ በመጽሀፉ ውስጥ ጡት ቆረጣ መፈጸሙን የሚያሳይ አንድም የታሪክ ሰነድ ማቅረብ አልቻለም»

(በእውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር”)

«በፍትህ በኩል ግን ጣሊያን ይሻል ነበር። አማራ ሲመጣ ሰው የገደለ ይገደል የሚል አዋጅ አመጡና እርስ በራስ መተላለቅ ሆነ»

(ተስፋዬ ገብረአብ “የቡርቃ ዝምታ”)

«የሁላችንም አባቶች የሁላችንም ጌቶች በፈረቃ ግፍ መፈጸማቸው በታሪክ ተመዝግቧል። በዘመናችን የምሬትንና የቂምበቀል ፉከራን ርግፍ አድርገን ትተን በሚያቀራርቡ በሚያስተባብሩ ሀሳቦች ላይ ከተጠመድን ከአባቶቻችን የተሻለ አለም እንደምንፈጥር ጥርጥር የለኝም»

(በእውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር”)

የበእውቀቱ ስዩምን «ከአሜን ባሻገር» አዲስ መጽሀፍ ካነበብኩ በኋላ፥ ጥቂት ዘመናት ወደፊትና ወደኋላ በምናቤ ተንጬ ሳበቃ፥ አንድ ጓደኛዬን የበእውቀቱ ስዩምንና የተስፋዬ ገብረአብን ሥራዎች እንዴት ታነጻጽራቸዋለህ? ብዬ ጠየቅሁት። “በይዘት ነው በቅርጽ?” በማለት ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰው። በ«ይዘት» አልኩት።

“ተስፍዬና በእውቀቱ ምንና ምን ናቸው፣
የጆሮ ጉትቻ፣ የአንገት ሀብል ናቸው” (እንደማይል ብጠብቅም)

“ተስፍዬና በእውቀቱ ምንና ምን ናቸው፣
የመርዝና የመድሀኒት ብልቃጥ ናቸው” (ይላል ብዬ ግን አልገመትኩም)

 

ይህች መጣጥፍ በ“መድሀኒት” እና በ“መርዝ” ብልቃጥ ሥራዎች ላይ አጭር ዳሰሳ የምታደርግ ናት። የተስፋዬ ገብረአብ እኩይ ፖለቲካዊ ትርክቶች ትዝታቸው ሳይደበዝዝ፥ ከእድሜው በላይ የበሰለው ወጣቱ ብእረኛ በእውቀቱ ስዩም፣ ለተስፋዬ መርዛማ ጽህፎች ማረከሻ መድሀኒት፣ ታሪክን በማስረጃ እያጣቀሰ ያቀረባት መጽሀፍ «ከአሜን ባሻገርን» ትሰኛለች። ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊያነባት የሚችል እጥር ምጥን ያለች ናት።

በእውቀቱ ስዩም ባለቅኔ ገጣሚና ድንቅ የወግ ጸሀፊ ሲሆን፥ አሁን ደግሞ የታሪክ ተመራማሪ እየሆነ ነው። ተስፋዬ ገብረአብ ጋዜጠኛና አጫጭር መጣጥፍ ጸሀፊ ነው። ተስፋዬ ገብረአብና በእውቀቱ ስዩም በጽሁፎቻቸው ይዘት ብቻ ሳይሆን፥ በጥበባዊ እውቀት (knowledge of wisdom) ደረጃም ቢሆን ሊወዳደሩ የሚችሉ አይደሉም። በእውቀቱ የትየለሌ ይልቃል። ተስፋዬ ገብረአብን ከበእውቀቱ ስዩም የሚለየው ዋና ነገር ደግሞ ከሙያ ስነምግባርና ከሞራል ሀላፊነት ውጭ፥ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጥላቻን ወይም ጠላትነትን ማእከል አድርጎ፥ የኦሮሞን ህዝብ እንደ ፖለቲካ መሳሪያነት በመጠቀም፥ ጥናት ያላደረገበትን ፖለቲካዊ ታሪክ፥ እንደ አፈታሪክ አጋኖ በመጻፍ፥ ህዝቦችን ለማጋጨት የሚጥር፥ እበላ ባይ የአስቤዛ ጸሀፊ መምሰሉ ነው። ይሁንና በ«ጀሚላ እናት» መጽሀፉ ምርቃት ላይ፥ በዋሽንግተን ዲሲ በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ በጣም ጥቂት የኦሮሞ ልጆች ብቻ በተገኙበት ባደረገው ንግግር ላይ ተስፋዬ ምኞቱን ከዚህ በታች እንደተጠቀሰው ገልጿል። (የቪዲዮ ክሊፑ ይገኛል) መልካም ምኞት ነው።

«በእውነቱ ቅር ነው የሚለኝ ዛሬ፥ የደስታዬ ቀን ነው አልልም። የልቤን ነው፣ የልብህን ተናገር ካላችሁኝ ደስተኛ ነኝ ልል አልችልም። ምክንያቱም የትግራይ ሰዎችም፥ ኤርትራውያንም፥ አማሮችም፥ ኦሮሞችም፥ አንድ ትልቅ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው መጽሀፌን ብመርቀው ደስ ይለኛል። ይኼ ባለመሆኑ ቅር ይለኛል። ይሄ እንዲመጣ ነው የምመኘው» (የተስፋዬ ገብረአብ «የጀሚላ እናት» የመጽሀፍ ምርቃት ንግግር)

