የ‹ፍቱን›ንን ጎጆ በህወሓት ‹መድፎች›! – ጋዜጠኛ ፍቃዱ በርታ

ኢህአዴግ  የግል ሚድያውን በመዝጋት እና ስጋት ላይ ጥለውት  የነበሩትን አንድነት ፓርቲን  በማፍረስ(መኢአድን  በማሽመድመድ) የ2007ቱን ምርጫ ማጅራቱን ብሎ ሊደፋው እንደሚችል እርግጠኛ ነበር፡፡ይህን አቅዱን ለማሳካት በተለይ የግል ሚዲያውን የመዝጋት ዘመቻውን የጀመረው ገና ‹ምርጫው› ከመድረሱ አመት ከመንፈቅ ቀደም ብሎ በቁጥጥሩ ስር ባሉት በኢቲቪ፣በሬዲዮ ፋና፣በአዲስ ዘመን እና በብሮድካስት ባለስልጣን አማካኝነት  ነበር፡፡

 

 

ህወሓት በሰላሙ ጊዜ የዘወትር ስራቸውን የሚከውኑ ፤በችግር ጊዜ በ‹ጠላቶቹ› ላይ እንዲዘምቱ፤ መልምሎና አሰልጥኖ  ያስቀመጣቸው -ከተሜው በተለምዶ ‹‹የህወሓት መድፎች›› የሚላቸው፡ ሬዲዮ ፋና፣ኢቲቪ፣ምርጫ ቦርድ፣ ብሮድካስት ባለሥልጣን፣ገቢዎችና ጉምሩክ ወዘተ የተሰኙት አጠቂ  ምድብተኞች አሉት፡፡ከላይ እንደተገለጠው የዚህ  ሰራዊት ግዳጅ እንደ ተጠባባቂ ጦር በሰላሙ ጊዜ አምራች  ህወሓት  ምጥ ውስጥ ሲገባ  ደግሞ እየተወነጨፉ  ‹ ጠላቶቹን›  ልክ ማስገባት ነው፡፡ ለህወሓት ‹ጠላት› የመተንፈሻ አካሉ ስለሆነ ‹የጠላት› ትንሽ የለውም ፡፡ ታንክና መድፍ አሰልፎም የሚዋጋው  ኃይልም ይሁን፣  ነውሩን የሚጋልጥበት ጋዜጠኛ ፣ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ  ሰላማዊ  ታጋይም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲ  በህወሓት ዘንድ ለውጡ እምብዛም ነው፡፡  ስጋት ውስጥ እስከ ጣሉት ድረስ መድፎቹን  አሰልፎ ‹‹ውረድ እንውረድ›› ማለት የሚኩራራበት ተግባሩ ነው፡፡

የግሉ  ፕሬስ  (ፋክት፤አዲስ ጉዳይ፣ሎሚ፣ ጃኖ ፣ ዕንቁ እና አፍሮ ታይምስ)  ጋዜጠኞች ላይ ህወሓት የወሰደው ኃላ ቀር  እርምጃ  ተሳታፊ የነበሩት ደህንነት፣ገቢዎችና ጉምሩክ፣ የብሮድካስት ባለሥልጣን፣ ሬዲዮ ፋና ኢቲቪ እንዲሁም ፍትህ ሚኒስቴር ነበሩ፡፡በጋዜጠኞቹ  ላይ በተካሄደባቸው  ያልተቋረጠ ክትትል ፣የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ  እና  በከፈተው ‹‹አመጽ የማነሳሳት›› ክስ ምክንያት ለህይወትና ደህንነታቸውን ዋስትና አሳጥቶ አገር  አልባ ሲያደርጋቸው ፤ ለወሬ ነጋሪት የተረፈው ፍቱን መጽሔት ሆነ፡፡

