የጎቤ መሰዋትና እንድምታው (ዝርዝር ሪፖርታዥ) – መስቀሉ አየለ

የወልቃይት ማንነት ጥያቄ መነሳትን ተከትሎ የዚህ ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴዎችን እና ኮ/ል ደመቀ ዘውዴን በጎንደር ለማፈን የተደረገውን ዘመቻ ተከትሎ በጎንደርና ጎጃም መጠነ ሰፊ የሆነ የህዝብ ተቋውሞ በስርአቱ መነሳቱ ይታወሳል። በርካታ ህዝብ ስርአቱን ለመፋለም ወደ ጫካ እንደገባም ይታወቃል። ወደ ጫካ ከገቡት ሰዎች መኋል አቶ ጎቤ መልኬ አንዱ ሲሆኑ በኋላም ከፋኝ ለኢትዮጵያ አንድነት ንቅናቄ የሚል ሸማቂ ሃይል አስከ ሟቋቋም ደርሰዋል። ባለፉት ወራቶች ይህ ሸማቂ ሃይል በተለያዩ ቦታዎች እራሱን የማደራጀትና ስርአቱ ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ ነበር። በዚህ ሂደትም ጎቤ በተደጋጋሚ ምህረት እንዲገባ አማላጅ ቢላክበትም አሻፈረኝ ብሏል። ከጎቤ ጋር አብረው ጫካ የወጡት የተወሰኑ ሰዎች ምህረት የገቡ ሲሆን ጎቤ በአቋሙ በመጽናት የስርአቱን ጎቤን በምህረት የማስገባትን ተስፋ ሙሉ በሙሉ አምክኖታል። ከዚህ በኋላ ነው ጎቤን የማሳፈን ወይም የማስወገድ እርምጃዎችን ለመፈጸም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በሃገር ውስጥ ደህንነት ዋና መምሪያ ስር በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ የሚመራው የጸረ ሽብር መምሪያ ሃላፊነቱን የተረከበው። ከዚህ ውጪ አደገኛ ናቸው ተብለው የተፈረጁ 4 ሰዎች ላይም እርምጃ እንዲወሰድ ተወስኖ ወደ ተግባር ተገብቷል። ከነዚህ ውስጥ አበራ ጎባው ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን የተቀሩት ሶስቱ ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ የተደረጉ ሙከራዎች ሊከሽፉ ችለዋል። በተለይ በአቶ አረጋ ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም እስካሁን ሊሳካ አልቻለም። በአሁኑ ሰአት አቶ አረጋ ቁጥር አንድ የወያኔ ታርጌት ነው።

 