በእውቀቱ ስዩም የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪነቱን ፍንጭ የሚያሳይ ጠንካራ ብእር ያነሳው እንደ ፕሮፌሰር አስመሮምና እንደ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ ለመሳሰሉት፥ የኢትዮጵያ መበታተን ለኤርትራ ህልውና የሚበጅ ለሚመስላቸው፥ በጠላትነትና በጥላቻ ስሜት በተዛባ ታሪክ ለጻፉት የፕሮፓጋንዳ ስራ አጻፋ ምላሽ፥ በጥናት የተደገፈች፥ ለማጠቃሻነት (Reference) የምትበቃ «ከአሜን ባሻገር»ን በመጻፍ ነው። በእውቀቱ ስዩም ፖለቲካዊ ታሪክን ያለአድሎ (witout bias) ለመጻፍ ከእድሜው በላይ የሚታትር ብርቱ ጸሀፊ የሆነበት ምክንያት ፖለቲካዊ ወገንተኛነት፤ የ«ዘሬን ያንዘርዝረኝ»፤ ወይም እበላባይነት ችግር ስለሌለበት ይመስለኛል። እርሱም በተዘዋዋሪ ጠቅሶታል። በፕሮፌሰር አስምሮምና በተስፋዬ ገብረአብ መካከል ላለው ልዩነትም፥ ፕሮፌሰር አስምሮም ኤርትራ ተመልሳ በኢትዮጵያ ውስጥ ትካለላለች ከሚል ስጋት (insecurity) ታሪክን

እያወቁ፥ ነገርግን እያጣመሙ የሚጽፉ ምሁር ሲሆኑ፥ ተስፋዬ ደግሞ ያለእውቀት በድፍረት፥ ያለጥናታዊ ማስረጃ አፈታሪክ ላይ ተመስርቶ የሚጽፍ የአስቤዛ ጸሀፊ መሆኑ ነው።

የተስፋዬም ይሁን የበእውቀቱ ጽሁፎች የአስተዳደግ ተጽዕኖ ይታይባቸዋል። በእውቀቱ ስዩም «አምላክ አልባ» (Atheist) መሆኑን በግልጽ እየተናገረ፥ ነገርግን በ«ከአሜን ባሻገር» መጽሀፉ «የሚያስታርቁ ብጹአን ናቸው» (ማቴ.5፥9) የሚለውን የክርስትና መርህ የሚከተል ጸሀፊ ተመስሏል። «አምላክ የለኝም» ቢልም ታሪካዊ እውነታን ግን በማስረጃ በመግለጽ፥ አድልኦ የሌለበት ስራ አቅርቧል። ተስፋዬ ገብረአብ ደግሞ «ክርስቲያን ነኝ» እያለ፥ ነገርግን የክርስትና መርህን ተገላቢጦሽ «በወንድማማች መካከል ጸብን የሚዘራ» (ምሳሌ 6:19) እኩይ ጸሀፊ ሆኖ ይገኛል። ተስፋዬ የክርስትና እምነት ቢኖረውም፥ በአስተዳደጉ ኢትዮጵያን እንዲጠላ የተደረገበት ለመሆኑ ማስረጃው የዘመናት የጥላቻ ምርጊት ወደጠላትነት ተቀይሮበት፥ የጽሁፍ ስራዎቹ በሙሉ ኢትዮጵያን ወደ መበታተን የሚገፋፉት መሆናቸው ነው።

በአንድ ሰው ውስጥ እንዲህ አይነት ተቃርኖ (paradox, self-contradictory) ከአስተዳደግ ተጽእኖ ውጭ በደም /በመወለድ ብቻ/ የሚመጣ አይደለም። መጽሀፍ ቅዱስም አንድ ዛፍ ጣፋጭም መራራም ፍሬ ሊያፈራ አይቻለውም ነው የሚለው። በርግጥ ተስፋዬ ኦሮሚያን እወዳለሁ ይላል። ኦሮሚያን መውደዱ በንጹህ ልብ ከሆነ ምንም ችግር የለበትም። ነገርግን ህዝብን በመሳሪያነት ለመጠቅምና ለእበላ-ባይነት ከሆነ፣ ጊዜውን ጠብቆ ተስፋዬ ክፉ ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ መሆኑ አይቀርም። ተስፋዬ ገብረአብ የአሰፋ ጫቦ ጽሁፍን የሚመስል እንደውሀ የሚፈስ የስነጽሁፍ ስጦታ ነበረው፤ ነገርግን በጽሁፎቹ ይዘት ምክንያት፥ ዛሬ እጅግ በጣም በጥቂት ሰዎች (ጥቂት ኦሮሞዎች ብቻ) ተወስኖ፥ ከአብዛኛው ኦሮሞም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦች ተነጥሎ በቅሬታ ውስጥ እንደሚኖር በ«የጀሚላ እናት» መጽሀፍ ምርቃት ላይ ራሱ መናገሩ ከላይ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ደግሞ ተስፋዬ አንድን ብሄር በጠላትነት በማየት እያብጠለጠለ በሚጽፋቸው እኩይ ስራዎቹ በመደሰት፥ ተራ ፖለቲካዊ ድጋፍን መፈለግ፥ የራስን ትልቅነት ባለመረዳትና በራስ ባለመተማመን የሚመጣ ጉድለት ያስመስላል። ይህም ተስፋዬ ገብረአብን የኦሮሞ «መሲህ አዳኝ» አድርጎ የማየት ችግር ነው። ይህንን በማለቴ “ነፍጠኛ ስለሆንክ ነው” ምናልባት የምትሉ ብትኖሩ፤ መግለጽ ካስፈለገ ከጃዋር መሀመድ የበለጠ ኦሮሞ መሆኔን ላረጋግጥ እችላለሁ። (ጃዋር መሀመድ በኢሳት ቲቪ ላይ «በአባቴ 50% እስላም ኦሮሞ ነኝ በእናቴ 50% አማራ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነኝ» ማለቱን ያስታውሷል) የሰው ልጅ መቸም ቢሆን ከአንድ ወይም ከሁለት ከሶስትም ዘር ሊወለድ መቻሉ እውነት ነው። ከዚህኛው ዘር ልወለድ ብሎ ጠይቆም አይወለድም። የሰው ትልቅነት የሚለካው ለዘሩ ከሚያደርገው ተቆርቋሪነት በላይ ለሌሎች በሚያደርገው መልካም ስራ መሆኑን አንዘንጋ። እምነታችንም ይህን ያዘናል።

