አብዮታዊ ዲሞክረሲ… የማያቋርጥ ሰቆቃ እንቅስቃሴ – ታሪኩ አባዳማ

ቃላት ይናገራሉ ፣ ተፈጥሮን ይገልፃሉ ፣ የሀሳብን ጥልቀት እና የጉዞን አቅጣጫ ያመለክታሉ — አብዮታዊ ሆኖ ዲሞክረሲያዊ – ሁለት ሸጋ ቃላት ፣ ሁለት ተፃራሪ የፖለቲካ ንግድ ማራመጃ ማድመቂያ ቃላት። ሁለተኛውን ቢጥሉት ሌላው ቀዳሚውን ራቁት ያስቀራል – ስለዚህ አብዮት የሚለውን ቃል ዲሞክረሲ የሚሉት ካባ ያጠልቁለታል – ተኩላን የበግ ለምድ አልብሶ ከበግ መንጋ እንደ መቀላቀል…

አብዮት ሲሉ የነበረውን እንዳልነበር አድርጎ መቀየር ማለት ነው። የነበረው እንዳልነበር የሚሆነው ህብረተሰብ ነው ፣ አገር ነው ፣ ህዝብ ነው… አብዮት በተመሰቃቀለ እና ህገ ወጥ በሆነ እርምጃ ስልጣን መቆጣጠር ማለትም ነው። አብዮት ግርግር ነው ፣ ምስቅልቅል ነው። የታመቀ ብሶት ገንፍሎ ግድቡን በመጣስ በስልጣን ላይ ያለውን አፋኝ ስርአት ሲያጥለቀልቀው ፣ ሲውጠው ፣ ሲሽረው አብዮት ተካሄደ ይባላል። አብዮት እንደ እሳተ ገሞራ ነው…

የታመቀ እሳተ ገሞራ ይፈነዳል ፣ ያካባቢውን መልክአ ምድር ይቀይራል – ሜዳው ኮረብታ ይሆናል ፣ ጫካው በድንጋይ ቋጥኞች ይተካል ፣ ሸንተረር እና ገደል ይፈጠራል… እሳተ ገሞራ የሚፈነዳው አንዴ ነው ፣ እዚያው ከደገመም ጉልበቱ ሀይሉ እንደ መጀመሪያው አይሆንም – ተነፈስ ብሏላ። የታመቀው እቶን ተንፈስ ሲል እሳቱ ይጠፋል ፣ አፈሩ ይቀዘቅዛል – አዲስ የተከሰተው መልካ ምድር የተፈጥሮን ህግ ተከትሎ ኡደቱን ይቀጥላል… የእፅዋት አእዋፍ ዘር ይራባበታል – የሰው ዘር ይሰፍርበታል… ይረጋጋል።

እንደ እሳተ ገሞራው ሁሉ አብዮት የሚፈጥረው ምስቅልቅል ካንድ እርከን ላይ ሲደርስ መገታት አለበት። ህብረተሰቡ ሲመሰቃቀል መኖር ፈልጎ አብዮት አያቀጣጥልም – እርጋታ ይፈልጋል ፣ ህግ ይፈልጋል ፣ ስርአት ባለው እና በረጋ ግንኙነት ህይወቱን መቀጠል ይሻል። የወያኔን አብዮታዊ ዲሞክረሲ ሰነድ በጥሞና ከፈተሻችሁት ግን መሬት ላይ በህዝብ ላይ የሚፈፅመውን ያላቋረጠ ግፍ ስታጤኑ አብዮት ልጓም የሌለው የማይዳፈን የማያቋርጥ ምስቅልቅል መፍጠር ማለት ሆኗል።