መጽሔታችን በንዴት በደፈረሱት  የህወሓት ዓይኖች  መታየት የጀመረው ስያሜውን ከላይፍ ወደ ፍቱን ቀይሮ ህትመት በጀመረ በጥቂት ወራት ልዩነት ነበር፡፡ በተለይም  ስድስቱ የህትመት ውጤቶች ከስራ ውጪ ሆነው  ፍቱን አንባቢ እጅ  የሚገባ  ብቸኛ  ሚዲያ መሆን  ሲጀምር    የሁሉም ቡጢ  የሚያርፍብን  የቦክስ መለማመጃ  ከረጢት መሆን  ግዴታችን  ሆነ፡፡ በተለይ ነጭ ለባሾች ቢሮአችን አካባቢ  ማዘውተር  የየዕለት ስራቸው ሆነ፡‹‹ ድጋፍ የሚያደርግላችሁ የውጪ  ኃይል  እንዳለ እናውቃለን፣ በሰላም አገር ማንም ባልታሰረበት  ፍቱን የሚባል መጽሔት እያሳተማችሁ የምታሰራጩት ህዝቡን ለአመጽ ለማነሳሳት እንደሆነ ደርሰንበታል ፤ ይህን አመጽ ቀስቃሽ መጽሔታችሁን የማትዘጉ ከሆነ በሽብር ክስ ቃሊት እንደምትከርሙ አትጠራጠሩ፤›› የሚሉ  ዛቻና  ማስጠንቀቂያች መዘውተር ጀመሩ፡፡

ህወሓት ወደ ፍቱን ጎጆ የተኮሰው  ተከታዩ መድፍ  የብሮድካስት ባለሥልጣን ነበር፡፡  በግዳጁ  መሰረት ባለስልጣኑ ‹‹አፍራሽ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ የግል ህትመቶችን  ልከስ ነው›› በሚል ማደናገሪያ ፤ በመጽሔታችን ላይ ብቻ ያነጣጠረውን  ክሱን አጠናቅሮ መጨረሱን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት  ቀርቦ አረጋገጠ፡፡http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=15222፤ ብሮድካስት ለፓርላማው ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት የግል ህትመቶችን-‹‹ገንቢ ፣ አፍራሽና  ገንቢም አፍራሽም  ያልሆኑ ዘገባዎቸን የሚያሰራጩ ›› በማለት በሶስት ምድብ ከፍያቸዋለሁ ያለ ሲሆን – ‹‹አፍራሽ  ዘገባ ያሰራጫል ›› ተብሎ የተወነጀለው ፍቱን መጽሔት እንደነበር ከታማኝ ምንጮች ለማረጋገዘጥ ችለናል፡፡

 በወቅቱ በገበያ ላይ የነበሩት የግል የህትመት ውጤቶች፡ ሪፖርተር፣ አዲስ አድማስ፣ሰንደቅ፣ ፎርቹን ፣ ካፒታል  እና ፍቱን  መሆናቸው ለሚያውቅ ማንኛውም ሰው  በብሮድካስት አማካኝነት ‹‹አፍራሽ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ የግል ህትመቶች ልከስ ነው›› በሚል ሽፋን  ለፓርለማ የቀረበው  ሪፖርት ቀጥታ ያነጣጠረው ፍቱን መጽሔት ላይ እንደነበር በቀላሉ መረዳት አይከብደውም፡፡

ወደ ፍቱን ጎጆ የተተኮሰው ሌላኛው መድፍ አገር ውስጥ ገቢ ነበር፡፡ በደህንነትቶች  የታጀቡት የሀገር ውስጥ ገቢ ሰዎች በድንገት ቢሮአችንን ወረው  ያገኙትን  መጽሔቶች እና ሌሎች ዶክሜንቶችን  በመውሰድ፤አጋጣሚ ሆኖ የድርጅቱ  የሂሳብ መዝገብ ሰነድ ለድጋሚ ኦዲት  ኦዲተሮች ወስደውት ስለነበር  ቢሮ ውስጥ ሊያገኙት ስላልቻሉ ከ5 ቀናት ውስጥ አጠናቀን እንደምናስረክባቸው ተስማምተን ቢሮውን ቀውልን ሔዱ፡፡

