ንገሩን፣ “መርዶም ይናፈቃል”! (ኃይለማርያም ለገሰ)

ኃይለማርያም ለገሰ ‘ደስታ ድልነሳሁ ታሪኩ` ትባላለች።  የመልክ ቀለሟ  ቀይ፣ ቁመትዋ/መጠኗ መካከለኛና በአዛዉንትነት የዕድሜ ክልል የምትገኝ፥  መሆኗ ይነገራል። የአለባበስ መሰረቷ ባህላዊ፣ አብዛኛውን ጊዜ ከዳርና ዳሩ በአረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ቀለማት የተቀመቀመ ቀሚስና ነጠላ ትለብስ እንደነበረ ታዉቋል። በሕዝብ በዓል ቀናት ጸጉሯን አጎፍራ ወይም ሹርባ ተሰርታ፣ ከአቡጀዴ ወይም ካኪ የተስፋ ተነፋነፍ ሱሪ ታጥቃና በላዩ ላይ የአበሻ ቀሚስዋን በመቀነት ሽብ አድርጋ፣ ጃኖ ኩታ ከትከሻዋ ላይ ጣል  የማድረግ ልምድና ባህል ነበራት። ከሁሉም በላይ ደግሞ፥ በሰዉነትዋ ላይ በተለይም ከፊት አገጯ ላይ የተነቀሰችዉ የመስቀል ምስል፣ በአንገትዋም ላይ `ሞዓ አንበሳ ዝዕምነገደ ይሁዳ“` የሚለዉ ንቃሳት  የዉበት ሳይሆን፣ የክብር መለያ ምልክቷ መሆኑም ይታወቃል። በቅርብ የሚያዉቋት፣ዘመድ ወዳጅ አፍቃሪ፣ ለጠላት የማትንበረከክ ኮስታራ ጀግና እያሉ ያሞግሷታል። ደስታ በሐዘንና ፍስሃ፣በሰላምና ጦርነት፣በአሸናፊነትና ተሸናፊነት የታጀበ አስደማሚ የሕይወት ታሪክ አላት። ገና በወጣትነቷ፥ በ1888 የአድዋ ጦርነት ሲታወጅ፣ የክተት ጥሪዉን ተቀብላ ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር አብራ ዘምታለች።ከሸዋ እምብርት እስከ አድዋ ድረስ ሲቻል በጋማ ከብት፣ ሳይቻል በእግር እየኳተነች ረጅሙንና አድካሚዉን ጉዞ  ከዳኘዉ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ፥ በአጠቃላይም ከኢትዮጵያ ገበሬ ሰራዊት ጋር ዘምታ፥ ሞትና ሽረቱን፣ ረሃብ ጥማቱን፣ ዉርጭና ነዲዱን እኩል ተካፍላለች። አጤ ምኒልክና የጦር አዛዦቻቸዉ የኢጣሊያን ወራሪ ጦር የሚመክቱበትን ዘዴ ሲመካከሩ፣ስልትና ስትራቴጂ ሲነድፉ በዚያዉ በቦታው ነበረች። ጀግናዉ የኢትዮያ ሰራዊት  ደረቱን ለጦር፣ እግሩን ለጠጠር፣ ግንባሩን ለአረር እየሰጠ፣ በፉከራና በሽለላ ከጠላት መሃል ገብቶ እያተራመስ የጠላትን አንገት በሰይፍ እየቀላ  ሲጥልና ሲወድቅ በመሃል ገብታ በለዉ እያለች አበረታታለች። የወደቀዉን በማንሳት፣ የተጠማዉን በማስጎንጨት፣ የተራበዉን በማጉረስ፣ የቆሰለዉን በማከም ግዴታዋን የተወጣች ጀግና ዘማች ነበረች ይላል ገድለ ታሪኳ። የጠላት ድል መሆን የምስራቹ ሲበሰር፣ የጥይት እሩምታ ሲተኮስ፣ ጀግኖች የጦር ሚዳ ዉሏቸውን  በሚኒልክ ፊት ሲያወኩ፣ ሲፎክሩና ሲሸልሉ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአድዋ ተራሮች ላይ ከፍ ብሎ ሲዉለበለብ፥ በቀይ ፊትዋ ላይ የደስታ ዕንባ አፍሳለች። የሶልዳቶና አስካሪ/ባንዳ/ ምርኮኛ እጁን ወደ ላይ ሰቅሎ፣ አንገቱን አቀርቅሮ በፍርሃት እየራደ ከኢትዮጵያ ጦር ማዘዣ ጣቢያ ሲገባ በዓይኗ በብረቱ እየተመለከተች፣ እንኳን ኢትዮጵያዊ ሆንኩ እያለች ልቧ በኩራት ተሞልቶ በደስታ ፈንድቃለች።   