ይህ እንዲሆን አስገዳጅ የሆነው ዋንኛው ሰበብ የወያኔ የራሱ ተፈጥሮ ነው። የዘረኝነት ተፈጥሮ ፣ ሌላውን አግልሎ በግል እና ጠባብ አመለካከት ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ብሎም በዚያ ጎዳና ገደብ የለሽ ዘረፋ እና ግድያ ማራመድ። ተፈጥሯቸውን ‘አብዮታዊ’ እናም ደግሞ ለምድ አጥልቀው ‘ዲሞክረሲ’ ብለውታል። ተፈጥሯቸው ዘረኛ ስለሆነ ዘረ ብዙ በሆነቸው አገር ውስጥ ተረጋግተው ስልጣናቸውን ማቆየት አይችሉም። ስለዚህ ሁሌም እንደባነኑ ፣ ሁሌም እንደደነበሩ ፣ ከራሳቸው ዘር በስተቀር ሁሉንም እንደጠረጠሩ ፣ እንደገነፈሉ ይኖራሉ። ተፈጥሯቸው ለተረጋጋ ህይወት ዋስትና አይሆንም – በመደናበር እና በማደናበር በሚያሰፍኑት ምስቅልቅል ውስጥ ዕድሜያቸውን ማራዘም ግባቸው ነው። ያንን ነው አብዮት የሚሉት…

ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ በፈጠሩት የማያቋርጥ የምስቅልቅል እንቅስቃሴ ውስጥ ገደብ የለሽ ሀብት ዘረፋ ያካሂዳሉ። ግርግር ከሌለ ፣ አብዮት ከሌለ ዘረፋ ማካሄድ አይቻልም… አገር ከረጋ ፣ ህግ የበላይ ይሁን ከተባለ ፣ ተጠያቂነት እና ግልፅነት ይረጋጋጥ ከተባለ ዘረፋ (ኪራይ ሰብሳቢነት ይሉታል) ይቆማል። ሰው በዘሩ ሳይሆን በብቃቱ እና ችሎታው ይመዘናል። ይህ መልካም የግርግር ዘመን ከሰከነ ያግበሰበሱት እና የሚያገበሰብሱት ሀብት ብቻ ሳይሆን ህልውናቸውም ፈተና ላይ ይወድቃል። አብዮት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ፣ የማያቋርጥ ግርግር ነው… እናም ያገሪቱን ጥሬ የተፈጥሮ ሀብት ላገኙት የባዕድ ቱጃር ይቸበችባሉ – ይጣደፋሉ ፣ ፋታ የላቸውም ሩጫው ከጊዜ ጋር ነው – እንቅስቃሴው ፈጣን ነው…

እስከ አሁን ድረስ ድሀው ህዘብ ላይ የሚዘንበውን የግፍ ውርጅብኝ ፣ ማፈናቀሉን ፣ ወህኒ ማጎሩን ፣ ቶርቸሩን ፣ አሸባሪ ብለው ያገቱትን ዜጋ ጥፍር እየነቀሉ ማሰቃየቱን… አረ ስንቱን… አስተውሉ… በማያቋርጠው አብዮታዊ እንቅስቃሴ የሚለበለው ዜጋ መድረሻ ጠፍቶት መፈጠሩን ከሚረግምበት ደረጃ ደርሷል። ወያኔዎቹ እያመሰቃቀሉ ፣ እያደናገሩ ፣ እያፈናቀሉ ፣ ወህኒ እያጎሩ ፣ እየገደሉ ካልሆነ አንድ ጀምበር ማደር አይቻላቸውም። ያንን የማያቋርጥ ምስቅልቅል ፣ ያንን የማያባራ ግርግር በዲሞክረሲ ለምድ ጀቡነውታል – መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ… አብዮታዊ ዲሞክረሲ ብለውታል። ‘አብዮት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው…’ የማያቋርጥ ምስቅልቅል