 የሂሳብ መዝገብ ሰነዱ  ድጋሚ ኦዲት ከተደረገ  በኋላ በተባልነው ቀን መገናኛ ከሚገኘው  ዋናው መስሪያ ቤታቸው ወስደን አስረከብን፡፡የሂሳብ መዝገብ ፋይላችን ሳሪስ ከሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ወደ መገናኛ ሲዘዋወር  በአምስት አመት  ጊዜ ውስጥ  የመጀመሪያ  ቢሆንም በአጋጣሚ ግን  አይደለም፡፡ ወደ መገናኛ የሚወሰዱ አብዛኞቹ ሰነዶች  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህወሓት የቅጣት ሰለባ እንዲሆኑ የሚፈረድባቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡በክፉ ዓይን ታይቶ እዚያ  ቤት የሚገባ  የድርጅት የሂሳብ ሰነድ እንኳን በሰው በመላዕክታትም ቢሰሩ የጅብ ራት ከመሆን  አይድኑም፡፡

‹‹ሕገ ወጡ›› ደረሰኝ!

የድርጅታችንን የሂሳብ ሰነድ ካስረከብንናቸው በኋላ ‹‹ማመሳከር እንፈልጋለን ›› የሚሉንን ሰነድ ለሁለተኛ ጊዜ  ወስደን አስረክበናቸዋል፤የከሳምንት  በኋላ ሌላ ማመሳከር እንፈለጋለን ያሉንን ደረሰኝ እንድናቀብላቸው በስልክ ነግረውን  ቢሮአቸው ስደርስ  የተቀበለኝ አቶ ቴዎድሮስ አብቹ የሚባል ‹‹የኢንስፔክሽንና ኦዲት ቡድን አስተባባሪ ››ነው፡፡

‹‹ ሕገ ወጥ ደረሰኝ ተጠቅማችኋል!›› አለኝ፣ገና ከመቀመጤ ፤

‹‹ ስለየትኛው  ህገ -ወጥ ደረሰኝ ነው የምታወራው? ›› ብስጭትና ግራ መጋባት ውስጥ ሆኜ ጠየቅኩት፤

ታትመው  ለረጅም ጊዜ  ጥቅም ላይ ያልዋሉ 2 ጥራዝ ደረሰኞችን  እያሰየኝ፤ ‹‹ስለእነዚህ ነው የማወራው፤››

‹‹ይሄ እኮ ከ 5  ዓመት በፊት  በ2002 ዓ.ም፣መገልገል የነበረብን በእናንተ እውቅና የሚታተም ደረሰኝ እንደነበር ሳታሳውቁን በፊት ስንጠቀምበት የነበረ ነጭ ደረሰኝ ነው፡፡ያም የሆነው  የእናንተ ቸልተኛነት ምክንያት ተፈጠረ ስለመሆኑ ሁለታችንም መግባባት ላይ ደርሰን  ቅጣት ከነወለዱ ከፍለን ያበቃ ጉዳይ ነበር እኮ ፡፡ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሰነድ በ2002ዓ/ም የሂሳብ መዝገብ ውስጥ ተያይዟል እኮ፤ አላየኸውም እንዴ? ››፤

