ቤት አልባው ባለቤት

የአንድ መንግሥት አላፊነትና አስፈላጊነት የአገርን አንድነትና ነጻነት ከማስጠበቁ በተጨማሪ ጎሳና እምነት ሳይለይ ለሁሉም ዜጋ የቆመ ሆኖ በችግር አሮንቃ ውስጥ የሚማቅቀውን ሕዝብ ከችግሩ ማውጣት፣በበሽታ የሚሰቃየውን የሕክምና እርዳታ አግኝቶ እንዲድን ማድረግ፣ሥራ አጡን የሥራ መስክ ከፍቶ እንዲሰማራ ፣ያልተማረው የሚማርበትን ዕድል ማመቻቸት፣ሰላም የናፈቀውን በሰላም ከፈለገበት የአገሩ መሬት ላይ የመኖር መብቱን ማረጋገጥ፣መጠለያ ያጣውን እንዲኖረው መርዳት….ነው።

ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ሥልጣኑን ለብቻው ጨብጦ የተቀመጠው መንግሥት ነኝ ባይ ቡድን እነዚህን አላፊነቶች በሚገባ መወጣቱን በቅርበት ሲመረምሩት ግን የዚህ ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን።

1. የአገርን አንድነት የማስከበር አላፊነትን በሚመለከተው አገራችን ጎሳና ቋንቋን መሰረት ባደረገ ልዩነት የክልል አጥር አበጅቶ ሕዝብ እንዲራራቅ፣እንዲጋጭ ብሎም ተለያይቶ የመንደር መንግሥታት አቋቁሞ እርስ በርሱ የሚፋጅበት ሕገ መንግሥት ነድፎ የሚንሳቀስ በመሆኑ አንድነትን የሚያስከብር መንግሥት አይደለም።በእምነትም በኩል አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ተጠቂ አድርጎ በማቅረብ የሃይማኖት ግጭት እንዲያመረቅዝ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።

2. የአገርን ነጻነትና ልዑላዊነት በተመለከተ ዳር ድንበሯን እየቆረሰ ለባእዳን ማስረከቡ፣የውጭ ሃይሎች ባገሪቱ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ የሚፈልጉትን ለማድረግ የሚችሉበት ገደብ የለሽ ነጻነት በመስጠቱና በኤኮኖሚው መስክም ብሔራዊ ኤኮኖሚ እንዳያድግ ቀስፎ በመያዝ፣አገሪቱን ከፍላ ከማትወጣው የብድር እዳ ውስጥ መጨመሩና ከአገር ውስጥ ባለሃብት ይልቅ ትኩረትና እንከብካቤው ለውጭ የንግድ ተቋማት ሆኖ ሕዝቡን ለብዝበዛ ማጋለጡ የአገርን ነጻነት ትርጉመቢስ አድርጎታል።

3. በጤና መስክም ለስሙ ብዙ የሕክምና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ቢቋቋሙም ለመድሃኒትና ለሕክምና እርዳታ የሚጠየቀው ክፍያ ከአቅም በላይ በመሆኑ አብዛኛው ሕዝብ በቀላል በሽታ እየተጠቃ ይሞታል።አገሪቱ በብዙ ወጭ ያሰለጠነቻቸውም የሕክምና ባለሙያዎች የዘር ግንዳቸው እየታዬ ለእስራት ሲዳረጉ፣የቀሩት ደግሞ ለተሻለ ኑሮ በውጭ አገር ተሰደው መሥራትን መርጠዋል፤የቀሩትም በሽተኛውን አክሞ ድኖ ከማየት ይልቅ የሚያነጣጥሩት በበሽተኛው ጀርባ በሚሰበስቡት ገንዘብ ላይ ሆኗል።አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ እንደሚባለው በመንግሥት ስልጣን ላይ የተቀመጡት ዘራፊዎች የሚያንጸባርቁት እራስ ወዳድነት እንደ አርአያ ተደርጎ ተወስዷል። ተቋሙ የገንዘብ ማዕድን እንጂ የጤና አገልግሎት መሆኑ ተዘንግቷል።በሌላውም መስክ፣በእምነት ተቋማት ሳይቀር ይኸው ወረርሽኝ ተዛምቶ ሰብአዊ ምግባርን እየናደ ፍቅረ ነዋይ የበላይነቱን ይዟል።የስርዓት ብልሹነት ሕዝቡን ጭምር እየበከለ ነው።