አብዮታዊ ዲሞክረሲ – ወያኔ ሁለቱንም ቃላት ይወዳቸዋል። እንቅስቃሴውን የሚመሩት ዘረኛ ነብሰ በላዎች የብሔረሰቦች ተቆርቋሪ እና ጠበቃ ያውም አብዮተኞች መሆናቸውን ይሰብካሉ። ለሚፈፅሙት ማናቸውም ወንጀል የሚጠየቁት በህግ ሳይሆን በአብዮታዊ ሂስ ብቻ ነው – አብዮተኞች ስለሆኑ ከህግ በላይ ናቸው። አብዮተኞች ስለሆኑ በፈለጉት ያገሪቱ ክልል ያሻቸውን ዜጋ ማሰር ፣ መግደል ፣ ንብረቱን መቀማት ፣ ከይዞታው ማባረር ማፈናቀል ይችላሉ… ጥፍሩን እየነቀሉ ያልፈፀመውን ሀጢያት ተናዘዝ ይላሉ… ብልቱን እየቀጠቀጡ ‘ዘር ማንዘርህን እናኮላሻለን’ ይላሉ… አረ ስንቱ።

ወቅቱ ስለ ዲሞክረሲ መኖር አለመኖር ሳይሆን ስለ አብዮቱ አለመቋረጥ ፣ ስለ ምስቅልቅሉ አለመገታት ነው። ባንድ ጀምበር ሰላሳ ሺህ ዜጎች ካንድ መንደር ሲፈናቀሉ አብዮቱ አለማቋረጡን ፣ ምስቅልቅሉ መቀጠሉን ፣ መንግስታዊ ህገ ወጥነት በህልውና መስፈኑን ያረጋግጣል —

እንግዲህ አብዮትን ከዲሞክረሲ ባህሪ ጋር አዳቅሎ ማራመድ የሚቻለው እንዴት ነው? ህግ የለም እንዳይባል የሆኑ ሸጋ አንቀፆች የታጨቁበት ሰነድ ያሳያሉ – ህጉን ግን የማያቋርጠው አብዮት እንደ አመቺነቱ ይተረጉመዋል ፣ ይሸረሽረዋል ፣ ይመደምደዋል። አብዮተኞቹ ሁልጊዜም ከዚያ ህግ በላይ ናቸው – ዜጎችም ከህግ ፊት እኩል በመሆን ሳይሆን በአብዮት ፊት ታማኝ በመሆን እና አለመሆን ፤ ለአብዮተኞቹ ቅን ታዛዥ እና ታማኝ ከመሆን አለመሆን አንፃር ይፈረጃሉ። ፀረ-አብዮታዊ ዲሞክረሲ የሆኑ ዜጎች አሸባሪ ተብለው በዚያ አብዮቱ በፃፈው ልዩ ህግ ለፍርድ ይቀርባሉ… ይጋዛሉ ፣ ወህኒ ይወረወራሉ – በአብዮታዊ ዲሞክረሲ ካራ ይቀላሉ…

 

ህግ አለ መስሏቸው ‘በህገ መንግስቱ እንደተፃፈው’ የሚሉ ቅን ዜጎች በዚያው ለምድ ባጠለቀው ህገ መንግስት ተፈርዶባቸው ወህኒ ይማቅቃሉ…

 

ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማምጣት አብዮት ማካሄድ አንድ ነገር ነው – አብዮት የአጭር ጊዜ

ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ከመሆን የሚያልፍ ነገር አይደለም። ዲሞክረሲ ደግሞ ዘላቂ የፖለቲካ ህይወት ነው። የህግ በላይነት ፣ የሰብአዊ መብቶች መረጋገጥ ፣ በነፃ የህዝብ ምርጫ ስልጣን ላይ መቀመጥ የመሳሰሉትን ያመለክታል። የዲሞክረሲ ባህል ግንባታ በአይምሮው የጎለመሰ ፣ በስነ ምግባር የተኮተኮተ ፣ አገሩን እና ህዝቡን የሚወድ እና የሚያከብር – በአስተዳደር ጥበብ ሁነኛ ተሞክሮ ያለው አስተዳደር ይጠይቃል። ከፍየል እረኝነት ወደ ህወሃትነት ብሎም ወደ መንግስት ስልጣን እና ሀላፊነት መሸጋገር

