ዘወሃቦ ወንዶ ወወለቶ ለደደቢት ርጉመ ለይኩን ( ማስታዎሻነቱ ለሓብታሙ አያሌው) – መስቀሉ አየለ

በጥቃትና በውርደት ውስጥ መኖር ምን ያህል ያማል።ወኔን አስታውኮ፤ ሃሞትንም ሸንቶ መኖር በቃኝ ለማለት ግፍን የሚያመርቱት ሰዎች እብሪት ከዚህ በላይ ምን ያህል እርቀት መሄድ አለበት ይሆን፣ ማንም ከአባቶቹ ደገኛ ታሪክ የተወለደ ኩሩ ዜጋ፣ ይሄ የአድዋ ድል በዓል በመጣ ቁጥር ያለ ልኩ የተሳፋ ለምድ ለብሶ እራሱን “የአባቶቹ ልጅ” እያለ የሚጠራው  ሁሉ ዛሬ እየሆነ ያለውንና ቃላት ሊሸከሙት የማይቻላቸውን ግፍ  ከአባቶቹ ዜና መዋእል ጋር እንዴት ቢያስማማው ነው ዝምታን የማርያም መንገድ አድርጎ እለቱ አመት እየሆነበት መኖር የቀጠለው?የደገኛ አባቶቸ የጀግንነት ታሪክ ለሽዎች አመታት ያለ ማቁዋረጥ ከአባይ ወንዝ እኩል ሲፈስባት በኖረች አገር ላይ ጥቂት ድኩማኖች በዚህ ደረጃ አገሩን ይፈቱት ዘንድ መንገዱን እንዴት አገኙት? ክፍተቱ የት ላይ ነው የተፈጠረው? በርግጥ ሃብታሙ አያሌው ላይ እና ሌሎች እንደሱ እድሉን ያላገኙ ነገር ግን በምድራዊ ገሃነም ውስጥ እየተቀቀሉ ያሉ ህልቁ መሳፍርት ወገኖቻችን ላይ እየሆነ ያለውን ለማወቅ  ዛሬም ነጋሪ ያስፈልገን  ይሆን? ለመስማት ያልተፈቀደውን ሁሉ ሰምተነዋል። ጥያቄው ይኽ በሃብታሙ አያሌው አንደበት የሰማነው ወደ ካንሰርነት ደረጃ የወረደ የትውልድ ደዌ ዛሬም እንደ ትናንቱ የአንድ ሰሞን የሚዲያ ሙቀት ሆኖ ይቀር ይሆን ወይንስ ሽህ ሚሊዮን ደመቀ ዘውዴንና አርበኛ ጎቤን ፈጥሮ ያልፍ ይሆን..? መርገምቱንስ ብንገላገል ይኽን የግፍ ጽዋ ሲግቱን ከኖሩት እኩያን ጋር እንደ ህብረተስብ አብረን የምንዘልቀው እንዴት ነው? የሚለው ነው።ይኽን የሃብታሙ ቃለምልልስ አዳምጨ እንደጨረስኩ በአይምሮዬ የመጣው ያ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ታሪኩ የተገለጣው ነገደ ኤፍሬማዊ ነበር፣”እግዚኦ እምዉሁዳነ ምድር ንፍቆሙ፤ በህይዎቶሙ”። ሉቃስ፩፮፤፪፭ ይለዋል። ይኽ ታሪክ በትርጓሜ ቤተክርስቲያን እንዲህ ተተንትኖዋል።
ውሁዳነ ምድር ያሰኘው እንደ ምንድን ነው ቢሉ ክህነ ደብረ ኤፍሬም ይለዋል።ሚስቱ ተጣልታው ወደ ሃገሩዋ ብትሄድ እርሱም ተከትሎ ሄደና በደጅ ተቀመጠ። ዘመዶቹዋም “ወንድማችን ሆይ ከሚስጥ እንደሆነ እናስታርቀኻለንና ከቤት ግባ “ቢሉት ገብቶዋል። እርቅም አደረጉለትና አመሰገኖ በነጋታው መንገድ ገባ ይላል።