4. በትምህርት በኩል ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ የዩኒቬርስቲ ድረስ ብዙ መቋቋማቸው ባይካድም፣ የትምህርቱ ጥራት ሲመረመርና ሲመዘን ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።በየተቋማቱ ውስጥ የመንግሥት ደጋፊዎችና አወዳሾች ካለችሎታቸው ተሰግስገው የስለላ ሥራ የሚሰሩበት መስክ ሆኗል። በችሎታቸው የሚሰጠውን የትምህርት ደረጃ በሚገባ የፈጸሙት ለመንግሥት ታማኝ አገልጋይ መሆናቸው ካልተረጋገጠ ወይም ከባለስልጣኖቹ ጋር ቅርበትና ዝምድና ከሌላቸው በተማሩት ሙያ ሥራ የማግኘቱ ዕድላቸው የመነመነ ነው።እህል ቀምሶ ለማደር ሲሉ በድንጋይ ፈለጣ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለዲግሪዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።አብዛኛው በየጎረቤት አገሩ ከመሰደድ ሌላ ምርጫ ባለመኖሩ በየአቅጣጫው ኬላ ሰብሮ በመውጣት ለተለያዩ አደጋዎች ተጋልጦ፣ ከሞት የተረፈው በደረሰበት አገር ለሌላ መከራ መጋለጡ የየእለቱ ትእይንት ሆኗል።በተለይ በሴት ወጣቶች ላይ በአገርም ውስጥ ሆነ ውጭ የሚደርሰው እንግልት መፈጠርን ያስጠላል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣኑን የሙጣኝ ብሎ በብቸኝነት የያዘው ቡድን ከላይ የተዘረዘሩትን አላፊነትና አደራዎች የተረጎመበት አሠራር ቢኖር ለራሱ ስርዓት ደጋፊና አገልጋይ ለሆነው የሕብረተሰብ ክፍል በሚጠቅም መልኩ እንጂ በኢትዮጵያዊነቱ የመብቱ ባለቤት ለሆነው ሁሉ አይደለም።በተለያዩት መስኮች ሁሉ ተጠቃሚው የስርዓቱ ደጋፊና አገልጋይ፣የመሪዎቹ የጎሳ አባል፣በጥቅምና በሙስና የተሳሰረው የአገር ውስጥ ባለሃብትና የውጭ አገር ኢንቬስተር የሆነው ብቻ ነው።

የዚህ ጽሁፍ እርእስ በሆነው የቦታና መኖሪያ ቤት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ብናተኩር ከአገር በቀል ዜጋ ቀርቶ ከውጭ አገር ወራሪ መንግሥት የማይጠበቅ ብዙ ድርጊቶችን እናያለን። በተለይም በአገሪቱ ዋና ከተማ በአዲስ አበባ ከላይ እስከታች ወሮበሎች በተጠቀጠቁበት አስተዳደር የሚፈጽመው እኩይ ተግባር ተዘርዝሮ አያልቅም።በከፍተኛ ደረጃ ቀውስ የሚታይበት አካባቢ በመኖሪያ ቤት ዙሪያ ነው።አንድ መንግሥት ቤት አልባ ለሆነው ዜጋ የተሻለ ቤት የማዘጋጀት አላፊነት ሲኖርበት የኢሕአዴግ አስተዳደር ግን ይብዛም ይነስም እንደአቅሙ ቤት ቀልሶ ይኖር የነበረውን ሕዝብ ሕገወጥ ሰፋሪና ለቦታሥ የማይስማማ በማለት ቤቱን አፍርሶ መሬቱን እየቀማ ለሚፈልገው በመሸጥ ብር ይሰበስብበታል። የእቅዱ ፈላስፋ ሟቹ ጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ሲሆን “አዲስ አበባ ደሃ ሕዝብ የሚኖርባት አትሆንም”የሚል መመሪያ መንደፉ የሚዘነጋ አይደለም ።ያንን መመሪያ ተከትሎ ተግባራዊ ለማድረግ ከሞት የተረፉት የወያኔ መራሹ መንግሥት ባለስልጣኖች “የመለስ እራእይ”በሚል መፈክር ማፈናቀሉን በሰፊው ቀጥለውበታል።