የበእውቀቱ ስዩም «ከአሜን ባሻገር» መጽሀፍ ይዘትዋ እንደ ርዕስዋ ነው። ዋና ጭብጧ በየዘመኑ የሚሰጠንን ፖለቲካዊ ታሪክ ኪኒን ዝም ብለን አንዋጥ። ሁላችንም በጋራ ላመጣነው በሽታ፥ በጋራ መድሀኒት እንፈልግ፥ በጋራ እንፈወስ ነው። ጸሀፊው በዚህች አነስተኛ መድብል ውስጥ ጠለቅ ያለ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ጭብጥ በማንሳት በጥናትም በመደገፍ፥ ብዥታ አለባቸው የሚላቸውን በግልጽ ይሞግታል። አብዛኛዎቻችን ወደዘራችን ባጋደለ ታሪክ አመለካከት በመፍገምገም፣ ሚዛኑን የጠበቀ ፖለቲካዊ እይታ ለመያዝ ተቸግረናል። አካሄዳችን ልከኛ ስላልሆነ ለማንኛችንም አይበጅም። በእውነተኛ የታሪክ ማስረጃ (historical facts) ይዘት እንከራከር፥ እንግባባ፥ የወደፊቱን በማሰብ በይቅርታና በምህረት እንኑር ይላል።

ኑ በስነስርዓት እንወቃቀስ፤ ማንም ከደሙ ንጹህ የለም። ሁሉም የኢትዮጵያ መሪዎች በጉልበት በግፍ የሚገዙ ነፍጠኞች ናቸው። የሩቁን ትተን ከአጼ ዮሀንስ እንኳን ብንጀምር፥ አጼ ዮሀንስ አጼ ቴዎድሮስን ለባእድ የእንግሊዝ ጦር በር ከፍተው ለሞት አሳልፈው በመስጠት ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ከሆኑ በኋላ፥ ኦሮሞንም አማራንም ሌሎችንም አስገብረው የገዙት በነፍጥ እንጂ በዲሞክራሲ አይደለም። አጼ ዮሀንስ ለንግስት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤ የአዘቦ ኦሮሞ ሙስሊሞችን በሀይል መግዛታቸውን ያሰፈሩበት ማስረጃ እንዲህ ይላል።

«ባገሬ ኧዘቦ የሚባል የኦሮሞ እስላም አለ። ከርሱም ሽፍታ ተነሳብኝ፤ ለማጥፋት ዘመትሁ፥ እነርሱንም በእግዚአብሄር ሀይል አጠፋሁኝ»

(በእውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር”)

አጼ ዮሀንስ ጎጃምን ለማስገበር በወረሩበት ጊዜ፥ የጎጃም ባላገሮች ከአጼ ዮሀንስ ጦር እግዚአብሄር እንዲታደጋቸው ተማጽነው ኖሮ፥ እግዜር ግን ባለመድረሱ፥ ንጉሱ በጎጃም ብዙ ጦርና ህዝብ በመጨረሳቸው ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ የወደቀች አንዲት ጎጃሜ የሚከተለውን ስንኝ ቋጥራ ነበር ይለናል «ከአሜን ባሻገር»።

ከሀበሻ ወዲህ ከሀበሻ ወዲያ፥
ሰውን ገረመው እኔንም ገረመኝ፤
ዮሀንስ እግዜርን ገድሎታል መሰለኝ፤ (በእውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር”)

*/ በዚህ አገላለጽ ግን የአጼ ዮሀንስን ታላቅነት እያቃለልሁ አይደለም። ለሀገራቸው ነጻነት አንገታቸውን ለሰይፍ የሰጡ በጀግንነት ከወደቁት የሀገራችን መሪዎች አንዱ መሆናቸውን ማንም አይክድም/

አጼ ሚኒልክም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ደቡብ ኢትዮጵያ በአንድ ማእከላዊ ንጉሰ ነገስት መንግስት ስር እንዲኖር ያስገበሩት፣ በወረራ በነፍጥ እንጂ፣ በሰላማዊ መድረክ በድርድር አልነበረም። በዚያ ስልጣኔ አልባ

ጭለማ ዘመን ቀርቶ ዛሬም በኢትዮጵያ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ድርድር አይሰራም። በ19ኛው ክፍለዘመን በኢትዮጵያ ይቅርና በአውሮፓና በአሜሪካ ግዛት የተስፋፋው በወረራ በሀይል በጠብ-መንጃ ነው። በተለይም ከሚኒልክ መንግስት መስፋፋት ጋር ለሚነሳው ወቀሳ፥ የሚኒልክ ወታደር መሉ በሙሉ አማራ ብቻ በማድረግ ታሪክ ማዛባት ለማንኛችንም አይጠቅምም። የአማራ ጦር ብቻ ይሆን ዘንድም አቅም (የህዝብ ብዛት) አልነበረውም። ስለዚህም አጼ ሚኒልክ በወረራም ሆነ በወዳጅነት (በአምቻ ጋብቻ) ከሸዋ ከኦሮሞና ከጉራጌ ባላባቶች (ያካባቢ ገዢዎች) ጋር ከዋና ዋና የጦር አበጋዞች እንደነ ራስ ጎበና ዳጨ የመሳሰሉ የኦሮሞ ታላላቅ መሪዎችን በፊት አውራሪነት በማዝመት ሀረርን፣ አርሲን፥ ከፋን ወላይታን በማስገበር አንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስትና ጦር አቋቁመዋል። በዚህም በአድዋ ጦርነት ለቅኝ ገዥ ያልተንበረከከ፥ መላው የአለም ጥቁር ህዝብ የኮራበት ጦር በመፍጠር አጼ ሚኒልክ ከሀገራቸው አልፎ በአፍሪካውያን ለዘላለም የሚዘከር ስራ ሰርተው አልፈዋል። */የራስ ጎበና ልጅና የአጼ ሚኒልክ ሴት ልጅ ጋብቻ ውጤት የሆነውን የወሰንሰገድ ወዳጆን ፎቶ ማስረጃ ደግፎ ያቀረበ ታሪክ ጸሀፊ ያገኘሁት በእውቀቱ ስዩምን ብቻ ነው/*

«ምኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ ወሳኝ የነበሩ ሰዎች ከተለያየ ብሄረሰብ የተገኙ እንደሆኑ ሁሉ በማስገበር ዘመቻ የተሳተፈው ሰራዊትም እንዲሁ ኅብረብሄራዊ መሆኑ እሙን ነው። ይልቁንም ኦሮሞ ያልተሳተፍበት የሚኒልክ ዘመቻ ማግኘት ይከብዳል» (በእውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር”)

እንደ ተሥፋዬ ገብረአብ «በፍትህ በኩል ግን ጣሊያን ይሻል ነበር። አማራ ሲመጣ ሰው የገደለ ይገደል የሚል አዋጅ አመጡና እርስ በራስ መተላለቅ ሆነ» ብሎ ለመናገር እጅግ ይከብዳል ለህሊና ይሰቀጥጣል። ምክንያቱም ሚኒልክ በአድዋ ጦርነት ጣልያንን ድል ባይመታ ኖሮ፥ የቅኝ ተገዢነት ሰለባ በመሆን ዘላለም በበታችነት ስሜት (inferiority complex) እንኖር ነበርና ነው። የኤርትራ ቅኝ መገዛት እንኳን ዝንተ አለም እየቆጨን የሚኖር ነው።

ኦሮሞና የሀገር መሪነት ስልጣን ጥያቄ፦ ኦሮሞ በህዝብ ብዛትም በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ ጂኦግራፊም አብላጫ (Majority) ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የመሪነት ስልጣን አልነበረውም የሚለው ዛሬም ድረስ ውሀ የሚያነሳ ጥያቄ ሆኖ ይገኛል። ቀደም ባሉት የዘውድ መንግስታት የኢትዮጵያ መሪዎች የኦርቶዶክስ እምነታቸው ከፖለቲካ አመራራቸው ጋር እየተቀላቀለባቸው ባሳደረባቸው “በጎ ተጸእኖ” የተነሳ፥ በኦሮሞ ስማቸው በንጉስነት አልተጠሩም እንጂ ኦሮሞ ኢትዮጵያን መርቷል የሚል ወገን ብዙ ነው። ለምሳሌም የወሎው ንጉስ ሙስሊምና ኦሮሞ የነበሩት ራስ አሊ (በኋላ በክርስትና ስማቸው ንጉስ ሚካኤል የተባሉት) ልጅ የሆነው አቤቶ/ልጅ ኢያሱ እንዲሁም ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴን ይጠቀሳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ከገዳ ባህል የተነሳ የኦሮሞ ንጉስ በኢትዮጵያ የነገሰ ባይኖርም በታሪክ በግልጽ እንደሚታወቀው በየጁ ዳይናስቲ (Yejju Daynasty) በ17ኛው ምዕተ አመት ኦሮሞዎች በገዳ አመራር (Collecetive Leadership) አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍል የስራ ቋንቋ *ኦሮምኛ በማድረግ እንደመሩ በታሪክ ተጠቅሷል። *ኦሮምኛ በዚህ ዘመን የስራ ቋንቋ እንደነበረ አንዳንድ የውጭ ጽሁፎች ጠቅሰዋል። አቶ ጃዋር መሀመድም እንደ ፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪነት እንደገለጸውም የኦሮሞ ባህል ለአግድሞሽ (Horizontal Leadership) እንጂ ከላይ ወደ ታች በሚወርድ በአንድ ፈላጭ ቆራጭ ሰው ወይም ንጉስ (Vertical Leadership) ለመተዳደር የገዳ ስርአትና ባህሉ አይፈቅድለትም ይላል። ስለዚህም ኦሮሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ንጉስ ለመሆን በማንኛውም መመዘኛ አቅም አጥቶ ሳይሆን፥ በባህሉ የተነሳ ለመንገስ አልቻለም ለማለት እንችላለን ማለት ነው። የሰሜን ሰዎች ግን (አማራና ትግሬ) ከኦርቶዶክስ እምነታቸው የተነሳ የቤተክርስቲያን የአደረጃጀት መዋቅርን በመከተል (በአንድ ሊቀ ጳጳስ መመራት) ነገስታቶቹ ሀይማኖትን ከፖለቲካ ጋር በመቀላቀል፥ እየተገለባበጡም ቢሆን በፈረቃ የንጉስ አመራርን እውን አድርገዋል። ኦሮሞም በጋዳ ስርአት (Collective Leadership) ከላይ እንደተጠቀሰው በየጁ ዳይናስቲ አገር መርቷል፥ ብለን መደምደም ሁላችንንም የሚያስማማ ይመስለኛል። በዚህ ከተስማማን የኋላውን/ያለፈውን ለትምህርታችን (ከስህተት ለመማር) እያነሳን የወደፊቱንም በጋራ የምንኖርበትን የሰላምና የእድገት ራዕይ በተነጠል ሳይሆን በአንድነት መተለም ለሁላችንም የሚያዛልቅ ነው።

