ውሸት ሲደጋገም. . . | ከአቻምየለህ ታምሩ

የሰው ልጅ እየተማረ፣ተሞክሮና ልምድ እያገኘ ሲሄድ በበጎ ምግባርና በመንፈሳዊ ፈቃድ እየተመራ፤በፀዳ አእምሮና ከወገንተኛት ነፃ በሆነ ህሊና እየተመለከተ፤ ያካበተውን ሞያዊ ክህሎትና የቀሰመው የምርምር መሳሪያ አጣምሮ እውነትን ከውሸት ይለያል፤ ወገኑን ከትክክለኛ የሀቅ ከፍታ ለማድረስ ይጥራል።

የኦነጋውያን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች መማርና ተሞክሮና ልምድ ማግኘት ትሩፋት ግን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የፈጠራ ታሪክና የሐጢዓት ክስ የማምረት እሽቅድምድም ይመስላል። አንዱ ኦነጋዊ ዶክተር የዲግሪ ማሟያ ወረቀቱን ሲያገባድድ ግኝቱን «ምኒልክ ኦሮሞን ጨፍጭፏል» ብሎ ለገበያ ሲያቀርብ ያየ ሌላኛው የመንፈስ ወንድሙ ተነሳና የዚህኛውን ዶክተር ድምጸት ከፍ አድርጎ «ምኒልክ አምስት ሚሊዮን ኦሮሞ ጨፍጭፏል» ብሎ ሌላ ሸቀጥ አመረተ። በዚህ ፉክክር የተማረከው ጀማሪ ደግሞ አውስትራሊያ ተሻገረና በሌጣው ላይ ዶክተርነት ደርቦ «ምኒልክ አፍሪካዊ ሂትለር ነው» ሲል ሳይማር መጠምጠሙ ሳያንሰው ወሲባዊ ብስጭቱን ወደ ፖለቲካ ለወጠው።

አንዳንዴ ኦነጋውያንን ሳስባቸው ትላልቅ ህጻናት መስለው ይታዩኛል። በልጅነታችን የምሰማው ሁሉ እውነት ይመስለን ነበር። ኦነጋውያንም ሰውን ሁሉ የሚያስቡት የክህደት ሸቀጣቸውን ከፍቶ የማያይ፤ መረጃና ማስረጃ አገላብጦ እውነቱን የማያወጣና ሳይሞግት የሚቀበላቸው ይመስላቸዋል። ወደ ሀምሳ አመት የሚጠጋ በያዙት ፖለቲካ ኖረውበትና እድሜያቸው የአዛውንት ቢሆንም አስተሳሰባቸው ግን ዛሬም የህጻን ነው፤ የ50 ዓመት ህፃናት። ጨቅላ መሆን ያልፈቀደ በኦነጋውያን መንደር የተወገዘ ነው። በኦነጋውያን መንደር የፈጠራ ታሪካቸውን ለመድገምና በውሸት ላይ ውሸት ለመደረብ ካልሆነ በስተቀር በየእለቱ የሚያመርቱትን የፈጠራ ታሪክ በእውነት መነጸር ለማየት የሚደረግ ጥረት ቢኖር ማንነቱን እንደካደ ይቆጠራል። በኦነግ የፈጠራ ታሪክ ልክ የተሰፋ ጥብቆ ፓለቲካዊ ተክለ ሰውነትን እንደ ማንነቱ ካልተቀበለ ማንነቱ እውቅና የለውም።