‹‹ባየውም  ለውጥ አያመጣም !››

‹‹ይኸውልህ አቶ ቴዎድሮስ ፤  የዛሬ አምስት ዓመት በ2002 PLC ተደርገን  ለምዝገባ ወደ መስሪያ ቤታችሁ ስንመጣ  ምን አይነት ደረሰኝ መጠቀም እንደነበረብ የ10 ደቂቃ ጊዜ ወስዳችሁ ሳትነግሩን ነበር የሸኛችሁን ፡፡ እኛ ደግሞ እንደ እናንተ ቸልተኞች መሆን ስላልፈለግን እናንተ ጋ ከመመዝገባችን በፊት እናደርግ እንደነበረው  ነጭ የሽያጭ  ደረሰኝ  አሳትመን መጠቀም ጀመርን፡፡ በመጨረሻም  18 ደረሰኞችን ከተጠቀምን በኋላ በ2003 ዓ/ም  አመታዊ ግብር ለመክፈል መስሪያ ቤታቹሁ ስንሄድ፤ ሽያጭ ያካሄድነው turnover tax(tot) ሳንጠቀም በመሆኑ በዚያው መሰረት ሂሳቡን  አስተካክለን  እንድንመለስ ተነገረን፡፡ እንደተባልነው የሽያጭ ሂሳቡን ከ2% ቲኦቲ ጋር  አስተካክለን አስረከብን፤የሂሳብ ሰራተኞቻቹም  ለ18 ወራት  ያካሄድነው  18 የሽያጭ  ደረሰኝ  ሂሳብ የኮምፕዩተር ሲስተም ውስጥ ሊያሰገቡ የሚችሉት  ከቅጣትና ወለድ ጋር ስለሆነ  ያንን ክፍያ መፈጸም እንዳለብን ነገሩን፤  እናንተ ለፈጠራቹሁት ችግር  እኛን መቅጣት ተገቢ ስላልሆ  መክፈል እንደማይገባን ለማስረዳት ሞከርን፡፡ ሰራተኞቹም  የምንጠቀምበትን  ደረሰኝ የማሳወቅ  ሓላፊነት የመስሪያ ቤቱ ስለነበር ቅሬታችን ተገቢ መሆኑን አምነው ነገር ግን የኮምፕዩተር ሲስተሙ ያለፉትን ወራት የሽያጭ ሂሳብ ሲያስገቡ ያለ ወለድና ቅጣት ስለማይቀበል የተባለውን ቅጣትና ወለድ ከመክፈል ውጭ አማራጭ እንደሌለን ነገሩን፡፡ እኛም የተጣለብን ቅጣት ከፍለን ከእዳ  ነጻ መሆናችን የሚያረጋግጥ ክሊራንስ  ወስደን  እስከ ዛሬ በሰላም ስንሰራ ነበር ፤›› በማለት ለማስረዳት ሞከሩ፡፡

‹‹ቢሆንም ለውጥ የለውም፤››

‹‹ ምን ማለት ነው ለውጥ የለውም ማለት? በ2002  ዓ/ም  የእናንተ ቸልተኛነት ውጤት መሆኑን ያመናችሁትን ጉዳይ ፤ ዛሬ  በድንገት   ከ5 ዓመት በ ኋላ እንዴት የእኛ ጥፋት ሊሆን  ቻለ?››

‹‹ ስለዚያ የማውቀው ጉዳይ የለም፤››

‹‹አቶ ቴዎድሮስ የሂሳብ ባለሙያም አይደለህ? ፍላጎትህ እውነቱን ለማወቅ  ቢሆን መዝገቡን በማየት ብቻ ትደርስበት አልነበር!››

ሰዉዬው  የጠራኝ  ግራ የተጋባበት ጉዳይ ኖሮት አልበረም፤ የጠራኝ መጽሔታችን የመስዋዕት በግ መሆንዋን ሊያረዳኝ ነው፡፡ የሚሞግተኝ  እውነታው ጠፍቶት ሳይሆን በመጽሔቱ ላይ ያገኘውን የሽፍትነት ድል ሊያረጋግጥልኝ ነው፤  ለነገሩ ስንት ጉድ በሚሰራበት አገር ይህ ሰው ለምን ብሎ  ለዕሊናው ይቆማል?፤

‹‹ አቶ ቴዎድሮስ መጽሔታችንን  ለመዝጋት የማትፈጽሙት ነገር እንደሌለ ይገባኛል፤ ነገር ግን ይህን ተልካሻ ምክንያት ትጠቀማላችሁ ብለን ግን  አልጠበቅንም፤››

‹‹እኛ  የተለየ ፍላጎት ኖሮን ሳይሆን ወንጀል ስለተሰራ ነው››

‹‹እሺ አለቃህን ማነጋገር እፈልጋለሁ?››

‹‹ስራውን እንድጨርስ የተመደብኩት እኔ ስለሆንኩ  የምታነጋግረው አለቃ የለኝም፤ ለማንኛወም ሁኔታው ተደውሎ ይነገርሃል፤››

በቀጣዩቹ ቀን በአንዱ፤ አንዱ የስራ ባልደረባዬ፡ ‹‹ፍቃዱ ደህንነቶች ሰፈር  ደረስ መጥተው ‹ከእንግዲህ እዚያ መጽሔት ላይ ብትሰራ  አጎቶችህ መስዋዕት ሆነው ያስኙትን ስርዓት  እንደከዳህ ነው የምንቆጥረው › ብለውኛል፤ ከዛሬ  በኋላ ስራው  ቢቀርብኝ  ምን ይመስልሃል? ››