ነፍጠኛነት፦ «ከአሜን ባሻገር» በታሪካዊ መረጃ ኦሮሞም ነፍጠኛ እንደነበረ ትሞግታለች። ኦሮሞ ነፍጠኛ አልነበረም ብሎ ማመን፥ ታላቁን የኦሮሞን ህዝብ ህዳጣን የማድረግ ያህል ነው። ለምሳሌ ያህል የሲዳሞ፥ የጉራጌ፥ የጌዴኦ፥ የደቡብ-ህዝቦች ነፍጠኞች የአማራ (የክርስትና) ስም ቢይዙም በርካታ ነፍጠኞች ኦሮሞዎች እንደነበሩ ወደ ቦታው ሄዶ ዛሬም ድረስ ያለውን አሻራ ለማረጋገጥ ይቻላል። እነዚ ነፍጠኞች ከታላቁ ጀግና አርበኛ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ሀገረ ገዥ ከነበሩት ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ጋር ጠብመንጃ አንግተው የሄዱት ኦሮሞዎች ናቸው። በኋላ ላይ በህዝቦች ውህደት (Assimilation) ኦሮሞነት እየቀነሰ በወቅቱ ክርስትና መነሳትና አማርኛ መናገር እንደ ስልጣኔ ስለሚቆጠር፥ ቀስበቀስ ኦሮሞው ክርስቲያን ወይም አማራ ነኝ ማለት ጀመረ። የአሰፋ ጫቦ «የትዝታ ፈለግ» መጽሀፍም የጋሞ ነፍጠኞች ኦሮሞዎች ነበሩ ይላል። በኢህአዴግ መንግስት፥ የጉራጌ ህዝብን ወክለው የፓርላማ አባል የነበሩ ዶ/ር ሀይሌ የተባሉ ሰው (የአባታቸው ስም የተዘነጋኝ) «የጉራጌ ነፍጠኛ እኮ ኦሮሞ ነው፥ ጉራጌ ወደ ሌላ የኢትዮጵያ ክፍል ሄዶ ጥሮ መኖር የጀመረው በኦሮሞ ነፍጠኞች መሬቱ ስለተወሰደበት ነው» በማለት በፓርላማ ውስጥ የተናገሩት በቴሌቪዥን ስርጭት መተላለፉን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያስታውሳል። በኢቲቪ ማስረጃው ይገኛል።

ስም የመቀየር ችግር፦ ስም መዋጥ ይለዋል በእውቀቱ። “ከቶሎሳ ወደ ቶማስ” “ከራስ አሊ ወደ ራስ ሚካኤል” “ከተስገራ ወደ ተስፋዬ” ወዘተ የተጀመረው ከገጠሬነት ወደ ከተሜነት በ“መሰልጠን” ሂሳብ እንጂ በዘር ጥላቻ ላይ አይደለም። እንዲሁም በሀይማኖታዊ በጎ ተጽእኖ፥ ይህም በጥምቀት (በክርስትና መነሳት) ስም ነው ይለናል «ከአሜን ባሻገር» መጽሀፍ። በወቅቱ በጥምቀት ወደ ክርስትና መግባትና የክርስትና ስም መያዝ የደህንነት ብቻ ሳይሆን የመሰልጠን ምልክት ተደርጎም ይቆጠር ስለነበረ ግለሰቦች ስማቸውን እስከመቀየር ደርሰዋል እንጂ “ስምህን ቀይር” የሚል አዋጅ አልወጣም ይላል። ኦሮሞውም፥ ደቡቤውም፥ ትግሬውም (አማራውም ቢሆን እርገጣቸው፥ ድፋባቸው፥ ልዋጥህ፥ ክንዴ፥ ጌጤ፥ ብርቄ፥ ማንጠግቦሽ የመሳሰሉትን ስሞች ይዞ) “ስልጣኔ” ፈልጎ ወደ ከተሞች ሲመጣ፥ የከተሜዎች ቀልድ እያስጠላው ስሙን ቀየረ እንጂ ዘርን ማጥላላት አልነበረም። የተስፋዬ ገብረአብ «ጫልቱ እንደ ሄለን» የተጋነነ ትረካ ዋጋ የሚያጣውም ለዚህ ነው።

የዘር ማንዘር ጉዳይ፦ በተለይም የመሪዎቻችን ዘር ተነሳ፥ ለምሳሌ ሀይለ ስላሴ ከኦሮሞነት ወደ አማራነት ራሳቸውን የቀየሩ ንጉስነገስት ናቸው። እናታቸው ከጉራጌ የተገኘች ቆንጆ ሴት፤ አባታቸውም ራስ መኮንን ጉዲሳ ኦሮሞ ናቸው። የሀይለስላሴ ባለቤት እቴጌ መነንም የወሎው ሙስሊም ኦሮሞ ንጉስ አሊ (በኋላ ንጉስ ሚካኤል) የልጅ ልጅ መሆናቸው ይታወቃል። አጼ ሚኒልክም አባታቸው የሸዋ አማራ፤ እናታቸው ብልህ ወላይታ ናት። መንግስቱ ሀይለማርያም ከኦሮሞ ከአማራና ከኮንሶ (ደቡብ) ብሄሮች ተወላጅ ነው። መለስ ዜናዊም ከኤርትራና ከኢትዮጵያ ወላጆች የተገኘ ነው። ኢሳይያስ አፈወርቂም ቢሆን ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ተወላጆች የተወለደ ነው። መሪዎቻችን ከዚህና ከዚያኛው ብሄር ተወለዱ ቢባሉም በሰብዕናቸው (በሰውነታቸው) የሰሩት በጎና ክፉ ስራዎቻቸው እንጂ ዘራቸው ምንም አያደርግልንም።

«እንደው ልፉ ሲለን ነው፥ ዜግነታችን እንጂ ዘራችን አይታወቅም» (በእውቀቱ ስዩም «ከአሜን ባሻገር»)

ፖለቲካዊ ታሪክ፦ ታሪካችን በብዙ ሺ ዘመናት የተሳሰረ፥ ውሉ የተወሳሰበ፥ ስንክሳር ነው። በቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ዘመን ብሄራዊ ጭቆና፤ በመንግስቱ ሀይለማርያም ዘመን እርስበርስ ጦርነት፤ በዚህ ላይ የማይረባ የግብርና ፖሊሲ ድርቅና ርሀብ አገሪትዋን አደቀቋት። ዛሬም ያገሪቱ ሩብ ያህል ህዝብ 25 ሚሊዮን ህዝብ ከድህነት ወለል በታች በሞትና በህይወት መካከል ይኖራል፤ ከ10ሚሊዮን በላይ ህዝብ በርሀብ ውስጥ ይገኛል። በዚህ ሂደት መቀጠል ያዋጣል ወይ? የሚያዋጣን ምንድነው? ተቃዋሚዎችን ቀርቶ፥ ኤርትራንም የሚጨምር ውይይት ድርድርና ብሄራዊ እርቅ በማድረግ አብሮ መስራት ያዋጣል። ይህም ባንድ ወገን አሸናፊነት (win/ loss) ሳይሆን፥ ሁሉም ወገኖች በሚያሸንፉበት (win-win) መፍትሄ ሰጥቶ በመቀበል (settling disputes by mutual concession) ነው። መግባባት ከሌለ በሂደት የሚከሰተው ችግር አደገኛ ነው። በተለይም በገቢ ልዩነት