 

እርግጥ ነው ሌኒን ነበር ‘አብዮት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው…’ ያለው። መፈክሩን በተግባር የተረጎመው ደግሞ ሌላ ሳይሆን ስልጣኑን ከሌኒን የወረሰው ጆሴፍ ስታሊን ነበር። ስታሊን ስልጣን ላይ በቆየባቸው ሁለት አስርት ከግማሽ ዘመን በማያቋርጠው አብዮት ስም እየተገዘተ ያገሩን ህዝብ የደም እንባ አስለቅሶበታል – ተቀናቃኝ መስለው የታዩትን የራሱን የቦልሼቪክ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት ሳይቀር በመረሸን ፣ የደረጁ ገበሬዎችን አፈናቅሎ በቅጣት ወደ ማጎሪያ ሰፈሮች በማጋዝ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ አብዮት ‘የማያቋርጥ እንቅስቃሴ’ መሆኑን ሲያስመሰክር ቆይቷል። ይሁንና ስታሊን በአብዮት ስም የአገሩን ዳር ድንበር ለማንም አልሸጠም – ፓርቲው በዘር እና ጎጥ ላይ የተገነባ ባለመሆኑ አገራዊ ብሔራዊ ክብር እንዳይደፈር በጀግንነት ተዋድቋል። በዚህ ረገድ ከወያኔ ፍፁም የተለየ ያደርገዋል። ተፈጥሯቸው ለየቅል በመሆኑ በሁሉም ነገር አይመሳሰሉም።

 

ወያኔ ከስታሊን የወረሰው መንፈስ ‘አብዮት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ’ ፣ የማያቋርጥ ምስቅልቅል መሆኑን ብቻ ነው። ለወያኔ ህልውና የሚጠቅመውም ይህ ብቻ ነው። ይህን የሚጠራጠር ካለ ሀያ አምስት አመታት ወደ ሁዋላ ሄዶ እነ መለስ ዜናዊ ስለ ጆሴፍ ስታሊን አብዮታዊ ተግባራት ይሰብኩ የነበረውን ማንበብ ይችላል። አዎ ሀያ አምስት አመታት ሙሉ ሳያቋርጡ ድሀን ማስለቀስ የማያቋርጥ የአብዮተኞች እንቅስቃሴ ነው። ለነሱ ድሀውን በማያቋርጥ ግርግር ካላዋከቡት ለከት የለሽ የዘረፋ ጥማቸው አይረካም። ስለሆነም በህግ ዳኝነት ሳይሆን በግርግር ይመነጥሩታል ፣ በወከባ ያስለቅሱታል ፣ በጥይት እሩምታ ይረፈርፉታል – ያንንም አብዮት ነው ይሉታል… የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ፣ የማያቋርጥ እንባ ፣ የማያቋርጥ የጥይት እሩምታ… አዲስ አበባ ፣ ጋምቤላ ፣ ኦሮሚያ…

 

ወያኔ የዲሞክረሲ ለምድ የለበሰ ተኩላ መሆኑን አፍቃሪ የሆኑ ምዕራባውያን ጭምር የሚስቱት አይደለም። ተኩላው ለምድ የለበሰው እነሱን ለማደናገር መሆኑም ጠፍቷቸው አይመስለኝም። ከወቅቱ አለም አቀፍ ቀውስ አንፃር የምዕራባውያንን ብሔራዊ ጥቅም ለመጠበቅ ተኩላም ቢሆን ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ይታገሱታል… ተኩላው ቀን የጎደለበት ቀን ግን ተኩላውን አያድርገኝ… በመዝገብ ቤታቸው ያከማቹትን የሰብአዊ መብት ረገጣ ታሪክ ፣ የታዘቡትን ፣ የመከሩትን ሁሉ አደባባይ ያወጡታል… ስንት ጉድ እንሰማ ይሆን?