በዚያው ሰሞን፤ እየጠራ ያለውን ስልኬን አንስቼ ‹አቤት› አልኩ፤ ከማተሚያ ቤት ነበር የተደወለልኝ፡ ‹‹ ፍቃዱ ከዚህ ሕትመት በኋላ መጽሔታችሁን ላለማተም ወስነናል፤ መቼም ጉዳዩን እንደምትረዳን ተስፋ እናደርጋለን ››፤

የህወሓት በደህንነቱ አማካኝነት  ከአገር የማልወጣ ከሆነ በጸረ ሽብር ህግ  ልከሰሰ ዝግጅት መጠናቀቁን  ካረዳኝ  ሳምንት ሆኖታል፡፡ሌላኛው  መድፈኛ በ‹‹ሕገወጥ ደረሰኝ መገልገል ›› ሊከሰኝና መጽሔታችንንም ሊዘጋ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አርድቶኛል፡፡የህወሓትን ‹‹መድፎች ›› በባዶ እጅ እየተጋፈጥኩ እንዳለሁ ተሰማኝ፡፡በገዛ አገሬ በሆነ ወራሪ ኃይል እንደተከበብኩ ተሰምቶኝ የተስፋ መቁረጥ ጽልመት ውስጥ ሰጠምኩ፡፡

የቅምጦቹ፡ ብሮ ወሸባዬ›!

በሳምንቱ ፤ለህወሐት የደረጃ ቅምጥነት ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ሬዲዮ ፋና እና ኢቲቪ መጽሔቱን እና እኔን ግዳይ ጥለው ‹ብሮ ወሸባዬ› ጭፈራ ላይ  ነበሩ፡፡ፋና ምሽቱን ጨምሮ  ቀኑን ሙሉ ፡‹‹ ሁለት ተመሳሳይ ደረሰኞችን በማሳተም ያልተገባ ጥቅም ሲሰበስብ በመገኘቱ ነው እገዳ የተጣለበት››፤በማለት አትቶ፡ ያለሁበትን‹‹ በመጠቆም ህዝብ ትብብር እንዲያደርግ›› ጥሪ  አስላለፈ፡፡ ኢቲቪ በበኩሉ የምፈለገው ‹‹ በሕገ -ወጥ ደረሰኝ እንጂ በፖለቲካ ጉዳይ›› እንዳልሆ ምስሌን አስደግፎ የድል ዜና› ሰራ፡፡ ከአገር እንድወጣ የሰጠኝን የአንድ ሳምንት ጊዜ ተግባራዊ  ካለማድረጌ ጋር ተያይዞ  ጉዳዩን  በመጽሔታችን ላይ ለህዝብ ይፋ እንዳላደርግ ስጋት የገባው ህወሓት፤በቅምጦቹ አማካኝነት፡ ‹‹መጽሄቱም ቢሆን በድብቅ እንዲታተም ቢመጣ እንኳን የህትመት ተቋማት ይህን ተረድተው ከማተም እንዲታቀቡ››አዋጅ በማስነገሩ፤ ጣጣውን የፈራው ማተሚያ ቤት ለደህንነቶች  በማሳወቅ ፣ለአንባቢ ሊሰራጭ የነበረ  ወደ 50 ሺህ ብር ወጪ የተደረገበት መጽሔት በማገት ለአንባብያን ዓይኖች እንዳይበቃ ማድረግ ችኋል፡፡

ብእር ብቻ የጨበጥን አስር  የማንሞላ የፍቱን ጋዜጠኞች፡ የህወሓትን አምስት ኋላቀር (አንዳንዶቹም ዘረኛ) ‹መድፎች› ተቋቁመናል፡፡ አለቆቻችን ለነበሩት አንባብያንና የኢትዮጵያ ህዝብ ቃል የገባነውን በታማኝነት የማገልገል ግዴታችንን ጠብቀናል፡፡ በማባበያም ፣ በማማለያም ሳንደለል የህዝቡ ታማኝ አገልጋይ ሆነን ከህሊና ወቀሳ የጸዳ ስራ ሰርተን በማቆማችን፤ ዛሬን ቀና ብለን እንድንሔድ ምክንያት ሆኖናል፡፡

posted tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s