(Economic Inequality) ምክንያት እየተባባብሰ ሄዶ ኢኮኖሚያዊና እና ሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለኝ። ወደብን በተመለከተም ኤርትራና ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ከሚያስፈጓት በላይ፥ ኤርትራና ጅቡቲ ኢትዮጵያ እንደምታስፈልጋቸው በተግባር ስለተረጋገጠ፥ አብሮ በመኖር በጋራ ለማደግ፥ መግባባት በስተቀር፥ የሀይል አማራጭ መጠቀም ቀውስ ነው። ከዚህ ጋር የሚያያዝ አንድ የኤርትራ ተወላጅ የሆነ ወንድማችን ያጫወተኝን እውነተኛ አባባል ላካፍላችሁ።

«ኢሳይያስ አፈወርቂ በነጻነት ማግስት ኤርትራን “ሲንጋፖር እናደርጋለን” ብለው ነበር። እውነትም ይኸው ሲንገር-ኤንድ-ፑር (Singer-and-Poor) አደረጉን»

ለዚህ ሁሉ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ምንጩ እኛው እንደሆንን ሁሉ፥ መፍትሄውም በኛው ዘንድ ብቻ የሚገኝ ነው። በታሪክ ላይ የተጠቀሰችው አልቃሽ እንጉርጉሮ፤

የገደለው ባልሽ፤
የሞተውም ልጅሽ፤ ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፥
ከቤትሽ አልወጣ፤

ሀዘን በሀዘን ላይ ለተደራረበባት ላንዲት ሴት ብቻ የተሰናኘ ሳይሆን ለእናት ሀገራችን ጭምር ለመሆኑ ታሪካችን ምስክር ነው። ይህ ጥልቅ ሀሳብ ያዘለ መልዕክት ከመካከላችን አንድም ንጹህ እንደሌለ ሁሉም ጥፋተኛ እንደሆነ የሚያሳይና በምህረትና በይቅርታ በጋራ እንድንነሳ የሚያሳስበን ነው። በእውቀቱ ስዩም በ«ከአሜን ባሻገር» መጽሀፍ ያለፈው አለፈ ለመጭው በማሰብ በጋራ በሰላም እንኑር የሚልባት ሶስት መስመር ስንኝ እንዲህ ተቋጥራለች።

አባትህ ለገዛ፥ አያትህ ለነዳ፥
አንተ ምን አግብቶህ ትከፍላለህ እዳ፤

(ተመስገን ተካ) ይልቅ መላ ምታ፤

ማሳረጊያ፦ በዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እምነት፥ ኢትዮጵያ እንኳን ልትበታተን ቀርቶ፥ ኤርትራም፥ ሶማሌም፥ ጅቡቲም፥ ሱዳንም፥ ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ሀገሮች፥ አንድነት በልዩነት በሚሆን (Unity with Diversity) እያንዳንዱ አካባቢውን በሚያስተዳድር የእድገት ትስስር በመጓዝ ወደ ታላቅ የምስራቅ አፍሪካ አንድ ሀገርነት መቀየር ይቻላል። “ግሎባላይዜሽን አለምን በሀይል እየገፋ ወደ አንድነት እያመጣን ነው” (የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚር ብሌር) በተለይም ኢትዮጵያ፥ ኤርትራና ጅቡቲ የኢኮኖሚ ውህደት

በመቀጠልም ፖለቲካዊ ውህደት የሚያመጡበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ለዚህም ራእይን ባለማጥበብ መስራት ይገባል ይቻላልም ብሎ ያምናል። ነገርግን «ኢትዮጵያ ብቻ ወይም ሞት» «ኦሮሚያ ብቻ ወይም ሞት» «ኤርትራ ብቻ ወይም ሞት» «ትግራይ ብቻ ወይም ሞት» «ኦጋዴን ብቻ ወይም ሞት» ወዘተ የሞት መፈክር ሞት እንጂ ዘላቂ ብልጽግናና ሰላም የሚያመጣ አይመስለኝም።

ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም። «የሶሻሊስት ጎራ» «የካፒታሊስት ጎራ» የሚል አይዶሎጂ ቀርቷል። አሜሪካ የአለምን ህዝብ 5% ብቻ ይዛ 95% አለምን የምታንቀጠቅጠው በኢኮኖሚ የበላይነት ነው። መጽሀፍ ቅዱስም «ላለው ይጨመርለታል፥ ከሌለው ያለውም ይወሰድበታል» ነው የሚለው (መንፈሳዊ ትርጉም ከአለማዊ ትርጉሙ በተቃራኒው ቢሆንም) በኢኮኖሚ በልጦ መገኘት ብቻ ነው በግሎባላይዜሽን ዘመን የሚያዋጣው። የኢኮኖሚ የበላይነት እንጂ የጉልበት ዘመን ላይ አይደለንም። አባይ አይገደብ የምትል ሁሉ ቆም ብለህ አስብ። አንድ ሀገር የሚሆን 25 ሚሊዮን ህዝብ በርሀብ እየተሰቃየ ሳለ፣ አባይ ሲገደብ ከጣና እጥፍ በሚሆን የግድቡ ኩሬ ላይ አሳ በማርባት አንድ ሚሊዮን ህዝብ እንኳን ይመግባል ብሎ ማሰብ እንዴት አይቻልም? ተቃውሞስ ቢሆን ይህ ምን አይነት የአስተሳሰብ ልዩነት ነው? ግድቡ ባለመገደቡ ይበልጥ የሚጎዳው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ገዢው መንግስት አይደለም። የአባይ መገደብ ከከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም በላይ ምስራቅ አፍሪካን ከጭለማ በብርሀን ሀይል ነጻ በማውጣት በኢኮኖሚ ጥቅም በማስተሳሰር ዘላቂ ሰላም የማምጣት ፖለቲካዊ ፋይዳው እጅግ ከፍተኛ ነው። የአፍሪካ ቀንድ ህዝብ በአለም ላይ የጎስቋሎች ጎስቋላ ድሀ ሲሆን፥ ምርጫው«ተባብሮ መልማት ወይም እየተበታተነ መጠፋፋት» ብቻ ነው።