ባለፈው አመት የODF አመራር አባል የሆነው «ፕሮፌሰር» ሌንጮ ባቲ «ልጅ እያሱ ሊነግስ ያልቻለው አበሾች ወይንም በሱ አባባል አቢሲኒያንስ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ላይ እንዲነግስ ስለማይፈልጉ ነው» አለን። ይህንን ቅቡል አድርጎ ከርሞ ከሰሞኑ ደግሞ አንዱ «ልጅ እያሱ ያልነገሰው ኦሮሞ ስለሆነ ነው» ሲል ደገመው። ይገርማል። ልጅ እያሱን የዙፋናቸው ወራሽ ያደረጉትኮ «አበሻው» ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ናቸው። ከእያሱ በፊት የዳግማዊ አጤ ምኒልክ አልጋ ወራሽ የነበረው የጎባና ዳጨ ልጅ ደጃዝማች ወዳጆ ጎበና ነበር። ደጃዝማች ወዳጆ ጎበና የሀድያ ገዢ የነበረ ሲሆን በሀድያ ላይ የሾመውን ደግሞ አባቱ ራስ ጎበና ዳጨ ነበር። ወዳጆ አልጋወራሽ በሆነ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ስለሞተባቸው ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ልጅ እያሱን አልጋ ወራሽ አድርገው በለጋ እድሜው መረጡት። በኢትዮጵያ ላይ ኦሮሞ እንዲነግስ ካልተፈለገ እንዴት ብለው «አበሻው» ዳግማዊ አጤ ምኒልክ «ኦሮሞዎቹን» ልጅ እያሱንና ደጃዝማች ወዳጆ ጎበናን አልጋ ወራሻቸው አድርገው መረጧቸው? እስቲ መልሱልን?!

የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያምን “ኦቶባዮግራፊ” [የሕይወቴ ታሪክ] ያነበበ ልጅ እያሱን በማውረድና ደጃዝማች ተፈሪ መኮነን አልጋ ወራሽ በማድረግ ረገድ እንደ ትግሬው ሚካኤል ስሑል ንጉስ አንጋሽ የነበሩት አባ መላ ወይንም ፊትአውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የተጫወቱትን ሚና ያውቃል። ፊትአውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ደግሞ የጨቦ ኦሮሞ ናቸው። ባጭሩ ልጅ እያሱን እንዳይነግስ ያደረጉት የዘመኑ አራጊ ፈጣሪ ፊትአውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ናቸው።

ፊትአውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ደግሞ ልጅ እያሱን ያባረሩት ቁም ነገር አልባ ስለ ሆነ እንደሆነ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያምን “ኦቶባዮግራፊ” የሕይወቴ ታሪክ ባሉት ግለ ታሪካቸው ገጽ 240 ላይ ስለልጅ እያሱ እንዲህ ጽፈዋል. . .

“ሸዋ ተሰብስባ ብትዶልት ምን ፍሬ ትሰጣለች? ሸዋ ዙርያዋን የከበባት እስላም ነው። እንድያውም ቆይ ታያለህ! ኢትዮጵያን አሰልማታለሁ። ይኸንን ያላደርግኩ እንደሆነ እኔ እያሱ አይደለሁም…ብለው ሲፎክሩ ደነገጥሁና ከፊታቸው ዘወር አልሁ።. . . . . . . . . . . . . . ሸዋ ቢዶልት የት ሊደርስ ይችላል? በአንድ ጊዜ እደመስሰዋለሁ። እኔ እያሱ፡ ሸዋን ልሽናብህ ብለው እንኳ፣ አፉን ከፍቶ እንደሚቀበለኝ የታወቀ ነው። ከፈለግኩ ደግሞ፡ የጉራጌውንና የጋላውን ባላባት አንድ ምልክት ብሰጠው አዲስ አበባን በአንድ አፍታ ሊያቃጥላት ይችላል።»

ይህንን የተናገረው ልጅ እያሱ ነው። ስለዚህ ልጅ እያሱ ያልነገሰው ይህ የልጅ ንግግሩና ለኢትዮጵያ ያለው አስተሳሰብ በነአባ መላ ስላልተወደደለት ነው። ከአልጋ ወራሽነቱ አውርደው የፈጠፈጡትም ከፍ ብሎ የቀረበውን ንግግሩን የሰሙት ኦሮሞው አባ መላ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ናቸው። እውነታው ይሄ ነው። ይህንን የሚጠራጠር ቢኖር የአይን ምስክሩ፣ በወቅቱ ከልጅ እያሱ ወገን የተሰለፉትና የደጃዝማች ተፈሪ መኮነን ነቃፊው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያምን የጻፉትን “ኦቶባዮግራፊ” ያንብብ።

posted tigi flate

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s