ደስታ ድልነሳሁ!!! ከድል በኋላም የኢትዮጵያ ሰራዊት ዳኘዉ ምኒልክንና እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያን ከዘማቹ ታቦት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከፊትና ከኋላ አጅቦ፣ ፉከራና ቀረርቶ እያሰማ ወደ አዲስ አበባ የመልስ ጉዞ ሲያደርግ፣ እሷም ሰራዊቱን  እያስጨፈረችና  የደከመዉን እያበረታታች አብራ ተመልሳለች። የድል ብስራቱ ተነግሮ የአዲስ አበባ ሕዝብ በራስ ዳርጌ ሳህለስላሴ አስተባባሪነት  በነቂስ ወጥቶ መለከት እየተነፋ፣ ነጋሪት እየጎሰመ፣ በሆታና በልልታ ጃንሜዳ/ጃንሆይ ሜዳ/ ተሰልፎ  ለድል አድራጊዉ ንጉስ ነገስት የጀግና አቀባበል ሲያድርግ፣ የተለያዩ አድባራት ካህናት በልብሰ ተክህኖ“ተሰብሆ ለእግዚአብሔር“ እያሉ፣ በከበሮና በጽናጽል እየወረቡና እያሸበሸቡ ምስጋና ሲያቀርቡ፣ ደስታ በደስታ እየፈካች የድል አቀባበሉን ከሕዝብ ጋር አክብራለች።  አጼ ምኒልክ ዙፋናቸው ላይ ተቀምጠዉ አገር እርጋ ሲታወጅ፣ ለሰራዊታቸዉ ልዩ ልዩ የዘማችነት ማዕረግ፣ ኒሻንና ሽልማት ሲስጡ በአካባቢዉ የነበረች ብቻ ሳይሆን ከከፍተኛ ኒሻን ተሽላሚዎች መካከልም አንዷ ነበረች። ከዚያም ለጀግና የሚገባዉ ክብር ሳይነፈጋት፣ በክፉም በደጉም ከምኒልክ ቤተ መንግስት ሳትለይና  ከሕዝብ ህሊና ሳተጠፋ ለአርባ ዓመታት በሰላምና በደስታ ኖራለች። ዘማች ደስታ ድልነሳሁ ታሪኩ!!! በአድዋ ሽንፈት ቂም የቋጠረችዉ ኢጣልያ ለአርባ ዓመታት ጦሯን ስታደራጅ ኖራ በ1928 ዓ ም በኢትዮጵያ ላይ ፋሺስታዊ ወረራ ስትፈጽም፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በደምና በአጥንቱ የጠበቀዉን ነጻነት ለማስከበር እንደ ወትሮው ሁሉ ዲሞትፈርና ዉጅግራዉን፥ ጦርና ጋሻዉን ታጥቆ ዘመተ። ሆኖም ግን ሰራዊቱ ጠላትን  በሙሉ ወኔና ጀግንነት  ቢጋፈጥም ድል ሳይገኝ ቀረ። ባህላዊና ኋላቀር የጦር መሳሪያ ታጥቆ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር፥ በጣም ዘመናዊ  የጦር መሳሪያ ታጥቆ የነበረውን የፋሺስት ጦር ሊቋቋመዉ የሚችል አልሆነም። ከሰማይ የእሳት አሎሎና የመርዝ ዝናም እየዘነበበት፣ ከመሬት  የእሳት አረርና የብረት ዘንግ አየተወረወረበት