ሰዎችን በርግጠኛነት ሊያሸንፍ የሚችለው ሀይል ፍቅር ነው። ለእኛም ችግር መፍትሄው ፍቅር ብቻ ነው። የጥበብ እውቀት (knowledge of wisdom) ያስፈልገናል። በጠብመንጃ የፖለቲካ ስልጣን መነጣጠቅና “በንጉስ ሀይለስላሴ መቃብር ላይ ኮ/ል መንግስቱ ሀይለማርያም” “በኮ/ል መንግስቱ ሀይለማያም መቃብር ላይ ጠሚ/ር መለስ ዜናዊ” “በ…መቃብር ላይ…” አንዱ በአንዱ መቃብር ላይ ቆሞ ስልጣን መጨበጥ መቆም አለበት። ለዚህም የአመለካከት ለውጥ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። ይህም ከእርስበርስ ጥላቻ ነጻ በመውጣት ይጀምራል። አመለካከትን መቃወም እንጂ ሰውን መጥላት መንፈሳዊም ሳይንሳዊም አሰራር አይደለም። አይጠቅምም። መጽሀፍ ቅዱስ የሚወድዱንን መልሰን መውደድ ፍቅር አይደለም ጠላቶቻችንን መውደድ እንጂ ይላል። መውደድ ቢያቅት ጠላት በአለመሆን በአለመግባባትም ቢሆን ተግባብቶ በጋራ መስራት ይቻላል።

ሰውን ጠላት ባለማድረግ ለማሸነፍ ሕንድን ወደ ነጻነት የመሩት ጋንዲና ጥቁር አሜሪካዊው ፓስተር ዶ/ ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጥሩ ሞዴልች ናቸው። ማህተማ ጋንዲ እንግሊዞች በሰጡዋቸው መጽሀፍ ቅዱስ «ጠላትህን እንደራስህ ውደድ» በሚለው መርህ ተመርተው ነው እንግሊዞችንም አለምንም ያሸነፉት። ዶ/ር

ማርቲን ሉተር ኪንግም ለጥቁር አሜሪካውያን ከባርነት ነጻ መውጣት የታገሉበት መንገድ ያለጠላትነት በፍቅር ጥበብ በሰላም መንገድ ብቻ ነው። እኛስ? 2ሺ አመት ሙሉ ክርስቲያን ነን እያልን እርስበርስ መፋለም የምናቆመው መቼ ነው? የምጽአት ቀን መጥቶ እስከሚገላግለን ድረስ ነውን?

ሁለት ክፉ ነገሮች ምዝበራና በእርስበርስ ጥላቻ አገር አጥፊዎች ናቸው። በነዚህ ሁለት ችግሮች የደነደነ ልብ ያላቸው ሰዎች ነጻ መውጣት አለባቸው። ጥላቻን ለማጥፋት፥ «ሀገር እንዳትወረር፥ ከውጭ ከመጣ ወራሪ ጋር ሲፋለሙ በጀግንነት ለወደቁት እንጂ፥ በእርስበርስ ጦርነት፥ ወንድም ወንድሙን በመግደሉ፥ በታሪክ መዘክር እንጂ ሀውልት ሊሰራና አንዱ ብሄር ሌላውን እንደ ጠላት እያየ ሊኖር አይገባም» ያሉት ሰው ማን እንደሆኑ ባላስታውስም፥ ፖሊሲ ሊሆን የሚገባ አባባል ነው። ይህንንም መፈተሽና ማስተካከል ግጭት እንዳይከሰት ለመከላከል ይረዳል። ከሀውልት ይልቅ ብሄራዊ እርቅ ነው የሰላም ቋሚ መሰርቱ። እንደዚሁም ዛሬ በትምህርት (merit) እና በጥረት ማደግ የቀረ ይመስላል። የሚዘርፍ ሁላ “Smart /ስማርት” እንጂ ሌባ አይባልም። በአቋራጭ ሚሊዬነር እየተሆነ ነው። «ከ7 ማስትሬት አንድ የሰበታ መሬት» የሚባልበት «ህጋዊነት»ን በጠ/ሚር ሰብሳቢነት በኢትዮጵያ ቲቪ አየን። የሀገር ሀብት ከድሀ ህዝብ ላይ እየመዘበሩ ከመኖር የሚበልጥ የሞራል ውድቀት የለም። የገቢ ልዩነት (Economic Inequality) በመንግስተ ሰማይና በሲኦል የመኖር ያህል ልዩነት እያመጣ በሀገሪቱ በግልጽ እየታየ ነው። ደላሎች ባለስልጣናትን ከላይ እስከታች በመዋቅር ይዘው “የጅምላና የችርቻሮ አከፋፋይ ኮርፖሬሽኖች” ሆነዋል። ሞራልና ስነምግባር ህዝባዊ እሴቶች እየወደቁ ሙስና ንቅዘት (Corruption) ከላይ እስከታች በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ሀገራዊ ባህል እየሆነ ነው።