በስመ የከተማ ግንባታ ለዘመናት ተወልዶ የኖረውን ዜጋ ቤቱን አፍርሶ እንዲለቅ፣በተለያዩ ዘዴዎች ያስገድዱታል። ካለአቅሙ በቦታው ላይ ከአምስት ወይም ከአስር ፎቅ በላይ እንዲሰራ ካልቻለ ቦታውን አስረክቦ እንዲለቅ፣ቦታው ለሌላ ተቋም ስለሚፈለግ ካለምንም ምትክ እንዲያስረክብ በማስገደድ የአንገቱ ማስገቢያ የነበረውን ዜጋ ቤት አልባ የማድረጉ ስልት የተለመደ ሆኗል። ከአርባ ዓመት በፊት ከቀዳሚ ነዋሪው ተገዝቶ የተሠራ ቤት አሁን አካባቢው ትኩረት እየሳበ ሲመጣ፣የቤት ፈላጊው ቁጥር ሲጨምር በአንጻሩም ዋጋው ከፍ ሲል መንግሥት ካለፈቃድ የተሠራ “የጨረቃ ቤት” በሚል ፈሊጥ እየነጠቀ ለሚችል በውድ ዋጋ እየቸበቸበ ገንዘብ ይሰበስብበታል።ኗሪው ልግዛ ቢል በካሬሜትር የሚጠየቀው ዋጋ እንኳንስ በቀን አንድ ዶላር በአማካኝ የሚያገኝ ሕዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ ቀርቶ በባለጸጎቹም አገር የሚጠየቅ አይደለም።ከሁሉም የሚገርመው መንግሥት ነጥቆ በሚሸጠው ቦታ ላይ የነበረውን ቤት ለማፍረስ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ያሳለፈ የቦታና ቤት ባለቤት የማፍረሻ ወጭውን እንዲከፍል መገደዱ ነው።ያም ቢሆን ቀላል ገንዘብ አይደለም፣ከሰላሳ ሽህ ብር በላይ ነው።በበደል ላይ በደል እንዲሉ ይህ አይነቱ አሠራር በደርግ ዘመን ዘመድ ለተገደለበት የጥይት ዋጋ እንዲከፍል ከሚያስገድደው ግዳጅ የሚለይ አይደለም።

ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ከሌላ ክፍለሃገር የሚመጡት ባልኖሩበት ከተማ የቤት ቅድሚያ እየተሰጣቸው ባለቤቶች ሲሆኑ በከተማው ውስጥ ተወልዶ ያደገው፣ለዓመታት የኖረው የቤት ባለቤት ቤት አልባ ሆኗል።