ጡረታ በወጣ መሳሪያ ተዋግቶ ማሽነፍ በታምር የሚቻል አልበረም። ስለሆነም  የማይጨው ጦርነት አሸናፊነት በአገር ፍቅር ወኔ ሳይሆን በቴክኖሎጂ የበላይነት ተደመደመ። ማይጨው ዳግማዊ አድዋ ሳይሆን ቀረ። ስለሆንም የማይጨዉ ሽንፈት ተከትሎ ንጉስ ነገስቱ ለቀድሞዉ የዓለም መንግስታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አቤቱታ ለማቅረብ ከሀገር ሲስደዱ ደስታም አብራ እንድትሰደድ ተደረገ። ምንም እንኳ የደስታ ፍላጎት በአርበኝነት አገር ቤት መቆየት የነበረ ቢሆንም፣ በአድዋ ያደረገችዉ ተጋድሎ ታሪክ በጠላት ዘንድ በደንብ ስለሚታወቅ፣ በአጋጣሚ በጠላት እጅ ብትወድቅ  ሊከተል የሚችለዉን ታሪካዊ  ዉርደት በማጤን፥ በፓለቲካ ዉሳኔ ከንጉሱ ጋር አብራ ወደ ስደት ዓለም ሄደች። በባህርና  በየብስ ተጉዛ አውሮፓ መሬት ገብታ፣ `ባዝ` ተብላ ከምትጠራው የእንግሊዝ ከተማ ከንጉሱና ቤተሰባቸዉ ጋር፣ ከስደተኛዉ መድሃኒዓለም ሳትለይ፥ ለአምስት ዓመት ያህል በስደት አሳለፈች። በ1932 ዓ ም ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት  ሲቀሰቀስና ኢጣሊያ ከጀርመን ጎን ቆማ በእንግሊዝና በተባባሪዎቿ ላይ ጦርነት ስታዉጅ፥ የኢትዮጵያና የደስታ ሕይወት ሌላ መንገድ ያዘ። ከአምስት ዓመታት በፊት በሸር ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያን ለፋሺስት ኢጣሊያ በገጸ-በረከትነት አሳልፎ ሰጥቶ የነበረዉ የእንግሊዝ መንግስት የኢትዮጵያን አርበኞችና የቀዳማዊ ሃይለስላሴን የትግል አጋርነት ሰለጠየቀና ንጉሰ-ነገስቱም ሲጠብቁት የነበረዉ አጋጣሚ በመፈጠሩ ጥያቄዉን በደስታ ተቀብለዉ ትግሉን ለማደራጀትና ለመምራት ጎረቤት ወደ ሆነችዉ ሱዳን ሲሄዱ፥ ደስታም አብራ ተጉዛ የአርበኝነት ትግሉን ተቀላቀለች። ከንጉሰ-ነገሰና ሳተለይ ከስድስት ወራት ለበለጠ ጊዜ በሱዳን በረሃ ከቆየች በኋላ፥ በጥር ወር 1933 ንጉሰ ነገስቱ  ከእንግሊዛዊዉ የጦር አማካሪያቸዉ ከሻለቃ (ጄኔራል) ዊንጌት ጋር ሆነዉ `ጌዲዎን` የተባለዉን በአብዛኛዉ ከስደተኛ አርበኞች የተደራጀዉን ጦራቸውን አስከትተዉ፥ ከብዙ አድካሚ ጉዞ በኋላ ከኢትዮጵያ ግዛት ገብተዉ ኦሜድላ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሲሰቅሉ፣ ፊትዋ በደስታ እንባ እየታጠበ የኢትዮጵያን መሬት እየሳመች የነጻነት አየር አሽትታለች።  