ጎቤን የማስወገድ ኦፕሬሽንን እንዲመራ የተመደበው ልኡል ታፈረ የተባለ ብዙ ሰዎችን በመግደልና በማስገደል የሚታወቅ ታዋቂ የወያኔ ደህንነት ነው። ይህ ሰው በዋናነት በሰሜን ጎንደር ከሱዳን እና ኤርትራ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ስራዎችን የሚፈጽም ሲሆን የግንቦት 7 ዋና ጻሃፊ የነበሩትና አሁን በወያኔ እጅ ላይ የወደቁትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በኤርትራ ውስጥ ሰርጎ ገብ በማሰማራት የግድያ እርምጃ ለመውሰድ የተደረገውን ኦፕሬሽን በበላይነት ከመሩት ውስጥ አንዱ ነው።
ጎቤ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ማድረግ መጀመሩ አብረውት ጫካ ከወጡትና ተመልሰው በምህረት ከገቡ ሰዎች በተገኘ መረጃ ሊረጋገጥ ተችሏል። ይህም የደህንነቱ መስሪያ ቤት ጎቤን ከግንቦት 7 ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት እንዲቋረጥ ለማድረግና በአካባቢው በግንቦት 7 ከተደራጁ ሃይሎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለማበላሸት የሚረዳውን ስራ መስራት እንዲችል አድርጎታል። ከግንቦት 7 ጋር መስራት የለብንም፤ ግንቦት 7 የአማራ ጠላት ነው፤ ስለዚህ አራሳችንን ችለን ብቻችንን ነው መንቀሳቀስ ያለብን የሚል ሃሳቦችን የሚያቀነቅኑ ለወያኔ የሚሰሩ ሰዎችን በማሰማራት ይህ ሃሳብ ገዢ ሆኖ እንዲወጣ የሚያደርግ ስራዎች ሲሰሩ ነበር። የዚህ ስራ ዋና ግቡ በአካባቢው የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ለማስቻል ነው። ይህ ስራ የሚፈለገውን ያህል አጥጋቢ ውጤት ባያመጣም በተወሰነ ደረጃ የተሳካ ነበር። ከዚህ ውጪ በጎቤ ዙሪያ በዋናነት ሶስት አይነት ቡድኖች ነበሩ:: አንደኛው የተነሳንለት አላማ የወልቃይት ማንነት ጉዳይ ስለሆነ ከዚህ ጉዳይ ውጪ ሌሎች ነገሮችን ማንሳት የለብንም የሚል ነው። ሌላኛው ቡድን ለአማራው ብቻ ነው መታገል ያለብን የሚል ሲሆን ሶስተኛው ቡድን የአማራው ችግር የሚፈታው በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ውስጥ ተኩኖ ነው እንጂ ለብቻው አማራ የሚል ይዘን መሄድ የለበትም የሚል ነው። የደህንነቱ መስሪያ ቤት የመጀመሪያው ቡድን ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ በተለያየ መንገድ ቢጥርም ሊሳካለት አልቻለም። የሁለተኛው ቡድን ሃሳብ የሚደግፉ በርካታ የደህንነት ሰዎች የአማራ ቤሄርተኝነት አቀንቃኝ ሆነው ተሰማርተዋል። ይሄ ማለት የሶስተኛውን ቡድን የሚደግፉ መስለው የተሰማሩ የወያኔ ሰላዮች የሉም ማለት አይደለም። ባጠቃላይ ሶስቱ ቡድኖች ከባህር ማዶ ወይም ዲያስፖራ ሆነው የየራሳቸው ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሃገር ውስጥ ካሉ አካላቶች ጋር በማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው። በዚህ ሂደት ላይ በውስጣቸው የተሰገሰጉ ለወያኔ የሚሰሩ ሰላዮች እንዳሉ ሁሉ በሚያምኑበት ሃሳብ ለመታገል የሚንቀሳቀሱ ንጹህ ሰዎችም አሉበት።

 