ካርታ ያለው ሕጋዊ መሬት ከሆነ ደግሞ ቦታውን እራሱ ባለቤቱ እንዳይሸጥ የሚከለክል ሕግም ተደንግጓል።የነበረው ካርታ ጥቅም የለሽ ተደርጎ አዲስ ካርታ እንዲያወጣ ይገደዳል፣ለማውጣት ሲጠይቅ ደግሞ በቦታው ላይ መሠራት የሚገባውን ለመስራት ውልና ስምምነት እንዲፈርም ይጠየቃል ።ይኖርበት የነበረበትን ቤት አፍርሶ በተወሰነ አጭር ጊዜ ውስጥ መሠረት የመጣል ግዴታም ይጣልበታል።ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ ችሎ ከዘመድ አዝማዱ ተበዳድሮና ካርታውን ለባንክ አሲዞ ለመሥራት ሲነሳ በራሱ ቦታ ላይ ጊዜያዊ ጎጆ ቀልሶ ግንባታውን እንዳይከታተል መብቱን ይነፈጋል። እዚህ ግባ ለማይባል ቤት በወር ሊከፍል የማይችለውን ኪራይ እየከፈለ እንዲኖር ይገደዳል።ለዚያውም ቢሆን ኪራይ ቤት ለማግኘት ቀላል አይደለም።የትናንትናው ባለቤት የዛሬው ቤት አልባ ፣የመከራ ተሸካሚ ይሆናል።ለቀበሌ ቤት ኪራይ ወይም ኮንደሚኒየም ለሚባለው ውሽልሽል ቤት ቅድሚያ የሚሰጠው በስለላና በጸጥታ ሥራ ላይ ለተሰማሩት ከየቦታው ተውጣጥተው ለመጡት የስርዓቱ አገልጋዮች ነው። በዚህ አይነት ዓይን ያወጣ የግፍ ሰንሰለት ውስጥ የተተበተበው ንጹህ ዜጋ የሚጠብቀው የመጨረሻው እጣፈንታ ቤት አልባ ሆኖ ንብረቱን ተቀምቶ በራሱ አገር መሬት ላይ ስደተኛ ሆኖ መኖር ነው።

በጣም የሚገርመው ደግሞ በስርዓቱ ተማምነውና ተዝናንተው ቤት የሠሩትም ቢሆኑ ከዚህ ደባ አላመለጡም።በተለይም በውጭ አገር የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ከቤት ግንባታ ድርጅቶች ጋር ተዋውለው የገዙት ቤት በጥያቄ ውስጥ ገብቷል።ቦታው በሙስና የተገኘ ነው በማለት ክስ የቀረበባቸው የቤት ግንባታ ድርጅቶች ቁጥር ከቀን ወደቀን እየጨመረ መጥቷል።በውጭ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ለገዥው ቡድን የማይመቹና ያላጎበደዱ ከሆኑ በዚህ ውንጀላ ስር መድቦ ንብረታቸውን እንዲያጡ ማድረግ መንግሥት የቀየሰው ሌላው የበቀል እርምጃ ነው።በተጨማሪም በልዩ ልዩ ዘርፎች ውስጥ ድርሻ እየገዙ ትርፍ እናገኛለን ብለው ይጠብቁ የነበሩት (share holders) ከአምስት ዓመት በላይ ገንዘባቸው በዋለበት መስክ የተገኘውን ትርፍ መካፈል ሲገባቸው የመደቡትን ገንዘብ ብቻ እንዲያገኙ ደንብ ወጥቷል።በመጨረሻ ያገኙት ትርፍ ቢኖር ላም አለኝ በሰማይ እንደሚሉት ሆኗል።ታዲያ ለነዚህ አይነቶቹ ቀደም ሲል የዚህን መንግሥት እኩይ ተግባር እንዲያውቁት የተደረገውን ምክር በመዘንጋትና ከመጤፍ ባለመቁጠር ለደረሰባቸው ጉዳት “ወትሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” ከሚለው ምክራዊ ስንኝ የተሻለ መጽናኛ መልእክት መስጠት አይቻልም።ለወደፊቱም በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ላይ ተማምኖ ገንዘቡን ለተለያዩ ተግባሮች አውላለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ ከዚህ ተመክሮ ሊማር ይገባዋል።አገራችን ዘረኞች፣ ሌቦችና ዘራፊዎች የሚቆጣጠሯት መሆኑን ሊያውቁት ይገባል።