በተቃራኒው የትውልድ ሞራል ለመገንባት የሚፍጨረጨሩ ጥቂት ወገኖችን መጥቀስ ይገባል። ለምሳሌ ያህል እንደነ ዶ/ር በላይ አበጋዝ (የህጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ሆስፒታል እያለቀሱ ገንዘብ በመለመን ያስገነቡ) ዲ/ን ዳንኤል ክብረት (የበጎ ሰው ሽልማት መስራች/ሰዎችን በመልካም ስራቸው እውቅና የሚሰጥ) ጎዳና የወደቁ ሰዎችን ሰብስቦ የሜቄዶኒያ አረጋውያን የመሰረተው ወጣት ቢኒያም፤ ወዘተ የመሳሰሉት ሰዎች በጎ ጅማሬዎች መተሳሰብና የልብ አንድነት የሚያመጣ ስለሆነ መደገፍ አለበት። ሌሎችንም ለበጎ ስራዎች እጃቸውን እንዲያበረቱ ማነሳሳት ያስፈልጋል። በሙዚቃ እንደነ ቴዲ አፍሮ (“አንድ ላይ ነን ስንል ተለያይተናል”) አብዱ ኪያርም ቢሆን (“እረ እኔስ ሀገሬ”) የመሳሰሉት ለሰላም ለፍቅርና ለአንድነት አቀንቃኞች ይብዙ። ጸሀፍትና ገጣምያን የቲያትርና የኪነጥበብ ሰዎች ለእውነት ለሰላም ለፍቅርና ለህዝቦች አንድነት ይጻፉ፤ የበጎ ሰዎች ስራ ትልቅ እሴት ነው፤ ከፍተኛ ውጤትም አለው። በእውቀቱ ስዩምም በ«ከአሜን ባሻገር» መጽሀፉ የሚያስተራርቅ ሆኗል። አስታራቂነቱ እየዋሸ ሳይሆን፥ ፖለቲካዊ ታሪካችንን እውነታን በማስረጃ በማቅረብ ነው።

የእምነት መሪዎች የት ናችሁ? ከንቅዘት ነጻ የሆነ መልካም ሰብዕና (Sound Mind) ያለውን ትውልድን ኮትኩቶ ማሳደግ፥ ከቤተሰብ ቀጥሎ የናንተ ሀላፊነት እንደሆነ ስለምን ትዘነጉታላችሁ? ከሀይማኖትፖለቲካ በመውጣት ለትውልድ የሚበጅ የሞራል እድገት መስራት የለባችሁምን? ህዝብን ለሰላምና ለፍቅር ማትጋት የለባችሁምን? ነው ወይስ ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ የሚሻልበት የመጨረሻው ዘመን ላይ ነን? “እኛን አላላውስ ያለን በአመለካከት ልዩነት አለመቻቻል (Differences by mutual concessions) ሲሆን፤ በጠላትነት የመጠላለፍ «ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ» (Zero-sum political game) ጨዋታ ከጥቅም ውጭ ሲያደርገን፤ ስለፍቅር ስለመቻቻል ስለምን አትሰብኩም? ጥላቻ ተጠይውን ብቻ ሳይሆን ጠይውንም የሚጎዳ የስሜት በሽታ ነው። ማንም በማንም ላይ ከፍቅር በስተቀር የጥላቻ እዳ ሳይኖርበት ተቻችሎ ተባብሮ ቢሰራ፥ ሁሉም በሰላም ያድራል” እያላችሁ ስለምን አታስተምሩም?

በመጨረሻም ወጎች፦ ከፖለቲካዊና ታሪካዊ ጽሁፎች በመለስ ያሉት የበእውቀቱ የወግ መጣጥፎች ፈገግ እያስደረጉ በሚያስደምሙ ግላዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትዝብቶች የተሞሉ በመሆናቸው አንባቢ ራሱን እንዲታዘብና እንዲፈትሽ የሚያደርጉ ናቸው። በዚህ ረገድ በእውቀቱ ስዩም ታዋቂና ተወዳጅ ከነበረው ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም ጋር የሚተካከል ይመስለኛል። እንዲያውም እንደቀልድ እያዋዛ ከሚጽፋቸው ምጸታዊ ኮርኳሪ መልእክቶች አንጻር ለየት ያለ ተሰጥኦ ያለው ነው። ለምሳሌ ያህል በፖለቲከኞቻችን ላይ ወዝ ያላቸው፤ ክብር ነክ ያልሆኑ ወጎች የሚቀልደው በእውቀቱ ስዩም ባንድ ወቅት ጠሚ/ር መለስ ዜናዊን በወግ ጨዋታ መካከል ለስልጣንም Expired Date ይኑረው ማለቱን አስታውሳለሁ። እንዲሁም ዛሬ ላይ «ፖለቲካዊ ሞት ሞተዋል» የሚባሉትና እርሳቸውም የገንዘቡን ምንጭ ሳይጠቅሱ፥ በትውልድ ቀዬአቸው በላሊበላ፥ ባለ5 ኮከብ አለም አቀፍ ቱሪስት ሆቴል ልሰራ ነው የሚሉን፥ የምርጫ-97 ባለረጅም ምላስ ጉምቱ ፖለቲከኛ ኣቶ ልደቱ አያሌውን በተመለከተችው የበእውቀቱ ወግ እንዲህ ትላለች።

“የምርጫ 97 ጦስ ልደቱ አያሌውን በሄደበት ያሳድደዋል። ባንድ ወቅት ልደቱ ከጓደኛው ጋር ምሳ በልቶ ጨርሶ ወደመቀመጫው ይመለሳል። በቦታው የነበረው አንድ ተራቢ ተመጋቢ ብድግ ይልና ወደ ልደቱና ጓደኛው ቀረብ ብሎ፥ «የእጅ መታጠቢያው በየት በኩል ነው?» ይላቸዋል። ልደቱ ተሽቀዳድሞ፥ «በዚህ በኩል» ብሎ በትህትና ይጠቁመዋል። ያን ጊዜ ተራቢው፥ «አንተን አላምንህም፥ እሱን ነው የጠየቅሁት» ብሎ መለሰ”

እግዜአብሄር ማስተዋልን ይስጠን!!

posted by tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s