በጠዋት ቢነሱ እለቱን ይደርሱ ነበር፤መሴፋ ሲደርሱ መሸባቸው። ብላቴናው ከዚህ እንደር አለው። የለም ከዚያ ወንድማችን የሚሆን አለ። አኗኗሩ እንደ ሎጥ ቢሆን ነው፤ለኛ እራት ለከብቶቻችንም ገፈር አንልህም ማደሪያ ብቻ ስጠን እንለዋለን ብለው ወደዚያው አቀኑ።የማን ወገን ናችሁ፣ ወዴት ስትሄዳላችሁ አላቸው፤ ንሕነ ኃለፍተ ቤተልሔም እንሔዳለን፣ ወገናችንም ከነገደ ኤፍሬም ነን አሉት። እናንተ እማ ወንድሞቻችን አይደላችሁምን፣ ግቡ አላቸው። ገቡ።
ራት አግባ ሄዶ እንዲህ ያሉ ሰዎች ገብተዋል ብሎ ለአገሩ ሰዎች ነገረባቸው። ነገረ እሊህ የገባኦን ሰዎች ግብረ ሰዶም የሚሰሩ፤ እንደ ሃብታሙ አያሌው ገራፊዎች መንፈስ ቅዱስ የተጠየፋቸው ናቸው። ተሰብስበውም ሄዱና አሳዳሪውን እንግዶቹን ስጠን አሉት። በሃይማኖት ያለ ነበረና በእግዚአብሔር ስም የመጡ ሰዎችን እንደምን ብዬ ብሎ ባይሆን የኔን ልጅ ወሰዱውት አለ። ያንተን ልጅም የት ልትርቀን አሉት፤ ከዚያም እሽ ሴቲቱን (ሚስቲቱን) ውሰዱዋት እንጅ እሱንስ አልሰጣችሁም ብሎ እርሱዋን ሰጣቸው። እንደ ሻንቅላ እየተፈራረቁ አደሩባት። ዘርም አስክሯት ሞታ አደረች። ባሏ ቢሆን ግን መቸ ነግቶልኝ አይኑዋን አይቻት እያለ ሲጨነቅ አደረ። ከደጅ አጋድመው ጥለዋትም ሄደው ኖሯል። ያለች መስሎት ተነሽ እንሂድ አላት። ዝም አለች፤ ገልጦ ቢያያት ሞታለች። አባቶቻችን ከግብጽ ምድር ከወጡበት ግዜ ጀምሮ እንዲህ ያለ ግፍ ተደርጎ አያውቅም፤ በኔማ አንድ ግዜ ተደርጎብኝ የለምን፤ የሚያሳዝነኝ የእስራኤል ስራት መፍረሱ ነው እንጅ ብሎ በአህያ ጭኖ ወዳገሩ ይዟት ሄደና ስጋዋን ለአስራ ሁለት ቦታ ቆራርጦ ከፍሎ ለአስራ
ሁለቱም ነገደ እስራኤል ልኮላቸዋል።
እስራኤላውያንም “ዘወሃቦ ወንዶ ወወለቶ ለገባኦን ርጉመ ለይኩን ” ብለው እየረገሙ ተነስተዋል። ኢያውሴምም ሲደርሱ መስዋእተ፡እግዚአብሔር ሰውተው የዚህች ሴት ደም እንደፈሰሰ የብድራት መክፈያውን መንገድ ምራን ብለው ሄደው ቢገጥሙዋቸው ስድስት መቶ ሰዎች ብቻ በኮካሃ አሞሬዎች ሲቀሩ ሌሎቹን ከምድረ ገጽ አጥፍተዋቸዋል ይላል።
እንግዲህ በነገደ ኤፍሬም ላይ የደረሰው የልብ ስብራት ከሺህ አመታት በኋላ እዚህ ደደቢት ዋሻ ውስጥ እንደ ክረምት አግቢ ግዜውን ጠብቀው ዳግም በሰው አምሳል በተከሰቱና የክፋታቸው ጥልቀቱ መለኪያ ሜትር የጠፋለትን የገባኦንን ሰዎች የደም ንክኪ በወረሱ ለምጻሞችያ የነው ይመስለኛል።ለውርደታችን ዳርቻ ይኖረው። እኛም ደግሞ ዘወሃቦ ወንዶ ወወለቶ ለደደቢት ርጉመ ለይኩን ብለን ነገደ ኤፍሬማውያን በሄዱበት የበቀል ጎዳና መንገድ መጀመራችንም  የግድ ይሁን።ታሪክም እዚህ ላይ እራሱን ቢደግም የሚከስርበት አይሆንም። አምላከ ኢትዮጵያ የሰናኦርን ሰዎች ባየበት አይኑ ይያቸው።
posted tigi flate
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s