የጎቤን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ መረጃዎችን ከሃገር ውስጥና ከባህር ማዶ የሚያስተላልፉ ሰላዮችን በመመልመልና በማሰማራት ስለ ጎቤ በቂ መረጃዎች እንዲገኙ ተደርገዋል። በተለይ በሃገር ውስጥ ያሉት እራሳቸውን የአማራ ብሄርተኛ አቀንቃኝና ወያኔን ለመጣል የሚደረግ ትግል ዋና ተሳታፊ መስለው በመቅረብ ውጭ ሃገር ካሉ ትግሉን የሚደግፉ ሰዎች ጋር የቀረበ ግንኙነት በመፍጠር የሃገር ውስጡን እንቅስቃሴ ወያኔ በቅርበት እንዲከታተለው ማድረግ ተችሏል። በሌላ በኩል በውጪ የሚኖሩ; በዋናነት መሰረታቸውን በሲያትል ባደረጉና ለወያኔ የሚሰሩ ሰዎች አራሳቸውን የትግሉ ደጋፊ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ የሚያገኙትን መረጃ ለወያኔ የሚያስተላልፉ አሉ። በዚህ አኳሃን ወያኔ መረጃዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝ ሆኗል።
ሌላው የወያኔ መረጃ መሰብሰቢያ መንገድ ከሆኑት አንዱ በፌስቡክ የሚወጡ መረጃዎችን በመሰብሰብ እያጣራ ጥቅም ላይ ማዋሉ ነው። በአማራና ኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቋውሞ ተከትሎ በፌስቡክ ላይ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሰፊው የሚዘገብ ስለሆነ በቀላሉ መረጃዎችን ማግኘት የሚቻልበት እድል ተፈጥሯል። ወያኔም በፌስቡክ ላይ የሚወጡ መረጃዎችን የሚሰበስቡ ሰዎችን አሰማርቶ እያንዳንዱን መረጃዎች እየሰበሰበ ለሚፈልገው ጉዳይ እየተጠቀመበት ይገኛል። ባብዛኛው ፌስቡክ ላይ መረጃ የሚያወጡ ሰዎች እንድን ክስተት ከመዘገባቸው ውጪ ለወያኔ የሚጠቅም መረጃ እያስተላለፉ እንደሆነ አያውቁም። ምን አይነት መረጃ መቼና እንዴት እንደሚዘገብ ብዙ ሰው ስለማያውቅ ብዙ ጊዜ ለወያኔ የሚጠቅም መረጃዎች ሲወጡ ይታያሉ። በሃገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያወጡ ሰዎች በደህንነቱ አይን ውስጥ እየገቡ የተያዙ ብዙ ሰዎች አሉ። በሌላ በኩል የወያኔ ደህንነቶች ሆነ ብለው የማሳሳቻ መረጃዎችን የሚያወጡ አሉ። በዚህም ብዙ ሰዎችን ያጠምዱበታል። ባጠቃላይ ከጎቤ ጋር የተያያዙ መረጃዎች ልቅ በሆነ መንገድ በፌስቡክ ላይ ሲወጡ ማየት የተለመደ ነው።

 

ስለጎቤ በተለያየ መንገድ መረጃዎች የሚሰበሰቡ ቢሆኑም መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ እርምጃዎችን ለመውሰድ ድህንነቱ ብዙ ጊዜ ውስዶ ሲያስብበት ነበረ። በተለያየ ጊዜ በጎቤ አቅራቢያ የወያኔ ሰላይን ለመትከል የተሞከረው ሙከራ ከሽፏል። ከዚህ በፊት የጎቤ የሩቅ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ተገኝቶ ከጎቤ ጋር በሚንቀሳቀስ ቡድን ውስጥ ሰርጎ ማስገባት ቢቻልም ሰውየው ስልክ ሳወራ ጠርጥረውኛ በማለት እነ ጎቤን ሸሽቶ ወደ ድህንነቱ መስሪያ ቤት ሊመለስ ችሏል። ሰውዬው የተሰጠውን ግዳጅ ባይፈጽምም ስለ ጎቤ እንቅስቃሴ የሚገልጽ ተጨባጭ መረጃዎችን ማቀበሉ ግን አሌ የሚባል አይደለም።

 