 

በቅርቡ ይፋ በሆነ ሰነድ የዞን 9 ጦማሪዎች ያጠናቀሩት የእስረኞች ሰቆቃ ጥናታዊ ሰነድ (ከዞን ዘጠኝ ወይንም ጎልጉል ድረ-ገፅ ላይ ታገኙታላችሁ) ከብዙ በጥቂቱ እንደሚያሳየው የወያኔ የማሰቃያ ተቋማት በየዕለቱ የሚፈፅሙት ግፍ ለጆሮ ይቀፋል። ከትግራይ መንደሮች ተመልምለው የመጡ ፍየል እረኞች መርማሪ ሆነው የነገሱበትን የማዕከላዊ እስር ቤት ምርመራ በጨረፍታ ያሳየናል።

 

ከትግራይ መንደሮች ተመልምለው በመርማሪነት የሰለጠኑት ሰቆቃ ፈፃሚዎች አንድን ዜጋ (በነሱ እምነት የአብዮታዊ ዲሞክረሲ ጠላት) አሰቃይቶ እንዴት ያልዋለበትን ፣ ያልፈፀመውን ሁሉ እንዲያምን ማድረግ መቻል እንዳለባቸው ያምናሉ። የመርማሪዎቹ አብዮታዊነት የሚለካው ወያኔ ጠላት ብሎ በፈረጀው ዜጋ ላይ በሚያወርዱት አበሳ ነው ፤ እርግጫው ፣ ጥፊው ፣ ስየሉ ፣ ጋጠ ወጥ ስድቡ… እዚህ ለመጥቀስ እጅግ አሳፋሪ የሆኑ ድርጊቶችን በእህቶቻችን እና ለጋ ወጣቶች ላይ የሚያደርሱት… አረ ስንቱ።

 

እንዳልኩት እነኝህ የማዕከላዊ መርማሪዎች ፣ የወህኒ ዘበኞች እና አዛዦቻቸው… ሁሉም አንዳችም የበቃ የትምህርት ብቃት ሳይኖራቸው ያው እንደ ሚኒስትሮቹ ፣ መምሪያ ሀላፊዎቹ ፣ ኮርፐሬሽን አስተዳዳሪዎቹ ሁሉ በድርጅታዊ ታማኝነት መለኪያ ብቻ የተቀጠሩ ወያኔዎች ናቸው። ህወሃት ለተዋጊነት ይመለምላቸው የነበሩ ፍየል እረኞች ዛሬ ለመርማሪነት ሰልጥነው ክቡር የሆነውን ሰብአዊ ፍጡር እንደ አውሬ ሲዘለዝሉት ማየት ያሳዝናል።

 

እነኝህ የወያኔ መርማሪዎች ‘በሰማዕታት መስዋዕትነት’ የተጎናፀፉትን ከፍየል እረኝነት ወደ መርማሪነት ያሸጋገራቸውን ስራቸውን ሊያጡና ወደ ፍየል እረኝነት ሊመለሱ የሚችሉት በሁለት ምክንያት ብቻ መሆኑን ያውቃሉ – አንድ ወያኔ ባስቀመጠው የጥራት ደረጃ ስራቸውን ማከናወን ካልቻሉ ፤ ማለትም ማናቸውንም አይነት የማሰቃያ ስልት ተጠቅመው እስረኛው ያልፈፀመውን ፣ ያልዋለበትን ሁሉ ማድረጉን አምኖ እንዲፈርም ማድረግ ካልቻሉ። የህወሃት መርማሪዎች ግምገማ አልፈው በመርማሪነት ስራ ለመቆየት ግፍ መፈፀም አለባቸው – የስራ ዋስትናቸው ሰቆቃ መፈፀም ብቻ ነው – ሌላ ዋስትና የላቸውም። አጋዚ የሚሾመው የሚሸለመው ለወያኔ ስልጣን ሲል ንፁሀን ዜጎችን በጭካኔ ለመግደል የማያመነታ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ብቻ እንደሆነ ሁሉ…