የጌዲዮን ጦር ወደ አገር ውስጥ ገፍቶ በላያ አምባ ላይ ሲሰፍር፣ ደስታም “በላያ በላያ፥ ነይ ያገሬ ቆንጆ የወንዜ ቡቃያ“ የሚለዉን የጎጃም አገርኛ እንጉጉሮ እያዳመጠችና፣ነጻነት መቅረቧን እያሰበች ከጦሩ ጋር ለወር ያህል ሰነበታለች። ከዚያም ቀዳማዊ ሃይለስላሴ በጌዲዮን ጦርና በኢትዮጵያ አርበኞች ታጅበው ወደፊት ገስግሰዉ፣ መጀመሪያ ቡሬ ላይ ሰፍሮ የነበረውን የፋሺስት ጦር ድል መትትዉ  ማርቆስ ሲገቡ፣  ከማርቆስ ወደ ጎሐጽዮን፥ ቀጥሎም የዓባይ በረሃን ተሻግረዉ ፍቼ-ደብረሊባኖስ ብሎም እንጦጦ፣ ወረድ ብሎም ሚያዝያ 27 ቀን 1933 በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ሲገቡ ደስታም አብራ ገብታለች። የደም፣ የመስዋትነትና የነጻነት አርማ  የሆነችዉ ብሄራዊ ባንዲራ እንደገና በሸገር ስትዉለበለብና ቀዳማዊ ሃይለስላሴ“የአዲስ ዘመን“መባጀትን ሲያበስሩ፥ ደስታ በደስታ ፈንድቃ፣ እግዚአብሔርን እያመሰገነች፣ አርበኞቹን እነ ዳጃዝማች በላይ ዘለቀን፣ አበበ አረጋይን፣ ታከለ ወልደሐርያትን፣ ገረሱ ዲኪን፣  ልጅ ዮሐንስ ኢያሱን፣ አሞራዉ ዉብነህን እያቀፈችና እየሳመች፣ ከሰልፉ መሃል ገብታ በኢትዮጵያ ባንዲራ ታጅባ በድል አድራጊነት ከምኒልክ ቤተ መንግስት ገባች። ድርብ የደስታ ድል!! ከነጻነት በኋላ በምኒልክና በኢዮቤል ቤተመንግስት እየተዘዋወረች ከንጉስ ነገስቱ ሳትለይ በእንክብካቤ ኖራለች። ደርግ ከመጣም በኋላ የአርበኝነት ተጋድሎዋን ዕዉቅና በመስጠት በአክብሮ ይዟት ነበር ይባላል። ነገር ግን ወያኔ/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በተፈጠረዉ ግርግርና አለመረጋጋት አደጋ ይድረስባት፣ ወይም የመኖሪያ አድራሻዋን በዉዴታ ወይም በግዴታ ትቀይር፣ ወይም ደግሞ እንደ ብዙዎች አገር ለቃ ትሰደድ አየሁ የሚል ሰዉ አልተገኘም።ብዙዉን የሕይወት ዘመኗን ያሳለፈችዉ በአዲስ አበባ ከተማ እንደነበረ ሲታወቅ፣ይኸዉና ከተሰወረች ወይም ደብዛዋ ጠፋ ከተባለበት ከሩብ ምእት ዓመት በላይ ወዳጅና አድናቂ የተባለ ሁሉ ቢጠይቅ፣ ቢያስጠይቅ፣ ቢወጣና ቢወርድ ሊያገኛት አልቻለም። የደስታን ማንነትና ምንነት  የሚያውቅ ዜጋ ሁሉ መጨረሻዋን ለማወቅ ቢፈልግም፥ የበላት አዉሬ አልጮህ አለ። ስለሆነም የደስታን መጨረሻ ለማወቅ የሚጓጓዉ ሕዝብ ብዙ ነዉና መረጃዉ ያላችሁም፣ የምታውቁ ወይም የሚመለከታችሁ ቁርጡን ንገሩ ይላል። አዎ፣የጀግነንትና  የመስዋዕትነት ቅርስ፣ የታሪክ ማማ፣ የነጻነትና ተጋድሎ  ተምሳሌት የሆነችዉ ታሪካዊቷ የዳኘዉ ምኒልክ የአድዋ ዘመቻ ድንኳን  “ደስታ“ ያለችበትን ሁኔታ በኢትዮጵያ እምላክ ንገሩን።  ካለችም ተመስገን እንበል። ከሌለችም ቁርጡን ንገሩንና እርማቸንን እናዉጣ። አዎ፣ መርዶም ይናፍቃል!!!

posted tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s