ይኸው ጉደኛ መንግሥት ተብዬው ይሉኝታ ቢሱ የዘራፊዎች ቡድን እራሱ አገሪቱን ለከተታት የገንዘብ እጥረት ሕዝቡን ተጠያቂ ማድረጉ ነው። በልማት ተብየው ለፈፋ ያልተጠቀመው፣ኑሮው ከእጅ ወደአፍ የሆነው ሕዝብ ከሚያገኘው ገቢና ደመወዝ እንዲከፍል የሚያስገድድ በየትም አገር ያልታዬና ያልተሰማ ሕግ ሰሞኑን ማውጣቱ ሌላው አስገራሚ ታሪክ ነው።ድሎቱንና ደስታውን ለብቻው፣ መከራውንና ዕዳውን የሕዝብ ማድረግ የለመደው መንግሥት ይህን ትእዛዝ በውድ ሳይሆን በግድ ለማስፈጸም ዝቶ ተነስቷል።ቀደም ሲልም በይበልጥ አገልግሎቱና ጥቅሙ ለባእዳን በሚሆነው የአባይ ግድብ ግንባታ ስም እስከአሁንም ድረስ አስጨንቆ መበዝበዙ ሳያንስ ይህን መጨመሩ የፈለኩትን ባደርግ የሚያቆመኝ የለም ከሚል ትእቢትና እብሪት የመነጨ ነው። ይህ አምባገነን የጎሳ ስብስብ ቡድን በሕዝቡ ላይ የሚፈጽመውን በደልና ግፍ ሁሉንም በዚህ ገጽ ለመተንተን አይቻልም።ከበደልና ከግፉ ለመላቀቅና ለመውጣት ግን የሚቻልበትን መንገድ መጠቆም ይቻላል፤ ያም ተባብሮ መታገልና ወያኔ መራሹን ኢሕአዴግ ማሶገድ ብቻ ነው። በየቦታው የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ትግል ማጎልበት ለዚያ ግብ ያበቃል።

የሕዝብ እምቢተኝነት እያደገ ሲመጣ ከወታደራዊ የጥቃት ዘመቻ ጎን ለጎን ሕዝባዊ ትጥቁን ለማስፈታት ሌላ አሻጥር በመቀመር ላይ ይገኛል። “የአገራችን ሰላም እንዳይናጋ፣የተጀመረው ልማት እንዳይደናቀፍ” የሚል ተደጋጋሚ መንግሥታዊ ጥሪ መሰል ውትወታ የሚያደርጉ ለሥርዓቱ ታማኝና አገልጋይ የሆኑት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የተካፈሉበት ጉባኤ ሰሞኑን አካሂዷል።እነዚህ በጉባኤው የተካፈሉት የሃይማኖት አባቶች በራሳቸው ውስጥ የተነሳውን አለመግባባት ለማሶገድ እንኳን ብቃት የሌላቸው ናቸው።ሕዝብ እየተራበ፣እየተሰደደ፣እየታሰረ፣እየተገደለ ሰላምና ልማት አለ ብለው አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ ካድሬዎች ናቸው።በእነሱ ጥቅምና ፍርሃት በከለለው የህሊና መነጽር መንግሥት የሚፈጽማቸው ወንጀሎች የእድገትና የሰላም ምልክቶች ናቸው። ወንጀለኛውን መንግሥት ሕጋዊና ትክክለኛ ፣ለመብቱ የቆመውንና የሚታገለውን ሕዝብ ሕገወጥና ወንጀለኛ አድርገው ፈርጀውታል። ያደረጉትን ስብሰባ በነጻነትና ካለማንም ተጽእኖ እንዳካሄዱ ሲገልጹ ነጻነት የሚለውን ቃል የተረዱት አይመስልም።የሕዝቡን ነጻነት መነፈግ መኖሩን አምነው አይቀበሉም።ዝርዝሩን ከዚህ በታች ባለው ቃለመጠይቅ ማዳመጥ ይቻላል።

http፡//amharic.voanews.com/a/3658534.html ምናልባት ይህ ሊንክ አልከፈት ቢል እሁድ በ01-15-2017 ከምሽቱ በሦስት ሰዓት ላይ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ክፍለ ጊዜ የተላለፈውን ስርጭት ቢከታተሉ ሙሉ ዝርዝሩን ሊያገኙ ይችላሉ