ከጎቤ ጋር ከሚንቀሳቀሱ ውስጥ የእህቱ ልጅ አንዱ ነው። ጎቤም በጣም ያምነዋል። ጎቤ አይኑን በተደጋጋሚ ስለሚያመው መድሃኒት ከሳንጃ የሚያመጣለትም የእህቱ ልጅ ነው። የወያኔ ደህንነት ይህን መረጃ ካገኘ በኋላ ሳንጃ ላይ ከሳንጃ አስተዳዳሪ ጋር በመሆን የጎቤ እህት ልጅ መድሃኒት ለመግዛት ሲመጣ በማግኘት ለወያኔ ደህንነት እንዲሰራ ይገለብጡትና ሚሽን ሰጥተው ይልኩታል። ሚሽኑም አጎቱን የመግደልና በምትኩ ሶስት ሚሊዮን ብር፣ ቤትና መሬት እንደሚሰጠው ቃል ይገባለታል። እሱም ተስማምቶ ይሄዳል። ከዚህ ሁኔታ በኋላ በየጊዜው ስልክ እየደወለ ስለ ጎቤ መረጃዎችን ያስተላልፋል። እሱም የተሰጠውን ሚሽን ለመፈጸም ሁኔታዎች እስኪመቻቹለት ይጠብቃል።በወቅቱ እንደ ማናቸውም ሌሎች ምድቦች ጎቤም ከአራት አርበኞች ጋር በመሆን ለተለዬ ተልእኮ በተሰማራበት ገዥ ቦታ ላይ ነው የነበረው። በዚህም ቀን ጎቤ አይኑን አሞት ተኝቶ የነበረ ሲሆን ይኽ ሰው ከጎቤ ጋር የነበሩ ሶስት ታጋዮችን ውሃ እንዲቀዱ ይልካቸዋል። ውሃ የሚቀዱበትን ቦታ ስልክ ደውሎ ለሚያገኘው ደህንነት እንዲታፈኑ መልዕክት ማስተላለፉን ተከትሎ ሶስቱ ታጋዮች በመከላከያ ቁጥጥር ስር ይወድቋሉ። ይህን ያረጋገጠው የጎቤ እህት ልጅ ጎቤን በተኛበት ገድሎት ሊሄድ ችሏል። የእህቱ ልጅም ከደህንነቶች ጋር በተቀጣጠረበት ቦታ በመገኘት ልጁን ወደ ባህርዳር ሊወስዱት ችለዋል። ከዚህ ሁነት በኋላም ደህንነቶቹ ለጎቤ ቤተሰቦች ስልክ በመደወል የጎቤን እሬሳ እንዲወስዱ ተደርጓል።

 

ወያኔ ለምን ጎቤ ላይ እርምጃ መውሰድ አስፈለገው

ጎቤ በአካባቢው ተጽኖ መፍጠር የሚችል ሰው ነው። የሚደረገውን ትግል ለማኮላሸት እንደ ጎቤ ያለን የትግሉ የሞራል አባት የሆነን ሰው ማስወገድ ለወያኔ ምርጫ የሚቀርብለት ጉዳይ አይደለም። ወያኔ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ የተከበሩ ሰዎችን ፈልጎ ማጥቃቱ የተፈጥሮው ባህሪው ነው። ጎቤ ያለውን ሁሉ ነገር ትቶ ዱር ቤቴ በማለት ለሃገሩ ሲዋደቅ የነበረ ታጋይ ነው። የወያኔ እንዱ ስትራቴጂ አውራውን ምታው የሚል ነው። ጎቤ የትግሉ አውራ ከሆኑት ሰዎች እንዱ ነው። በመሆኑም በወያኔ የኢላማ መነጸር ውስጥ ከገቡ ሰዎች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ይገኝበት ነበር።

 

የጎቤ መሰዋት ያለው እንድምታ

ጎቤ ታጋይ ነው። ታጋይ ይሰዋል። ነጻነት በነጻ የሚገኝ አይደለምና። ታጋዩ የሚሞትለት አላማ የሱን ፈለግ ተከትለው በሚሄዱ ተከታዮቹ ከግብ ይደርሳል። በትግል ሂወት በከፍታና ዝቅታ ውስጥ ማለፍ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው። የጎቤ መሰዋት ትግሉን በቁርጠኝነት ለማስኬድ የበለጠ ሃይል ይሆናል። ትስስሩ በደም የታነጸ ይሆኗልና። የጎቤን ፈለግ የሚከተሉ ብዙ ጎቤዎች ይመጣሉ። ለነሱም የጽናት መሰረት ይሆናቸዋል። በሌላ በኩል ጎቤ በትግል አጋሩ በተለይ በራሱ የቅርብ ዘመድ ጥቃት ሰለባ መሆኑ ቀጣይ በሚኖረው የትግል ሂደት ላይ በታጋዮች መካከል የመተማመን ትስስሮችን የማላላት አቅም ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ በመውሰድ የትግሉን መሰረት በደንዳና መሰረት ላይ መጣል ያስፈልጋል።

posted tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s