 

ሁለተኛው ስራቸውን የሚያሳጣ ሰበብ ወያኔ ከስልጣን ከተወገደ ብቻ ይሆናል። ይኼ ሁለተኛ ሰበብ የመርማሪነት ስራ ከማጣታቸውም በላይ ሌላ መዘዝ አለው ፣ ተጠያቂነት።

 

ከፍ ብዬ የጠቀስኩትን የዞን ዘጠኝ ጥናታዊ ሰነድ በቅጡ ካነበባችሁት የምትገነዘቡት ነገር አለ…. ባልተለመደ ሁኔታ አንድ እስረኛ ለምርመራ ሲጠራ አይኑ ይታሰራል። መርማሪዎቹ ሲደበድቡት ፣ ሲያዳፉት ፣ ቃሉን ሲቀበሉ ወይንም ሲያስፈርሙት ሁልጊዜም አይኑ ጥፍር ተደርጎ ታስሮ ነው። በዚህ ላይ መርመሪዎቹ ስማቸው እንዳይታወቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ ፤ ልክ አለቆቻቸው የታጋይ ስም እንዳላቸው ሁሉ የወያኔ መርማሪዎች የመርማሪ ስም ለራሳቸው ያወጣሉ። የትግል ስም የመርማሪ ስም… ይኼ ለምን ሆነ ብላችሁ እንደኔ ታሰላስሉ ይሆናል። መልሱ አጭር ነው – ይኸውም የወያኔ መርማሪዎች ለፈፀሙት ሰቆቃ ሁሉ አንድ ቀን ተጠያቂነት መኖሩ የማይቀር መሆኑን በደመ ነብስ ይገምታሉ።

 

አይን በማሰር እና ስማቸውን በመቀየር በነሱ ቤት የዛሬ ሰቆቃ ተቀባይ ነገ አንድ ቁጥር መስካሪ ሆኖ ዳኛ ፊት ሊመሰክርባቸው የሚችልበትን ዕድል ማጥበባቸው ነው። ስም በመደበቅ እና አይን አስሮ በመግረፍ ከህግ ፊት ማምለጥ ይቻል እንደሆነ ግን ወደ ፊት የምናየው ይሆናል።

 

እንቅስቃሴው የማያቋርጠው የወያኔ አብዮት አንቀላፍቶ አያውቅም – መንደሮቸን ያተራምሳል፣ ድሀ ዜጎችን ያፈናቅላል ፣ ቱጃሮችን ባንድ ጀምበር ይፈጥራል… ይተክላል (ቱጃሮቹን ታወቋቸዋላችሁ) ፣ ባንኮችን ያራቁታል ፣ መሬቶችን ይወራል ፣ የፀሀፊዎችን ብእር ብቻ ሳይሆን ጣት ይቆርጣል ፤ ደግሞ ህግ አለ ይላል ወዲህም አብዮት የማያቃርጥ እንቅስቃሴ ነው ይ። ዳኞችንም ይሾማል ፣ በአብዮታዊ ዲሞክረሲ አቅጣጫ ይበይናል። በህግ አምላክ ለማለት የከጀላቸውን ዳኞች በብቃት ማነስ ያባርራል ፣ ግፍ እና ሰቆቃ መፈፀም ያልቻሉ መርማሪዎችንም ያሰናብታል…

 

ሰቆቃ ፈፃሚ መርማሪዎች የሚታደጉበት ፣ ፍትህ አዛብተው የሚበይኑ ዳኞች ሸንጎውን የተቆጣጠሩበት ፣ በሙስና የተዘፈቁ ሹማምንት ትከሻ የደነደነበት ድህነትን ሳይሆን ድሆችን እየጠራረገ በመራመድ ላይ ነው… የወያኔ አብዮታዊ ዲሞክረሲ… የማያቋርጥ እንቅስቃሴ…

posted by tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s