በሚመጣው አጭር ቀናት ውስጥ ደግሞ ይህንኑ መሳይ ስብሰባ በመዳፉ ስር የወደቁትን፣ሕገመንግሥቱን ተቀብለው በስመ ተቃዋሚ ድርጎ እየተሰጣቸው የሚያደናግሩ፣ የረባ ሥራ ሳይሰሩ መሪዎቻቸውን ሳይቀር ለእስራትና ለሞት ሰለባ የዳረጉትን የፖለቲካ ድርጅቶች ሰብስቦ ለማነጋገር ዕቅድ አውጥቷል። በወያኔ አዳራሽ ውስጥ ሊካሄድ የታሰበው ይህ ጉባኤ ለእውነተኛ ለውጥ መንደርደሪያ ሳይሆን እንደ ሃይማኖት ተቋማቱ የመንግሥትን እኩይ ተግባራት የሚያወድስ ውሳኔ ለማሳለፍ የተዘጋጀ መሆኑ አይካድም።ለእውነተኛ ሕብረብሔር የፖለቲካ ድርጅቶች በር የከፈተና የሚሳተፉበት እንዳልሆነ ገና ከጥንስሱ ተረጋግጧል።ቁጥራቸው ከሃያ በላይ የሚገመቱት እነዚህ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶች እውነት ለሕዝቡና ለአገሪቱ የቆሙ ከሆነ ምንም እንኳን ድፍረት አላቸው ተብሎ ባይጠበቅም ጉባኤውን ከመሳተፋቸው በፊት የሚከተሉትን መንግሥት እንዲያሟላ እንደ ቅድሚያ ሁኔታ ቢያስቀምጡ ለራሳቸው ክብር ና ከበደሉት ሕዝብ ጋር ለመታረቅ ይጠቅማቸዋል።

1.የጊዜያዊው አስቸኳይ አዋጅ እንዲነሳ፣በየከተማው ቋንቋ የማይናገሩና ከሕዝቡ ጋር የማይግባቡ የታጠቁ ወታደሮች በሕዝቡ ስነልቦና ላይ ጭንቅና ሽብር ስላሳደሩበት ወደመጡበት ቦታ በአስቸኳይ እንዲመለሱ፣
2.የታሰሩት የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱ፣

3.የዲሞክራሲ መብቶች፣በተለይም የነጻ ሚዲያና የጋዜጠኞች መብት እንዲከበር
4.በሕዝባዊው ተቃውሞና እንቅስቃሴ ላይ የሚደረገው ወታደራዊ ዘመቻ እንዲቆም፣ሕዝብ ላቀረበው ጥያቄ ተገቢ መልስ እንዲሰጥ
5. በከተማዎች የሚደረገው የቦታ ነጠቃና ማፈናቀል በአስቸኳይ አንዲቆም፣
6.በውጭ አገር የሚገኙት የተቀዋሚ ድርጅቶች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ አገር ውስጥ ገብተው በነጻ የሚንቀሳቀሱበት መብት እንዲረጋገጥ
ይህን ሳያስከብሩ ለድርድር መቅረብ ማለት ያለው መንግስት በያዘው አጥፊ ጎዳና እንዲቀጥል ማበረታታትና አጋር መሆን ነው።
የአገር ወዳዶች አንድነት ትግል ያሸንፋል!
አገሬ አዲስ

 posted by tigi flate
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s